>
5:13 pm - Wednesday April 20, 8214

በኦነግ የተሰጠ መግለጫ! 

ከኦነግ የተሰጠ መግለጫ! 

ዛሬ በኢትዮጵያ የሚታየዉን የፖለቲካ ለዉጥ ያስገኘዉ፤ የኦሮሞ ህዝብ ለነፃነቱ ስል ያደረገዉ መራራ ትግል እና ዛሬም ድረስ እየከፈለ ያለው ዉድ መስዋእትነት መሆኑ ማንም ልክደዉ የማይችለዉ እዉነታ ነዉ፡፡ በትግሉ ሂደት ዉስጥ ደግሞ ኦነግ እንደ ድርጅት ያበረከተዉ ድርሻ፣ የድርጅቱ አባላት እና ደጋፊዎች (Qeerroo Bilisummaa Oromoo – ቄሮን ጨምሮ ) የከፈሉት መስዋዕትነት ተወዳዳሪ የሌለዉ የላቀ ድርሻ እንዳለዉ በገሃድ የሚታይ ሐቅ ነዉ፡፡
በኦነግ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ስምምነት ተደርጎ የኦነግ ከፍተኛ አመራር በክብር ወደ ፊንፊኔ እንድገባ በሩን የከፈተዉም በዚህ መልኩ የተፈጠረዉ ለዉጥ እና ዕድል ነዉ፡፡ የኦነግ አመራር በዚህ ስምምነት መስከረም 05, 2011 ዓ.ም ፊንፊኔ ስገባ ለ27 ዓመታት የኦሮሞን እና የሀገሪቷን ህዝቦች በወታደራዊ አገዛዝ እያሰቃየ የነበረዉ የኢህዴግ አስተዳደር ተለዉጦ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች እና ድርጅቶች በሰላማዊ መንገድ ዓላማቸዉን ያራምዳሉ በሚል ተስፋ ነበር፡፡ ዶ/ር አብይ አህመድም ወደ ስልጣን እንደመጡ የህግ የበላይነትን ማስከበር በሚል ስም ማሰር፣ መግደል፣ ዝርፊያ፣ የመብት ተፋላሚዎችን ጥላሼት በመቀባት (ስም በማጥፋት) በጠላትነት መፈረጅ ከእንግዲህ ኣይቀጥልም በሚል ለህዝብ ቃል መግባታቸዉ ይታወሳል፡፡
በእርቅ እና በሰላም አብሮ ለመስራት የተገባዉ ቃል ሙሉ በሙሉ ሳይከበር ቀርቶ እስከ አሁንም መጓተቱ መንግስት ለዚህ ጉዳይ በቂ ፍላጎት ከማጣቱ የመነጨ እንጂ በኦነግ ምክንያት እንዳልሆነ ግልጽ ነዉ፡፡ ለዚህም ማሳያ ደግሞ በግንቦት 21, 2011 ዓ.ም  በኦነግ እና በመንግስት መካከል ስምምነት ከተደረሰ ወድህ መንግስት በኦሮሚያ ዉስጥ እየፈፀመ ያለዉ አሳዛኝ ተግባር በቂ ማስረጃ ነዉ፡፡
ግንቦት 21, 2011 ዓ.ም ለእዉነተኛ እርቅ መንገድ ልከፍት ይችላል በሚል ተስፋ የኦነግ አመራር መሄድ ከሚገባዉ ርቀት በላይ በመሄድ ከኦዴፓ፣ ከኦሮሚያ ከልላዊ መንግስት እንዲሁም ከፌዴራል መንግስት ጋርም በሰላም አብሮ ለመስራት ፍላጎቱን አሳይቷል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳም ከዚህ በኋላ ኦነግ ቢሮዎቹን ከፍቶ በሙሉ ነፃነት መንቀሳቀስ እንድችል ሙሉ ትብብር እንደሚያደርጉና በተጨማሪም እስር ቤት ያሉትን የኦነግ አባላት እና ደጋፊዎችን እንደሚስፈቱ ቃል ገብቷል፡፡
ይሁን እንጂ ከዚያ ወድህ በተግባር መሬት ላይ እየታዩ ያሉ እዉነታዎች በዚያ ዕለትም ሆነ ከዚያም በፊት በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉት ስምምነቶቻችን ተቃራኒ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት የታሰሩትን የድርጅቱን አባላት እና ደጋፊዎችን መፍታት ቀርቶ በአድስ መልክ እስራት እየተፋፋመ ነዉ፡፡ በበኩላችን የመብት ጥያቄ ያነሱትን ዜጎች እስር ቤት ከማጎር እና እስካሁን ሳይመለሱ የቀሩትን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አባላትን “ሽፍታ” በማለት ስም ለማጠልሸት ከመሞከር ፋንታ የችግሩን ምንጭ በማመን ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም ሊያስገኝ የሚችል መፍትሄ ማፈላለጉ አስፈላጊ ነዉ ብለን እናምናለን፡፡
በአጠቃላይ እንዲህ ዓይነቱ በመተማመን እና አንዱ የሌላዉን አቋም በማክበር ላይ የልተመሠረተ የፖለቲካ አካሄድ ለለዉጡ ግብ እና ወደ ዲሞክራሲ ሽግግር እየተባለ ላለዉ ሂደት እንቅፋት እንደሚሆን ሊታወቅ ይገባል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታም ሰላም እና መረጋጋትን አያስገኝም፡፡ ስለሆነም ገዢዉ ፓርቲ እና መንግስትም እራሱን ፈትሾ ልስተካከሉ የሚገባቸዉን በማስተካከል ከኦነግም ሆነ ከሌሎች ባለጉዳዮች ጋር ተቀራርቦ በመተባበር እና በመቻቻል መንፈስ መስራት ለህዝባችን ጥቅም እንዲሁም ለመላ ኢትዮጲያ ሰላምም ዉጤታማ ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡
በሌላ በኩል በአሁኑ ሰዓት በሰሜን ኦሮሚያ (ወሎ) ዉስጥ በሚገኙ ኦሮሞች ላይ እየደረሰ ያለዉ ብሔር ተኮር ጥቃት እጅግ የሚያሳስበን ጉዳይ ነዉ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በነዚህ ዜጎች ላይ ይህንን ጉዳት እያደረሱ ያሉት ኀይሎች የጥፋት ተግባራቸዉን ለመደበቅ ስሉ እዚያ እየታየ ያለዉን ችግር ከኦነግ እንቅስቃሴ ጋር በማያያዝ የሚነዙት ፕሮፖጋንዳ ከእዉነት የራቃ መሆኑንም እናስገነዝባለን፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በኦነግ ላይ ሚነዛዉ ፕሮፖጋንዳ በአንድ በኩል የሕዝቡን እራስን የመከላከል መብትና ፍትሃዊ ጥያቄዉን ለማፈን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኦነግ እና የኦሮሞ ህዝብ የነፃነት ትግልን በማጠልሸት አጠቃላይ የነፃነት ትግሉን ዓላማ ለማደናቀፍ የሚደረግ የፖለቲካ ሸፍጥ ስለሆነ በኦነግ እና በህዝባችን ላይ የሚፈጸም እንዲህ ዓይነቱ ደባ ባስቸኳይ ሊገታና ልታረም ይገባል እንላለን፡፡ የአማራ ክልላዊ መንግስትም ሆነ የፌዴራል መንግስት ይህ ጉዳይ ከዚህ ወደ ከፋ ሁኔታ ሳይሸጋገር የነዚህን ዜጎች መብት የሚያስከብር ትክክለኛ መፍትሄ በመስጠት ሃላፊነታቸዉን መወጣት እንዳለባቸዉ እናስገነዝባለን፡፡
በመጨረሻም፣ ካለ ምንም ጥፋት በፖለቲካ ደባ እና መድልዎ ብቻ የታሰሩት የኦነግ አባላትና ደጋፊዎች (የአመራር አባላቱን ጨምሮ) በአስቸኳይ እንዲፈቱ አጥብቀን እየጠየቅን፣ በተጨማሪም በአባላቶቻችን እና ደጋፊዎቻችን፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ህዝባችን ላይ የተከፈተዉ የስም ማጥፋት፣ ማስፈራራት፣ ዝርፊያ፣ እስራትና ግድያ እንድቆም ደግመን እናሳስባለን፡፡ መላዉ ህዝባችን (በተለይም ቄሮ)፣ የተለያዩ ሸፍጦችን በመጠንሰስ እና የዉሸት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት የኦነግን ስም በማጠልሸት ድርጅቱን ከፖለቲካ ጫወታዉ ሜዳ ዉጪ በማድረግ እልፍ-ኣእላፍ የተሰዉለት የኦሮሞ ህዝብ የነፃነት ትግል ዓላማ ከግቡ እንዳይደርስ ለማድረግ የሚፈጸሙትን ደባዎች እና የሚሸረቡ ሤራዎችን ሁሉ በንቃት በመከታተልና ጠንቅቆ በመረዳት በቁርጠኝነት ተጋፍጦ እንዲያከሽፍ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አጥብቆ ያሳስባል፡፡
ድል ለኦሮሞ ህዝብ !
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር
ሰኔ 05, 2011 ዓ.ም
Filed in: Amharic