>
5:13 pm - Wednesday April 19, 4350

የብርሃኑ ነጋ እና የሰለሞን ተካልኝ የ"ይምራን!" አባዜ!!! (ጌታቸው ሽፈራው)

 የብርሃኑ ነጋ እና የሰለሞን ተካልኝ የ”ይምራን!” አባዜ!!!
ጌታቸው ሽፈራው
ሰለሞን ተካልኝ የሚባለው ዘፋኝ ያኔ ግንቦት 7 ሳይመሰረት ኤርትራ በርሃ ወርዶ ይዘፍን ነበር። እንደ ጉድ አድናቆት ጎርፎለት ነበር። ትንሽ ቆይቶ የገዥዎቹ ጠበቃ ሆኖ ቁጭ አለው።  ሰለሞን ተካልኝ  የገዥዎቹ ጠበቃ የሆነበት ጊዜ ያህል አስደንጋጭ ጊዜ አልነበረም። ያኔ ከዳያስፖራው ወገን ወደ ገዥዎቹ የሚሸበለለው “ታዋቂ” ብዙ አልነበረም። ሰለሞን ተካልኝ ሲለይለት “ይምራን” የሚል ዘፈን አውጥቶ ነበር።  ዘፈኑ ለመለስ ዜናዊ ነው። መለስን ለማንቆለጳጰስ ብዙ ቃል ደርድሯል። አዝመሪ ነው የሆነው።  ያ የታጋይ ዘፋኞች ቁንጮ ተደርጎ ይቆጠር የነበር ሰው “ይምራን” ሲል አሳዛኝ ነበር። ከዛ ተንቆ መቀለጃ ሆነ!
በዚህ ወቅት የሰለሞን ተካልኝ እጣ እየገጠማቸው የሚገኙት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ይመስሉኛል። ከአመታት በፊት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የደረጃ ሰንጠረዥ አናት የነበሩ ሰውዬ፣ ከአመታት በፊት “ሰውዬውኮ ኤርትራ ወረደ!” እየተባለ “ወረደ ወረደ!” የተዘመረላቸው ሰውዬ  በሰሞኑ አቋማቸው እየገጠማቸው ያለው የሰለሞን ተካልኝ አይነት ዕጣ ይመስላል።  ሰለሞን ተካልኝ በዛ ክፉ ወቅት ኤርትራ በርሃ ሲወርድ እንደተሞገሰው ሁሉ ፕ/ር ብርሃኑም የተጋድሎው የጭንቅ ወቅት ኤርትራ በርሃ ወርደው ከተከዜ ማዶ ናቸው ሲባል “መቼ ይመጣሉ?” ተብለው ተጠብቀው ነበር። ተጠብቀው፣ ተጠብቀው፣… ከቀሩ በኋላ ሲመጡ ለጠ/ሚ ዐቢይ “ይምራን!” እያሉ ነው።
ሰለሞን “መለስ  ነው መምራት ያለበት” እንዳለው፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑም ጠ/ሚ ዐቢይ “ይምራን”እያሉ ነው።  የሰለሞን በዘፈን ሲሆን፣ የፕ/ር ብርሃኑ በፕሮፖንዳ ነው። ልዩነቱ ሰለሞን “ይምራን”  ሲል እንደ አዝማሪ ነው፣ ፕ/ር ብርሃኑ እንደ ፖለቲከኛ ነው።
ዞሮ ዞሮ ኤርትራ በርሃ ወርደው ከፍተኛ አድናቆት የተለገሳቸው ሁለቱ ታዋቂ ሰዎች የገዥዎቹን ቁንጮዎች “ይምራን” እያሉ ከነበሩበት ¨ዲቪዚዮን¨ እየወረዱ ነው!
Filed in: Amharic