>

የነበርን አለን፡ የመጡት ሄደዋል (መሳይ መኮንን)

የነበርን አለን፡ የመጡት ሄደዋል

መሳይ መኮንን

ለሁለተኛ ጊዜ እመጣለሁ ብዬ ቃል ስለገባሁ እንጂ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ መመለሱን ውስጤ አልፈቀደውም። ቢያንስ ለቃሌ ክብር ስል ወደዚህ መንደር ዳግም መጣሁ። ለሶስተኛ ጊዜ እንደማልመለስ ግን ከወዲሁ አረጋግጥላችኋለሁ። ክፉ ጊዜ ገጥሞን ትላንት ስለአንድ ዓላማ የተሰለፈን የአንድ ቤት ልጆች አደባባይ ወጥተን ትዝብት ላይ በሚጥል እንካሰላንቲያ ውስጥ መግባቱን የማልመርጠው ነገር ግን እየተናነቀኝም ቢሆን ላደርገው የወሰንኩት መራር ነገር ሆኖብኛል። የቅንዎችን ተማጽዕኖ ወደጎን ገፍቼአለሁ። ስለኢሳት ብላችሁ አደብ ግዙ የሚለውን የበጎ አሳቢዎችን ‘’የተኩስ አቁሙ’’ ልመና ባለማክበሬ ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ።  ይሉኝታን ደፍጥጦ፡ ዓይኑን በጨው አጥቦ ‘’የእውነትና የመርህ ሰው’’ የሚለው ዲስኩር  ሲደጋገም ትዕግስትን መፈታተኑ አይቀርም። ደግሞም ህዝብ ማወቅ ያለበት እውነት ተጣሞ እየተነገረ፡ ህዝብም እየተደናገረ እስከመቼ በዝምታና በትዕግስት ይዘልቃል?  በድጋሚ እንዲሰመርልኝ የምፈልገው የነበረንን አብሮነት የማጣጣል አልያም የማራከስ ሀሳብ የለኝም። የዚህ ጽሁፍ ግብ ከተገፋን ውሳኔአቸው ጋር የተያያዘውን የተወላገደና ቅንነት የጎደለውን ትርክታቸውን ለማስተካከል ብቻ ነው።

ከላይ የተጠቀምኩትን ርዕስ ባልጠቀመው እመርጣለሁ። ኢሳት ሲመሰረት ጀምሮ የነበሩ፡ ዓላማና ግቡን ተረድተው፡ አፈር ላይ ተንከባለው፡ ጠረጴዛ ላይ እየተኙ ያቀኑት ሰዎች አሁንም ከኢሳት ጋር ናቸው። በህዝብ ድጋፍ ኢሳት በሁለት እግሩ ከቆመና ህዝባዊ ደጋፉ በማያወላውል መሰረት ላይ ከጸና በኋላ ሌሎች ባልደረቦች ተቀላቅለዋል። በተሰራና ሁሉን ባለቀ ቤት ገብተዋል ለማለት ባያስደፍርም የመጀመሪዎቹ አራት ዓመታት የነበረው ውጣ ውረድን ያየ ከኢሳት ጋር ቃልኪዳኑ እስከመቃብር ሊሆን እንደሚችል ይሰማኛል። ምሶሶው በቆመ፡ ጣሪያው በጥሩ ሁኔታ በታነጸ የኢሳት ቤት ውስጥ ኋላ ላይ የተቀላቀሉት ዲኮሬት አድርገው ውበት ያለው ጥሩ ህንጻ እንዲሆን ሚና ተጫውተዋል። የኢሳት ቤት ዘላለሙን የማይፈርስ ነው ባይባልም በደምና በወዛቸው ያቆሙት ባልደረቦች ግን በክፉ ጊዜ ከፋን ብለው ለአደጋ ጥለውት እንደማይሄዱ የሰሞኑ ግርግር ምስክር ሆኖ ለኢትዮጵያ ህዝብ ቀርቧል።

የመርህ፡ የእውነት ምናምን የሚለውን ዘባተሎ ማንጠልጠያና ለገበያ ፍለጋ የተለቀቀ ዲሪቶ ለጊዜው የሚሸምተው ሸምቶታል። ለእውነት ልቦናውን ጥርቅም አድርጎ የዘጋና በአሉባልታ ወሬዎች የዕለት ቀለቡን እየሰፈረ መኖርን ህይወቱ ያደረገው የመንጋ ስብስብ ድጋፍና ጭብጨባ ጊዜያዊ ሙቀት መሆኑን ያልተረዳ ካለ እሱ የዋህ ብቻ ነው። መልክና ስሙን ደብቆ በማህበራዊ ሚዲያ የሚያደነቁረው ጩኸት የእውነትን ዋንጫ የሚያሽልም አይደለምና ቦታም የሚሰጠው አይሆንም። ስድብ የድንቁርና መገለጫ መሆኑን ግን ማስታወስ ያስፈልጋል። ስድብ የተሳዳቢውን እንጂ የተሰዳቢውን ማንነት ፈጽሞ አይገልጸውም። ዋናው እውነት ነው። ከሀቅ ጋር መቆም። አርነት የሚያስገኘው የእውነት መንገድ እንጂ በመንጋ ዘመቻ፡ በባዶ ጩኸት የታጀበ ጉዞ አይደለም። እውነት ለመናገር ማህበራዊ ሚዲያውን ያጥለቀለቀው፡ ሳያላምጥ የሚውጠው የሰነፍ መንጋ ጭብጨባ ምን ያህል ርቀት እንደሚወስድ አብረን የምናየው ይሆናል። ሽልም ከሆነ ይገፋል ቦርጭም ከሆነ ይጠፋል።

በባለፈው ጽሁፌ እንዳልኩት ኢሳት ውስጥ አፈና ተፈጸመብን የሚሉት የቀድሞ ባልደረቦች በእነሱ መልክና ቅርጽ የቆመ ኢሳት እንደማይኖር ቁርጡን ማወቃቸው ለውሳኔ አብቅቷቸዋል። ኢሳት ፕሮፌሽናል ሚዲያ እንዲሆን፡ ከስሜትና ከተዛቡ መረጃዎች የራቀ የሚዲያ ስራ ይዘን በአዲስ መልክ እንውጣ የሚለው ውሳኔ ፈጽሞ አልተመቻቸውም። ፖለቲካዊ አቋማቸው ምንም ይሁን ምን ሚዛናዊ የሆነ መረጃና አቀራረብ እንዲኖር የሚያስገድደው አዲሱ የኢሳት ኢዲቶሪያል ፖሊሲ በእነሱ ሚዛን የአፈና እርምጃ ተደርጎ መታየቱ አይደንቀኝም። መኖር የሚችሉት፡ አቅማቸውና ችሎታቸውም የሚፈቅደው በዚያ የሚዲያ አውድ እንደሆነ እረዳለሁ። እኛም ትግል ሆኖብን ጋዜጠኝነቱን በአንድ እጅ አክቲቪዝሙን በሌላ እጅ አድርገን መዝለቃችን የኢሳትን ቤት አንድ መልክ ብቻ እንዲኖረው አድርጎታል። ይህ የኢሳት ባህሪ ከጋዜጠኝነት ጋር ባይተዋር የሆኑ ግን ደግሞ በሌላ ዘርፍ አቅምና ችሎታ ያላቸውን ወዳጆቻችንንም መድረክ እንዲኖራቸው አድርጓል።

ለሁለት ቀናት ስድስት ሰዓታት የፈጀውን ስብሰባ የተመለከተ የድምጽ መረጃ በኢሳት ዋና አዘጋጅ ፋሲል የኔአለም አማካኝነት የሚለቀቅ እንደሚሆን ሰምቼአለሁና እውነተኛ ዕይታ እንዲኖረው የሚፈልግ ቅን ሰው ከድምጹ መረጃ የራሱን እውነት ያገኛል ብዬ እጠብቃለሁ። ፋሲል የድምጹን መረጃ እንዲያወጣም በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ። ልብና አይኑን በአሉባልታ ወሬዎች የሸበበው መንጋ የማህበራዊ ሚዲያ ሰራዊት እውነት ቆሞ፡ ደም፡ ስጋና አጥንት ለብሶ ቢመጣለት አንገቱን በገጀራ ቆርጦ ከመጣል ወደኋላ የማይል በመሆኑ ለዚህ ሰራዊት የድምጹ መረጃ ላይጠቅመው እንደሚችል ከወዲሁ መገመት እችላለሁ። በነገራችን ላይ አሁን ተገፋን ከሚሉ ባልደረቦች አንደኛው የዚያን ዕለት ስብሰባውን በድብቅ ለራሱ ሲቀዳ እጅ ከፍንጅ ከተያዘ በኋላ ነው እንዲያቆመው ተደርጎ ሁሉም በተስማማበት ፋሲል የኔዓለም ብቻ እንዲቀዳ የተደረገው። ያ ባልደረባ ግን በድብቅ ሊቀዳው ለምን ፈለገ?

የአዲስ አበባ የኢሳት ጉዞ

በቀድሞ የኢሳት ባልደረቦች እየተለቀቁ ያሉት የአፈናና የተገፋን ትርክቶች ብዙም አልደነቀኝም። ለአደባባይ መብቃታቸው እንጂ ለወራት በዘለቀው የውስጥ ፍጥጫና ሹክቻ በየዕለቱ የምንሰማቸው ነበሩ። የአዲስ አበባ ጉዞአችን በሴራና አሉባልታ የተንቆጠቆጡ ትርክቶችን በብዙ እጥፍ እንዲራቡ አድርገዋል። ለስድስት ሳምንታት ኢትዮጵያ ቆይተን ስንመጣ ከቢሮ የጠበቁን የዛሬዎች ከሳሾች አሉባልታን ታጥቀው፡ በሴራ የተጎነጎኑ ክሶችን በፋይል አደራጅተው ነው። ያስደነግጣል። ለዓመታት አብረን የዘልቀን ከመሆናችን አንጻር ባህሪ ለባህሪ የተግባባን፡ ማን ምን እንደሚፈልግና እንደሚጠላ በቅጡ የተናበብን መስሎኝ ነበር። የህወሀት የትኛውም ድለላም ሆነ ማስፈራሪያ የማይበግረውን የኢሳት ስብስብ በትንንሽ አሉባልታዎችና፡ በልውጡ አንጻር ከያዙት አቋም በመነሳት ፍረጃ ውስጥ የገቡት የዛሬዎቹ ከሳሾች ‘’የአብይ ተላላኪ፡ የኦዲፒ ቃል አቀባይ፡’’ የሚሉ የሹክሽኩታ ወሬዎችን በግልጽ በስብሰባዎች ላይ መናገር ሲጀምሩ አፍን በአግራሞት ከመያዝ ያለፈ ምላሽ ለመስጠት እንኳን የሚችገር ሆነብን። አንተዋወቅም ማለት ነው? የጀመርነው የነጻነት ጉዞ መንገድ ላይ በገንዘብ ድለላ የሚጠለፍ አድርገን እናምን ነበርን?

የኢሳት የአዲስ አበባ ጉዞ የሁሉንም ስምምነት ያገኘ እንደነበረ ቃለጉባዔዎች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። የሚሄዱት አባላት ምርጫ ላይ የተወሰኑ ውዝግቦች ቢኖሩም በመጨረሻም የሁሉም ስምምነት ተገኝቶ ጉዞው ተደርጓል። የወረቀት፡ የጉዞ ሰነድ ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች መሄድ የማይችሉ ባልደረቦች ዛሬ ላለመሄዳቸው በስምምነት የተደረገውን ጉዞ ሆን ተብሎ የ’አብይ ደጋፊዎች’’ ብለው የተፈረጁ ባልደረቦች ተመርጠው የተላኩ አድርገው መክሰሳቸው አስገራሚ ሆኖብኛል። ቢያንስ ተገፋን ካሉት ከሳሾች መሃል በፊተውራሪነት የሚታዩት ሁለቱ የጉዞው አካል እንዲሆኑ ተጠይቀው የራሳቸውን ምክንያት በማቅረብ መሄድ እንደማይችሉ መግለጻቸውን የሚዘነጉት አይመስለኝም። እነሱ አብረው ላለመሄድ ያቀረቧቸው ምክንያቶች ለአሁኑ ክስ ለማመቻቸት ነው የሚል የሴራ ትንታኔ ውስጥ መግባት አልፈልግም። ነጥቦችን በማገናኘት የሚሰጠው ድምዳሜ ግን የያኔውን ምክንያታቸውን ጥርጣሬ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርገዋል። ሁለቱ የዛሬዎቹ ከሳሾች የአዲስ አበባው ጉዞ አካል ቢሆኑ ኖሮ አሉባልታውም ሆነ ሴራው እንኳን ለውጭው ይቅርና ለራሳቸው ቡድን አባላትም የሚያሳምን አይሆንም ነበር።

ሴራና አሉባልታ የከሳሾቻችን ዋልታና ማገር ናቸው። አንድ ምሳሌ ላንሳ። አዲስ አበባ የሄደው የኢሳት ቡድን ኢሳትን ጠቅልሎ ለራሱ ሊያደርግና ለዶ/ር አብይ በገጸበረከትነት ሊያስረክብ ነው የሚል አፍና ጭራ የሌለው ነገር መዘዙ። ኢሳትን ከማንኛውም አካል ተጽዕኖ ለማላቀቅ በብርቱ ያደረግነው እንቅስቃሴ ጠምዝዘው በአዲስ አበባ በስማቸው ሊከፍቱ፡ ዓለም አቀፍ የኢሳት ቻፕተሮችንም ፈንግለው ኢሳትን በባለቤትነት ሊቆጣጠሩት ነው የሚል ፍጹም ልብወለድ የሆነ ታሪክ በመፍጠር ሌሎችን ከማሳመን ባለፈ በመላው ዓለም ለሚገኙ የኢሳት ደጋፊ ቻፕተሮች አሰራጩት። ይህን ሲያደርጉ በተባባሪነት በዓለም አቀፉ ቻፕተር ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የራሳቸው አጀንዳ ያላቸውን ሰዎች መጠቀማቸው የፈጠራ ድርሰታቸውን የእውነት አድርጎታል። ባልዋልንበት፡ ባላደረግነው፡ ባልፈጸምነው ሃጢያት ፡ የተቀደሰ ዓላማ ይዘን ብቻ የተነሳነውን የኢሳት ባልደረቦች በቻፕተሮች ዘንድ ጥላቻና ተቃውሞ እንዲፈጠርብን ዘመቻ ከፈቱ። ይህን ያደረጉት ለሁለት ምክንያት ነው። አንደኛው የኢሳትን አካሄድ የጸረ ለውጡ ልሳን እንዲሆን አድርገው ለመቆጣጠር የእኛ መኖር እንቅፋት ስለሆነባቸው ነው። በውጤቱም ኢሳትን በመዳፋቸው ውስጥ አስገብተው እንቅልፍ አጥተው ለሚያድሩለት ‘’የጸረ አብይ’’ ፡ ‘’ጸረ ለውጥ’’ ዘመቻቸው ሁነኛ መድረክ እንዲሆን ማድረግ ነው። ያ ካልተሳካ ደግሞ ኢሳትን በደቦ አፍርሶ በኢሳት ፍርስራሽ ላይ በልባቸው የጸነሱትን አዲስ ሚዲያ የማቋቋም ህልም እውን ማድረግ ነው።

የመጀመሪያው አልተሳካላቸውም። ሊሳካላቸውም አይችልም። የሚችሉትን አድርገዋል። በቅንነት ቢሆን የእኛም ድጋፍ ከጎናቸው ይሆን ነበር። በጎሪጥ ከምንተያይ በመከባበር አብረን መዝለቅ አያቅተንም። ነገር ግን የስንቱ ላብ ጠብ ያለለትን፡ የስንቱን ተስፋ የሰነቀውን ተቋም በአንዲት ጀምበር አፍርሶ መሄዱ ለምን አስፈለገ? በኢሳት ፍርስራሽ ካልሆነ ሚዲያ ማቋቋም የማይቻልበት አማራጭ መንገድ እንዴት ጠፋቸው? እቅዳቸው በአድማ እግራቸው ከኢሳት ደጃፍ የወጣ ዕለት የኢሳት ቤት እንዲዘጋ ማድረግ ነበር። አልሆነም። ከእነሱ ይልቅ በአሉባልታ ወሬዎች የተጠለፈው ዓለምዓቀፉ የኢሳት ቻፕተር ለአሁኑ ግርግር በአንድም ይሁን በሌላ አስተዋጽኦ እንዳለው ያውቀው ይሆን?

በአከሌ የሚመራና ኢሳትን የግላቸው ለማድረግ የሞከሩ ባልደረቦች ቡድን ከአዲስ አበባ መልስ አሜሪካ ሲደርሱ እቅዳቸው ከሸፈባችው የሚል ባዶ የሴራና የአሉባልታ ትርክት ከሽኖ ሌሎችን አሳምኖ፡ ለአቅመ አድማ አብቅቶ፡ አይኑን ሳያሽና ሳያርገበግብ በአደባባይ የሚናገር ባልደረባ እንደምን በአንድ ጣሪያ ስር አብሮን ኖረ? ይህን ፍጹም ሀሰትና ከኬስ የወጣ ወሬ አምኖና አሳምኖ ብቅ ያለን ይህን ወዳጅ ከዚህ በፊት ያሳተማቸውን መጽሃፍትንና ለዓመታት አፍ ያስከፈተባቸውን ትንታኔዎቹ ጥርጣሬ ውስጥ የሚከቱ ሆነውብኛል። እኔ ባልኖርበት በእርግጥ አምነው ነበር። ያለሁበትን፡ በፊት መሪነት የተሳተፍኩበትን የኢሳትን የወደፊት አቅጣጫ የመዘርጋት ስራ በሴራና አሉባልታ ጠልፎ አድማ ማስመታት ያሳፍራል። ያስገምታል። ቀድሞ የተጻፈልንና የተነገረንን መልሰን እንድንፈትሽ ያደርጋል። ይህንንም በፊት ለፊት በስብሰባ ለወዳጃችን ገልጬአለሁ። ያልተጀመረ ነገር አይከሽፍምም። የሌለ ነገር አይጨናገፍም። የእሱን ሴራ የእውነት አድርገው ተቀብለው ከኢሳት በአድማ የወጡት ሌሎች ባልደረቦች የሚጸጽት ውሳኔ ላይ ለመድረሳቸው ጊዜ ሲገልጥላቸው የሚሉትን እንሰማለን። ከአፈርኩ አይመልሰኝ ካላሸነፋቸው በቀር እውነቱን በተረዱ ጊዜ የሚሉትን እንደሚሉ ተስፋ አደርጋለሁ። ቢያንስ ለህሊናቸው ዋጋ የሚሰጡ መሆናቸውን አምናለሁና።

ኢሳትን በተመለከተ የአዲስ አበባው ጉዞ አባላት ያደረጉትን ለማወቅና እውነት መሻት የፈለገ ጉዳዩን የያዩዙት ታዋቂው የህግ ባለሙያ አቶ ሞላ ዘገየ በቦሌ መንገድ ላይ በሚገኘው ቢሮአቸው ጎራ በማለት አልያም በስልካቸው በመደወል ማረጋገጥ ይችላል። ኢሳትን በአክሲዮን ያስመዘገቡ አካላትን አወያይተን፡ በአዲስ አበባ የተመሰረተውን ቦርድ አባላት አነጋግረን ኢሳት የህዝብ ሚዲያ Public media ሆኖ እንዲቋቋም ያደረግነውን ጥረት ገልብጦ ህዝብን እያደናገሩ ድጋፍ ለመሸመት አደባባይ መውጣት ከትንሹ እግዚያብሄር ከሆነው ህሊናችን መቼም የማናመልጠው ክህደትና ሃጢያት ነው።

ኢሳት ገፋን፡ አፈነን ብለው የወጡትና በአንዲት ጀምበር ሚዲያ ያቋቋሙት የቀድሞ ባልደረቦች ላለፉትሶስት ወራት ምን እያደረጉ እንደነበረ ከአሉባልታ የራቀ፡ እውነት የሆነ፡ መሆኑንም አሁን ላይ ያረጋገጠ መረጃ እንሰማ ነበር። ከኢሳት ዓለም ዓቀፍ ቻፕተሮች በአንዳንድ ከተሞች ያሉትን በመቅረብ ወደፊት ስላሰቡት እቅድ ሲያማክሯቸው እንደነበርና ተለጣፊ ሚዲያ ለማቋቋም እንደተዘጋጁ በመግለጽ የተባበሩን ጥያቄ ማቅረባቸው ከሀሜት የዘለለ መረጃ ነበረን። ምናልባት በቅርብ ጊዜ በተወሰኑትና ፍቃደኝነታቸውን ባሳይዋቸው ከተሞች የገቢ ባሰባሰቢያ ዝግጅቶችን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይጠበቃል። ኢሳትን ማፍረስ ከባድ ነው፡ አንድ አካል የራሱ ማድረግም አይችልም የሚል አቋምና እምነት ስለነበረን በውስጥ ለውስጥ ሲያደርጉ የነበሩት እንቅስቃሴ ብዙም ርቀት እንደማይወስዳቸው አውቀናል። በቅንነት ያልተጀመረ ጉዞ መንገድ ላይ እንደሚያስቀር አምናለሁ። በሌላው ኪሳራ የሚሰላ ትርፍ አይኖርም። በኢሳት ውድቀት የሚቆም ሚዲያ እድሜው አጭር ነው።

አሁን ላይ ከየቻፕተሮቹ የምንሰማቸው ነገሮች እነዚህ ባልደረቦች የቆየ እቅድ እንደነበራቸው ነው። የመልቀቂያ ደብዳቤ አዘጋጅቶ የኢሳት የወቅቱ ዳይሬክተር ከኢትዮጵያ እስኪመለስ የሚጠብቅ ባልደረባ በዚሁ በተገፋን፡ ታፈንን ትርክት አደባባይ መውጣቱም አሁን እየተደረገ ያለው የተጠቃን ጩኸት በአጋጣሚ የተከሰተ ላለመሆኑ አንዱ አስረጂ ጉዳይ ነው። ሌላው ቢቀር ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ በዋሽንገተን ዲሲ አዲስ ስቱዲዮ ለመገንባት የሚያስችል የካሜራና ሌሎች እቃዎች ግዢ ምክርና የእቃዎቹን ስፔሲፊኬሽን ሲጠይቅ የከረመው የዛሬው አንዱን ከሳሽ ባልደረባችንን ጉዳይ ሳስበው ግርም ይለኛል።

የማያልቀው፡ መጨረሻ የሌለው ሴራ

ተገፋን ብለው የወጡት የቀድሞ ባልደረቦች የሴራ ትንታኔአቸው መነሻ ከኦዲፒ ቢሮ ነው። አንዳንድ ጊዜም ከቤተመንግስት ቅጥር ግቢ ይነሳል። በፕሮፓጋንዳው ዘርፍ የተካነ ሰው ትርክቱ ጆሮና ቀልብ እንዲያገኝ ተቀናቃኝ መፍጠርን የመጽሀፍ ቅዱስ ያህል ያምናል። ጠላትና ወዳጅ መፍጠር የትርክቱ የጀርባ አጥንት ነው። በእኛ ላይ የተከፈተው ዘመቻም ከዚሁ ፕሮፖጋንዳ ጽንሰሀሳብ የሚነሳ ነው። ኢሳትን ኦዲፒ ሊያፍረሰው ነው፡ ዶ/ር አብይ ከሌሎች ሚኒስትሮቻቸው ጋር ቁጭ ብለው ኢሳትን አጀንዳ አድርገው የተደመሩና ያልተደመሩትን ለይተው፡ ያልተደመሩት እንዲባረሩ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡ ለዚህም ረብጣ ዶላር ሰጥተዋል ብሎ የሚነግርህና ይህንንም ደምስሩ እስኪቆም በንዴት ጦፎ የሚገልጽልህን ባልደረባህን ምን መልስ ትሰጠው ይሆን? እነዚህ መሪዎች ስራ ፈትተው የኢሳትን ጉዳይ አጀንዳ አድርገው ተወያዩ ብለው የተነሳህ ጊዜ በእርግጥ ጤንነትህን መጠራጠር አለብህ። ምናልባት ያለታማኝ ፍቃድ ይህን መረጃ ባወጣው የሚቀየመኝ ከሆነ ይቅርታ እጠይቃለሁ። በማህበራዊ ካፒታሉ፡ በስራውና በባህሪው ሳር ቅጠሉ የሚያመሰግነውን ታማኝ በየነንና ቢዝነሱን መስዋዕት አድርጎ ከኪሱ ጭምር በማውጣት ትግሉን ሲያግዝ የከረመውን ነአምን ዘለቀን ከአብይ ገንዘብ ተቀብላችሁ ኢሳትን ለኦዲፒ ሸጣችሁ ብለው በአደባባይ የሚነግሩን እነዚህ ባልደረቦች የሞራል መሰረታቸው በምን ይሆን የተገነባው?

እንግዲህ ለትርክታቸው ማዳመቂያ ኦዲፒና ዶ/ር አብይ እንደመስዋዕት በግ ቀርበዋል። በኢትዮጵያ የተፈጠረውና ዘርን መነሻ ያደረገው ጥቃት የወለደው ብሶት አብዛኛውን ሰው ቁጭት ውስጥ እንዲገባ ማድረጉ ለዚህ ትርክት ማረፊያ የሚሆን ቦታ አላሳጣውም። የውሸት ትርክት ቢሆንም ሜዳ ላይ የሚወድቅ አይደለም። ገዢ ሞልቶታል። ሰሞኑን ኢሳት የኦዲፒ መፈንጪያ፡ የኦሮሞ ብሄርተኞች ማቀንቀኛ እንደሚሆን አትጠራጠሩ የሚል በትንበያ መልክ የተገለጸ ሴራ ወለድ ዲስኩር ያሰማው የቀድሞ ባልደረባችን አሁንም ይሄን የማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተኮለኮለውን መንጋ በባዶ ሴራ እያጠመቀ እንደሚዘልቅ እርግጠኛ መሆኑን ያመነ ይመስላል። አልተሳሳተም። ሳያላምጥ መዋጥ ባህሪው የሆነው የማህበራዊ ሚዲያው የመንጋ ሰራዊት ይህን ዲስኩር ለማስተጋባት ደቂቃዎች አልፈጀበትም። የመድሃኒት እንክንብል እንኳን በሰውነት ውስጥ ለመስራት 20 ደቂቃዎችን ይፈጃል። እንዲህ ዓይነት ትልቅ ክስ ኢሳት ላይ ሲቀርብ ተቀብሎ ለማራገብ ሰከንዶች አለማስፈለጋቸው አስገራሚ ያደርገዋል።

በእርግጥ ባለፈው ጽሁፌም እንዳልኩት ኢሳት በስምንት ዓመት ጉዞው የመጣበት የሚዲያ አገልግሎት አሁን ላይ መቀየር እንዳለበት እናምናለን። የሚቀየረው ግን ለመጣው ለውጥ ጭፍን ድጋፍ ለመስጠት አይደለም። ይልቅስ ለውጡ ያመጣቸውና ትላንት ያልነበሩ አደጋዎችን የምንሻገረው ሃላፊነት በሚሰማው የሚዲያ ስራ ነው ከሚል እምነትና እምነት ብቻ ነው። ሌላ ነገር የለም። ካለም ከሀሜት ያለፈ አይሆንም። ይህ የሃላፊነት ውሳኔ በመንግስት ደጋፊነት ሊያስፈርጅ አይገባም። የሚያሳስበን የኢትዮጵያ ሁኔታ ነው። ለውጡ የኢትዮጵያን አንደነትና ህልውና አደጋ ውስጥ እንዳያስገባው ሁሉም ወገኖች በሃላፊነት ስሜት እንዲንቀሳቀሱ በእውነተኛ መረጃና ከስሜት በራቀ ትንታኔ በሚዲያችን አማካኝነት ጫና መፍጠር ነው አዲሱ አቅጣጫ። በለውና ፈንግጪው አካሄድ ሀገር ያፈርሳል ማለት በየትኛው መዝገበ ቃላት ውስጥ የመንግስት ደጋፊ እድርጎ እንደሚያስፈርጅ ሊገባኝ አልቻለም። በአጭሩ ተገፋን ብለው የወጡት የኢሳት ባልደረቦች ቀልብ የሚስብ፡ አንጀት የሚያራራ ነው ብለው ያመኑት የሴራ ትርክት ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው።

የቴዎድሮስ ጸጋዬ ቃለመጠይቅና ከዕለታዊ ‘ተገፋሁ’ ክስ

በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ዋና ተዋናይ ስለነበርኩ እኔ ዘንድ ያለውን እውነት ለመናገር እፈልጋለሁ። ከዕለታዊ ተገፋሁ ክስ ልጀምር። ይሄን ክስ ያቀረበችው የቀድሞ ባልደረባ ሀቅ ለመናገር ድፍረት ማጣቷ በፊት ስለእሷ ከነበረኝ ግንዛቤ ጋር ፍጹም የሚላተም ሆኖብኛል። ስለክራችን መመስከር ብንችል ጥሩ ነው። እውነትን በየትኛውም መልኩ ቢገለባብጧት ቀለሟን አትለቅም። የሆነው እንዲህ ነው።

በዚያን ቀን የዕለታዊ ተረኞች የነበርን አራት ባልደረቦች የመወያያ ርዕስ ለመምረጥ ተቀምጠናል። የዚያን ዕለት ትልቁና አነጋጋሪ የሆነው ዜና የሜቴክ ዳይሬክተር ብ/ጄነራል ክንፈ እጆቻቸውን በካቴና ተጠፍንገው በብጫዋ ሄሊኮፕተር ወደ ቃሊቲ የተወሰዱበት ክስተት ነበር። እንኳን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ይቅርና የውጭ ብዙሃን መገናኛ ድርጅቶች የዚያን ዕለቱ ቀዳሚ አጀንዳቸው የክንፈ መታሰር ነበር። ከዚህ ጉዳይ ልቆ ሊያወያየን የሚችል ርዕስ አይኖርም። የክንፈን መታሰር መግለጫ የሰጡትን የጠቅላይ አቃቤ ህግ ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኑ ጸጋዬን መረጃ ይዘን የውይይቱን አካሄድ ፍሬም ለማስያዝ ተቀምጠናል። ከዕለታዊ ተገፋሁ የሚል ክስ ያቀረበችው የቀድሞ ባልደረባ በውይይቱ ላይ የምትሳተፈው ከክንፈ ይልቅ በጠቅላይ አቃቤ ህጉ ላይ ያተኮረ ትንታኔ መስጠት ከቻለች ብቻ እንደሆነ አስቀድማ አሳወቀች። ምክንያቷ ደግሞ ክንፈና ብርሃኑ ሁለቱም ወንጀለኞች ናቸው፡ ብርሃኑ ኦህዴድ ስለሆነ ነው ያልታሰረው የሚለው ሀሳብ የውይይቱ ምሶሶ መሆን አለበት፡ ለዚህም ሁለት የቪዲዮ ክሊፖችን አዘጋጅቼአለሁ አለችን። እንግዲህ ከዕለቱ ክስተት ይልቅ መግለጫውን ስለሰጠው ባለስልጣን እንወያይ አይነት አቋም ይመስላል። ሌሎች ተሳታፊዎች ተከራከርናት።

የአቶ ብርሃኑን ወንጀል በተመለከተ ከዚያ ቀደም በሎ በተደረጉ ውይይቶች በዚህችው ባልደረባችን እስከዶቃ ማሰሪያ የተነገሩ ትንተናዎች ቀርበዋል። እኛም ጭምር የጠቅላይ አቃቤህጉን የኋላ ታሪክ አንስተን የዶ/ር አብይ መንግስት እንደሳቸው ዓይነት ሰዎችን መሾም የለበትም ብለን ወትውተናል። አዲስ ርዕስ አይደለም። በዕለቱ አነጋጋሪ በሆነው ጉዳይ ላይ ማተኮራችን ለተመልካቹም ወጥ የሆነና ያልተዘበራረቀ ውይይት እንዲከታተል ያደርገዋል ብለን ብንሞግታት ልትቀበለን አልቻለችም። እንደአማራጭም የቪዲዮ ክሊፖቹ ሰዓታችንን ስለሚወስዱብን በትንታኔሽ የፈለገሽውን ያህል ብርሃኑ ላይ ትንታኔ ስጪበት ብለን የማርያም መንገድ ጠየቅናት። በእልህ ውስጥ ሆና የምታናግረን ይህቺው ባልደረባ ለክብራችን የማይመጥን፡ ከስድብ የሚፈረጅ አስተያየት ሰጥታን ከእንግዲህ ከዕለታዊ ራሷን ማግለሏን አሳወቀች። ‘’ እናንተው ተንቦራጨቁበት’’ ብላን ወደ መቀመጪያዋ ሄደች። በቃ! ታሪኩ ይሄ ነው። ከዕለቱ አጀንዳ ወጥቼ የኦህዴዱን ብርሃኑን ካልወቀጥኩት የሚል ምክንያት አቅርባ ከዕለታዊ ራሷን አግልላለች። ይህ እውነት ነው። ሌሎች ባልደረቦችም የሚያውቁት ሀቅ ስለሆነ ማስተባበል የሚቻል አይመስለኝም።

የቴዎድሮስ ጸጋዬ ቃለመጠይቅ ደግሞ ለዚህችው የቀድሞ ባልደረባችን የነበረኝን የተዛባ አመለካከት እንዳስተካክል አድርጎኛል። የቱንም ያህል ብትበደል የምትሰራበትን ተቋም ለአደባባይ አጋልጣ በነጋታው ወደ ስራ ለመምጣት መድፈሯ በየዕለቱ ከአፏ ለማይጠፋው ‘መርህ’ ለሚለው ቃል ያላትን ቦታ በግልጽ የሚያሳይ ነው። በገቢር የማይታይ የመርህ ተቆርቋሪነት ለትዝብት ከመዳረግ ያለፈ ትርፍ የለውም። ለወራት በጉዳዩ ላይ ዝምታን የመረጥኩት በዚህን ክፉ ጊዜ አወጣለሁ ብዬ አድፍጬ በመጠበቅ እንዳልሆነ ግን ይታወቅልኝ። በግል ጉዳዩ ምን እንደሆነ ለጠየቁኝ ወዳጆች በዝርዝር ሳጫውታቸው እውነቱ በአደባባይ መነገር እንዳለበት በመግለጽ ግፊት አድርገው ነበር። የሆነው እንዲህ ነው።

ሲሳይ አጌና በአዲስ አበባ በአንዳፍታ ሚዲያ ላይ ቀርቦ ስለቴዎድሮስ ጸጋዬ አስተያየት ይሰጣል። እውነት ለመናገር ያንን የሲሳይን ቃለመጠይቅ እኔም አልወደድኩትም። የዚያኑ ዕለት ምሽት ስልክ አዲስ አበባ ድረስ ደውዬ ሞግቼዋለሁ። ተገቢ እንዳልሆነ፡ ቢያንስ የእኛን ባልደረቦች በተመለከተ የቀረበውን አስተያየት መከላከል መቻል እንደነበረበት ገልጬ ተቃውሜዋለሁ። አሁንም የማምነው ያንን ነው። ጠዋት ቢሮ ስመጣ ሀገር ቀልጦ ነበር የጠበቀው። በሲሳይ ቃለመጠይቅ የተበሳጩት ባልደረቦች በጠዋቱ የቁም ስብስባ ቅሬታቸውን ገለጹ። እኔም አስተያየት ሰጠሁበት። እንግዲህ ከቴዎድሮስ ጸጋዬ ጋር ቃለመጠይቅ ለማድረግ ጥንስሱ የተጀመረው የዚያን ዕለት ይመስለኛል።

ቀኑን እርግጠኛ ባልሆንም ይህ በሆነ ከአንድ ሳምንት በኋላ ቴዎድሮስ ጸጋዬን ቃለመጠይቅ ለማድረግ ከግለሰቡ ጥያቄ እንደቀረበላት አሳወቀችን። ጥያቄው ከእሱ ይምጣ በእሷ ጋባዥነት ይታቀድ እሱ ላይ የማውቀው ነገር የለም። ምንም እንኳን በኢዲቶሪያል ኮሚቴው እውቅና በሲሳይ ውክልና ሰጪነት የዲሲው ኢሳት ጊዜያዊ ኤዲተር ብሆንም በይፋ ስራውን እየሰራሁ አልነበረም። ይህን የቃለመጠይቅ ፍላጎት ጥያቄ እንዳቀረበችልን ከአንዳንዶች ተቃውሞ ተሰማ። እኔ ግን መቅረቡ ላይ ችግር የለውም፡ ይሁንና ግለሰቡ አቋሙ ይታወቃል፡ አንቺም አቋምሽ ግልጽ ነው፡ የተሟላና ተቃራኒ ሀሳቦች የሚደመጡበት ውይይት እንዲሆን ሌላ ከቴዎድሮስ ሀሳብ በተቃራኒው አቋም ያለው ተወያይ ፈልጊ የሚል አስተያየት ሰጠሁ። ቃለመጠይቁ በቅንነት የታሰበ እንዳልሆነና ጫጫታ ፍለጋና ኢሳትን ለማሳጣት ወጥመድ ለመዘርጋት የታሰበ ለመሆኑ ማሳያ የሆነ ነገር ተናገረች። የቴዎድሮስን ቃለመጠይቅ የማትፈቅዱ ከሆነ በስም ጠቅሼ ማን እንደከለከለ አጋልጣለሁ የሚል ማስፈራሪያ አቀረበች። ከዚህ ውይይት ምን እንደተፈለገ ለማወቅ የሚያስችል ፍንጭ ነበር የተናገረችው።

የሆነ ነገር አለ። አቧራ ለማንሳት ተፈልጓል። ይሄን መንገድ መዝጋት እንዳለብን አምኜአለሁ። ለዚህም ነው ውይይቱ ቢደረግ ችግር የለውም፡ ግን አንድ ሰው ጨምረሽ አድርጊው የሚል ሀሳብ ያቀረብኩት። እንግዲህ ስምምነት ላይ ሳንደርስ፡ ሌላ ተወያይ እንዲፈለግ በሚል ተንጠልጥሎ የነበረ ጉዳይ ሳይቋጭ ቴዎድሮስን ቃለመጠይቅ ተደረገ። አሰራሩ ተጥሶ ማለት ነው። ቃለመጠይቁ መደረጉ ከአሰራር አንጻር ህጉን የጣሰ ቢሆንም አንድ ጊዜ ተደርጓልና መታየት አለበት የሚል ውሳኔ ላይ ደረስን። የዲሲው የኢሳት ጊዜያዊ ዳይሬክተር ታማኝ ፕሮግራሙን እንድመለከተው ሰጠኝ። ይህ ሲሆን ሲሳይ አጌና ምንም የሚያወቀው ነገር የለም። ልጆች አሉኝና ሀሰት መናገርን አልደፍረውም።

ቃለመጠይቁን ቁጭ አየሁት። በአምስት ክፍሎች ልግለጸው። የመጀመሪያው አራት ደቂቃዎች ስለቴዎድሮስ የህይወት ታሪክና ስራ በአጭሩ የሚገለጽበት ነው። ከአራተኛው እስከ 12ኛው ደቂቃ ድረስ የሲሳይ አጌና ስም ሳይጠራ የሚወቀጥበት ክፍል ነው። ሲሳይ ራሱን መከላከል በማይችልበት መልኩ ቃለመጠይቅ አድራጊዋም ጭምር በፊት ገጽታ በሚገለጽ ድምጽ አልባ ቋንቋ ሳይቀር  ውግዘትና እርግማን ሲያዥጎደጉዱ የሚደመጡበት ክፍል ነው። እዚህ ላይ ቴዎድሮስ ራሱን መከላከል የለበትም የሚል አቋም የለኝም። ይሁንና በሌላ ሚዲያ ለቀረበ ክስ ኢሳት ላይ ምላሽ የሚሰጥበት አሰራር የለም። ቴዎድሮስ ክሱ በቀረበበት አንዳፍታ ሚዲያ ላይ ምላሽ መስጠት ይችላል። ኢሳት በምን እዳው ነው በሌላ ሚዲያ ለቀረበ ፕሮግራም የራሱን ባለደረባ ሚዛናዊነት በጎደለው ክብረነክ አገላለጽ እንዲብጠለጠል መድረክ የሚሰጠው? ቢያንስ ሲሳይ ምላሹ ቢካተትበት አንድ ነገር ነው። ወይም በቃለመጠይቅ አድራጊዋ ሚዛናዊ ጥያቄ ጉዳዩን ማስተናገድ ቢቻልም የተሻለ ይሆን ነበር። ተጋግዘው ስም ሳይጠሩ ሲሳይ መሆኑን በሚያስታውቅ መልኩ መቀጥቀጥ ግን በየትኛውም መለኪያ ተቀባይነት የለውም።

የቃለመጠይቁ ሶስተኛ ክፍል የህወሀትን የዘር ፖለቲካ ጥንስስና መዘዙን የሚያሳይ ነው። ቴዎድሮስ በታሪክ እውቀቱና የትንተና ብቃቱ የሚያቀርበው ትርክት ጥሩ ነበር። አራተኛው ክፍል ደግሞ አሁን ያለውን መንግስት ጥምብ እርኩሱን ማውጣት ነው። ይህም ችግር የለውም። አንዳንድ ለክስ እንዲመቹ ተደርገው ለትንታኔ የቀረቡ የተዛቡ መረጃዎች ቢኖሩም የግለሰቡን ሀሳቡ በነጻነት የመግለጽ መብቱን ከማክበር አንጻር ችግር አይኖረውም። አምስተኛውና የማጠቃለያው ክፍል ደግሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚደረግ ጥሪ ነው። የቃለመጠይቁ አደገኛው ክፍልም ይሄው ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ባለው የለውጥ ሃይል ላይ እንዲነሳ የሚያደርግ የክተት ጥሪ የሚያደርግ ሰፊ ክፍል ነው። ቀውስ ውስጥ ላለችው ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት የአመጽ ጥሪ አደገኛ ነው። በተለይ አንድን ብሄር የወከሉ ፖለቲከኞችንናን የፖለቲካ ትርክትን ነጥሎ ከቀጠቀጡ በኋላ ህዝቡ እንዲነሳ መቀስቀስ ጊዜው የሚፈቅድ ጥሪ አይደለም።

በአጠቃላይ ቃለመጠይቁ ሚዛን የጎደለው፡ የአንድ ወገን አቋም ያለልክ የጮኸበት፡ ግለሰቦች ስማቸው ሳይጠቀስ የተደበደቡበት፡ ከመደበኛው የቃለመጠይቅ ባህሪ በማፈንገጥ ወደ ሀሜት የተጠጋ ነው ማለት ይቻላል። ቃለመጠይቅ አድራጊዋና ተደራጊው አንድ መስመር ላይ ሆነው፡ ሚናቸውን መለየት በማያስችል መልኩ የተዘጋጀ ነው። ጥያቄዎች ያልቀረቡበት፡ ቃለመጠይቅ ተደራጊው የቋንቋና የአገላለጽ ችሎታውን ተጠቅሞ ስሜን አጠፉ ያላቸውን አካላት እንዲወርፍና እንዲያብጠለጥል መሪ የሆኑ ሀሳቦች እየቀረቡ የሚደመጡበት ነው። ቀድሞውኑ ቃለመጠይቁ የታሰበለትን ዓላማ እንዲመታ ተደርጎ የተቀረጸ በመሆኑ ኢዲት ለማድረግም የማይመች ነው። በተረፈ አዲስ ሀሳብ የለውም። ይህን ያህል ‘ታፈነ’ በሚል አቧራ የሚያስጬስ ነገር ያለበት አይደለም።

የቴዎድሮስ አቋም በየጊዜው በተለያዩ ሚዲያዎች የሚሰማ በመሆኑ አዲስ ነገር አለበት ተብሎ ለአፈና የሚያበቃው አይደለም። ሰሞኑን በዋሽንግተን ዲሲ በተደረገውና ኢሳትም ሰፊ ሽፋን በሰጠው መድረክ ላይ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ካቀረበው ዲስኩር የተለየ ነገር የለውም። ግን በእነዚያ ሁለት የቃለመጠይቁ ክፍሎች ምክንያት ማስተላለፍ እንደማይቻል ገለጽኩኝ። ከዚህ ውሳኔ ላይ ስደርስ ማንንም አላማከርኩም። የማንም እጅ አልገባበትም። በአዘጋጇ በሴራ ገመድ ተጠልፎ እንዳይተላለፍ ተደረገ የሚለው የተቀናበረ ክስ ፍጽሞ ሀሰትና ግምት ላ የሚጥል ነው። የህሊና ሚዛን እንዳልስት አድርጌ የደረስኩበት ድምዳሜ ነው። ይህም ለአዘጋጇ ተነገራት። አቧራውን ለማጬስ እጅ ማፍታታት የተጀመረውም ወዲያውኑ ነበር።

በቀጣይ ለዋና አዘጋጁ ፋሲል የኔዓለም ማመልከቻ ያስገባችው አዘጋጇ የተባሉትን ክፍሎች በመቁረጥ ቃለመጠይቁ መተላለፍ ይችላል የሚል ምላሽ ሲሰጣት ወደ አደባባይ ወጥቶ ለመናገር ጊዜም አልወሰደባትም። የተፈለገውን አቧራ በማጬስ እቅዱ ተግባራዊ ሆነ። የኢሳትን ስም ለማጉደፍና ቀብሩን በቁማቸው ማየት ለፈለጉ የተለያዩ ወገኖች ጮማ የሆነ ወሬ እንካችሁ አለቻቸው። የኢሳትን ገበና አደባባይ በማስጣት የባልደረቦቿን ክብር በማንኳሰስ፡ እሷ የእውነት፡ የዲሞክራሲና የነጻነት ጠበቃ ሌሎቻችንን ደግሞ አደርባይና የኦዲፒ አፈቀላጤ አድርጋ አቀረበችን። በቃለመጠይቁ የታገደው ከኦዲፒ ጽ/ቤት በተላለፈ መመሪያ አድርጎ ለማሳየት የተከሸነው ቲያትር በእርግጥ አስደናቂ ነው። በጠዋቱም ምንም እንዳልተፈጠረ፡ ስሙን በአደባባይ ወዳሰጣችው ተቋም መጣች። እኔ ብሆን አደርገው ይሆን? ያን ያህል ርቀት ሄጄ ያዋረድኩትን መስሪያ ቤቴን ተመልሼ የማየው አይመስለኝም። እንግዲህ መርህ ማለት ምንድን ነው?

ማጠቃለያ

በዚህ ጉዳይ ተመልሼ አልመጣም። ለኢትዮጵያ ህዝብ በግሌ እንዲያውቅ የምፈልገው ግን ለየትኛውም ቡድን የሚያጎነብስ አንገት እንደሌለኝ ነው። የኢትዮጵያን ሁኔታ በሰከነ መንገድ እንመልከተው ማለት የመንግስት ደጋፊነት ካባ የሚያስደርብ ከሆነ ምንም ማድረግ አልችልም። ደራርቤ ከመልበስ ውጭ አማራጭ የለኝም። ይልቅስ ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ናት። እያንዳንዷ ያልተጣራች መረጃ እንደትላንቱ መረጃ ብቻ ሆና አትቀርም። እሳት ልትጭር እንደምትችል መገንዘብ አለብን። ከትላንት አንጻር ዛሬ የኢትዮጵያ ህልውና ያሳስባል። ለውጡ መልካም ነገሮችን የማምጣቱን ያህል አደገኛና በፊት ያልነበሩ አደጋዎችንም አስከትሏል። ለውጡን ወደምንፈልገው መስመር ለማውጣት ሃላፊነት የሚሰማው ሚዲያ እንዲሆን ከማድረግ ያለፈ የየትኛው ግለሰብም ሆነ ቡድን አፈልቀላጤ ለመሆን የሚፈቅድ ህሊና የለኝም። የኢትዮጵያ ህዝብ አምነኝ! ከአንተ በልጦ ለሌላ የሚያጎበድድ አቋም የለኝም። በልጆቼ እምልልሃለሁ። እነዚህ ከኢሳት ተገፋን ብለው አዲስ ሚዲያ ያቋቋሙት ወገኖች አማራጭ ሚዲያ መጀመራቸው የሚበረታታ ቢሆንም ቀውስ ለማቀጣጠል በሚል ከሆነ የጀመሩት ቆም ብለው እንዲያስቡ በቀደመው ወዳጅነታችን ስም እለምናቸዋለሁ። በተረፈ back to square one የነበርን አለን። ፋሲል የኔዓለም እየጠበቅንህ ነው። መልካም የስራ ጊዜ።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!

Filed in: Amharic