>
5:13 pm - Wednesday April 19, 4845

የዶ/ር አብይ አህመድ አባት  የሀጅ አህመድ አሊ ቀብርና ትዝብቴ!!! (ኡስታዝ አህመዲን ጀበል)

የዶ/ር አብይ አህመድ አባት 
የሀጅ አህመድ አሊ ቀብርና ትዝብቴ!!!
ኡስታዝ አህመዲን ጀበል
የጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድ አባትን ለማስቀበር ዛሬ ጠዋት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመጓዝ ተዘጋጀን። በርካታ የመንግስት ባለስልጣናት በተለይም በርካታ የፓርላማ አባላት ጭምር በቀብሩ ላይ ሊገኙ ስላመለከቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ ሰው የሚያሳፍር አውሮፕላን ለዛሬ ጠዋት በሁለት ሰዓት የሚነሳ ልዩ በረራ ተመደበ። እኛም በዚሁ አውሮፕላን ለመጓዝ ትኬት ለማግኘት ትናንት ተመዝግበን በ12 ሰዓት ላይ ኤርፖርት እንድንደርስ ተነገረን። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድም የመንግስት ባለስልጣን እንዲሁም አንድም የመንግስት መኪና ለለቅሶ ወደ ጅማ እንዳይንቀሳቀስ አዘዙ። በቀብር ላይ ካልተገኘን ላሉ ባለስልጣናት “እኔ ሄጄ አባቴን አስቀብራለሁ። ሌሎቻችሁ ስራችሁን ቀጥሉ። በትክክል በስራው ላይ ተገኝቶ ስራውን የከወነ የኔን ለቅሶ እንደደረሰ እቆጥራለሁ።” ብለው ስላሉ የጠዋቱ የአውሮፕላን በረራውም ተሰረዘ። ባለስልጣናቱም ቀሩ። እኛም እስከ ጅማ በአውሮፕላን ልንጓዝ የነበረውን ጉዞ በመኪና ለመጓዝ ስንል ሌሊት 10 ሰዓት ላይ ጉዞ ጀመርን።
ዶ/ር አብይ አህመድ በአቶ ሽመልስ አብዲሳና በፀጥታ አካላት ታጅበው ከቀብሩ አጠገብ ቆመው በሀዘን ተውጠው አባታቸውን ያስቀብራሉ። ሼህ ሀጂ በንግግራቸው መሃል “ከዚህ በፊት የዶ/ር አብይ አባት ሀጅ አህመድ አሊ በአዲስ አበባ ተገናኝተን ስሞት በመጨረሻ ኡለሞች አደራችሁን አስታውሱኝ” ብለውኝ ነበር ብለው አስታውሰው ዱዓ አደረጉላቸው።
ከዚያም ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ አባታቸው ቤት አመሩ። የጠቅላይ ሚ/ሩ ባለቤትም አብረው ወደ ሀጅ አህመድ አሊ ቤት ወደ ለቅሶው ቤት ገቡ። በድንኳን ዉስጥ ከጎናቸው ተቀመጥን። ጠቅላይ ሚ/ሩን አጽናናን። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በለቅሎው ድንኳን ዉስጥ ሆነው “ለምን ለፍታችሁ መጣችሁ?” አሉን። ቆይተውም ተነስተው ወጡ። እኛም ወደ ዃላ ቀርተን የጠቅላይ ሚ/ሩን ሁለቱን ወንድሞች አፅናናን ተነስተን ወጣን።
የዶ/ር አብይ አህመድ አባት የቀብር ስነስርዓትን የሚቀርፅ አንድም ካሜራ አለመኖሩ እንዲያውም እንደማንኛውም ለቅሶ በተለመደው መንገድ ሳይካበድ መከናወኑ ጠቅላይ ሚኒስተሩን እንዳደንቅ አደረገኝ። በተለይ ደግሞ በረመዳን ወር የዶ/ር አብይ አባት ጋር በተገናኘን ጊዜ ለልጃቸው ያላቸውን ልዩ ፍቅርና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለአባታቸው ያላቸውን ፍቅር ሳስታውስ የዛሬው የቀብር ሁኔታ እንደማንኛውም ሰው አባት ቀብሩ እንዲከናወን መደረጉ አስገረመኝ። ሌላ ባለስልጣን ቢሆን ለቀብርና ለቅሶ ያልመጡትን ነበር በቅሬታ የሚያየው። ዶ/ር አብይ ግን ለቅሶዬን የደረሱት በስራ ገበታቸው ተገኝተው ስራቸውን የፈፀሙት ናቸው ብሎ ልንጓዝበት ያሰብነው በረራ ተሰርዞ አሁን ገና ወደ አዲስ አበባ የመልስ ጉዞ መንገድ ላይ ነን።
አሁን ከምሽቱ 3:20 ላይ ይኸው ገና ወሊሶ ገባን። ጉዟችንን ቀጥለናል። ጠቅላይ ሚ/ሩ ባይከለክሉ ዛሬ ለለቅሶ ተነስተው የነበሩ ባለስልጣናት በሙሉ ወደ ለቅሶው ቢመጡ ኖሮ ሀገራችንን ብዙ ወጪ ያስወጣት ነበር። በሀዘን ቀን ያውም በአባት ለቅሶ ቀን በሀዘን ተውጦ ያለ ሰው እንዲህ ለሀገሩ የሚያስብ መሪ ሆኖ ሳየው አደነቅሁት። አላህ ለመሪያችን መፅናናቱን፣ ትክክለኛ አመራርንንና ሂዳያውን ይስጠው እያልኩ ፅሁፌን እቋጫለሁ!
Filed in: Amharic