>

ብርሀኑ ነጋ እንደ ካሱ ኢላላ!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

ብርሀኑ ነጋ እንደ ካሱ ኢላላ!!!
አቻምየለህ ታምሩ
ብርሀኑ ነጋ በዛሬ እለት ዲሲ በተደገው የኢዜማ ብሰብባ ስለ ዐቢይ አሕመድ ያደረገው ንግግር ነፍሳቸውን ይማርና አቶ አሰፋ ጫቦ ካሱ ኢላላን ስለ ስለ ሽፍቶቹ ወያኔዎች ያስረዳቸው ዘንድ ቢሮው ሊጠይቁት ሄደው ነገረኝ ብለው በኢሳት ቴሌቭዥን በሰጡት ቃለ መጠይቅ የተናገሩትን አስታውሶኛል።
ታሪኩ እንዲህ ነው። አቶ አሰፋ ጫቦ በሰኔ 1983 ዓ.ም. ወያኔ፣ ኦነግና ሻዕብያ በአፍሪካ አዳራሽ ባዘጋጁት “የሠላምና ዲሞክራሲ ጉባዔ” ተሳታፊ በነበሩበት ወቅት ከሽፍቶቹ ከእነ መለስ ዜናዊ ጋር በነበራቸው እሰጥ እገባ መግባባት ባለመቻላቸው «ስለነዚህ ልጆች ያልተረዳሁት ነገር እንዳለ ቢያስረዳኝ» ብለው ያስረዳቸው ዘንድ ውስጠ አዋቂና የተማረ ሰው ፍለጋ ወደ ካሱ ኢላላ ቢኖር ሄደው ነበር።
ከዚያ «ከእነዚህ ልጆች ጋር እንዴት መግባባት የሚቻል ይመስልሀል? የኔ አቀራረብ የሰራ አይመስለኝም? እንዴት ይሻላል?» ሲሉ ጋሽ አሰፋ ካሱ ኢላላን ይጠይቁታል። ካሱ ኢላላም በምላሹ የወያኔን ገድል ከመመስረታቸው ጀምሮ «ጀግንነታቸውን» ፣ «ታሪካቸው»፣ «የፈጸሙ» በረጅሙ መተርተር ሲጀምር «አመሰግናለሁ ፤ እግዜር ይስጥህ፣ ከነመለስ፣ ከነስዩም ጋርኮ ነው የምውለው፤ ስለ ሕወሓት ተጨማሪ እውቀት ካስፈለገ ከባለቤቱ እጠይቃለሁ፣ ካንተ አልፈልግም» ብለው ጥለውት መሄዳቸውን ነግረውናል።
እኔም እንደ ጋሽ አሰፋ ሁሉ ብርሀኑ ነጋ ከዲሲ ያደርግ የነበረውን ንግግር ዓባይ ሜዲያ በቀጥታ ሲያስተላልፍ ለመከታተል ገብቼ  ስለምናውቀው ዐቢይ አሕመድ ልዕለ ሰብነት፣ ኢትዮጵያውያንን በእኩል ስለመውደዱ፣ ኢትዮጵያን ወደ ዲሞክራሲ ለማሸጋገር ስላለው ቁርጠኛነት፣ ለኦሮሞ የማያዳላ ስለመሆኑ፣ መንግሥቱንና መከላከያውን በኦሮሞ ሞላው የሚባለው ወሬ ሐሰት ስለመሆኑ፣ ወዘተ በረጅሙ መተርተር ሲጀምር በየሜዲያው አብሮን ስለሚውለው ዐቢይ አሕመድ ተጨማሪ እውቀት ካስፈለገ ከባለቤቱ እከታተላለሁ፣ ከብርሀኑ አልፈግልም ብዬ በቀጥታ እከታተለው የነበረውን ንግግሩን አቋረጥሁት።
አንዳንዴ የነገሮች  መገጣጠም ይግርማል። ግጥምጥሞሹ ካሱ ኢላላ ስለ መለስ ዜናዊና ወያኔ፤ ብርሀኑ ነጋ ደግሞ ስለ ዐቢይ አሕመድና ኦዴፓ/ኦነግ ልዕለ ሰብነትና አሳቢነት የተናገሩት  መመሳሰሉ ብቻ አይደለም፤  ወቅቱ ገጥሟል።  መመሳሰሉ ያልሁት ሁለቱም ጉራጌዎች ቢሆኑም ጉራጌዎችን መሆናቸውን አይደለም። ካሱ ኢላላ ስለ መለስ ዜናዊና ወያኔ ልዕለ ሰብነትና አገር ወዳድነት የተተረተረው ከ28 ዓመታት በፊት በሰኔ ወር  ነበር ፤  ብርሀኑ ነጋም  ካሱ ከ28 ዓመታት በፊት የተተረተረውን  ስለምናውቀው ዐቢይ አሕመድና ኦዴፓ/ኦነግ  የደገመው በያዝነው በሰኔ ወር ነው። በዚህም  ብርሀኑ ነጋ የወያኔውን ካሱ ኢላላ ተክቶ የኦዴፓው ካሱ ኢላላ ሆኗል 🙂
Filed in: Amharic