>
5:13 pm - Tuesday April 20, 3819

አቢይ ባንድ ድንጋይ መከላከያውን አስተካክሎ፤ ብዓዴንን ታማኝ ሎሌው አድርጎ ወደቤቱ ተመልሷል!!! (ዮናስ ብርሀኑ)

አቢይ ባንድ ድንጋይ መከላከያውን አስተካክሎ፤ ብዓዴንን ታማኝ ሎሌው አድርጎ ወደቤቱ ተመልሷል!!!
 
ዮናስ ብርሀኑ
 
* መከላከያውን የኢትዮጵያ ሊያስብለው ይችል የነበረው ብቸኛ ግለሰብም ተወግዶ አሁን ኦፊሽያሊ መከላከያውን የኦህዴድ ሆኗል!!
ድሮ ድሮ በሕወሐት/ኢህአዴግ ዘመን ነው አሉ። «ምርኮኞች» በሚል ስያሜ በአብዛኛው የኦሮሞ ማሕበረሰብ የሚታወቁት ኦህዴዶች ከኦነግና ደጋፊዎቻቸው መቀናቀን ሲበዛባቸው ጉዳዩን በሚስጥር ለሕወሐት ይነግሩና እነርሱ ዳር ይይዛሉ። ሕወሐት ያንን የፈረደበት አግዓዚ አዝምታ ለኦህዴዶቹ ተቀናቃኝ የሆኑትን ሰዎች በሙሉ በኦነግ ስም የምትችለውን ገድላ የተቀረውን ወደ ማጎርያ ታግዛለች። ኦህዴዶቹ አንዲትም ቃል አይወጣቸውም። ሕዝቡ ደሞ «እነርሱ አይደሉም ጥፋተኞች ሕወሐት ናት የወረረችን… እነርሱማ ምን አቅም አላቸው?» ይላል። ድራማው ተሳካ ማለትም አይደል? ኦህዴዶች ስልጣናቸው ጫፏ ሳትነካ እንደገናም በሕዝቡ ዘንድ ሳይጠሉ (እንዲያውም ታዝኖላቸው) ምስኪን ወጣት ግን በኦነግ ስም ታስሮ፣ ተጋድሎና እድለኛ የሆነው ተሰድዶ ሕይወት ይቀጥላል። በተለይ በሰማንያዎቹ ውስጥ ይህ አሰራር እጅግ የተለመደ ነበረ።
•°•
ዘመኑ ተቀይሮ ኦህዴድ የሕወሐትን ቦታ ይዟል። ብዓዴን ደሞ ኦህዴድን ተክቷል። በብዓዴን ውስጥ «ምርኮኛ አንሆንም (ያው በጦርነት የተማረኩ ባይሆንም አጎብዳጅ አንሆንም ለማለት ያህል ነው)» በሚሉና «ምንም አናመጣም አርፈን ስልጣናችንን አስጠብቀን እንቀጥል…» በሚሉ መሐከል ክፍተት ተነስቷል። አርፈን እንቀመጥ ባዮች በመጨረሻ ከኦህዴድ እርዳታ ጠየቁ። ኦህዴድ እርዳታውን ይዞ ከች አለ። ምን ያደርጋል ታድያ አናጎበድድም የሚሉት በቀላሉ መውደቅ አልፈለጉምና ይዘን እንውደቅ ብለው ያው ቅዳሜ ማታ የሆነው ነገር ሆነ። ብ/ጄ አሳምነው ቅዳሜ የደረሱበትን ውሳኔ ባይወስኑም ኖሮ ዞሮ ዞሮ በቁጥጥር ስር ውለው የሆነ bogus ክስ ተመስርቶባቸው ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው አይቀርም ነበረ። የብዓዴን ከፍተኛ አመራር ሆነው በፌደራል መንግስት የተወከሉት የነደመቀና ገዱ ዝምታ ይህንን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ኦዴፓ ባህር ዳር ዘው ብሎ የገባው በአዴፓ ተጋብዞ እንጂ ዝም ብሎ አይደለም።
•°•
እናም ኦነግ 19 ባንክ ሲዘርፍና በቤኒሻንጉል ክልል ያ ሁሉ ሰው ሲሞት ቶሎ መድረስ ያልቻለው መከላከያ ሰራዊት (ኦህዴድ) በብዓዴን አባላት እየተመራ አማራ ክልልን ለመቆጣጠር አንድ ቀን አልፈጀበትም።
•°•
 የድሮውን መከላከያ የሕወሐት ካልነው ዘንዳ ያሁኑን መከላከያ ደግሞ የኦህዴድ መባሉ ትክክለኛ አግባብ ይመስለኛል።
•°•
በዚህ puzzle ውስጥ ቦታው ላይ አልገጥም ያለው አንድ ሰዓረ የተባለ piece ነበረ። ሰዓረ የሕወሐት የተባለው መከላከያ በሪፎርም ሲታመስ እሱ እንዲቀርና ከፍተኛውን ስልጣን እንዲይዝ ያደረገው አንድ ብቸኛ ኩዋሊቲ ስለነበረው ነበረ። ይኸውም ኩዋሊቲው በኢትዮጵያዊነቱ አለመደራደሩና ወደ አንድ የዘር ጥግ ለመሸጎጥ ፈቃደኛ አለመሆኑ ነበረ። ይህ ኩዋሊቲው ከሕወሐት መከላከያ መበተን ቢያተርፈውም ቅሉ በዚህኛው puzzle ውስጥ ምንም ቦታ እንዳይኖረው አድርጓል። እንደ ኤታማጆር ሹምነቱ ደሞ ያለርሱ ፈቃድ መከላከያ ሊንቀሳቀስ አይችልም። ለዛም ነው ዛሬ የቀብር ስነ ስርዓቱን የተከታተልነው። «ሰዓረ በአሳምነው ቅጥረኛ ነው የተገደለው…» የምትለዋ አባባል ለሕፃን ልጅ እንኳ ፍፁም ስሜት የማትሰጥ ነገር ናት። እንዲያውም ሰዓረና ገዛዒ ባይገደሉ ኖሮ የባህር ዳሩን ክስተት በስሜታዊነት የተከሰተ ድንገተኛ የእርስ በእርስ ግጭት አድርጎ ማቅረቡ በጣም ቀላል ይሆን ነበረ። በብዓዴን ውስጥ ከፍተኛ መሰንጠቅ (ሕንፍሽፍሽ) እንደተከሰተ የታወቀው ገና ከወራት በፊት ነበረ።
•°•
At the end of this situation, የአቢይ መንግስት በሁሉም ረገድ አሸናፊ ሆኗል። ብዓዴን ውስጥ ምርኮኛ አንሆንም ባዮች ከጨዋታው ውጪ ሆነዋል። አሁን በአስተዳደር ላይ ያለው አካል ለጊዜውም ቢሆን የአቢይ አስተዳደር ታማኝ ነው። መከላከያውን የኢትዮጵያ ሊያስብለው ይችል የነበረው አንድ ብቸኛ ግለሰብም ተወግዶ አሁን ኦፊሽያሊ መከላከያውን የኦህዴድ ሆኗል። እንደገና ዛሬ እንደተሰማው ከሆነም የባልደራስ ምክር ቤት አደራጆችን፣ የድሮው ግ7 አፈንጋጮችንና ሌሎች በተቃዋሚነት የሚጠረጠሩ ዜጎችን በእስክንድር አንደበት «ከወቅታዊው ጉዳይ ጋር በተያያዘ» በተጠርጣሪነት በቁጥጥር ስር ውለዋል። አብዛኛዎቹ የተያዙት ከተከሰተው ጉዳይ ጋር ግንኙነት ኖሯቸው ሳይሆን ያው ስነ ልቦናቸውን ለመስበር ስለሆነ በቅርቡ ይለቀቃሉ። ባይሆን ባህር ዳር ከተያዙት ውስጥ ጥቂቶች ከፍተኛውን ፍርድ እንዲጎነጩ ይደረጋል። አቢይ ባንድ ድንጋይ መከላከያውን አስተካክሎ፣ ብዓዴንን ታማኝ አድርጎ ባልደራስንና ለኢዜማ ፈተና የሆኑ አካላትን ስነ ልቦና ሰብሮ ወደቤቱ ተመልሷል።
•°•
ይህ አካሄድ ጊዜያዊ ሰላም ለሐገሪቷ እንደሚፈጥር ጥርጥር የለውም። ሰላሙ ዘላቂ ይሆናል ወይ የሚለው ግን አጠራጣሪ ነው። ምክንያቱም ይህ ስታይል ድሮ ለሕወሐት ቢሰራም በዚህ ዲጂታል ዘመን ላይ ውጤታማ ይሆናል ማለት የሚቻል ነገር አይደለምና።
Filed in: Amharic