>

ሕወሓት የትግራይ ሕዝብን የማይወክል ከሆነ ሌሎቹ የወያኔ ድርጅቶች እንዴት የሕዝብ ወኪል ሊሆኑ ይችላሉ? (ከይኄይስ እውነቱ)

ሕወሓት የትግራይ ሕዝብን የማይወክል ከሆነ ሌሎቹ የወያኔ ድርጅቶች እንዴት የሕዝብ ወኪል ሊሆኑ ይችላሉ?

ከይኄይስ እውነቱ

ሰሞኑን ዐቢይ ዜና ሆኖ የሰነበተው የወያኔ (ኢሕአዴግ) ባለሥልጣናት ግድያ ጉዳይ ነው፡፡ በባለሥልጣኖቹ ግድያ ዙሪያ ሁሉም የመሰለውን ይቀበጣጥርና የአንድ ሰሞን ግርግር ሆኖ ያልፋል፡፡ ቀደም ባለ አስተያየቴ እንደገለጽኹት የወያኔ መንግሥት መሠረቱም ጉልላቱም ውሸት ነው፡፡ ድርጅቱ እንደ ግብር አባቱ ዲያቢሎስ ሐሰትን ከራሱ አንቅቶ የሚናገር ለመሆኑ ያለፉት 28 ዓመታት ጉልህ ምስክሮች ናቸው፡፡ በዋናነት በተቆጣጠረው የሕዝብ ብዙኃን መገናኛዎች እና የአገዛዙ አፈ ቀላጤ በሆኑ በዚሁ ነውረኛ ድርጅት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ባለቤትነት ሥር በሚገኙ ዉኁዳን መገናኛዎች ባደባባይ ሲዋሹና ሕዝብንም ውሸት ሲያለማምዱ ኖረዋል፡፡ በዚህ ረገድ ቤተመንግሥቱም፣ ቤተመስጂዱም፣ ቤተክህነቱም ተካክለው ሐሰት በኢትዮጵያ ምድር እንዲነግሥና ኅብረተሰባችን ሐሰት/ቅጥፈትን እንደ ነውር ሳይሆን መልካም እሤት ገንዘቡ እንዲያደርጋቸው ሆኗል፡፡ በመሆኑም ዛሬ ሐሰት ሳይጎረብጠው የሚናገር ትውልድ አፍርተናል፡፡ ከመነሻው መንግሥትም ሆነ አመዛኙ ኅብረተሰብ እውነትን ይፈልጋል ወይ? እኔ እጠራጠራለሁ፡፡ ባጭሩ ለማለት የፈለግኩት በወያኔ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት በርካታ የተፈጸሙ ግፎችና በደሎች፣ ሁነቶችና ‹ድንገቶች› ተድበስብሰው አልፈዋል፡፡ የወያኔን አገዛዝ ካለባሕርይው እውነትን አጣርቶ ለሕዝብ እንዲያስታውቅ መጠበቅ አሁንም አላወቅነውም ማለት ነው፡፡ ድርጅቱን ወያኔ ትግሬ (ሕወሓት) መራው ወይም ‹ወያኔ ኦሮሞ› (ኦሕዴድ) መራው ልዩነት አያመጣም፡፡ ስለሆነም በግሌ ገዳዮች ይፋ ይሆናሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ገለልተኛና ነፃ አካል ያጣራል የሚልም እምነት የለኝም፡፡ አንዳንዶች የውጭ ኃይል ጣልቃ እንዲገባ ይፈልጋሉ፡፡ እውነት ገለልተኛና ነፃ የውጭ ኃይል አለ? ከተፈጠረው ‹ድንገት› ጋር ተያይዞ በቅርቡ አንድ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላት፣ ልጡ የራሰ ጉደጓዱ የተማሰ ፣ የእንጨት ሽበት የተሸከመና ቀላል ‹ሽማግሌ› አንድ ነገድን በሙሉ ሲዘልፍ አስተውለናል፡፡ አሳቡ የግሉ ብቻ ነው ለማለት አንደፍርም፡፡

የባለሥልጣኖቹን ሞት ለጊዜው ወደጎን አድርገን እስቲ ለአፍታ ትኩረታችንን በዚህ ነውረኛ ድርጅት/‹ግንባር› ላይ እናድርግ፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የትግራይ ሕዝብንና ሕወሓትን አንድ አድርጎ አይመለከትም፤ የሕዝቡም ወኪል ነው ብሎ አያምንም፡፡ ይህ ማለት ግን (በመንደርተኝነትም ሆነ በጥቅም ምክንያት) በርካታ ተከታዮች የሉትም ማለት አይደለም፡፡ ሳናሰምርበት የማናልፈው እውነት ግን በየትኛውም መመዘኛ የትግራይ ሕዝብ ወኪል አይደለም፡፡ ይህ አባባል በተመሳሳይ መልኩ ለኦሕዴድ፣ ብአዴን እና ለደሕዴን ይሠራል፡፡ በሕዝብ ላይ በጉልበት የተጫኑ ኃይሎች በየትኛውም መሥፈርት የሕዝብ እንደራሴዎች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እነዚህ ድርጅቶች የሕወሓት አሽከሮች ሆነው ወክለነዋል የሚሉትን ሕዝብ በገፍ ሲገሉ፣ ሲያስሩ፣ ዕርቃኑን አስቀርተው ሲዘርፉ፣ ባጠቃላይ ለመናገር የሚከብድ ግፍና በደል ሲፈጽሙበት መኖራቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ አሁንም በውንብድናቸው ለመቀጠላቸው በርካታ ምልክቶች አሉ፡፡ ባገራችን ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሥርዓተ አልበኝነት የነገሠው በነዚሁ እውነተኛና መሠረታዊ ለውጥ በማይፈልጉ የ‹ግንባሩ› ኃይሎችና ባደራጇቸው አሸባሪ ቡድኖች ነው፡፡ እኔ ከዝንጀሮ ‹ቆንጆ› (ከዘረኞች÷ መንደርተኞች÷ ሤረኞች÷ በተረኝነት መንፈስ ለግድያና ለዝርፊያ ካሰፈሰፉ ኃይሎች) መካከል መምረጥ አልፈልግም፡፡ የሕግ ባሉሙያ ባልሆኑ ሰዎች አነጋገር ልጠቀምና በነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ያሉና የነበሩ ከላይ እስከ ታች በአመራርነት የተቀመጡ አብዛኞቹ ግለሰቦች (የመጠን ልዩነት ካልሆነ በቀር) በወንጀል የተዘፈቁ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም (ለፍርድ መቅረባቸው ቀርቶ) በዐቢይ አገዛዝ ውስጥ ዋና ተዋናዮች ናቸው፡፡

ስለሆነም በግለሰብ ደረጃ ጥቂቶች እዚህም እዚያም በጎ ለማድረግ ፈቃደኝነት ያላቸው፣ ለሕዝብ በመሥራት ለመካስ የሚያስቡ መኖራቸው፣ በግንባሩ የታቀፉትን አራት ድርጅቶች እንደ ፖለቲካ ተቋም ከሥርዓት÷ ከመዋቅር÷ ከአመለካከት÷ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለማጥፋት በጻፉት ‹ሕገ አራዊት› ላይ ባላቸው አቋም ወዘተ. ልዩነት የላቸውም፡፡ በመሆኑም ሥልጣናቸውንና በዚህም የሚገኘውን የማይገባ ዝርፊያ ለማስጠበቅ ካልሆነ የይስሙላ ‹ሕገ መንግሠታቸውን› እንኳ መሠረት አድርገው ሳይወክሉት ወክለነዋል የሚሉትን ማኅበረሰብ/ነገድ/ጐሣ ደኅንነትና ጥቅም ማስጠበቅና ማስከበር አልቻሉም፤ አይችሉም፡፡ ተቀባይነትን ፍለጋ ግን በጐሣ/ነገዳቸው ስም ከመነገደ ወደኋላ አይሉም፡፡ እውነቱን ለመናገር ሕወሓትን ሳንጨምር (እሱ ፈጣሪያቸው በመሆኑ) በወራድነት ደረጃ ብናስቀምጣቸው ብአዴን የሚባለው እጅግ ነውረኛና ወራዳ ድርጅት ነው፡፡ ስለሆነም ሳይወክለው እወክለዋለሁ ከሚለው ማኅበረሰብ/ነገድ ጋር ባይያያዝ መልካም ይመስለኛል፡፡ የድርጅቱን ተግባርም ሆነ በአመራርና ተራ አባላቱ የሚፈጽሙት ድርጊቶች ከአንድ ማኅበረሰብ/ነገድ ታሪክ፣ ባህል፣ ትውፊት፣ እሤቶች፣ ምንነትና ማንነት ጋር ተያያዥነት ያለው አድርጎ (ለዚህ ማኅበረሰብ/ነገድ የማይመጥን እያሉ ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጥሎ) የሚሰጡ መግለጫዎችም ሆኑ የሚደመጡ ንግግሮች ተገቢነት የላቸውም፡፡ ለዚህ ሁሉ ጠንቁ ወያኔ ዜግነትን አጥፍቶ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ የአገር ባለቤትነት/ሉዐላዊነት ነጥቆ መያዣ መጨበጫ ለሌለው ‹ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› ለሚል ጣዖት መስጠቱና የኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገራትን በጐሣና በቋንቋ ሸንሽኖ ‹ክልል› የሚባል ክፉ ደዌ መትከሉ ነው፡፡ሐሕሐ

Filed in: Amharic