>

መከፋፈሉ፤ ጎራ ለይቶ መባላቱ እልቂትን በራስ ላይ ከመጋበዝ ያለፈ ፋይዳ የለውም!!! (ውብሸት ሙላት)

መከፋፈሉ፤ ጎራ ለይቶ መባላቱ እልቂትን በራስ ላይ ከመጋበዝ ያለፈ ፋይዳ የለውም!!!
ውብሸት ሙላት
በሰኔ 15ቱ ድርጊት ወንድሞቻችንን አጥተናል፡፡ መሪዎቻችንን አጥተናል፡፡ ተጎድተናል፡፡ አዝነናል፡፡ ከዶ/ር አምባቸዉ፣ምግባሩ፣ እዘዝና ብ/ጀ አሳምነዉ በተጨማሪ በጸጥታ ሥራ ላይ የተሠማሩ ፖሊሶችን አጥተናል፡፡ በተፈጠረዉ አሳዛኝና ቅስም የሚሰብር ክስተት በአማራ ሕዝብ ላይ መቼም የማይረሳዉ የታሪክ ጠባሳ አሳርፎብናል፡፡
ይህ ወቅት ለአማራ ሕዝብ በተለዬ ሁኔታ ፈታኝ ነዉ፡፡ ይህን የፈተና ወቅት ለመዉጣት የአማራ ሕዝብ አንድነት ከመቼዉም ጊዜ በላይ አስፈላጊ ነዉ፡፡ አንድ ከመሆን ያነሰ ማናቸዉም አካሄድ ለአማራ ሕዝብ የከፋ ጉዳትን ያስከትላሉ፡፡ እንግዲህ ያለፈዉ አልፏል፡፡ በታሪካችን ጥቁር ነጥብ ሆኖ ይመዘገባል፡፡
እንደ ሕዝብ ከእዚህ   የከፉ ወቅቶችንም አሳልፈናል፡፡ ብዙ ዋጋ አስከፍለዉንም ቢሆን በብቃትም ተወጥተናቸዋል፡፡  ከመቼመዉም ጊዜ በላይ የሚያስፈልጉንን ወንድሞቻችንን፣መሪዎቻችንን አጥተናል፡፡ አሁን የሚያስፈልገዉ ከእዚህ የፈተና ወቅት በአፋጣኝ የምንወጣበትን አካሄድ መከተል ነዉ፡፡
ለአሁኑ ሦስት ነጥቦችን ብቻ ላንሳ፡፡
1.መላዉ የአማራ ሕዝብ ከመቼዉም ጊዜ በላይ አንድ መሆን የሚያስፈልገበት ወቅት ነዉ፡፡ ወቅቱ የፈተና ነዉ፡፡ ለአማራ ሕዝብ ክረምት ነዉ፡፡ በፍጥነት ከዚህ ክረምት መዉጣት ይጠበቅብናል፡፡ ክረምትነቱን ሊያከብዱ የሚችሉ ፍላጎቶችን መበራከታቸዉን እያስተዋልን ነዉ፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያዉ ቢዘጋም በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሲተላለፉ የነበሩ ፕሮግራሞች በቂ ምስክር ናቸዉ፡፡
ከዚህ ባለፈም፣ የባህር ዳሩን ድርጊት “መፈንቅለ መንግሥት” ብለዉ መሠየማቸዉ ሳያንስ፣ በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በፌደራል መንግሥቱም ላይ እንደነበር አስመስለዉ በመተረክ ሌላዉ ሕዝብ የአማራ ሕዝብን እንዲጠራጠር እንዲጠላ  የሚያደርግ እኩይ አካሄድም እያየን ነዉ፡፡ ባህር ዳርም አዲስ አበባም የተፈጸመዉ ድርጊት አስነዋሪም ዘግናኝም ነዉ፡፡
መፈንቅለ መንግሥት ሊባል አይችልም፣ሊሆንም አይችልም ማለት የተፈጸመዉን ድርጊት ማቃለል አይደለም፤ መፈንቅለ መንግሥት ስለማይሆንም የአማራ ሕዝብንም ቀድሞ ትምክህተኞች፣ነፍጠኞች ወዘተ እያሉ ለሌላዉ ሕዝብ በመንዛት ከሌላዉ ሕዝብ ጋር ለማጋጨት፣ጥርጣሬ ዉስጥ ለመክተት እንደተደረገዉ ሴራ አሁንም አማራ መፈንቅለ መንግሥት ሊያደርግ ነበር፣የማድረግ ፍላጎት አለዉ ወዘተ በማለት ቀድሞ ሕወሃት ሲጠቀምበት የነበረዉን አካሄድ በሌላ አገላለጽና ቃል በመጠቀም ፕሮፓጋንዳ መንዥያ ስለሆነ ነዉ፡፡
ከሁሉም የከፋዉ፣ የጀኔራል ሰዓረ መኮንን እና የብ/ጀ ገዛኢ አበራ የግዲያ ሁኔታ ሳይጣራ፣ የገዳዩ ማንነትም ይሁን ምክንያቱ ሳይታወቅ፣ ባህር ዳር ላይ ከተፈጸመዉ ጋር ያለዉ ግንኙነት ሳይታወቅ እንደዚህ ዓይነት አደገኛም ስህተትም ስያሜ መጠቀም የአማራ ሕዝብን ከሌላዉ ጋር ቅራኔ ዉስጥ ለመክተት የተሸረበ ሴራ እንጂ ሌላ ሊባል አይችልም፡፡ የሚያስከትለዉን ጣጣም ሳይገነዘቡ ይህንን ስያሜ የሚጠቀሙ ሰዎች በድጋሜ ሊያጤኑት ይገባል፡፡ የእነ ጀኔራል ሰዓረ መኮንን አሟሟትን በሚመለከት በርካታ መላምቶችም ጥያቄዎችንም ማንሳት ቢቻልም ለጊዜዉ ይቆይ!
2.መፈጸም የሌለበት ድርጊት ተፈጽሟል፡፡ መታረም ያለባቸዉ አካሄዶች ግን መታረም አለባቸዉ፡፡ በተለይ በተለይ ያጣናቸዉንን ወንድሞቻችንን የሚያጣጥል እና እንኳንም እንዲህ ሆኑ የሚል አገላለጽም ሆነ የሚመስል ይዘት ያለዉን አገላለጽ በፍጹም መታገስ የለብንም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ “የእኔ መሪየ እንቶኔ እንጂ እንትና አይደለም፣ እንቶኔ እንትናን እንዲህ ሊያደርገዉ ነዉ” ወዘተ ከሚሉ ዘመቻዎች እራሳችንን መቆጠብና እንዲህ ዓይነት ወሬዎችን በፍጹም ለዓደባባይ መዋል አይገባቸዉም፡፡ ሁሉም የክርስቶስ መሆናቸዉን ዘንግተዉ “እኔ የአጵሎስ ነኝ እኔ የጳዉሎስ ነኝ” ሲሉ የነበሩ ዝንጎችን አንምሰል፡፡ አማራና የአማራ መሆናቸዉን ዘንግተን “እኔ የዶ/ር አምባቸዉ ነኝ እኔ የጀ/አሳምነዉ ነኝ” ሲባል የነበረዉን የእርጉሞች መንገድ ልናቆም ልንደግመዉ አይገባም፡፡ ሁለቱንም አሳጥቶናል፡፡
ከእዚህ ጋር ተያይዞ፣ አዴፓም ይሁን አብን ወይም ሌላ አደረጃጀት ፓርቲያዊ አንድነታችሁን ከመቼዉም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ማጠናከር ይጠበቅባችኋል፡፡ በድርጅት ዉስጥ ባሉ አባላት፣በተለይም አመራሮች፣ ሕዝብን ሊሚከፋፍል የሚችሉ የአቋም ልዩነቶችን ወደ ዓደባይይ ይዞ የመሮጥ ዝንባሌ ሊቆምም፣ሊታረምም ይገባዋል፡፡ አዝማሚያዎች ሲኖሩም በፍጥነት ማረም ነዉ፡፡ ዋጋ አስከፍሎናል!!!!!!!!
3.አሁን ላይ አዴፓ፣ አብን፣ ቤተ-አማራ፣አንድ አማራ ወዘተ በሚል ክፍፍል የሚደረግበት ጊዜ አይደለም፡፡ አንዱ ሌላዉን የሚቃወምበት ጊዜ አይደለም፡፡ ሁሉም አደረጃጀቶች በአንድነት የሚታገሉበት እንጂ፡፡ የሰማእቶቻችን ደም ከንቱ ከንቱ እንዳይሆን፣ ከመቼዉም በላይ በትብብር እና በጋራ መሥራትን ወቅቱ ይጠይቃል፡፡
ባህር ዳርም አዲስ አበባም ላይ ሕይታቸዉን ያጡ መሪዎችም፣ ፖሊሶችም ነፍሳቸዉ ፈጣሪ በሰላም ያሳርፍልን! ከማናቸዉም በላይ፣ ለቤተሰቦቻቸዉም መጽናናትን ይስጥልን!
Filed in: Amharic