>

አቶ ያሬድ ሀይለማርያምን እና መሰሎቻቸውን የሚሰማ መንግሥት ከወዴት አለ?! (መስፍን ማሞ ተሰማ)

አቶ ያሬድ ሀይለማርያምን እና መሰሎቻቸውን የሚሰማ መንግሥት ከወዴት አለ?!

መስፍን ማሞ ተሰማ

ሠላም ለናንተ ይሁን!

በኢትዮጵያ ሥነ መንግሥትና ሥነ ህዝብ መስተጋብርና ሀላፊነት፣ ህጋዊነትና ተጠያቂነት ላይ የአቶ ያሬድ ሀይለማርያም ምልከታና ምክረ ሀሳብ ሁሌም ያስደምመኛል። ለአብነት ጁን 13/2019 ‘ፖለቲከኞቻችን ጠዋት ጥምጥም ከሰዓት ኩፊ’ በሚል ርዕስ በፌስ ቡክ ገፃቸው ያሰፈሩት ጥልቅና ውስጠትን ጠያቂ የሆነ የወቅቱን ፖለቲካዊ ዱካ የቃኙበት ፅሁፍ አንዱ ነው። የኢትዮጵያ መሪዎች ወይም የመንግሥት ሀላፊ ፖለቲከኞች ግን እንዲህ ያለ ቅን መንፈስና ቅን ሰብዕና ከሀገራዊ ራዕይ ጋር ያጣመሩ ዜጎችን አያስጠጉም። አያነጋግሩም። አያዳምጡም።

እነርሱ – የሀገረ መሪዎቹ – በዙሪያቸውና በመንግሥታቸው መዋቅራት ሁሉ (አልፎ አልፎ አንዳንድ ሁለ ገብ ቅቡልነት ያላቸውን ለገፅታ መሳመሪያና ማድመቂያ ካልሆነ በስተቀር) በአብዛኛው የሚያሰባስቡትና በሚመሩት መንግሥት መዋቅራት ሀላፊነት የሚሰጡት በዕድሜያቸውና በዘመናቸው ካሳለፉት ፖለቲካዊ ኩነት ያልተሞረዱ፣ እንዳረጀ እባብ የውጪ ቆዳቸውን እንጂ ውስጣቸውን ያልቀየሩ ካፖርት ገልባጭ፣ ቡድን/ቲፎዞ አደራጅ፣ የከሸፉ የሴራ ፖለቲከኞችን ነው።

እኒህ ተገለባባጭ ፖለቲከኞች ደግሞ በኖሩባቸው ዘመናት ሁሉ ድርጅት ሲቀላቀሉ፣ ድርጅት ሲያፈርሱ፣ ድርጅት ሲመሰርቱና ወጣቱን በቱማታ ቲዎሪና በተኮፈሰ ሁሉን አውቅ ባይ ሰብዕና በተገነባ ቲፎዙ ሲያምሱ የኖሩ ናቸው። ‘ከደርግ የባሰ አይመጣም/አልመጣም’ በሚለው እጅግ አድር ባይ መፈክራቸው ከያሉበት ብሪፍ ኬዞቻቸውን አንጠልጥለው ቤተ መንግሥት የገቡ፣ የዘር ልክፍተኞቹን በዋናነት ህወሀትንና ኦነግን ዕውቅና የሰጡ፣ የኢትዮጵያ ሰቆቃ አልፋና ኦሜጋ የሆነው የኢህአዴግ አርኪቴክቱን መለስ ዜናዊ “ቢሳሳት እንኳን ሆን ብሎ ኢትዮጵያን ለመጉዳት ሳይሆን ባለማወቅ ስለሚሆን በገንቢ ሂስ ማስተካከል ይቻላል” ብለው ለአያሌ ዓመታት ኢህአዴግ ስር እንዲሰድ የረዱትን መለስ ብለን ስናስታውስና ዛሬ ያለንበትን “ባለህበት እርገጥ” ወይም “አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ወደሗላ” ፖለቲካዊ ሁኔታ ስንመዝን የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችን ዐይነተኛ ወይም ተፈጥሯዊ በህሪያቸውን ‘ታሪክ ራሱን ደግሞ’ ያሳየናል።

ኢትዮጵያ በዘረኛው የኢህአዴግ መንግሥትና በዘዋሪው መለስ ዜናዊ የገባችበትን አዘቅት ከየተኛውም ፖለቲከኛ ወይም የፖለቲካ ሳይንቲስት ነኝ ባይ ተንታኝ በፊት በገሀድ ያሳዩትና የተናገሩት ታላቁ የሀይማኖት አባት አለቃ አያሌው ታምሩ ነበሩ። አለቃ አያሌው በ1987 ዓ/ም (ምድረ ፖለቲከኛና ምሁር ከዘመኑ ባለጊዜዎች ጋር ሂስ እየተዋዋጠ ውስኪውን ሲቀዳና ቁርጥ ሲያወርድ) አሳቸው በምድሪቱ ላይ ግፍ ፈፃሚዎችንና አስፈፃሚዎችን በአደባባይ አወገዙ። “ኢትዮጵያ በመንፈሳዊና ዐለማዊ ህይወቷ በሽተኛ ሆናለች” አሉ። ስለ ዕውነትና ስለ ኢትዮጵያ ብቻቸውን ቆመው የአቡነ ጳውሎስንና የመለስ ዜናዊን ጣምራ በቀል ተቀብለው አረፉ። ስለ እርሳቸው ዕውነት፣ ስለደረሰባቸውም ግፍ የትኛውም የኦርቶዶክስ ወይም የሌላ ሀይማኖት አባት ከጎናቸው አልቆመም። የትኛውም ሂስ ሰጪም ሆነ ሂስ ተቀባይ ፖለቲከኛ ስለ አለቃ አያሌው ድምፁን አላሰማም። አለቃ አያሌውን መለስ ዜናዊና አቡነ ጳውሎስ የበቀል ዶፍ ያወረዱባቸው ከምርጫ 97 አስር አዓመት በፊት ነው። ይህን ሁሉ ማንሳቴ ጠቢቡ ደራሲ በዓሉ ግርማ ‘የሰው የማስታወስ ችሎታ አጭር ነው” ብሎ የፃፈው ያሳለፍነውንና የምንገኝበትን ፖለቲካዊ ዕውነታ አስታውሶኝ እንጂ።

ወደ ቀደመ ጉዳያችን እንመለስ፥

አቶ ያሬድ ሀይለማርያም አስቀድሜ በጠቀስኩት ርዕስ ስር እንዲህ አንጥበዋል፥ “ህግ ማስከበር፣ ከተማ ማዘመንና ፅዳት በድሀ ዜጎች መቃብር ላይ መሆን የለበትም። እነሱን ከፍ ማድረግ እንጂ።
“ቅዱስ መፅሀፍ ‘የግፏን አፍ ጥልቅ ጉድጓድ ነው’ እንዳለው ከዚህ ጥልቅ ጉድጓድ ጫፍ ላይ ቆማችሁ ግፍ ባማረረው ሕዝብ ላይ የምትዘባበቱ ባለሥልጣናት፣ የኃይማኖት አባቶችና ፖለቲከኞች ብታስቡበት መልካም ነው። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ጉድጓዱ የቀደሙትን ግፈኞች እንደበላው ሁሉ እናንተንም ይበላል። በየስርቻው ፎቶ ተነስቶ መለጠፍ የናንተን ገፅታ ይገነባ ይሆናል እንጂ ለተገፋው ደሃ ጠብ የሚል ነገር የለውም። ይህንን ስል የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአንድ ዓመት ቆይታ የሚያሳየውን የፎቶ ኤግዚቢሽን ልብ ይለዋል” በማለት ፅፈዋል። እንግዲህ ጆሮ ያለው ይስማ ልብ ያለውም ልብ ያድርግ። ያም ሆነ ይህ ግን፥ ኢትዮጵያ ስለ እርሷ የሚሰቃዩና የሚጨነቁ ልጆቿን የምታቀርባቸውና የምትሰማቸው መች ይሆን?! ብዙ እስክንድሮችንና ብዙ ያሬዶችን የኢትዮጵያ መንግሥትና አጋሮቹ ፖለቲከኞች “የለውጥ እንቅፋቶችና የእንጀራ ልጆች” አድርገው ማየትና መፈረጅ የሚያቆሙት መቼ ነው? ለማንኛውም ነገ ሌላ ቀን ነው!

በያለንበት ቸር ይግጠመን!

ሰኔ 2011 ዓ/ም (ጁን 2019)
ሲድኒ አውስትራሊያ mmtessema@gmail.com

Filed in: Amharic