>
5:13 pm - Sunday April 20, 2679

የባህርዳሩ ጉዳይ፤ እውነትን እና የግምት ትርክቶቻችንን አንደበላልቃቸው!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የባህርዳሩ ጉዳይ፤ እውነትን እና የግምት ትርክቶቻችንን አንደበላልቃቸው!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
በአንድ ክስተት ዙሪያ ያለ እውነት ያለ ማስረጃ ወሬ ነው የሚሆነው። ለወሬ ማስረጃ አያስፈልግም። ለእውነት ግን ማስረጃ የግድ ይላል። የወሬ ክምር ማስረጃ ወይም እውነት አይሆንም። በደመነፍስ እየተነሱ ግልብ የሆነ መያዣ እና መጨበጫ የሌለው፣ በበቂና ትክክለኛ ማስረጃ ያልተደገፈ ነገር ግን ጥርጣሬ ላይ ብቻ የተመሰረተ ትንታኔም ሆነ እርግጠኛ ሆኖ የሚደረግ መደምደሚያ ለትልቅ ስህተት ይዳርጋል። ከዛም በላይ ጉዳዩ የሰዎች ሕይወት የጠፋበትም ጭምር ስለሆነ በርካቶችን ወደተሳሳተ መደምደሚያ፣ እልህ፣ ቁጭትና ጥላቻ ውስጥም ይከታል። መንግስት እና ሕዝብ በማይተማመኑበት አገር ደግሞ ይህ አይነቱ ችግር ሌሎች የፖለቲካም ዳፋዎች አሉት።
በባህርዳሩ ግድያ አንዳንድ መረጃዎች መውጣት ጀምረዋል። አሁንም ግን ውዥንብሩ እንደቀጠለ ነው። ብዙ ግዜ በአንድ ክስተት ዙሪያ የሚነሱ የተለያየ ጫፍ እረገጥ እና የሚጋጩ እውነታዎች መነሻቸው የማስረጃ ክፍተት ነው። የተፈጠሩትን የማስረጃ ክፍተቶች ሁሉም ከራሱ ግንዛቤ፣ የእውቀት ደረጃ፣ ለጉዳዩ ካለው ቅርበት እና ተቆርቋሪነት ወይም ወገንተኝነት ተነስቶ የራሱን ጥርጣሬም ወደ ታሪክ ቀይሮ የማስረጃውን ክፍተት ለመሙላት እና ሙሉ ስዕል ለመፍጠር ይጥራል። በዚህም የተነሳ በአንድ ክስተት ውስጥ ብዙ ትርክቶች እንደ እውነት ሊቀርቡ ይችላሉ። ሰሞኑን እየሆነም ያለው ይሔው ነው።
ከበርካታ ሰዎች ጋር በዚህ ጉዳይ አውርቻለሁ። ሁሉም አንድ እና ከአንድ በላይ የሆኑ ጥርጣሬዎች ስላሏቸው ስለ ክስተቱ የተለያየ አረዳድና መደምደሚያ ነው ያላቸው። አንዳቸውም ግን ለሚናገሩት ነገር ከጥርጣሬ እና ከየቦታው ከቃረሙት ወሬ ውጪ አንዳችም አሳማኝ ማስረጃ በጃቸው የለም። ስለዚህ አብዛኛው ትርክ ከወሬ የዘለለ ፋይዳ የለውም።
እንደ አገር፣ እንደ ሕዝብ እና እንደ መንግስት ከዚህ ክስተት ብዙ ነገሮችን መማር ይቻላል።
+ በመንግስት በኩል ያለው ችግር በአንድ ወይ በሌላ ምክንያት እንዲህ ያሉ አሳሳቢ አገራዊ ችግሮች ሲገጥሙት የመጀመሪያው እንቅስቃሴ መረጃዎችን መደበቅ እና እሱ በሚፈልገው መጠን እና ልክ ብቻ እየቆነጠበ ለሕዝብ ማሳወቅ ነው። አንዳንዴ ያጋንናል፣ አንዳንዴ ዋናውን ታሪክ ሸፋፍኖ ሌላ ታሪክ ይናገራል፣ አንዳንዴ እውነታውን አኮስሶ ምንም እንዳልተፈጠረ ያህል ያስመስላል። ባጭሩ ባለፉት አስርት አመታት የነበሩት መንግስታት ሕዝብን ሲዋሹ እና ሲቀጥፉ ሕዝብ በአንክሮ ይከታተል ስለነበር መንግስት ላይ እምነት የለውም።
+ አዲሶቹ የለውጥ አራማጆች ይህን የቆየ ችግር ይቀርፉታል የሚል ተስፋ ነበረኝ። ይሁንና እየሆነ ያለው ግን ያንኑ የመጣንበትን የመሸፋፈ ወይም የመደበቅ አባዜ የሚያጠናክር ይመስላ። በመንግስት አላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ሁሌም እራሳቸውን የሕዝብ ሞግዚት አድርገው መቁጠራቸውም ይመስለኛ ሕዝብ ምን ማወቅ እንዳለበት እና እንደሌለበት፤ በምን ግዜ ማወቅ እንዳለበት እራሳቸውን ወሳኝ አድርገው የሚቆጥሩት። ይሄ እጅግ የተሳሳተ እና በሰለጠኑት አለም ተቀባይነት የሌለው የሞግዚት ልሁን ባህሪ በአግባቡ ሊስተካከል ይገባል። ለአገር ደህንነት ሲባል ከሚያዙ ቁልፍ ሚስጥሮች ውጪ የአደባባይ ክስተት ከሕዝብ አይደበቅም። ለእዚህ አንድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው፤ ከወራቶች በፊት ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሯቸው ድረስ የሄዱ ታጣቂ ወታደሮችን አባብለው ከመለሱ በኋላ ለሕዝብ የሰጡት መግለጫ እና ከክስተቱ ሳምንታት በኋላ ፓርላማ ቀርበው ነገሩ መፈንቅለ መንግስት እንደ ነበር መግለጻቸው ጥሩ ማሳያ ነው። ይህ አይነቱ ልማድ የእረኛውን እና የቀበሮውን ታሪክ ነው የሚያስታውሰኝ። ትላንት ለቅን እሳቤ ብሎ የዋሸን ሰው ዛሬም ቅን አስቦ ወይም በሌላ ምክንያት ላለመዋሸቱ ሕዝብ ዋስትና ይፈልጋል። አጉል ልማድ አጉል ግንዛቤን ይፈጥራል።
+  ሌላው ትልቁ ችግር በምሁራኖቻችን፣ በጋዜጠኞቻችን፣ በመብት አቀንቃኞች እና በመገናኛ ብዙሃን በኩል ለመረጃ እና ማስረጃ የተሰጠው እጅግ የወረደ ግምት ነው። በዚህም ሆነ በሌሎች በርካታ አገራዊ ጉዳዮች ላይ እነዚህ የህብረተሰቡ ወሳኝ ክፍሎች የሚያደርጓቸው ትንተናዎች፣ ውይይቶች፣ ማብራሪያዎች፣ ዜናዎች እና የሚያሰራጯቸው ጽሁፎች ብዙን ጊዜ በበቂ መረጃዎች ያልተደገቡ እና ለማስረጃ ክብደትም ምንም ቦታ የማይሰጡ፤ አንዳንዴም የደመነፍስ ትንታኔዎች መሆናቸው ሕዝቡን ግራ እንዲጋባ እና በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮችም ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ፤ ወሬን፣ አሉባልታን እና የሸር ትንታኔን እውቀት አድርጎ እንዲይዝ የሚገፋፉ ናቸው። እውነት በየሜዳው ወድቃ ስለማትገኝ ልፈትን፣ ምርምርን እና እንቅል አጥቶ መስራትን ትጠይቃለች። ሰነፍ ልሂቃን ይህን ዋጋ መክፈል ስለሚከብዳቸው የራሳቸውን ግምት እና ጥርጣሬ እንደ እውቀት አድርገው ለማህበረሰቡ ያቀርባሉ። ሰነፍ ልሂቃን ከሚመራመሩበት እና እውነትን ለመፈለግ ከሚያጠፉት ጊዜ ይልቅ የሚያወሩበት ጊዜ ይበዛል። የፖለቲካ እና የሲቪክ ምህዳሩ በሰነፍ ልሂቃን የተወረረ አገር ከፖለቲካውም ሆነ ከኢኮኖሚ ቁስሉ ቶሎ አይሽርም።
+ ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ የሚፈጸሙ ነገሮችን በወቅቱ የማወቅ መብት አለው። ያንን መብቱን መንፈግ ከመብት ጥሰት ባለፈ ሕዝብን ለውዥንብር እና የተሳሳተ መረጃ ሊሚያራቡ ሰነፍ ልሂቃን ያጋልጠዋል። የመንግስት ሰዎች ይህን የተረዱት አይመስለኝም። ችግር በተፈጠረ ቁጥር እየተነሱ ስልክ እና ኢንተርኔት እያቋረጡ ሕዝብን ጨለማ ውስጥ መክተት ችግሩን ያባብሰዋል እንጂ አይቀንሰውም። ሕዝብ ጭምጭምታውን እንደሰማ ድሮም መንግስት እውነት ይናገራል የሚል እምነት ስለሌለው ሌሎች የመረጃ አማራጮችን ለመፈለግ ይገደዳል። ያኔ ሲሳይ የሚሆነው የሃሰት መረጃ ለሚፈበርኩ፣ የሸር ትርክት ለሚጎነጉኑ እና በቅንነትም ቢሆን ሳያጣሩ ሰበር ወሬ ለሚያራግቡ ሰነፍ ልሂቃን ነው። በደርግ ዘመን ከመንግስት ሚዲያዎች ውጭ ሌላ ማዳመጥ በተከለከለበት ዘመን እንኳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጆሮው እስኪበላሽ ጥራት በሌላቸው የሬዲዮ ሞገዶች ቪኦኤ እና ጀርመን ድምጽ የሰማ እንደነበር፤ በናንተም ዘመን ኢሳትን ይከታተል እንደ ነበር አትዘንጉ። በየትም አገር እንደሚደረገው በአገሪቱ ውስጥ የሚከሰቱ ነገሮችን መንግስት ባወቀው መጠን እና ልክ፤ ለሕግ ሥራ እንቅፋት በማይሆን መልኩ ለሕዝብ በየወቅቱ መረጃ ቢያደርስ ይህ ሁሉ መደናበር እና የሃሰት ዜናዎች አይራቡም ነበር። ሕዝብም አይደናበረም።
የባህርዳሩን ክስተት ተከትሎ የአማራ ክልል ባለሥልጣናትን የፌደራል መንግስቱ ነው ያስገደላቸው የሚለው ውሃ የማይቋጥር፣ ምንም አይነት የማስረጃም ሆነ የመረጃ ድጋፍ የሌለው ምናባዊ ትርክ እውነታውን የሚያመላክቱ መረጃዎች ከወጡ በኋላም መቀጠሉ እጅግ አስገራሚም፤ አስተዛዛቢም ነው። ነፍሳቸውን ይማረውና ብ/ጀ አሳምነው ጽጌ ድርጊቱን በማናቸውም ምክንያት ተገፋፍተው ይፈጽሙት እሳቸው የመሩት ልዩ ኃይል በሰዎቹ ላይ ጥቃት ማድረሱን እስከ አሁን የወጡት ማስረጃዎች በግልጽ ያሳያሉ። እነ አብይን መፋለም የሚፈልግ ሰው ሌሎች መድረኮችን ይጠቀም እንጂ በሸር ትርክት  እውነታውን ሊቀይረው አይችል።
ከጀርባው ያለውን የፖለቲካ ሸርም ሆነ ስንክ ሳር መተንተን ይቻላል። ነገር ግን ክስተቱን በተመለከተ የወጣውን እውነታ ግን ሊቀይረው አይችልም። ላለማመን የቆረበ እዛው እቦታውም ላይ ቆሞ እያንዳንዱን ክስተት በአይኑ ቢያይም እንኳ ሊያምን አይችልም። ይሔ ሁሉ ጩኸት እና ንቁሪያ እውነቱን ለማወቅ ከቅን ልቦና ከመነጨ ተቆርቋሪነት ከሆነ ግን ተጨማሪ ማስረጃ መጠየቅ ወይም የቀረቡትን ማስረጃዎች ጥንካሬ እና ብቃት በአግባቡ እና በባለሙያ ማስፈተሽ ይሻላል እንጂ ያንኑ ዜማ መደጋገም ክስተቱን እንደ አንድ አጋጣሚ ለመጠቀም ከማሰብ ያለፈ ቅን ልቦና በውስጡ አይታይም።
በመንግስት በኩል እየተቆርራረጠ የሚወጣው ማስረጃ ብዥታውን ይበልጥ ሊያሰፋው ስለሚችል በአፋጣኝ ሁኔታውን በዝርዝር መግለጽ ተገቢ ነው። ሕዝብም የሚሰጡትን መረጃዎች በቅን መንፈስ ውስጥ ሆኖ ትክክለኛና ተአማኒነታቸውን እያገናዘበ እውነታውን ለመረዳት ልቦናውን ክፍት ቢያደርግ ይበጃል። በመሃል ያለው ልሂቃንም እውቀቱን እና ጊዜውን በእውነት ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ ለሕዝብ ለማስጨበት እና መንግስትም በቂ ማስረጃዎች እንዲያቀርብ እየወተወተ አገሪቱ ወደ ተረጋጋ ሁኔታ እንድትመጣ በቅን መንፈስ ድርሻውን ቢወጣ ይሻላል። የሸር ፖለቲካ ያዋረዳትን እና ያኮሰሳትን አገር በቅን ልቦና እና በቅን እሳቤ እንጂ በሌላ የሸር ትርክት መታደግ አይቻልም።
ሸር ይብቃ!
Filed in: Amharic