>

"መንግስት" አማራው እንዲረጋጋ አይፈልግም! (ጌታቸው ሽፈራው)

“መንግስት” አማራው እንዲረጋጋ አይፈልግም!
ጌታቸው ሽፈራው
ሰኔ 15/2011 ዓ/ም ባሕርዳር ላይ የተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት አማራውን ትልቅ ፈተና ላይ የጣለ ነው። ሰኔ 16/2011 ዓ/ም ሕዝብ ውዥንብር ውስጥ እንዳይገባ  ወጣቶች፣ አክቲቪስቶች እንዲሁም ከአሁን ቀደም ደፍረን የማንደውልላቸው ካድሬዎች ጋር ሳይቀር እየደወልን ሕዝብን እንዲያረጋጉ ጠይቀናል። ይህን ስናደርግ በግልፅ ነበር።  ይህን የሰማው “መንግስት” ታዲያ ወዳለንበት በርካታ ክትትሎችን ላከብን። በምንሄድበት ሁሉ እየተከተሉ ሲያዋክቡን ዋሉ። በ17/2011 ዓ/ም ወደኔ ቤት መጥተው ሲፈልጉ እንደነበር ሰማሁ። ከቀናት በኋላ በሪሁን አዳነ፣ ጌታቸው አምባቸው፣ ሲሳይ አልታሰብን ጨምሮ ብዙዎቹን እንዳሰሯቸው ሰማሁ። ቀሪዎቹን አሁንም እያዋከቧቸው ነው። ይህ የሆነው አማራው እንዳይረጋጋ በሚፈልጉት ተረኞች ነው።
እነ ጄኔራል ተፈራ ማሞ፣ ኮ/ል አለበል አማረና ሌሎች ከፍተኛ የአማራ ክልል ፀጥታ ኃላፊዎች ሰኔ 15 ታግተው እንደነበር ይታወቃል። አንዳንዶቹ ከሞት በተአምር ያመለጡ ናቸው።  እነዚህ ኃላፊዎች አጣዬ፣ ከሚሴና አካባቢው በነበረው ጥቃት ከተረኞቹ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብተዋል። ከታሳሪዎቺ መካከል አንደኛው “እኔ  የታሰርኩት በኦሮሞ መኮንኖች ጫና ነው” ብሎ እንደተናገረ ከታማኝ ምንጭ ተሰምቷል። እነ ተፈራ ማሞ፣ አለበል አማረ ከተፈጠረው ጉዳይ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው የሚታወቅ ነው። የታሰሩት  የፀጥታ መዋቅሩን አደራጅተው ማረጋጋት ስለሚችሉ ነው። የታሰሩት አማራው እንዳይረጋጋ ስለሚፈለግ ነው።
ከሰኔ 15 ጀምሮ ፋኖን ማሳደድ ተጀምሯል። ልዩ ኃይሉ እርስ በእርስ ግጭት ውስጥ እንዲገባ ብዙ እኩይ ስራ ተሞክሯል።  ፋኖ እና ልዩ ኃይል የመከላከያ ሰራዊቱ ላይ፣ የአካባቢው አስተዳደር ላይ ጥቃት ይፈፅሟል የሚል የሀሰት ዜና ሲናፈስ ሰንብቷል። ዋናው አላማ ጥቃት ይፈፀምባችኋል የተባሉ አካላት   በሕዝብና በሕዝብ መከታ ላይ ኃይል  እንዲጠቀሙ ነው። በዚህ ሰበብ አማራው እንዲበጣበጥ ነው። አማራው እንዳይረጋጋ ነው።
ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ሕዝብ ጉዳዩን ተረጋግቶ  እያሳለፈው ነው።  በሀዘን ውስጥ ሆኖ ስሜቱን ተቆጣጥሯል። ከዛሬው ሀዘን በላይ የነገውን አይቶ ተረጋግቷል። የአማራ ሕዝብ ታላቅነቱን ያሳየበት ወቅትም ነው።  ሆኖም መንግስት ነኝ የሚለው አካል የአማራውን መረጋጋት እንደማይፈልገው ታይቷል። አማራው ላይ የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅሞ የሚተቹትን፣ የሚያደራጁትን አስሯል። የገቢዎች ሚኒስትር አማራን እያገለለ መሆኑን ተጨባጭ መረጃ ይዞ ያጋለጠውን ማስተዋል አረጋን ጨምሮ በርካቶችን ስለ አማራ በመከራከራቸው ጊዜ ጠብቆ አስሯቸዋል። አጋጣሚውን ተጠቅሞ አሥራትንና መሰል ሚዲያዎችን ለማዳከም እየጣረ ነው። ኦሮሚያ ውስጥም በርካታ አማራዎች አፈና ውስጥ ናቸው። መንግስት ነኝ የሚለው የፈለገው አማራው ከሀዘኑ ባሻገር የሚደርስበትን አፈና ምሬት  እርስ በእርስ ሌላ ውጥንቅጥ ውስጥ እንዲገባ ነው። መንግስት ነኝ የሚለው አካል የፈለገው አማራውን በሀዘኑ ወቅት አንገቱን አስደፍቶ ቀና እንዳይል ማድረግ ነው። አማራው ግን ተረኞቹና የተባረሩት ጠላቶቹ እንዳሰቡት ለሌላ ውድቀት አልሆነም።  ታላቅነቱን በማሳየት  ላይ ነው።
በጠብ ሲፈላለጉ የነበሩት የትህነግ እና የኦነግ ጥላቻ መር ኃይሎች በአማራው ላይ የተፈጠረው ክስተት አንድ አድርጓቸዋል። ባለጊዜዎቹና የተባረሩት በአንድ መንፈስ የሚሰጡት መግለጫ የሚያሳየው ይሄ ነው። ተግባራቸው እያሳየን ያለው ተመሳሳይ ነው። አማራው እንዳይረጋጋ ማድረግ ነው!
በእርግጥ ከእነዚህ አማራ ጠል ኃይሎች ምንም አይጠበቅም። የሚጠበቀው ለአማራ ቆመናል ከሚሉትና ከአማራ ወዳጆች ነው። በተለይ ለአማራ ቆመናል የሚሉት ከሕዝብም ልቀው መገኘት አለባቸው። እስካሁን ከፍታ ላይ ያለው ሕዝብ ነው። አማራ ጠሎች እያደረጉት ያለውን እያየ፣ ከዛሬው ባለፈ ለነገ የሚደገሰውን እያወቀ በሰሞኑ እርስ በእርሱ የሚናቆር ሁሉ እታገልለታለሁ ከሚለው ሕዝብ ልዕልና እና ታላቅነት መማር ይገባዋል። ወቅቱን ተጠቅመው አማራውን አንገቱን ማስደፋት የሚፈልጉትን አካላት ሴራ ወደጎን ብሎ በሟችና ገዳይ መካከል ጎራ ከፍሎ፣  ከኋላ ያሉትን ሴራዎች ረስቶ ጉንጩን የሚያለፋ ካለ ለአማራ ሕዝብ የመቆም ሞራል እንደሌለው ማወቅ ይገባዋል። ሕዝብ ከያዘው ልዕልና ዝቅ ብሎ ለሕዝብ መቆም፣ መታገል አጉል ነው።  የአማራ ሕዝብ ሌላ የጥፋት ድግስ፣ የከፋፍለህ ግዛ እቅድ በወጣለት ወቅት እርስ በእርሱ ድንጋይ የሚወራወር ካለ እርሱ ከሟቾቹ የባሰ ሙት ነው። ብዙ ሴራ ለሚጠብቀው ሕዝብ ከገዳዮች በላይ ገዳይ፣ ከአደናቃፊዎቹ በላይ ጠላፊ ነው።
 የመረጃ ክፍተት ያመጣቸውን የአመለካከት ልዩነቶች ችሎ ሕዝብ ላይ የተደገሰውን መመከት ላይ ትኩረት የማያደርግ ለአማራ ጠሎች መሳርያ ከመሆን ባለፈ ለአማራ ሊፈይድ አይችልም። ለአማራ የተደገሰውን ለማለፍ ይችል ዘንድ ስሜቱን ማረቅ የማይችል አማራ ጠሎች አማራን ለማነቅ የሚጠቀሙበት ገመድ ከመሆን ባለፈ አማራን ማዳን አይቻለውም።
የሴራው ዳራ፣ በሴራው የተሳተፉ አካላትና ሌሎቹም ይፋ የሚወጡበት ጊዜ ሩቅ አይደም። ለአማራ ቆሜያለሁ የሚል ሁሉ ማተኮር ያለበት ግን አማራ ሌላ የአገዛዝ ቀንበር ውስጥ እንዳይገባ በተደነቀነው ፈተና ላይ በማተኮር ነው። የእርስ በእርስ ንትርኩ እነ በሪሁንን፣ እነ ጌታቸውን፣ እነ  ማስተዋልን እንዳይታሰሩ አልታደጋቸውም። በየቦታው የሚታሰሩትን፣ የሚገደሉትን አይታደጋቸውም።  እርስ በእርስ መጨቃጨቁ ገዥዎች  ወቅቱን ተጠቅመው አማራውን ሌላ የአገዛዝ ቀንበር ውስጥ እንዲያስገቡ እድልና ኃይል ከመሆን ባለፈ አምባቸውንም ሆነ አሳምነውን ወደሕይወት አይመልሳቸውም። ለአማራውም ፋይዳ የለውም።  እንዲያውም ለአማራው ሌላ እዳ ነው፣ ሸክም ነው። በዚህ ወቅት በሞቱት አማራዎች መካከል ጎራ ለይቶ መጨቃጨቅ ከሞቱት በባሰ በቁም የሞሞት ያህል ነው።
በቁም ከመሞት ያድነን!
ለህዝባችን ሸክምና የሌሎች መጠቀሚያ ከመሆን ያድነን!
 አማራ በገዥዎቹ ተጨማሪ የጥቃት ድግስ በታሰበበት ወቅት እንታገልለታለን እያልን ተጨማሪ እዳ ከመሆን ያድነን!
(ፎቶው ሕዝብን ለማረጋጋት ሲሰሩ የታሰሩት የጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ እና ጌታቸው አምባቸው ነው።)
Filed in: Amharic