>

አንዳንድ ነገሮች…… (አቤል ዋበላ)

አንዳንድ ነገሮች……
አቤል ዋበላ
የተፈፀመውን ግድያ በብርጋዴል ጄኔራል አሳምነው ፅጌ፣ በአብን ወይም በፀንፈኛ አማራ ናሽናሊዝም ማላከክ የችግሩን ምንጭ ከመከለል በቀር ምንም አይፈይድም። መነሻ ምክንያቱን መፈተሽ ብልህነት ነው።
* ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሀገሪቱን ከሴራ ፖለቲካ ማላቀቅ አልቻሉም። ባንዳንድ ሁኔታዎች ራሳቸውም የሴራው አካል መሆናቸውን መገመት በመቻሉ ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ ሆኗል።
* ሁሉን አካታች ፍኖተ ካርታ ማቅረብ አልተቻልም። የተረኝነት መንፈስ ገኗል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገሪቱን አሻግራለኹ ብለው የገቡትን ቃል በአቅም ማነስ ይሁን በዳተኝነት አጥፈው በዘር ላይ በተመሰረተው ፌደራሊዝም እንደማይደራደር በፓርቲያቸው በኩል አሳውቀዋል።
* ይህ እንዲፈጠር የኢህአዴግ አባል ድርጅቶቸ አስተዋፅኦ እንዳለ ሆነ የቀድሞውን አስተዳደር ሲቃወሙ የነበሩ ነገር ግን አሁን መንግስትን የተለጠፉ ፖለቲከኞች፣ የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው መንግስታዊ ኃላፊነት የተረከቡ ባለሙያዎች፣ የዐቢይ አህመድን አስተዳደር ነባራዊ እውነታውን እንዳይረዳ አድርገዋል። ያልተገባ አፕሩቫል ሰጥተዋል።
* አንዱ ሀገር እንደሌለው እየተሰማው ሌላው በተረኝነት (entitlement) መንፈስ እየተንጎማለለ በሰላም መኖር አይቻልም።
* ለዚህ የባለጊዜነት/ተረኝነት እና የሀገር አልባነት ስሜት መፈጠር አስተዋፅኦ ያደረጉ በርካታ ነገሮቸ ቢኖሩም እንደሕገ መንግስቱ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ የለም።
* የአማራ ክልል በዚህ የዘር ፌዴሬሽን ከሚኖር የራሱን ሀገር ቢመሰርት ይሻለዋል።
* በህይወት የተረፉት እና ወደፊት የሚመጡት የክልሉ መሪዎች ይህንን ኢፍትሃዊ ‘አማራ-ጠል’ ስርዓት እልባት እንዲያገኝ ማድረግ የመጀመሪያ ተግባሩ መሆን አለበት። አለበለዚያ የህዝቡ ፍላጎት የሚፈጥረው ጫና ሁለተኛ ዙር መተላለቅ እንዳይፈጠር ያሰጋል።
* የአዲስ አበባ ህዝብ በዜጎችን ስም በሚነግዱ እና ኢህአዴግን በምርጫ ሊቀጡ ቀጠሮ በሚይዙ ቡድኖች እየተታለለ መኖር የትም አያደርሰውም። ለኢትዮጵያ ህልውና ከተቻለ መታገል ነው። ካልሆነ ተስፋው ስደት ብቻ ነው።
*በትግራይ ልሂቁ እና ፖለቲከኛው አራት ኪሎን እየናፈቀ ህዝቡን በፕሮፓጋንዳ እየጠመዘዘ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብትፈርስ የሚጎዳው ህዝቡ ነው፡፡ ከአማራ ክልል ጋር የሚገናኘው መንገድ በመዘጋቱ የፈጠረው ችግር የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ ይህንን የሚያስተውል በቂ ልሂቅ እና ፖለቲከኛ በመድረኩ የለም፡፡
* ደቡብ ክልል ተብሎ በሚጠራው የሀገሪቱ ክፍል አማራጮች ያሉት ይመስለኛል፡፡ አንደኛው ደቡብ በተባለው ከረጢት ውስጥ ሆኖ የሀገሪቱ ገዢዎች ደጋፊ እና ተባባሪ እና በስልጣን ላይ ያሉት በሚሰጡት ድርጎ መኖር ነው፡፡ ሁለተኛ የሲዳማ መንገድን በመከተል ክልልነት በማወጅ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚሰሩ ኃይሎች ጋር በመተባበር በሚመሰረተው ኩርማን ሀገር ውስጥ ከመጀመሪያው ባልተለየ አጃቢነት መኖር ነው፡፡ ሦስተኛው በዜግነት በእኩልነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር መታገል ነው፡፡
* የኦሮሞ ልሂቅ ከጥቂቱ በቀር Live with it በሚባል ትዕቢት ተወጥሯል፡፡ ኢትዮጵያ እስክትሰበር ድረስ ለመመዝበር ቁርጠኝነት አለው፡፡ ስትሰበር ደግሞ ኩርማን ሀገር ለመመስርት ስለማይዳዳ Nothing to care ሁለተኛው መፈክሩ ነው፡፡ ይመክራሉ ይዘክራሉ የተባሉት በለው በለው የሚል ማደናበር ላይ ናቸው፡፡ ይህንን ታሪካዊ ኃላፊነት የሚረዱ እና ለመስራት የማይለግሙ ወዴት አሉ?
*ሶማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል በዳር ሀገር (periphery) ስም ሁሌ አጋር ተብለው ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተገልለው መኖር ይመርጡ ይሆን?  መቼም ወደ ፖለቲካ ስልጣን የማያመጣቸውን ከዜጎች እኩል የማያደርጋቸውን ስርዓት ካላዋለዱ በኩርማን ሀገር መረገጥ እጣ ፈንታቸው ነው፡፡
* ይህ የተረኝነት እና የሀገር አልባነት መንፈስ እንዲፈርስ ህገ መንግስቱ እንዳይነካ ከሚፈልጉ እና ህገ መንግስቱ እንዲለወጥ የሚፈልጉ ሰዎችን ያካተተ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ እምነት የሚጥልበት በግልፅነት እና በታማኝነት የሚሰራ የሕገ መንግስቱን ጉዳይ በምን አይነት መንገድ መፍትሔ እንደሚያገኝ የሚያማክር ቡድን በተቻለ ፍጥነት መቋቋም አለበት።
* በአሁን ወቅት በጠቅላይ አቃቤ ህግ እየተደረገ ያለው አፋኝ ህጎችን የማሻሻል ሂደት በግልፅነቱ፣ በተዓማኒነቱ እና በአሳታፊነቱ እንደመነሻ የሚያገለግል ስለሆነ ይህ ህገ መንግስቱን የሚያሻሽል/የሚለውጥ ሂደት ትምህርት ቢወስድ መልካም ነው።
* የህገ መንግስቱ ጉዳይ እልባት ሳያገኝ ምንም አይነት የምርጫ ወሬ፣ ሽርጉድ፣ ክርክር መጀመር የለበትም።
* የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ እንዳሉት ይህ ወቅት የሸግግር ነው። በሽግግር ወቅት የሚኖር ስልጣን በመደበኛ ጊዜ ከሚኖር ስልጣን ያነሰ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ስለዚህ በዚህ ወቅት ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ራሳቸውን እንደ ባለሙሉ ባለስልጣን ሳይሆን ለጊዜው መደበኛ የመንግስት ስራዎችን ለማከናወን በአደራ መልክ በኃላፊነት ስልጣን እንደያዘ በመቁጠር ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያማከሉ ስራዎችን ማኀበረሰቡን እያማከሩ እንዲሰሩ ይደረግ።
* በአዲስ አበባ አስተዳደር እና በአንዳንድ የመንግስት ከፍተኛ መዋቅሮች የሚታየው እብሪት፣ ትዕቢት እና ተረኝነት ሰከን ቢል መልካም ነው። ማንንም አይጠቅምም።
**********
መጀመሪያ፡-  ሰላም፣ መረጋጋት፣ ጸጥታ፣
ሁለተኛ ፡- ብሔራዊ እርቅ፣ የልሂቃን ድርድር፣ ሕገ መንግስት ማሻሻል፣ ፖለቲካዊ መረጋጋት
ሦስተኛ፡- የህዝብ ቆጠራ በመቀጠል ምርጫ
Filed in: Amharic