>

ማነው መክሥተ ደደቢትን አገራዊ ሰነድ ያደረገው? (ከይኄይስ እውነቱ)

ማነው መክሥተ ደደቢትን አገራዊ ሰነድ ያደረገው?

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

መክሥተ ደደቢት ወይም የወያኔ መግለጫ ያልኩት ሕወሓት በደደቢት ወጥኖት ከግብር ወንድሙ ኦነግ ጋር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለማጥፋት ተማምለው ያዘጋጁት እነሱ ‹ሕገ መንግሥት› የሚሉት መርዘኛ ሰነድ ነው፡፡ ይህን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጫኑትን ጠንቀኛ ሰነድ ነው ዐቢይ ‹‹ ሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰነድ ነው፡፡›› በማለት በቅርቡ በተካሄደው የወያኔ ጉባኤ ላይ የተናገረው፡፡ ድንቄም ሕገ መንግሥት፡፡ ኢትዮጵያ አንድ ሉዐላዊ አገር ናት ብለን የምናምንና የምንቀበል ከሆነ፣ ባንድ አገር ውስጥ የሚኖረው (በጐሣ፣ በነገድ ብንመድበውም፣ የተለያየ ባህልና ትውፊት ቢኖረውም) አንድ ሕዝብ ነው፡፡ ሕዝቦች የምንለው ከአንድ አገር በላይ ላለ ሕዝብ ነው፡፡ (ሕዝብ የሚለው ቃል በራሱ ብዙ ነው፡፡) እንዲያው ተራ የቋንቋና የጸጉር ስንጠቃ ጉዳይ እንዳይመስለን፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ተፋልሶ ወያኔዎች ሆን ብለው የሚያራምዱት የአቋም መግለጫ ነው፡፡ ተራ አባባል የሚመስለንና ወያኔዎችን ተከትለን የምናስተጋባ ሰዎች በእጅጉ ተሳስተናል፡፡ የዚህ አጥፊ ሰነዳቸው አንድ የማዕዝን ደንጊያ ነው፡፡ አንደምታው ከ80 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ አገር ‹ሕዝቦች› በ‹ፈቃዳቸው› የመሠረቷት አገር ነች ለማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው ሰነዳቸው የአገር ባለቤትነት መለያ ለሆነው ዜግነት ዕውቅና ከመስጠት ይልቅ የአገርና የሕዝብ ሉዐላዊነትን ግዑዝና ትርጕም አልባ ለሆነው ‹‹ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›› ለሚባል ካልእ ‹ፍጥረት› የሰጠው፡፡ የኢትዮጵያን ህልውናና አንድነት ለድርድር አላቀርብም የሚል መሪ አብዛኛው ዜጋ የኔ አይደለም የሚለውን ሰነድ በግድ የናንተ ነው ማለቱ ተገቢ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ ያለውን የሕዝቡን አቋም ማወቅ ካስፈለገ የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ ድምጽ (Public Opinion Poll) በባለሙያ አካል እንዲደረግ በማድረግ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

በኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ ጊዜያት በጉልበት ሥልጣን የያዙ አገዛዞች ዕውቀትና እውነት ከሥልጣን የሚመነጭ ይመስላቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በማያውቁት ጉዳይ በድፍረት መናገር የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህም የድፍረት ንግግር እንደ ዕውቀት እየተወሰደ የአገዛዛቸው ታችኛው መዋቅር ድረስ በደናቁርት ካድሬዎቻቸው አማካይነት ይስተጋባል፡፡

የሕጎች ሁሉ የበላይ (አንድ ጸሐፊ እንዳሉት ‹ርእሰ ሕግጋት›) ከጽሑፉ ዝግጅት እስከ አፀዳደቁ የራሱ ሥነሥርዓት ያለው ሲሆን፣ ሕጋዊ ተቀባይነት (legal legitimacy) የሚያገኝበትም ዓለም አቀፍ መርሆዎች አሉት፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ቀደም ባለ ጽሑፌ* ስላነሳሁት አልመለስበትም፡፡

ወያኔ/ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን ሕዝብ በጐሣ፣ በነገድ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት ልዩነት እያጋጨ ሥልጣን ላይ ለመቆየትና በዚሁ የሚገኘውን ዝርፊያ ለማደላደል የጻፈውን የድርጅት ደንብ የአገር መተዳደሪያ የሕዝብ ሰነድ ነው ብሎ ያለኀፍረት መናገር ያስተዛዝባል፡፡ የለውጥ ሐዋርያ ነኝ ከሚል የአገር ‹መሪ› በጭራሽ አይጠበቅም፡፡ የአገራችን ህልውና በቋፍ ሆኖ ዜጎች ላለፉት 24 ዓመታት (የወያኔ ሰነድ ይፋ የሆነበትን ጊዜ ይመለከታል) በሥጋትና በጭንቀት ተወጥረው ከሚገኙበት ዐበይት ምክንያቶች ቀዳሚው እኮ ይህ ‹ሕገ አራዊት› የፈጠረው ምስቅልቅል መሆኑ ከዐቢይ የተሠወረ አይመስለኝም፡፡

ብዙዎች ስለ ወያኔ የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› ሲነሳ የሚያደናግራቸው በሰነዱ ውስጥ የተካተቱት ነገር ግን ተግባራዊ የማይሆኑት የሰብአዊ መብቶች እና ነፃነቶች ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንደዶች አለዕውቀት ሰነዱ ‹ጥሩ ድንጋጌዎች› እንዳሉት ይናገራሉ፡፡ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም ወዲህ ይህንን ቀመር አብዛኛዎቹ አምባገነን መንግሥታት እንደ ፋሽን የሚከተሉት ሲሆን፣ ዓላማውም ብድርና ርጥባን የሚሰጡ ምዕራባውያንን

‹ለመግዛት› ያለመ ነው፡፡ የኋለኞቹም እነዚህ ድንጋጌዎች ለለበጣ እንደገቡ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ የወያኔን ሰነድ 3 እጅ ገደማ የሚይዙት እነዚህ ድንጋጌዎች ከወያኔ ሰነድ ብናወጣቸው (በተግባር የወጡ ስለሆነ) ‹ወረቀቱ› ዕርቃኑን ይቀርና የወያኔን እኩይ ዓላማ የሚያጋልጥ ይሆናል፡፡ ይህ ሰነድ አሁንም ደግሜ እናገራለሁ የኢትዮጵያ ሕዝብ መተዳደሪያና ከመረጠው መንግሥት ጋር የተፈጣጠመው ጽኑ ቃል ኪዳን/ማኅበራዊ ውል ሳይሆን አንድ ወያኔ የሚባል ዘረኛ ቡድን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጫነው የባርነት ደብዳቤ ነው፡፡ ሥርዓታዊ ወይም መሠረታዊ ለውጥ ተደርጓል ለማለትም ውኃ ልኩ ይህ የወያኔ ሰነድ ሕዝባችን አምኖበት በሚያፀድቀው ሕገ ኢትዮጵያ ሲተካ ነው፡፡

ስለሆነም ይህን የ‹ዕዳ ደብዳቤ› ማሻሻል ባርነቱ በከፊል እንዲቀጥል መስማማት ነው፡፡ ከባርነት ነፃ ለመውጣት ከፈለግን የ‹ዕዳ ደብዳቤው› መፋቅ፣ ተቀዳዶ መጣል ነው ያለበት፡፡ በምትኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወያይቶና መክሮበት በሕዝበ ውሳኔ የሚያፀድቀው ሕገ-ኢትዮጵያ ወይም ‹ርእሰ ሕግጋት› በባለሙያዎችና ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሚወከሉ ኢትዮጵያውያን በሚገኙበት ጉባኤ መጻፍ እንዳለበት ጽኑ እምነቴ ነው፡፡ ስለ ሽግግርም፣ ምርጫም የምንናገረው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ ለዚህም ነው ባገር ውስጥም በውጭም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስለ አገራዊ የሽግግር ጉባኤ አስፈላጊነት ደጋግመውና አጥብቀው የሚናገሩት፡፡ አገርን ለማረጋጋት፣ በአንኳር አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመግባባት፣ አዲስ ሕገ መንግሥት ለመጻፍ፣ ብሔራዊ ዕርቅ ለማድረግ፣ ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብ ፍትሕ ለማስፈን፣ አገራዊ ምጣኔ ሀብት እንዲያገግም (አጣዳፊ የሆነውን ሥራ አጥነትን ለመቀነስና የኑሮ ውድነትን በመጠኑ ለማርገብ) ለማድረግ ወዘተ. ብሔራዊ የሽግግር ጉባኤ ያስፈልገናል፡፡ ዐቢይ እኔ አሻግራችኋለሁ የሚለው ግትርነት የማይቻልበት ደረጃ እንደደረሰ በቂ ምልክቶች እያያን በመሆኑ፣ በመንደርተኞች ተከቦ ማሸጋገሩን ተግባራዊ ለማድረግ እንደማይቻል ከማንም በላይ ስለሚያውቅ፣ እያሽቆለቆለ ያለውን ተቀባይነቱን ለማደስም ሆነ የዐቢይን አገዛዝ ማገዝ የሚቻለው በዚህ መልኩ ይመስለኛል፡፡ አገራዊ የሽግግር ጉባኤ በማድረግና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል በሚያሳትፍ ምክክር፡፡

ይህን የወያኔ ሰነድ ተቀብለው ስለ ሽግግርም ሆነ ምርጫ የሚያወሩ የጐሣ ፖለቲካ ስብስቦችና ሌሎችም ከጐሣ ውጭ ተደራጅተናል የሚሉ የፖለቲካ ቡድኖች ‹ሕገ መንግሥት› እያሉ የሚጠሩትን ሰነድ ይዘት በውል ተረድተውት ከሆነ፣ የወያኔ ተቀጽላ በመሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ባልካዱት ነበር፡፡ ከመነሻውም የመታገያና ተቃውሞ አጀንዳቸው ይሄ ካልሆነ የእነሱም ዓላማ እንደ ኦነጋውያን ኦሕዴዶች ወር ተረኞች ለመሆን ነው ብሎ መገመቱ ስህተት ይሆን?

በየትኛውም መስክ የምንሰማራ ኢትዮጵያውያን፣ ለዚህ አገር በታኝ ሰነድ ታማኝነትን በቃልም ሆነ በጽሑፍ መግለጽ ውድ አገራችንን እና ሕዝቧን መካድ ነው፡፡ በተግባር ስናየው ኢትዮጵያ ባለፉት 28 ዓመታት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት (de facto constitutional order) አልነበራትም፡፡ አሁንም የላትም፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን የወያኔ መግለጫ እንደ ሕገ መንግሥት ለመቀበል ቢያንስ ሞራላዊ ግዴታ የለብንም፡፡

የወያኔ ሰነድ ዐቢይ ባገር ደረጃ ‹ለውጥ› ብሎ የሚያስበው ዓይነት የጥገና ለውጥ አይደለም የሚፈልገው፡፡ በእኔ እምነት አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኔ ነው ብሎ በባለቤትነት የማያየውና ታማኝነቱን የማይገልጽለት ሰነድ መሻሻል ሳይሆን ባዲስ መቀየር/መተካት ነው ያለበት፡፡

* የወያኔ የማስመሰያ ‹‹ሕገ መንግሥት›› (façade constitution) ፤ በማር የተለወሰ እሬት [ከይኄይስ እውነቱ] 29/11/2016 |
https://www.ethioreference.com/archives/7242፤
– እውን የወያኔ የይስሙላ ‹‹ሕገ መንግሥት›› ችግር አንቀጽ 39 ብቻ ነው? [ከይኄይስ እውነቱ] Posted by admin
16/04/2018 http://www.zehabesha.com/amharic/archives/89902፤
– አገር በአንድ ጠንቀኛ ‹‹ሰነድ›› ምክንያት ስትጠፋ እያየን እንዴት ዝም እንላለን? (ከይኄይስ እውነቱ) Posted by admin March 18,
2019 https://www.ethioreference.com/archives/16899

Filed in: Amharic