>

CPJ: በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች እንደሚያሳስቡት አስታወቀ!!!

CPJ በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች እንደሚያሳስቡት  አስታወቀ!!!
ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት በምህጻሩ CPJ
 
ዶቼቬለ
 
ከአንድ ዓመት ወዲህ ኢትዮጵያ በፕሬስ ነጻነት ረገድ ያስመዘገበችውን መልካም ስም የሚያጎድፉ አንዳንድ የቅርብ ጊዜ እርምጃዎች እንደሚያሳስቡት ዛሬ ባወጣው ጽሁፍ አስታወቀ።
የጽሁፉ አቅራቢ የCPJ ከሰራ በታች የሚገኙ የአፍሪቃ አገራት ተወካይ ሚስ ሙቶኪ ሙሞ በተለይ ባለፈው ግንቦት እና ሰኔም የተካሄደው የጋዜጠኞች
እሥር እና አንዳንዶቹም የተከሰሱት መንግሥት ራሱ ችግር እንዳለበት በሚናገረውና ሊያሻሻልወም ቅድሚያ በሰጠው በፀረ ሽብሩ ህግ መሆኑ CPJ እንደሚያሳስበው አስረድተዋል።ከዚህ ሌላ በሃገሪቱ በቅርቡ እና ከዚያ በፊትም ያጋጠመው የኢንተርኔት መቋረጥም በጋዘጠኞች እና በፕሬስ ነጻነቱ ላይ ትልቅ ተጽእኖ አሳድሮ እንደነበርም አስረድተዋል። ሙሞ እንዳሉት ጋዜጠኞች በኢንተርኔት እጦት ከመረጃ ምንጮቻቸው ጋር መገናኘት አልቻሉም፤ መረጃዎችን ለማጣራትም ሆነ ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት ለማቅረብም ተቸግረው ነበር።ሙሞ ከግንቦት አንስቶ እስካሁን የጋዜጠኞች እስር መጨመሩን ድርጅታቸው መገንዘቡንም አስረድተዋል። በCPJ ምርመራ መሠረት «ታምራት አበራ የተባለ የራድዮ ጋዜጠኛ በግንቦት በዘገባው ምክንያት ከቢሮው ታስሮ ኦሮምያ ክልል ተወስዶ ለሦስት ቀናት መታሰሩን ሊጠይቀው የመጣም ጋዜጠኛም ታስሮ እንደነበር» ገልጸዋል።አሁን ባላቸው መረጃ መሠረትም« የታምራት እና የባልደረቦቹ ጉዳይ በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑንም» አስረድተዋል።ከሰኔ 15 ቱ የባለሥልጣናት ግድያ በኋላም ቢያንስ ሦስት ጋዜጠኞች በጸረ ሽብሩ ሕግ መታሰራቸውንም ገልጸዋል።ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የሰላ ትችት የሚሰነዝሩ ጋዜጠኞችን ለመበቀል ጥቅም ላይ ይውል ነበር ያሉት የፀረ ሽብሩ ሕግ እንደገና ጋዜጠኞችን መክሰሻ መደረጉ ያሳስበናልም ብለዋል።
መንግሥት ጋዜጠኞቹ የታሰሩት ከጋዜጠኝነት ሞያቸው ጋር በተያያዘ ምክንያት አለመሆኑን መናገሩን የጠቀሱት ሚስ ሙሞ ጋዜጠኞቹ በትክክል በምን ምክንያት እንደታሰሩ፣በየትኛው እንቅስቃሴያቸው ምክንያት ለእስር እንደተዳረጉ ብዙም ግልጽስላልሆነ ይህም እንደሚያሳስባቸው ጠቁመዋል።ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ስላሉት ጋዜጠኞች ጉዳይ አስተያየት በመጠየቅበሰኔ እና በሐምሌ CPJ ለላከው የጽሁፍ መልዕክት የኦሮምያ ክልል መንግሥት ቃል አቀባይ መልስ እንዳልሰጡ በሐምሌ ወር ስልክ ሲደወልላቸውም ከአንድ ሰዓት በኋላ መናገር እንደሚችሉ ገልጸው ባሉት ሰዓት አለመገኘታቸውን ሙሞ በጽሁፋቸው አስፍረዋል።
ሙሞ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት የፕሬስ ነፃነትን እንተገብራለን እስከተባለ ድረስ ግልጽነት አስፈላጊ ነው።መንግሥት ለህዝቡ በመገናና ብዙሀን አማካይነት መረጃ የመስጠት ሃላፊነትም እንዳለበት አስገንዝበዋል።በመጨረሻም መንግሥት በፊት ወደነበረው ጋዜጠኞችን ወደማያስርበት የማሻሻያ እርምጃ እንዲመለስ የድርጅታቸው ፍላጎት መሆኑን አስረድተዋል። በኢትዮጵያ የመጡ ለውጦች እንዳሉ የተናገሩት ሙሞ ፣ የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሀን የወደፉት እጣ ፈንታ ግን ያሳስበናል ብለዋል። «የምናነሳቸው ስጋቶች መልስ አግኝተው ኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት የሚከበርባት ሃገር ትሆናለች፣ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
Filed in: Amharic