>

የብ/ጄ አሳምነው ፅጌ ልጅ ዳዊት አሳምነው ከኢትዮጲስ ጋር ያደረገው ቆይታ

*ዳዊት አሳምነው ይናገራል፦

*የብ/ጄ አሳምነው ፅጌ ልጅ ዳዊት አሳምነው ከኢትዮጲስ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ኢትዮጲስ፦በመጀመሪያ ከስምህና ከእድሜህ ልጀምር…

ዳዊት አሳምነው፦ስሜ ዳዊት አሳምነው ይባላል ፤እድሜዬ 15 ነው፤የተወለድኩት አዲስ አበባ ነው።በሚቀጥለው ዓመት 10ኛ ክፍል እገባለሁ።

ኢትዮጲስ፦ከ9 ዓመታት በፊት አባትህ ሲታሰሩ፣አንተ ትንሽ ልጅ ነበርክ።ያንን ጊዜ ምን ያህል ታስተውሰዋለህ?

ዳዊት አሳምነው፦አስታውሰዋለሁ፣የ5 ዓመት ልጅ ነበርኩ።አንዳንድ መጥፎ ነገሮች ሲፈጠሩ፣የልጆች አእምሮ ውሰጥ ተቀርፆ ይቀራል፤አይረሳም።አስፈሪ ጊዜ ስለነበር አልረሳሁትም፤በጣም አቅልሼ ነበር።ሁሉም የደነገጠበት ሰዓት ነበር።እስር ቤት እየሄድኩኝ እጠይቀው ነበር።

ኢትዮጲስ፦ እስር ቤት እያሉ ምን ይሉህ ነበር?

ዳዊት አሳምነው፦መጠንከር እንዳለብኝ፣መበርታት እንዳለብኝ፣ድንገት እሱ እንኳን ቢቀር፣የእሱን ራእይ እንዳሳካ ያስተምረኝ ነበር።ለሀገሩ እንደታገለ ብዙ ጊዜ ይነግረኝ ነበር።የታሰረው ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ እንደነበር እየደጋገመ ይነገረኝ ነበር።መልካም መልካም ነገሮችን ነበር የሚነግረኝ።ቃሊቲ እስር ቤት እያለ፣በየሳምንቱ ነበር የምንሄደው።ዝዋይ እስር ቤት ሲሄድ ግን፣ሩቅ ቢሆንም ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ አንቀርም ነበር።

ኢትዮጲስ፦አባትህን እንዴት ትገልፃቸዋለህ? ምን ዓይነት ሰው ነበሩ?

ዳዊት አሳምነው፦የእኔ ጀግናዬ ነው አባቴ።ለእኔም ጭምር እንደሚታገል ነበር የሚነግረኝ።ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ህዝብ የታገለ ጀግና ነበር።እኔ ሳይሆን “እኛ”ነበር የሚለው።ያለውን የሚሰጥ ነበር፣ልብሱ እንኳን አይቀርም ነበር።ለእኔ ብሎ አያውቅም።እርቦት እንኳን የያዘውን ዳቦ ለሌላ የሚሰጥ ነበር።

ኢትዮጲስ፦ከተፈቱ በኋላ፣ምን ይሉህ ነበር?

ዳዊት አሳምነው፦”ትርፍ ህይወት ነው የምኖረው”ይለኝ ነበር።”ከዚህ በኋላ ህዝቡን ማገልገል ነው
የምንፈልገው”ይለኝ ነበር።

ኢትዮጲስ፦አሁን የተፈጠረውን ነገር ሰምተሃል።በዚያ ላይ ምን አስተያየት አለህ?

ዳዊት አሳምነው፦አንደኛ፣ድርጊቱ በጣም አሳዛኝ ነበር።አባቴ የተባለውን ፈጽሟል ብዬ አላምንም።እሱ፣ለህዝብ፣ለሀገር፣ለአንድነት ይታገል የነበረ ነው።እግዚአብሔር ይፍረድ ነው የምለው።እሱ የሰው ህይወትን ለማትረፍ እንጂ፣ለመጉዳት የሚፈልግ ሰው አልነበረም።ድርጊቱ ከተፈጸመበት ቅዳሜ በኋላ ባለው ማክሰኞ እኛ ከአዲስ አበባ ወደ ባህር ዳር ለመሄድ እየተዘጋጀን ነበር።ሰራተኛ ሁሉ ተቀጥሮ ዝግጅት እየተደረገ ነበር።ወደ ባህርዳር ለመብረር አንድ ሁለት ቀን ብቻ ነበር የቀረን።በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን፤ይህ ነገር ያደርጋል ብዬ አላምንም።

ኢትዮጲስ፦በመጨረሻ የምታስተላልፈው መልእክት ካለህ እድሉን ልስጥህ….

ዳዊህ አሳምነው፦በመጀመሪያ ለእነ ዶ/ር አምባቸው ቤተሰቦች መናገር የምፈልገው ነገር አለ።አሁንም በፍቅር ሆነን እንድንቀጥል እፈልጋለሁ።ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን እፈልጋለሁ።ለኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ የኋላውን ትቶ ወደፊት እንዲመለከት ነው ጥሪ የማስተላልፈው።መጥፎውን እረስቶ በፍቅር መኖር ነው የሚገባን።”

 

 

Filed in: Amharic