>

አቶ አዲሱ አረጋን ነጻ ያወጣችው የእስክንድር ፌስታል!!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

አቶ አዲሱ አረጋን ነጻ ያወጣችው የእስክንድር ፌስታል!!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
ከወያኔ ጋር የተደረገው የነጻነት ትግል የዛሬ ሦስት አመት የተጀመረ የመሰላቸው አንዳንድ የኦዴፖ አመራሮች አልፎ አልፎ የሚሰጡት መግለጫ እጅግ አስተዛዛቢ እና አስነዋሪም ነው። ባላፊት ሃያ ሰባት አመታት ብዙዎች የህውሃት የማፈኛ መሳሪያ እና አሽከር ካድሬ ሆነው የገዛ ህዝባቸውን ሲያሰቃዩ፣ ሲገድሉ፣ ሲገርፉ እና ሲያሰድዱ እንዳልኖሩ፤ በብዙ ሚሊዮኖች ጎመን በጤና ብለው የአፈና እንቆቋቸውን እየተጋቱ ሁሉንም ነገር እንዳላየ እና እንዳልሰማ መስለው ለሥርዓቱ ጉልበት እንዳልሆኑ፤ ዛሬ በለውጥ ማግስት ያንን የአፈና ሥርዓት ያለፍርሃት ሲታገሉ፣ ሲታሰሩ እና ሲገረፉ የቆዩ የእስክንድር ነጋ አይነት የነጻነት ታጋዮችን ሲያጣጥሉ፣ ሲያንኳስሱ፣ ሲያስፈራሩ እና ሊያሸማቅቁ ሲሞክሩ ማየት እጅግ ያማል።
እነ ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ እና ሌሎችም የመንደር ነጻ አውጪ ቡድኖች ሳይፈጠሩ ወይም መኖራቸው ሳይታወቅ በፊት ከወያኔ ጋር የነበረውን የሃያ ሰባት አመት ትንቅንቅ እና እልህ አስጨራሽ ትግል ብቻቸውን የተጋፈጡት እስክንድርን ጨምሮ በጣት የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች፣ የመብት አቀንቃኞች እና ተሟጋቾች፣ ጥቂት ምሁራን እና ጥቂት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓይያርቲ ድርጅቶች አመራር እና አባላት ናቸው። የዛሬዎቹ ሹማምንት የህውሃት ጥርስ እና ክርን ሆነው የገዛ ሕዝባቸውን ይገዘግዙ እንደነበር እንዲህ ባጭር ጊዜ መዘንጋታቸው የሚያስገርም ነው። ከህውሃት ጫና ተላቀው ዛሬ እንደልብዎ እንዲናገሩ ያደረገችዎት ነጻነት ከእነ እስክንድር ነጋ እና ሌሎች ለዜጎች መብት መስዋትነት የከፈሉ ኢትዮጵያዊያን በመከራ ጊዜ ከሸከፏት ፌስታል መመንጨቷን ያወቁ አልመሰለኝም።
ቄሮ ነጻ ያወጣው እስክንድር ነጋን ሳይሆን እድሜያቸውን ሙሉ የህውሃት ተላላኪና ማላገጫ ሆነው የኖሩትን አቶ አዲሱ አረጋን እና ሌሎች የኢህአዴግ ካድሬዎችን ነው። እስክንድር ነጋ እና ሌሎቹ በግፍ ታስረው የነበሩ የመብት ታሟጋቾች እና የነጻነት አቀንቃኞች ነጻ የወጡትእራሳቸው በከፈሉት መስዋዕትነት ነው። ያጣጣሏት የእስክንድር ነጋ ፊስታል ለእርሶም ነጻ መውጣት ትልቅ ድርሻ አላት።
የመብት ተሟጋቾችን፣ በክፉ ቀን ለሕዝብ ነጻነት ዋጋ የከፈሉ ጋዜጠኞችን፣ ሲታሰሩና ሲሰቃዩ የኖሩ የፖለቲካ መሪዎችን፣ ምሁራንን እና የአገር ባለውለተኛ የሆኑ ግለሰቦችን ባልተገራ የካድሬ አንደበት መዝለፍም ሆነ ክብራቸውን መንካት እና መብታቸውን ማፈን ለውጥ እንመራለን ከሚሉ አካላት አይጠበቅም።
Filed in: Amharic