>

የኦነግ መንታ መንገድ ወዴት ያደርሰዋል? (ያሬድ ሀይለማርያም)

የኦነግ መንታ መንገድ ወዴት ያደርሰዋል?
ያሬድ ሀይለማርያም
በለውጡ ላይ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩት መንግስት ላይ እምነት ከማጣት ይሁን ሌላ ድብቅ አጀንዳ ከማንገብ፤ ኦነግ የመንታ መንገድ ጉዞውን ከጀመረ አረፋፍዷል። ኦነግ ለውጡ እሱ በሚፈልገው መንገድ እየሄደ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ሰገልጽ ቆይቷል። ከዛም አልፎ ሕግ እና ሥርዓትን በጣሱ የተለያዩ የወንጀል አድራጎቶችን ሲፈጽም እንደቆየ በመንግስት ሚዲያ ጭምር በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። መንግስት የአገሪቱን ዘላቂ ሰላም እሳቤ ውስጥ በማስገባት ይመስላል ለኦነግ ያሳየውን ያህል ትዕግስት ለማንም አላሳየም። ይህ የመንግስት አድራጎት በአንድ በኩል የአገሪቱን ዘላቂ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚቻለውን ያህል ሆደ ሰፊ መሆኑ የሚያስመሰግነውን ያህል ከለከት ያለፉ የሕግ መተላለፎች ሲፈጸሙም ተመጣጣኝ ሕግ የማስከበር እርምጃ አለመውሰዱ ደግሞ ችግሩ እንዲባባስ ምክንያት ስለሆነ በዛኑ ያህል ያስወቅሰዋል።
እንደማይተማመን ባልንጀራ ከኦነግ ጋር በየወንዙ የሚደረገው መማማል ብዙም ፋይዳ እንደሌለው ግን ድርጅቱ በዚህ ሳምንት ያወጣው መግለጫ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ኦነግ እንደ ድርጅት እና የሰራዊቱም አመራሮች በፈጸሙት የወንጀል አድራጎት እና የመብት ጥሰት አለመጠየቃቸውን እንደ እድል ተጠቅመው ወደ ሥልጡን የፖለቲካ ትግል አለመመለሳቸውንም መግለጫው ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል በሰራዊታቸው በኩል እየተፈጸሙ ያሉት እርምጃዎችም ጥሩ ማሳያዎች ናቸው።
ከቡራዩ እልቂት ወዲህ ጎልቶ መሰማት የጀመረውና አንድም ሁለትም መሆናቸው የሚገለጸው የምርጫ ፖለቲካው መስመር ላይ የተሰለፈው ኦነግ እና ዱር ቤቴ ያለው ኦነግ ሽኔ ጉዳይ የዶ/ር አብይን አስተዳደር ክፉኛ እየተፈታተኑት ይመስላል። ይህ ስልታዊ መሰንጠቅ፤ የኦነግ እንቅስቃሴ ሲበርድ በጅ፤ ሲፋጅ በማንኪያ አይነት የፖለቲካ ቀመር ይመስላል። በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ የለውጡን ሂደት የተቀበለው በግማሽ ልብ ስለሆነ ሰራዊቱን ጠቅሎ እነ ዶ/ር አብይ እጅ መክተት አዋጪ ስልት እንዳልሆነ በአማካሪዎቹ በኩል በደንብ የተገለጸለት ይመስላል። ስለዚህ ካለው በአስር ሺ የሚቆጠር ሰራዊት ውስጥ ለምርጫው ፖለቲካ እጅ መንሻ የምትሆን ሲሶ ያህል የሰራዊት ቁጥር፤ እሱም ከብዙ ደጅ ጥናት እና የመንግስት ልምምጥ በኋላ ወደ ተዘጋጀላቸው ካምፕ እንዲገቡ አድርጓል።
የቀረውን በአሥር ሺ የሚቆጠር ሰራዊት ልክ ከዋናው ኦነግ የተገነጠለ በማስመሰል ዋና ስሙ ላይ ቅጥያ ለጥፎ ጫካ ውስጥ አድፍጦ እንዲቆይ የተደረገው የክፉ ቀን ወይም የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ኃይል እንዲሆን ይመስላል። ኦነግ እሱ በሚፈልገው መልኩ ለውጡን መጠምዘዝ ያልቻለ እለት ወይም በዶ/ር አብይ መንግስት የመዋጥ አደጋ የተጋረጠበት በመሰለው ጊዜ ጫካ ያስቀመጠውን የመጠባበቂያ ኃይል በቀጭን ትዕዛዝ ትግሉን እንዲያጧጡፍ ጥሪ ከማድረግ ወደኋላ አይልም። ይሄ በአንድ ጊዜ በሁለት ታንኳ ለመቅዘፍ የተቀየሰው የኦነግ ሥልት ኦሮሚያ ክልልን በተለየ ሁኔታ እና በአጠቃላይም አገሪቱ እንዳትረጋጋና የለውጡ ኃይልም አገሪቱን ወደ ሚቀጥለው የዲሞክራሲ እና ልማት ምዕራፍ እንዳያሸጋግር እንቅፋት የሚሆን ይመስለኛል።
ኦነግን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች እና ምሁራን ለውጡ የተጀመረውን አገራዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በሙሉ ልብ ተቀብለው እና በለውጡ ኃይል የጎደሉ ወይም ያልተሟሉ ያሏቸውን ነገሮች ገንቢ በሆነ መልኩ እንዲስተካከሉ እያሳሰቡ ሕዝብ የተሰዋለት ለውጥ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ሁሉም የበኩሉ አወንታዊ ሚና ካልተጫወተ ምርጫው የሚታሰብ አይሆንም። ምርጫው በታሰበለት ወይም በአጭር የማራዘሚያ ጊዜ ካልተካሄደ ደግሞ ካለንበት የሽግግር ምዕራፍ ወደ ተረጋጋ ፖለቲካ ልንሄድ አንችልም። ምናልባትም ግጭቱ ሌላ መልክም ሊይዝ ይችላል።
በዶ/ር አብይ የሚመራው የለውጥ ኃይል ችግሮች ቢኖሩበትም እንደ እኔ እምነት አገሪቱ ከተቀረቀረችበት አረንቋ ለማውጣት አቅሙም ሆነ እድሉ ያለው ብቸኛ ኃይል ይመስለኛል። ይህን ኃይል ማዳከም ወይም ወደጎን መግፋት ለውጡንም አብሮ ማሽቀንጠር ነው የሚሆነው። ብዙዎች ምሁራን፤ ለውጥ የለም፣ የዶ/ር አብይ አመራር ድብቅ ተልዕኮ አለው፣ ኢትዮጵያ የከሸፉ አገሮች ተርታ ገብታለች፤ የተጀመረው የፖለቲካ ለውጥ ተቀልብሷል የሚሉ እሮሮውችን በማሰማት ላይ ናቸው። በግሌ እነዚህን መደምደሚያዎች አልጋራቸውም። ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎች ግን ሊሆኑ ይችላሉ።
በእኔ እይታ ለውጥ አለ። ለውጡ የት ደርሷል? በምን ያህል ፍጥነት እየተጓዘ ነው? የታሰበለት ደረጃ ላይ ደርሷል ወይ?  በሚሉት ጥያቄዎች ላይ እኔም የራሴ ቅሬታ ቢኖረኝም ልንወያይባቸው እንችላለን። እነ ዶ/ር አብይን ከሃዲ እና ድብቅ አላማ ያነገቡ አድርጎ የሚተረከውን ነገር ለእኔ ከተረት ተረት የዘለለ አይደለም። መሬት ላይ አፍጠው የሚታዩ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም የለውጥ ኃይሉ ግን ሕዝብን እያታለለ ነው የሚል እምነት የለኝም። ተግዳራቶቹ የለውጡ ፈተናዎች ናቸው። እነሱን እንዴት ተቋቁሞ ይውጣ የሚለው ነው አሳሳቢ ጉዳይ። ፈተናዎቹን የለውጡ መሪዎች እራሳቸው ሆን ብለው ያመጡት እና ለድብቅ ተልዕኮ ማሳኪያ ተደርጎ መገለጹ ግን ውኃ የሚቋጥር ሙግት አይደለም። ከዛም አልፎ ኢትዮጵያን በጦርነት ከወደሙት ሌሎች አገሮች እኩል የከሸፈች (failed state) አድርጎ ማቅረብም ሌላው ጽንፍ የያዘ ትንታኔ ይመስለኛል። በዚህ ጉዳይ ወደፊት እመለስበታለሁ።
ወደ ዋናው እርዕሴ ስመለስ አሥርት አመታትን ጫካ ውስጥ ላሳለፉ የትጥቅ ድርጅቶች ትልቁ ፈተና ከትግላቸው ማግስት እራሳቸውን ወደ ሥልጡን የፖለቲካ ጨዋታ ለማምጣት ያለው ትንቅንቅ ነው። ሁለቱ አለሞች ፍጹም የተለያዩ ናቸው። ስነ ልቦናውም የዛኑ ያህል የተለያየ ነው። በነፍጥ ትግል ጥርሱን የነቀለ እና እድሜውን የፈጀ ሰው ከጫካ ወጥቶ አዲስ የዲሞክራሲ ጨዋታ ለመጫወት ቅድሚያ ከራሱ ጋር መታገል አለበት። ዘመናት ጫካ ውስጥ መሽጎ የኖረ ኃይል በስነ አዕምሮም ሆነ በአካላዊ ዝግጅት ከነፍጥ ወደ ዲሞክራሲ እና የምርጫ ካርድ መምጣት እንዲህ ቀላል አይደለም። እንኳን ስልጣኑ በሌላ አካል ተይዞና ተሳታፊ ለመሆን ይቅር እና ህውኃት ከትጥቅ ትግል ማግስት ሥልጣኑንም ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥራ ለሃያ ሰባት አመታት በድንበር ተጋዳላይ ስነ ልቦና ነው የቆየችው።
ዛሬም ህውሃት በዛው ስነ ልቦና ውስጥ ትገኛለች። በአስራ ሰባት አመቱ የጫካ ትግል ዘመን፣ ከደርግ ውድቀት በኋላም በሃያ ሰባቱ አመት የሥልጣን ዘመን እና ባለፉት አንድ አመት ተኩል ከስልጣን የመገለል ዘምን ውስጥ ሕውሃት የስነ ልቦና ወይም የባህሪ ለውጥ አላሳየችም። ዲሞክራሲና ህውሃት ሳይተዋወቁ ግማሽ ክፍለ ዘመን ሊሆን ነው። የኦነግም ችግር ከዚህ የራቀ አይመስለኝም።
ቅን እያሰብን፣ በጎ እየሰራን በቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic