>

መንግሥት እስክንድር ነጋን ከሌሎች ዜጎች ነጥሎ እያዋከበው ነው!!! (ውብሸት ሙላት)

መንግሥት እስክንድር ነጋን ከሌሎች ዜጎች ነጥሎ እያዋከበው ነው!!!
ውብሸት ሙላት
እስክንድር ነጋ ሁለተኛው መንግስት ጥርስ ውስጥ እንደገባ ጥርጥር የለውም። የሁለተኛው መንግስት ትልቁ ህመም ደግሞ ለውጡን እርሱ ብቻ ያዋለደው የሚመስለው መሆኑ ካለእርሱም በከተማው የነጻነት ‘ ታጋይ’ ማየት አለመፈለጉ ነው። ሁለተኛው መንግስት ባጭሩ ቀናተኛ ጣዖት ነው ማለት ይቻላል። የእስክንድር ብቸኛው ጥፋቱ የዚህ ጣዖት ካዳሚ ሊሆን አለመፍቀዱ ነው።
ዛሬ ያየነው የእስክንድር መግለጫ ክልከላ ፈጽሞ ድንገቴ አይደለም። ኢትዮጵያ ሆቴል ጻፈው የተባለውም ደብዳቤ እንዲሁ የቀልድ መሆኗ አይጠፋንም። የሆነ ደህንነት ጽፎ ያዘጋጃት የሆቴሉም ስራ አስኪያጅ እዚህች ጋር ፊርማህን አኑር ተብሎ የተዘጋጀች ነች። ይህንን ለመረዳት ትላልቅ የሚባሉ የሆቴል ባለንብረቶችን ወይም ስራ አስኪያጆችን መጠየቅ በቂ ነው። አንድ የማውቀው ሆቴል ስራ ላይ ያለ ሰው እንደነገረኝ ፓሊስ ሆቴሎችን በጸረ እስክንድር ዘመቻ ማዋከብ ከጀመረ ቆይቷል። ብዙ ሆቴሎች ለእስክንድር አዳራሽ ከማከራየታቸው በፊት ሚሊዮን ጊዜ ማሰብ ግድ ከሆነባቸው ሰንብቷል።
ዛሬ ፓሊስ ፣ ደህንነት ቢሮ ውስጥ ሆነው አፈና የሚፈትሉ ሰዎች ፣ ከሁለተኛው መንግስት ይሁን ከማዘጋጃ ቤት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ እመቃን የሚነድፉ ሹማምንት እያፈኑ ያለው የእስክንድርን ድምጽ ብቻ ከመሰላቸው ተሳስተዋል። ህገወጥነትን ሲገምዱ የራሳቸውንና የልጆቻቸውን ነጻነት እያሰሩ እንደሆነ አይረዱትም። ኢትዮጵያ ውስጥ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተከበረ ማለት አምባገነንት ልጓም ተበጀለት ፣ ተጠያቂነት ሰፈነ ፣ ሹማምንቱ የተንጠለጠሉበት የስልጣን ማማ ወደ ምድር ሊቀርብ ሆነ ማለት ነው።
ለማንኛውም እስክንድርን ማሳደድ ግለሰብን ማሳደድ ብቻ አይደለም። የመናገር ነጻነትን ማሳደድ ነው ፣ እርሱ የሚጮህለትን የአዲስ አበቤ ህልውና ማሳደድ ነው !
ሁላችንም በእስክንድር ነጋ የፓለቲካ አቋሞች ላንስማማ እንችላለን ፣ በእስክንድር ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ላይ ግን ልንስማማ ግድ ይላል። ያ መብት የሁላችንም ነውና ። በእስክንድር የተጀመረ አፈና እስክንድር ጋር ይቆማል ብሎ ማሰብ ጅቡ ጎረቤቴን ዘንጥሎ እኔን ግን አይነካኝም ብሎ የማሰብ ያህል ገራገርነት ነው !
እስክንድር ነጋ ባለፈው ራስ ሆቴል መግለጫ ሊሰጥ ሲል የጸጥታ ተቋማት ሲከለክሉት፣ የጠቅላይ ሚኒስቴር የፕሬስ ኃላፊ መግለጫ ሰጥተው ነበር። በወቅቱ የጸጥታ ችግር እንደነበርም ግልጸዋል። ይሁን እንጂ የፖሊስ የምርመራ ውጤት እስካሁን ይፋ አልሆነም። ፖሊስ የምርመራ ውጤት ካልገለጸ በወቅቱ ችግር ኖሮ ሳይሆን መግለጫ እንዳይሰጥ ስለተፈለገ ጉልበተኞች ከልክለውት ለእነሱ ሕጋዊ ከለላና ጥበቃ ተሰጥቷቸዋል ማለት ነው።
 ያኔ፣ ባልደራስን በሚመለከት ነበር መግለጫ የሚሰጠው። ዛሬ ደግሞ አዲስ ስለሚያቋቁመው የቴሌቪዥን ጣቢያ መግለጫ ሊሰጥ ሲል እንደተለመደው አሁንም መግለጫ እንዳይሰጥ ተከለከለ።
መንግሥት እስክንድርን መግለጫ እንዳይሰጥ ምክንያት የሆኑት ላይ ወይም የከለከሉት ላይ እርምጃ ካልወሰደ የኢትዮጵያ መንግሥት በግልጽ እስክንድር ነጋን ብቻ ከሌሎች ዜጎች ነጥሎ እያዋከበው ነው ማለት ይቻላል። እነዚህ ድርጊቶችም የመንግሥት አቋም ናቸው ማለት ነው። የመንግሥት አቋም ላለመሆኑ የማስረዳት ሸክምም የመንግሥት ነው። ምክንያቱም እስክንድር መግለጫ እንዳይሰጥ ከልካዩ መንግሥት ሆኖ ሳለ ለክልከላው መነሻ የሆኑት ችግር ፈጣሪዎች ላይ ምንም ዓይነት ይፋዊ መግለጫ አለመስጠቱ ነው።
Filed in: Amharic