>
5:13 pm - Friday April 19, 4335

ፊውዳሎቹ እነ ማን ናቸው? (አቻምየለህ ታምሩ)

ፊውዳሎቹ እነ ማን ናቸው?
አቻምየለህ ታምሩ
ሀያ ሰባት ዓመታት ሙሉ ሲዘርፍና ሲገድል ኖሮ መቀሌ በወታደር ታጥሮ የመሸገው አባይ ጸሐዬ ፊውዳሊዝምን ለማጥፋት እንደወየነ ሲናገር ሰማሁት ልበል? በርግጥ አርባ አራት ዓመታት ሙሉ ተመሳሳይ ትርክት ሲሰማ የኖረ ሁሉ ፋሽስት ወያኔ፣ ደርግ፣ ናዚ ኦነግ፣ የኢትዮጵያ ጠላቶች አገር በቀል ወኪል የሆነው ኢሕአፓ፣ ወዘተ ፊውዳሊዝም ለማጥፋት ታገልን የሚለውን ያልተመረመረ ሸቀጥ ቢቀበል አይፈረድበትም።
ለመሆኑ ፊውዳሊዝም ምን ማለት ነው? ለመሆኑ  ፊውዳሊዝም የመሬት ከበርቴነት ማለት  ነውን? በፍጽም! አሜሪካዊው ባለሀብት ጆን መሎን ዘጠኝ መቶ ሺሕ ሄክታር መሬት አለው ፤ አውስትራሊያዊቷ ጊና ሬልኸርት 12 ሚሊዮን ሄክታር መሬት አላት ፤ ኤሲያዊው ቱጃር  ራስለን ሚልዳኮቭ 1 ሚሊዮ ሄክታር መሬ አለው፤ ሆኖም ግን አንዳቸውም ፊውዳሎች  አይደሉም። በኛ አገር ያ ትውልድ «ፊውዳል» ብሎ ሀብታቸውን የወረሰባቸውና የገደላቸው አርበኞች የመሬት ይዞታ ሁሉ ተደምሮ የአንዱን  የአሜሪካ፣ የአውሮፓ፣ የኤስያና የአውስትራሊያ የመሬት ከበርቴ  የሚያህል መሬት አልነበራቸውም። በኢትዮጵያ ታሪክ ኦሮሞዎቹን የመተኮ ጃራ የልጅ ልጅ የሆኑትን ራስ መስፍን ስለሺንና ራስ ብሩ ወልደ ገብሬል ከተሬን የሚያህል የመሬት ከበርቴ አልነበረም። ሆኖም ግን አንዳቸውም ፊውዳል አልነበሩም።
ፊውዳሊዝም የየራሳቸው ጦር ያላቸው፣ ያሻቸውን መሬት የሚነጥቁና ባንክ የሚዘርፉ፣ የግላቸው እስር ቤት ያላቸው፣ የግላቸውን ግብር የሚጥሉና ተጠያቂ የሚያደርግ የበላይ አካል ወይንም ሕግ የማያውቁ ጉልበተኞች ስርዓት ነው። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የራሱ ጦር ያለው፣ ያሻውን መሬት የሚነጥቅ፣ የግሉ እስር ቤት የነበረው፣ የግሉን ግብር የሚጥል፣ ተጠያቂ የሚያደርግ የበላይ አካል የሌለውና ሕግ የማያውቅ አንዳች ጉልበተኛ መስፍን አልነበረም።
በኢትዮጵያ ታሪክ ፊውዳሊዝምን ያጠፉት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው። ፊውዳሊዝም ነበር በተባለበት ዘመን ፊውዳል በተባሉት ሰዎች ቤት ከያንዳንዳችን የተዘረፈ ሀብትና ንብረት፣ ከያንዳንዳችን የተነጠቀ  መሬት ካርታና ፕላን፣ እንዲሁም የግል እስር ቤት አይገኝም ነበር። የደርጉ ኀምሳ አለቃ ለገሰ አስፋው ለገነት አየለ አንበሴ በሰጠው ምስክርነት የፊውዳል ምልክት ተደርገው በቀረቡት ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ ቤት ደርጎቹ ሲሄዱ ተሰቅሎ ካገኙት የስራ ሱፍና ክራባት፤ እንዲሁም ከተደረደሩ መጽሐፍቶቻቸው በስተቀር ያገኙት አንዳች ቤሳ ቤስቲ ነገር በተወረሰው ቤታቸው ውስጥ አልነበረም።
በደርጎቹ የጭካኔ አገዛዝ ዘመን፤  በፋሽስት ወያኔና በናዚ ኦነግ የአፓርታይድ አገዛዝ ዘመናት  ግን በያንዳንዱ የአገዛዙ ባላደራ ቤት ውስጥ ከያንዳንዳችን የተዘረፈ ሀብትና ንብረት፣ ከያንዳንዳችን የነጠቁት ቤትና  መሬት ካርታና ፕላን፤  እንዲሁም ድሀ የሚያሰቃዩበት የግል እስር ቤት ሳይቀር ይገኛል።
ከዘመነ መሳፍንት በኋላ የራሳቸው ጦር ያላቸው፣ ያሻቸውን መሬት ባሻቸው ጊዜ ድሃ እያፈናቀሉ የጎሳቸው አባላት ለሆኑ ቱጃሮች መድለቢያ የሚሰጡ፣ የግላቸውን ግብር የሚጥሉና ተጠያቂ የሚያደርግ የበላይ አካልም ሆነ ሆነ ሕግ የሌለባቸው ፊውዳሎች ፋሽስት ወያኔዎችና ናዚ ኦነጎች  ብቻ ናቸው።
ከዘመነ መሳፍንት በኋላ የፋሽስት ወያኔና የናዚ ኦነግ የአፓርታይድ አገዛዝ ከመታወጁ በፊት  ለማዕከላዊው መንግሥት አልታዘዝም ብሎ በወታደር እየተጠበቀ መንደሩ ገብቶ የመሸገ ፊውዳል ኑሮ አያውቅም። ከዘመነ መሳፍንት በኋላ የመዕከላዊውን መንግሥት ትዕዛዝ አልቀበልም በማለት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያወጣውን የእስር ትዕዛዝ አልቀበልም ብለው ከሕግ በላይ በመሆን ከማዕከላዊው መንግሥት በማፈንገጥ በወታደር እየተጠበቁ መንደራቸው የመሸጉት ፊውዳሎቹ አባይ ጸሐዬና የወንጀል ባልደረቦቹ እነ ጌታቸው አሰፋ ብቻ ናቸው። ለዘመነ መሳፍነ  በኋላ በፓርቲ አባልነት ስም የግዴታ የጎሳ ግብር የሚጥሉ፣ ለሚገዙት ሕዝብ ቅንጣት ታህል ክብር የሌላቸው፣ የራሳቸው ወታደር ያላቸውና ከሕግ ሁሉ የበላይ ሆነው የግፍ ክብረ ወሰን እየሰበሩ ያሉት ነውረኛ ፊውዳሎች አሁንም ፋሽስት ወያኔዎችና ናዚ ኦነጎች  ብቻ ናቸው።
ሆኖም ግን አደንቁረው ሊገዙ የጫኑብን የመከራ አገዛዝ ሸክም ክብደት ግፋቸው እንዳይሰማንና እንዳንመረምር ስላደረገን  ራሳቸው ዋነኞቹ ከሕግ በላይ የሆኑ ፊውዳሎች ሆነው ሳለ  ያልነሸረ ፊውዳሊዝም ለመዋጋት  ጫካ እንደገቡ  ሲደሰኩሩ እንኳ ማጠየቅ ተስኖን ኖርን። በዛሬዎቹ ግፈኞች ጨለማ ተደርጎ የሚቀርበው የነ አክሊሉ ሃብተወልድ ስርዓት ግን «በሕግ አምላክ» የሚለውን የሞራል ሥልጣኔ ባህል አድርጎ የተከለ፣ ሕዝብን የሚያከብር፣ ንጉሠ ነገሥቱ ሳይቀር ሕዝብን ለማክበር ሲሉ የዙፋን ችሎት ሙሉውን ቆመው የሚያስችሉ፣ ሕዝብንና ባለሞያን የሚያከብሩ የኢትዮጵያ አገልጋዮች ነበሩ።
ስለዚህ ፊውዳሎቹ የራሳቸው ጦር የሌላቸው፣ ያሻቸውን መሬት የማይነጥቁና ባንክ የማይዘርፉ፣ የግላቸው እስር ቤት የሌላቸው፣ የግላቸውን ግብር የማይጥሉና ተጠያቂ የሚያደርግ የበላይ አካል ያለባቸውና ከሕግ በታች የነበሩት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አርበኞች ሳይሆኑ ላወጡት ሕግ የማይገዙት፣ የራሳቸው ጦር ያላቸውና ባንክ የሚዘርፉት፣ በጠቅላይ በፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸው እነሱ ግን ለማዕከላዊው መንግሥት አንገብርም ብለው መንደራቸው በመመሸክ በጦር እየተጠበቁ ከሕግ በላ የሆኑት ፋሽስት ወያኔዎችና ናዚ ኦነጎች ናቸው።
ፋሽሽት ወያኔም ሆነ ናዚ ኦነግ ፊውዳሊዝምን ለማጥፋት፤ ሰላም ለማስፈን፣ ዲሞክራሲ ለማምጣትና በኢትዮጵያ «ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች» መካከል በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ለመፍጠር ጫካ አልወረዱም ፤ ለነዚህ አላማዎች የከሰከሰሱት አጥንትና ያፈሰሰው አንድ ጠብታ ደም የለም! ፋሽስት ወያኔም ሆነ ናዚ ኦነግ ጫካ የወረዱት ፊውዳሊዝምን ለማጥፋት ፤ ሰላም፣ ዲሞክራሲና እኩልነት ለማምጣት ሳይሆን በኢትዮጵያ ምድር ሰላምን፣ እኩልነትና ዲሞክራሲን ለመቅበር፤ በ1966 ዓ.ም. ከጠፋ 120 ዓመታት ያስቆጠረውን ፊውዳሊዝምን መልሰው ለመትከልና ራሳቸው ከብረ ወሰን የተቀዳጁ፣ ከሕግና ከማዕከላዊው መግሥት በላይ የሆኑ የእድሜ ዘመን ቱጃር ፊውዳሎች ሆነው ሲገዘግዙን ለመኖር ነበር። ይኼው ነው!
Filed in: Amharic