>

እውን ይህ ሁሉ የሆነው በዳያስፖራው ነውን???  (ግርማ ካሣ )

እውን ይህ ሁሉ የሆነው በዳያስፖራው ነውን??? 
     ግርማ ካሣ 
1) በሶማሌ ክልል ፣ በኦሮሞ ክልል በሃረርጌ፣ በባሌ፣ በቦረና ..ከስድስት መቶ ሺህ በላይ ኦሮሞዎች፣ ከአራት መቶ ሺህ በላይ ሶማሌዎች ተፈናቅለዋል። በሺሆች የሚቆጠሩ ሞተዋል። ይህ የሆነው በዳያስፖራው አይደለም። በሶማሌ ክልል ሚሊሻዎችና በኦሮሞ ክልል በኦህዴድ ሚሊሻዎች ምክንያት ነው። በአጭሩ በገዢው ፓርቲ ድርጅቶች ነው።
2) ከጌዲኦ ከስምንት መቶ ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል። ይህ የሆነው በሕዝቡ ሳይሆን በአካባቢው ባሉ የኦህዴድ ባለስልጣናት ነው። በኢሕአዴግ ምክንያት ነው።በዳያስፖራው አይደለም።
3) በለገጣፎ ከሰላሳ ሺህ በላይ ቤቶች የፈረሱትን ዜጎች ሜዳ ላይ የተጣሉት በዳያስፖራው አይደለም፣ በኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች ነው።
4) በሰሜን ጎንደር የቅማንት ኮሚቴ በሚል በተነሳው ግጭት ከሰማኒያ ሺህ በላይ ዜጎች ተፍናቅለዋል። የቅማንት ኮሚቴ የሚባለውን ያደራጀውና ያስታጠቀው ሕወሃት ነው። ዳያስፖራው አይደለም።
5) ከቢነሽንጉል ከሁለት መቶ ሺህ በላይ አብዛኞቹ ኦሮሞዎች ከጉሙዞች ጋር በተደረገ ጦርነት ተፈናቅለዋል። የጸቡ ምክንያትም ኦነግ ነበር። ኦነግን ትጥቁን ሳይፈታ በአገር ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ኦህዴድ ነው። ዳያስፖራው አይደለም።
6) በአጣዬና በማጀቴ ለተፈጠረው እልቂት ዋና ተጠያቂ ከነጃዋር ጋር የሚሰራው እስላማዌ ኦነግና በከሚሴ መስተዳደር የነበሩት ጽንፈኞች ናቸው። እነዚህን ደግሞ እያባበለ ያኖረው ኦህዴድ ነበር። እንጂ ዳያስፖራው አይደለም።
7) በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ሰኔ 15 የተፈጠረው ቀውስ የተከሰተው ኢህአዴግ ውስጥ ካለው የውስጥ ሽኩቻ የተነሳ ነው። እርስ በርሳቸው ነው የተገዳደሉት። ዳያስፖራው እዚህ ውስጥ የለም።
ታዲያ የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስተር ራሳቸውንና የችግሮቹ መንስኤ የሆነው ድርጅታቸው መመልከት ሲገባቸው ጣታቸውን ወደ ዳያስፖራ ማዞራቸው ለምን ይሆን ? ምን አልባት ያኔ እነ መለስ ጽንፈኛ ዳያስፖራ ይሉት የነበረው ትዝ ብሏቸው ይሆን ?
Filed in: Amharic