>

... የለውጥ ኃይሉ መዝረክረክ አገሪቱን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ነው!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

አያያዙን አይተህ  ሽልጦውን …
የለውጥ ኃይሉ መዝረክረክ አገሪቱን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ነው!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
የሰሞኑ ግርግር፣ አሳዛኝ እና ልብ የሚያደሙ ክስተቶች እና የመፈንቅለ ትርምስ ዜናዎች ከብዙ አቅጣጫ እጅግ ተቃራኒ የሆኑ ብዙ አወዛጋቢ መረጃዎች እየወጡ ስለሆነ ለጊዜው በዝርዝር ጉዳይ ላይ አስተያየት ከመስጠት እቆጠባለሁ። እጄ ላይ ያሉት መረጃዎች ድምዳሜ እንድይዝ ሊያደርጉኝ የሚችሉ ቢሆንም መረጃዎቹ በሚመለከታቸው አካላት በኩል በዝርዝር ተገልጸው እስኪወጡ ድረስ ሕዝብ ሊያደናግሩ ስለሚችሉ አንዳንድ ጠቋሚ አሳቦችን ለጊዜው ወደጎን ብዮ በጥቅል አገሪቱ አሁን የምትገኝበት እና አሁን ላለችበት ችግር መንሰዔ ይሆናሉ ያልኳቸውን ሃሳቦች ለውይይት ይረዳ ዘንድ በዝርዝር ለማንሳት እሞክራለሁ።
ባለፉት አሥርት አመታት ሕዝብን እርስ በራሱ ለመከፋፈል ከተከናወኑት በርካታ ነገሮች ባልተናነሰ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲከፋፈል እና አንዱ በሌላው ላይ እምነት እንዲያጣ በዚህ አጭር የለውጥ ጊዜም ውስጥ ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል። ሚዲያዎች፣ በሁሉም ክልል የሚገኙ አክራሪ ብሔረተኞች፣ የብሔር መብት አቀንቃኞች፣ የፌደራል እና የክልል መንግስታት፤ እንዲሁም የማህበረ ድህረ ገጾች ለዚህ ችግር የየራሳቸውን አስተዋጽዖ አበርክተዋል።
ከሁሉ የከፋው እና አሁን ወዳለንበት ትርምስ ውስጥ ከከተቱን ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል፤
+ የፌደራል መንግስት በሕገ መንግስቱ የተጣለበትን የሕግ የበላይነትን የማስከበር ተግባሩን ችላ ብሎት መቆየቱ እና በአግባቡ ሳይወጣ መቅረቱ፤
+ የፌደራል መንግስቱ ከክልሎች ጋር ያለውን ግንኙነት በአግባቡ አለመያዙ እና ክልሎች እራሳቸውን የቻሉ አገር እስኪመስሉ ድረስ እጅግ የተለጠጠ እና ልጓም ያልተበጀለት ሥልጣን እና ጉልበታቸውን እንዲያፈረጥሙ መልቀቁ፤
+ እያንዳንዱ ክልል የራሱ ልዩ ኃይል እና ሚልሺያ እያሰለጠነ በትጥቅ እና ውትድርና በሰለጠነ ኃይል እንዲደረጅ መደረጉ እና የፌደራል መንግስቱም ይህን በቀጥታ የሚቆጣጠርበትን መንገድ ከመዘርጋት ይልቅ ጉዳዩን ሙሉ በሙሉ ለክልሎች መተዉ፤ በቅርቡ በደሴ በተደረገ ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዳንድ ክልሎች በጀታቸውን ሚሊሻ ይቀልቡበታል ያሉትን ልብ ይለዋል፤
+ በመከላከያ ሠራዊት፣ በክልል ልዩ ኃይል፣ በሚሊሺያ እና በፌደራልና በክልል ፖሊሶች መካከል ያለው የሥራ ግንኙነት እና የኃላፊነት ድርሻ ግልጽነት የጎደለው እና በመካከላቸውም በግልጽ የሚታይ ፉክክር መፈጠሩ፤ ይህንንም ችግር የፌደራል መንግስቱ እያወቀ አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃ አለመውሰዱ፤
+ በክልሎች መካከል የሚታዩ ፉክክሮች እና ፍጥጫዎች በወቅቱ ምላሽ አለማግኘታቸው እና የፌደራል መንግስቱም ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት እጅግ አነስተኛ መሆኑ፤
+ የክልል የጸጥታ እና የደህንነት አወቃቀር እና ተቋማቱን የሚመሩት ሰዎች አሿሿም በቅጡ ጥናት ያልተደረገበት እና ከዚያ ይልቅ በክልሎቹ መካከል ያለውን ፍጥጫ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የትግራይ ክልል ጌታቸው አሰፋን መሾሙን ተከትሎ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የተደረጉት የጸጥታ ዘርፍ ሹመቶች የክልሎቹን የወደፊት አብሮነት ሳይሆን ፍጥጫን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ፤
እና ሌሎችም በርካታ ምክንያቶች ተደማምረው ይህ ለውጥ ፈተናዎች እንዲበዙበት እና አገሪቱም እንዲህ ያለው ጭንቀት ውስጥ እንድትገባ አድርገዋል።
ሌላው የዚህ ለውጥ ትልቁ ፈተና ሥርዓት በያዘ መልኩ ያልተከናወነው የአገራዊ መግባባት፣ የተጠያቂነት እና የእርቅ ጉዳይ መልሰን መላልሰን ተመሳሳይ ችግሮችን እንድናይ እያደረገን ይመስለኛል። ለውጡ ለእነዚህ ነገሮች ቅድሚያ እና በቂ ትኩረት ካለመስጠቱ የተነሳ ሁለት አደጋዎችን ይዞ እየተጓዘ ነው።
፩ኛ/ ባላፉት አሥርት አመታት በአገሪቱ ውስጥ የተፈጸሙ በደሎች እና የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ጥፋቶቹንና ወንጀሎቹን ሁሉ በጥቂት ሰዎች ላይ እንዲቆለል የተደረገ ይመስላል። በጠአት የሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ የሥርዓቱ አስነዋሪ ሥራ እንዲሸከሙ እና ወደ ፍርድ አደባባይ እንዲቀርቡ ከተደረገ በኋላ አብረዋቸው የወንጀሉ ዋና ተሳታፊ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ደረጃ ያሉ ባለሥልጣናት ሸክማቸው ቀሏቸው እና ገሚሶቹም እራሳቸውን እንደ ጻድቅ ቆጥረው እየተመጻደቁ ሥልጣናቸውን እንደያዙ እንዲቀጥሉ አድርጓል። ይህ ጥቂቶችን ተጠያቂ ያደረገው የተንሻፈፈ የፍትሕ ሂደት ብዙዎች አጥፊዎችን ከተጠያቂነት እንዲያመልጡ ብቻ ሳይሆን በሕዝብ እና በአገር ላይ ላደረሱት ጉዳት ለደቂቃም እንዳይጸጸቱ አድርጓቸዋል። ትላንት ገራፊ እና አስገራፊ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ቅዱስ ተሿሚዎች ሆነው ስለፍቅር እና ሰላም ከኛ በላይ ሰባኪዎች የለም ብለዋል።
፪ኛ/ በተቃራኒው ባለፉት አስርት አመታት ከላይ በጠቀስኳቸው ተሿሚዎች ሲሳደዱ፣ ሲገረፉ፣ ሲዋከቡ እና ታስረው ሲሰቃዩ የነበሩ ሰዎች በአካል እና በስነ ልቦና የደረሰባቸው ጠባሳ በቅጡ ሳይድን እና ሳይታከም ገሚሶቹ ለመደለያ በሚመስል መልኩ ተሹመዋል። ገሚሶቹም ይህ ለውጥ ለበደላችን ካሳ ይሰጠናል ብለው ደጅ ሲጠኑ ቆይተዋል። ገሚሶቹም በተለያየ መልኩ የፖለቲካ ትግሉን ከነ ቁርሿቸው ተቀላቅለዋል።
ይህ ለውጥ በቅድሚያ በእነዚህ ሁለት ኃይሎች፤ በዳይ እና ተበዳይ መካከል ያለውን ቂም እና ቁርሾ ያመረቀዘ እባጭ እውነት ላይ በተመሰረተ ፍትህ እና እርቅ ሳያመክን በሌሎች ሥራዎች ላይ ተጠምዶ ቆይቷል። ቂም ተይዞ ጉዞ እንዲሉ፤ ይህ የዘመናት ቁርሾ ሳይቀረፍ አገር የማዘመን እቅድ እና ቅዥት ውስጥ ገብቶ መጠመድ መዘዙን በቅጡ ያለማጤን ይመስለኛል። ይህ አይነቱ የቁርሾ እባጭ ተበዳዮችን በሹመት በመደለልም ሆነ ስብከት በሚመስል የፖለቲካ ዲስኩር እና የተስፋ ቃል አይሽርም። ብቸኛ ምሱ እውነት፣ ፍትሕ እና እርቅ ናቸው።
ለውጡ መስመሩን እየሳተ እና አገሪቱን ወደ ግጭት እንድታመራ እድል እየፈጠረ  እንደሆነ ምልክት የታየው እኮ የትግራይ ክልል በወንጀል የሚፈለገውን እና የንጹሃን ደም በእጁ ያለውን ጌታቸው አሰፋን የክልሉ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ አድርጋ ስትሾም፤ ያንኑ ተከትሎ በዚህ ጨካኝ ሰው ታስሮ ሲሰቃይ የነበረውን ብ/ጀ አሳምነው ጽጌን የአማራ ክልል መንግስት የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ አድርጎ ሲሾም እና በዚሁ ሥርዓት ተገፍቶ እና ቂም ቋጥሮ ከመንግስት በመክዳት ኤርትራ ጫካ የወረደውን ጀ/ል ጀማል ገልቹን የኦሮሚያ ክልል መንግስት የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ አድርጎ የሾማቸው እለት ነው። ይችን አገር አንድ አድርጎ እና ሰላም አስፍኖ ለመምራት የሚፈልግ ኃይል በምንም ሂሳብ እነዚህን ሦስት ሰዎች የዚህ ቁልፍ የሆነ ሥልጣን ኃላፊንተ ተሿሚዎች ሊያደርጋቸው አይገባም።
ሦስቱም በውስጣቸው እሳት አለ።  ጌታቸው አልዋጥ ያለውን ሽንፈት እና የሥልጣን ንጥቂያ ለመበቀል ያቄመ ሰው ነው። የእሱ ቦታ ሹመት ሳይሆን ወደ ፍርድ አደባባይ ነው። ብ/ጀ አሳምነው ብዙ ስቃይ እና ሰቆቃን ያሳለፈ እና ለአገሩ የከፈለው መስዋዕትነት በዜሮ ተባዝቶ በዘረኛ ገራፊ መርማሪዎች በደል ይተፈጸመበት እና ለበደሉም ተገቢውን ፍትሕ ያላገኘ ሰው ነው። እሱ ላይ በደል ያደረሱ ሰዎች በሌላኛው ጫፍ መቀሌ መሽገው ሲደነፉ ማየት የዚህን ሰው ቁስል እንደመጓጎጥ ነው። በተጨማሪም በእሱ እስር እና ስቃይ ላይ እጃቸው እንዳለበት የሚገለጽ አንዳንድ የበአዴን አመራሮች ዛሬም አብረው በአንድ ግንባር ተሰልፈዋል። ይህ ሰው ለደረሰበት የአካል እና የስነ ልቦና ጉዳት በቂ ድጋፍ እና ካሳ እንዲያገኝ ተደርጎ በክብር ጡረታ እንዲወጣ ይደረጋል እንጂ እንዲህ ያለ እሳት ውስጥ እንዲገባ አይደረግም። ጀነራል ጀማል ገልቹም እንዲሁ የኦነግን አላማ አንግቦ ሲታገል የቆየ እና የተገፋ ሰው ሲለሆነ፤  በኦዴፓ ላይም ከህውሃት እኩል አቂሞ የቆዩ ሰው ስለሆነ በእንዲህ አይነት ኃላፊነት ላይ ሊቀመጥ አይገባውም ነበር። ኦዴፓ ቀድሞ እኚህን ሰው ማስወገዱ ዛሬ ባህርዳር ላይ የተከሰተው አደጋ የመጀመሪያው ገፈት ቀማሽ እንዳይሆን ሳያደርገው አልቀረም። የባህርዳሩ መፈንቅለ ትርምስ ከወራት በፊት አዳማ ላይ ሊሆን የማይችልበት ምን ምክንያት አለ?
ነገሬን ልቋጭና የለውጥ ኃይሉ መዝረክረክ አገሪቱን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ነው። እነ አብይ ከግርግሩ መልስ በጥሞና ከላይ የተነሱትን እና ሌሎች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ቅድሚያ ሰጥተው ከወዲሁ ነገሮችን ቢያስተካክሉ መልካም ነው። አንዱ የአብይ አስተዳደር ክሽፈት መገለጫ በዚህን ያህል ጊዜ ውስጥ ከትግራይ ክልል ጋር ያለውን ተቃርኖ መፍታት አለመቻሉ ነው። የትግራይን ህዝብ የወያኔ ምርኮኛ አድርጎ ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ ነች የሚለው ትርክት ለውጡን እሩብ ሙሉ ነው የሚያደርገው።
ቸር ያሰማን!
Filed in: Amharic