>

አጼ ኃይለ ሥላሴና ዘመናዊ ትምህርት በአንዳርጋቸው ጽጌ እይታ!!! (ሲሳይ ተፈራ መኮንን) 

አጼ ኃይለ ሥላሴና ዘመናዊ ትምህርት በአንዳርጋቸው ጽጌ እይታ!!!
ሲሳይ ተፈራ መኮንን 
አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመናዊ ትምህርት ለማስፋፋት ያደረጉት ጥረት አሁን አሁን በኔ ትውልድ እየታወቀ መጥቷል፡፡ በመጀመሪያው ዘመን መሳፍንቱና መኳንንቱ ከቤተክህነት ጋር በመመሳጠር ዘመናዊ ት/ት አገሩን ካቶሊክ ሊያደርገው ነው እያሉ ት/ት እንዳይስፋፋ እንቅፋት ሆነዋል፡፡
አጼው ተቃውሞ ሳይፈሩ በትዕዛዝና በማስገደድ ት/ቤቶችን መክፈትና ተማሪዎችን መመልመል የቻሉት በራሳቸው ሙሉ ቁጥጥር ስር በነበሩት በሸዋና በሐረር ጠቅላይ ግዛቶች ነበር፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሳይቀር ተማሪ ለማግኘት የነበረውን ችግር ታዋቂው ክብደት አንሺና የስፖርት ሰው ግርማ ቸሩ በአንድ ወቅት እንደሚከተለው ገልጾታል፣
“መሀል አዲስ አበባ ከአባቴ ጋር እየሄድኩ ነበር፡፡ ወታደሮቹ ከአባቴ እጅ መንጭቀው በጉልበት ወሰዱኝ፡፡ ከዛም ተፈሪ መኮንን ት/ቤት አዳሪ ተማሪ ተደረግኩ፡፡ የኪስ ገንዘብ እየሰጡ በከፍተኛ ቅንጦት አንደላቀው አስተማሩን፡፡”
በኃይለ ሥላሴ ዘመን ከአገሪቱ የመጀመሪያ ምሁራን አብዛኞቹ የሸዋ ሰዎች የሆኑት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በሌሎች መሳፍንት ቁጥጥር ስር በነበሩ ጠቅላይ ግዛቶች በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ ኃይለ ሥላሴ እንኳን ት/ቤት መክፈትና ተማሪ መመልመል፣ የጉምሩክ ታክስ መሰብሰብ አይችሉም ነበር፡፡ በሸዋም ቢሆን የደሃ ልጆችን ነበር በቀላሉ ማስገደድ ወይም ማባበል የሚቻለው፡፡
ከሸዋ ውጭ ኤርትራውያን ተማሪዎች በዝተው የተገኙበት ምክንያትም የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት ከነበረችው ኤርትራ የመጡ ወላጆች የትምህርትን ጥቅም አስቀድመው በመገንዘባቸው፣ ልጆቻቸውን ወደ ት/ቤት ለመላክ ብዙ ግፊት የማያስፈልጋቸው ስለነበሩ ነው፡፡
የኃይለ ሥላሴ ዘመናዊ የሲቪልና የሚሊቴሪ ቢሮክራሲ በአብዛኛው በሸዋ ሰዎች የተሞላው ተማሪዎች ሆነን እንደምናስበው፣ የአጼው መንግስት ዘረኛ በሆነ መንገድ ቢሮክራሲውን በሸዋ ሰዎች በተለይም በሸዋ አማሮች ለመሙላት በማሰቡ አልነበረም፡፡ ሥርአቱ ማስተማር የቻለው የሸዋን ደሃ ልጆች በመሆኑ ነበር፡፡ የሸዋ ሰዎች የምለው ከሸዋ አማራ ውጭ የሸዋ ኦሮሞዎችና ከሁለቱ ብሄሮች የተወለዱ በርካታ ምሁራን በቢሮክራሲው ውስጥ ይገኙ ስለነበር ነው፡፡
ሥርአቱ ከሌሎች አካባቢዎችና ብሄሮች ባጋጣሚ ያስተማራቸውን ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ ስልጣን የሰጣቸው ስለመሆኑም በቂ ማስረጃ አለ፡፡ በኃይለ ሥላሴ ቢሮክራሲ ውስጥ ለጎጃም፣ ለጎንደርና ለትግራይ ምሁራን አነስተኛነት ተጠያቂዎቹ ኋላቀር የነበሩት የአካባቢው መሳፍንትና መኳንንት እንጂ የኃይለ ሥላሴ መንግስት አይደለም፡፡ የጎጃምና የጎንደር ምሁራን እንደ ትግራይ ምሁራን ቀደም ባለው ቢሮክራሲ ውስጥ አለመታየታቸውም፣ ጉዳዩ የአማራነት ላለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ ነው፡፡
አጼ ኃይለ ሥላሴ የተማረ ሰው ካገኙ ስራ ለመስጠት ብቻ ሳይሆን፣ በተለይም በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ሃሳቡንም ለማዳመጥ ዝግጁ ነበሩ፡፡ በጀርመን አገር የተማረውን የታዋቂውን የትግራይ ምሁር የነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝን መንግስትና አስተዳደር የሚል ድንቅ መጽሀፍ አሳትመው ማንበብ የሚችል ሁሉ እንዲያነበው ያሰራጩት ኃይለ ሥላሴ ናቸው፡፡
ከኤርትራ የፌዴሬሽን ውህደት በፊት 1600 የሚሆኑ ኤርትራውያን በኃይለ ሥላሴ መንግስት የአስተዳደር ስልጣን ላይ የነበሩ ሲሆን አንዳንዶቹም በኃይለ ሥላሴ ለት/ት ወደ ውጭ አገር ተልከው በሚኒስትርነት ጭምር ያገለገሉ ነበሩ፡፡ ይህም ጉዳዩ የዘር ላለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ ነው፡፡
አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር፣ ገጽ 202-205
Filed in: Amharic