>

ኢትዮጵያ በሌላኛው አብዮት ምዕራፍ? (ጌታቸው ሺፈራው)

የፋታ ጊዜውንም እየጨረሰ ያለው የዐቢይ አህመድ  መንግስት!!!
ጌታቸው ሺፈራው
ኢትዮጵያ በሌላኛው አብዮት ምዕራፍ?
ኢትዮጵያ ውስጥ ተደርገዋል ከሚባሉት ለውጦች መካከል በስፋት የሚወራለት የ1966ቱ “አብዮት” ነው። ለዚህ ለውጥ እንደ ትልቅ ስንቅ የሚቆጠረው በማይታሰብበት ወቅት በ1953 ዓም የተደረገው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ነው። ከዚህ ሙከራ በኋላ መንግስት የተለያዩ እቅዶችን በማውጣት የኢኮኖሚ ለውጥ አመጣለሁ በማለት የወቅቱን ትኩሳት ለማብረድ  ጥሯል። በየጊዜው ይተገበራሉ የተባሉ የአመታት ገድብ የተቀመጠላቸው እቅዶች በአጤው ዘመንም የነበሩ መሆናቸውን ድርሳናት ይጠቅሳሉ። ከዚህም ባሻገር የአባይን ውሃ ለመገደብ ጥናቶችና አጓጊ እቅዶች እንደነበሩ ድረሳናቱ ያወሳሉ። ይህም ሆኖ በመፈንቅለ መንግስቱ የተደፈረው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት በውስጥም ከውጭም እንከን አላጣውም። የመፈንቅለ መንግስቱን ሙከራ፣ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ፣ የሕዝቡን ፍላጎት የተመለከቱ ምሁራን  የስርዓቱን ቁንጮዎች መክረዋል። የስርዓቱ አካላትና ተቆርቋሪዎች ሳይቀሩ ስርዓቱን ሕዝብ ሊበላው እንደሚችል በመገመት የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት አንዳንድ ለውጦችን እንዲያደርግ ይመለክሩ እንደነበር ይገለፃል።
ይህ በኢህአዴግ ዘመንም የሆነ ክስተት ነው። የ1997 ዓም ምርጫና እመቃን እንደ አንድ ምዕራፍ ማየት ይቻላል። 1997 ኢህአዴግ ከስልጣን ሊወርድ እንደሚችል የጠቆመና የተደፈረበት ከመሆኑ ባሻገር ከምርጫው ማግስት የወሰደው እርምጃም ከሕዝብ ጋር እንዲቆራረጥ፣ የአረመኔነቱ ጥግ የታየበት ነበር። ይህን አረመኔነቱንና የወቅቱን  የፖለቲካ ከባቢ ለመቀየር ልማትና ኢንቨስትመንት ወደሚባሉ ማስቀየሻዎች ዙሯል። በእርግጥ እንደ 1953ቱ አይሁን እንጅ ኢህአዴግ በይፋ ያመነው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መደረጉ አይዘነጋም። የንጉሱ ስርዓት ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ድል ማስመዝገቡን በመግለፅ ስለ አንድነት በሚያወራበት ወቅት እንደተሞከረበት ሁሉ ኢህአዴግም “ሚሊኒዬም” ባለበት ወቅት ይኼው መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተጠንስሶበት እንደነበር ራሱ ያመነው ሀቅ ነው።
የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት ከመፈንቅለ መንግስት በኋላ በኢኮኖሚውና በሌሎች መስኮች አጓጊ እቅዶችን እንዳወጣው ሁሉ ኢህአዴግም በምርጫ 97 ያልተጠበቀ ሽንፈት ከገጠመው በኋላ እንዲሁም ከመፈንቅለ መንግስቱ ሙከራ ማግስት አጓጊ እቅዶችን አውጥቷል። የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት  ተከታታይ (የ3/5 አመት?)  የኢኮኖሚ እቅዶችን እንዳወጣው ሁሉ ኢህአዴግም የአምስት አመት እቅድ፣ እንዲሁም ጊዜው ተመሳሳይ ሆኖ የእድገትን ትራንስፎርሜሽን እቅድ እያለ የፖለቲካ ውድቀቱን ለመሸፈን ጥሯል። የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት የአባይ ወንዝን ለመገደብ እንዳደረው እቅድ ሁሉ እነ መለስ ዜናዊ እስካሁን ያልተጠናቀቀውን ግድብ ያስጀመሩት ከ1997  ዓም ምርጫ በኋላ ከተደረገው ከመፈንቅለ መንግስት ሙከራው ማግስት ነው።
የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት በመካሪዎቹ ዘንድ እንዲያሻሽል እንደተነገረው ሁሉ የሕወሓት/ኢህአዴግ ጀኔራሎች ሳይቀሩ ለስርዓቱ መቆየት ሲባል ለውጥ እንደሚያስፈልግ በጠባብ ውይይት ያልተሳካላቸውን በየጋዜጣው ወትውተዋል። በተለይ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ ኢህአዴግ ውስጥም “ለውጥ” የምትባል ሕዝብን ለመደለልም ሆነ ስርዓቱ ይቆይ ዘንድ የተደረገች ክርክር እንደነበረች እየተገለፀ ነው።
የአጤ ኃይለስላሴ መንግስት ግፊቱ ሲበዛበት አንዳንድ ለውጦችን አድርጓል። በዛ ዘመን በማይታሰብ መልኩ የካቢኔ ለውጦች ተደርገዋል። የአልጋወራሽ ጉዳይ እንዲሁም ሌሎች አካላት ስልጣን ከፍ እንዲል፣ የዘውዳዊ ስርዓቱ ከቀደመው ባሕሉ እንዲቀየር ምክረ ሀሳቦችም፣ ሙከራዎችም ተካሂደዋል። በኢህአዴግ ዘመንም ሕወሓት የነበረውን ስልጣን አጥቶ እነ ኦዴፓ/ኦህዴድ አልጋ ወራሽ  ሆነው ኢህአዴግን አድሰው ያስቀጥላሉ የተባሉበት ፖለቲካ ወቅት ደርሰናል። ከንጉሱ ስርዓት አንፃር  ሲታይ ብዙ ይመስሰልና ይባልለት እንጅ ከካቢኔ ለውጥ ከፍ ያላለ ስርዓቱን ለማቆየት የሚደረግ ሙከራ እየተደረገ ነው። የንጉሱ ስርዓት በእነ እንዳልካቸው ካቢኔ ለቀደመው የአጤው ስርዓት ያለው እምነት እየተሸረሸረም ቢሆን ዘውዳዊ ስርዓት እንዲቀጥል ፍላጎት እንደነበረው ሁሉ  የኦዴፓ/ኦህዴድም የቀደመው የኢህአዴግ አድራጊ ፈጣሪ ሕወሓት ላይ ያላቸው አመለካከትና ታዛዥነት ቢቀየርም የሚያስቀጥሉት ሕወሓት ጠፍጥፎ የሰራውን ኢህአዴግን ነው። የአጤው ዘመን ለውጥ ለማምጣት ጥረዋል የተባሉት በተለያየ መንገድ የዘውዱን ስርዓት አድሰው ለመቀጠል እንደጣሩት ሁሉ የዛሬዎቹም ኢህአዴግን አድሰን እንቀጥላለን ብለዋል።
የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት አጓጊ እቅድ፣  ተገድዶ ያደረጋቸው ለውጦች ቢኖሩም በዘውዳዊ ስርዓቱና በንጉሱ ላይ የነበረው እምነት እየቀነሰ፣ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የስርዓቱ አካላትም ባሳደጋቸው ስርዓት ላይ እያሾከሸኩ በመሃል ክፍተቶች ተፈጥረዋል። እነዚህ ክፍተቶች ለተማሪዎች፣ ለሲቪክ ማኅበራትና ሕቡዕ አደረጃጀቶች  ትልቅ እድል ሰጥተዋል። በተለይ ሕዝብን አፍኖ መግዛት አማራጭ እንዳልሆነና አቅምም እንደሌለው የተረዳው ስርዓት በወቅቱ የሚፈለጉትንና በሕዝብ የተጠየቁትን፣ የስርዓቱ አካላት የሚያንሾካሹኩባቸውን የለውጥ ሀሳቦች ለመተግበር እንኳ ቁርጠኛ አልነበረም። በዚህም በሕዝብና ለውጥ ፈላጊ የውስጥ ኃይሎች ተስፋ እየተቆረጠበት፣ ቀድመው ተስፋ በቆረጡት ዘንድ ትግል እየበረታበት ሄዶ የመጨረሻ ግብዓቱ  ኢትዮጵያን አጉል መንገድ ላይ የጣለ ነበር።
የአጤ ኃይለስላሴ ዘመን መጨረሻ ላይ የሚታዩ ምልክቶች በዛሬዋ ኢትዮጵያም ላይ ውር ውር ማለት ጀምረዋል። የአጤው ስርዓት ጊዜው የሚጠይቀውም ማሻሻያ ለማድረግ እየፈዘዘ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከውስጥም ከውጭም ያሉትን ጫናዎች ለመቋቋም የካቢኔና የአልጋወራሽ ጉዳይ ላይ ሲጨነቅ ለጠላቶቹ ብርታት፣ ለሕዝብና ደጋፊዎቹ ተስፋ መቁረጥን እንደሰጠው ሁሉ የወቅቱ ገዥዎች ተመሳሳይ ችግር ላይ ወድቀዋል። የጠ/ሚ ዐቢይ መንግስት ከአሳዳጊው ሕወኃት ጋር ያለው ግንኙነት “ሰማይ አይታረስ ንጉስ አይከሰስ” በሚባልበት ዘመን ዘውዱ እንዳለ ሆኖ የንጉሱ አልጋዎራሽ ስልጣን እንዲይዙ ሀሳብ ሲያቀርብ ከነበረው የ1960ው የውስጥ ኃይል እምርታ ያሳየ ነው ለማለት ይከብዳል። የ1960ዎቹ የንጉሱ ስርዓት አካላት የንጉሱን ስርዓት ለማዘመን ጥረት እንዳደረጉት ሁሉ የዛሬዎቹም ኢህአዴግን ከተቸከለበት ኋላ ቀርነት ነፃ እናወጣዋለን ከማለታቸው ውጭ መሰረታዊ የስርዓት ለውጥ አልጠየቁም።  የ1960ዎቹ ዘውዱ ይበልጥ ተቀባይነት ኖሮትና ዘምኖ እንዲቀጥል እንደፈለጉት ሁሉ የ2011 ዓም አልጋወራሾችም ኢህአዴግን እንዲታደስ ይፈልጋሉ። የዘውዳዊ ስርዓት በውስጥና በውጭ በነበረው ግፊት መሰረታዊ ለውጥ ሳያመጣ እዘምናለሁ ሲል ከወዳጆቹ ተቆራርጦ፣ ለጠላቶቹ ሀይል እንደሰጠው ሁሉ ኢህአዴግም መሰረታዊ ለውጥ  (የሕገ መንግስት፣ የፌደራል አወቃቀር፣ የስልጣን ውክልና እና አጠቃቀም) ሳያመጣ በመሃል ብዙ ክስተቶች ተፈጥረዋል። ኢህአዴግ መሰረታዊ  ሳያመጣ ኢህአዴግ በተደጋጋሚ ሲወቀስባቸው ከነበሩት መካከል የተወሰኑትን ክፍተቶች አሻሽላለሁ ሲል ወዳጆቹ መሻሻል እንደማይችል እንዲያስቡ፣ ተቀናቃኞቹም የቆየ አቋማቸውን እንዲያጠናክሩ አድርጓል። በንጉሱ ዘመን ዘውዱን ለማዘመን በተደረገ ጥረት መሰረታዊና ወቅቱን የሚመጥን ለውጥ ባለመደረጉ የወላወሉ እንዳሉ ሁሉ ሲቪክ ማኅበራት ለውጡ በቂ እንዳልሆነ ጠይቀዋል። ሲቪክ ማሕበራት በየፊናቸው መብታቸውን ሲጠይቁ በየ ሲቪክ ማኅበራቱ የነበሩ ግንባር ቀደሞች ከሲቪክ ማሕበረሰብ ሚና ያለፈና በኋላም አብዮቱ የፈነዳበትን ሚና ተጫውተዋል። በዚህ ወቅትም ኢህአዴግን አድሼ እቀጥላለሁ ከሚለው ጋር እየዋሉ፣ ከተቃዋሚ ጎራ ነን እያሉ የሚወላውሉ ቢኖሩም መሰረታዊ ለውጥ የሚፈልጉና ይህን አቋም እየተቀበሉ ያሉም በመበራከት ላይ ናቸው።
የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት መሰረታዊ ለውጥ ሳያመጣ የይመሰል ለውጥ ላይ ሲያተኩር የአጤውን ስርዓት ደፍረው መብት የማይጠይቁ ሁሉ በድፍረት መብታቸውን ጠይቀዋል።  ስርዓቱ እየወላወለ ከወቅቱ ጋር መሄድ ሲሳነው የነገሌው ጦር፣ መምህራን፣ ሙስሊሞች፣ ሴቶች፣ ተማሪዎችና ሌሎቹም ጥያቄዎቻቸውን በይፋ አቅርበዋል። ለይምሰል የሚደረጉ ለውጦች ለሀገርም የማይጠቅሙ፣ የራሳቸውን ጥቅሞችም የማያስጠብቁ መሆናቸውን በውል የተረዱ አካላት ትግሉን ከፍ አድርገውታል።
ከአጤው መንግስት የባሰ ችግር ውስጥ የገባው የዐቢይ  አህመድ መንግስት 
የአጤው መንግስት መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት በፈራበት ወቅት የነገሬው ጦር ስለምግብና ውሃ ጥያቄ እንዳነሳው ሁሉ ጠ/ሚ ዐቢይ ስልጣን በያዙ በጥቂት ወራት መከላከያ ሰራዊቱ ጥያቄውን አንግቦ ቤተ መንግስት ድረስ ከእነ ትጥቁ ገብቷል። የአጤ ኃይለስላሴ መንግስት በወቅቱ የሚጠየቀውንና በርካታ ጥያቄ ለመመለስ ቁርጠኝነትና አቅም ባጣበት ወቅት ማሕበራት በድፍረት ንቅናቄ እንደጀመሩት ሁሉ የጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ መንግስት አፋኙን ኢህአዴግ በየ አደባባዩ በሚሰሙ ድስኩሮችና አንዳንድ ለውጦች አድሼ እቀጥላለሁ ሲል ከመምህራን፣ ከጤና ባለሙያዎችና መሰል ማሕበራት ጠንካራ ጥያቄዎች እየተነሱበት ነው።  አንዳንዴም ተማሪዎችንና ጥያቄ ያነሱትን ቤተ መንግስት ድረስ ተቀብሎ በክብር አነጋግሮ ይመስልስ ከነበረው ከአጤ ኃይለስላሴው ወቅት በባሰ የእነ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ መንግስት የደመወዝን ጨምሮ ሌሎች ጥያቄዎችን የሚያነሱት ጋር ትዝብት ውስጥ መግባቱን የጤና ባለሙያዎችን ጉዳይ በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። በአጤው ዘመን የተቃዋሚ ፓርቲዎች አልነበሩም፣ የሙስሊሙና ሌሎች እንቅስቃሴዎች  እንደ አዲስ የተጀመሩ እንጅ ለውጥ ከተባለው በፊትም አገዘዙን ያን ያህል ያስጨነቁ አልነበሩም። በአጤው ዘመን ብሔርተኝነት የእነ ስታሊንን መፅሐፍ የሸመደዱ በጣም ጥቂት ባለጎፈሬዎች እንደ ፋሽን የያዙት እንጅ እንደዛሬው በየአደባባዩ የሚዘመርና ይህን የሚያስፈፅሙ አካላት የተደራጁበት አልነበረም።  ከአጤ ኃይለስላሴው አንፃር ሲታይ የጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ መንግስት ለትችት የተጋለጠ ነው። በአንድ በኩል አሳዳጊው ጋር በይፋ የተኮራረፈ ነው። በሌላ በኩል ባለፈው የነበረውን የዘር ፖለቲካ በባሰ መንገድ እያስቀጠለ ነው ተብሎ የከፋ ትችት እየደረሰበት፣ አደባባይ ወጥተው ባሞገሱት ዘንድ እንኳ እምነትም እያጣ ነው። ከምንም በላይ በአጤው ዘመን ያላቆጠቆጡ የፖለቲካ ኃይሎች የወለዱት የጠ/ሚ ዐቢይ መንግስት አብዛኛው ትግሉ ከፈጣሪዎቹም ጋር ጭምር መሆኑ አደጋው የከፋ መሆኑን እንረዳለን። የዘመኑ ሚዲያና ሌሎች ጉዳዮች ሲታከሉ የአልጋወራሽና ሌሎች ጉዳዮችን አንስቶ ዘውዳዊ ስርዓቱን ለማዘመን ሀሳብ ከነበረው የአጤው መንግስት በላይ የሕወሓት አልጋወራሽ የሆነው ኦዴፓ/ኢህአዴግ ወቅቱ የሚፈልገውን ለውጥ ባለማምጣትና ኢህአዴግን አድሶ ለመቀጠል በሚደረግ የፖለቲካ ጨዋታ እየዳከረና ራሱን ለአብዮት ሰይፍ እያዘጋጀ መሆኑን መገንዘብ አያቅትም። ይህ በወዳጆቹና እምነት በጣሉበት ሳይቀር ተስፋ የሚያስቆርጥ፣ ተቀናቃኞቹ አቋማቸውን እንዲያከሩ የሚያደርገው የጠ/ሚ አገም ጠቀም የፖለቲካ አካሄድ በወቅቱ ከሚታየው ንፋስ ጋር ሲደመር ኢትዮጵያ በሌላ አብዮት ቋፍ ላይ ነች ወይ? የሚል ጥያቄን ያስነሳል። በአጤው ስርዓት ዘውዳዊ ስርዓቱን በማዘመን ከውድቀት ለመዳን ሲጥሩ “የለውጥ አቀንቃኝ” የተባሉ፣ ለሀገርም ባለውለታ የነበሩት ሳይቀር መጨረሻው የሆነው ከአደናቃፊዎቹ ጋር በአንድ ጉድጓድ ነበር። ጠ/ሚ ዐቢይ የሚመሩት የ”ለውጥ” ኃይል አልጋአውራሹ ሕወሓት ከሚመራው በተቃራኒ ተስፋ ተጥሎበት የነበር ቢሆንም እየቆየ ግን “ኢህአዴግ ኢህአዴግ” ነው እየተባለ ነው። በአጤው ዘመን አዲስ ሀሳብ አምጥተዋል ተብለው ከተሞገሱ በኋላ በተግባር ሲታዩ በአደባባይ “ምድጃ ቢቀያየር   ወጥ አያጣፍጥም”  ተብሎ “ኧረ ፋታ ስጡኝ፣ ፋታ” ብሎ ከረፈደ ሆነና ፋታ የሚሰጠው አላገኘም። መጨረሻው የሆነው አዘምነዋለሁ ካለው ዘውዳዊ ስርዓት ጋር መውደቅ ነው።
በተመሳሳይ በአንድ ወቅት ተስፋ  ተጥሎበት የነበረው የእነ ዐቢይ አህመድ ቡድን  ከተጠላው ጋር ተነፃፅሮ “ለውጥ የለም” እስከመባል እየደረሰ ነው። “ያው ናቸው” እስከመባል ያደረሱ “ከለውጥ ኃይል” የማይጠበቁ የቀደመው ነገስት/ሕወሓት ተግባራትን እየፈፀመ ነው። የጠ/ሚ ዐቢይ መንግስት  የሚተችባቸውን ካላስተካከለ (የሚያስተካክል አይመስለም)፣ ወቅቱ የሚጠይቃቸውን ጥያቄዎች ካልመለሰ (ከዘውዱ ስርዓት በባሰ አቅምና ቁርጠኝነት ያለው አይመስልም)  የ1960ዎቹ ገዥዎች የለውጥ ኃይልና ለውጥ አደናቃፊ ተብለው እምብዛም ሳይለዩ “ፋታ፣ ፋታ” እያሉ የፋታ ጊዜ አልፎባቸው ወደ አንድ ጉድጓድ እንደተወረወሩት ሁለ የጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ መንግስትም የእፎይታና የፋታ ጊዜውን እያለፈ ይመስላል። ከዘውዱ  ስርዓትም በባሰ የድሮውን አንጋሽ  ሕወሓትን ጨምሮ የያዘውን ኢህአዴግን “ለማደስ” ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ያለው የዐቢይ መንግስትም እጣው በአንድ ጉድጓድ ላይ መጣል ላለመሆኑ የወቅቱን የፖለቲካ ከባቢ መሞገት የሚቻል አይመስልም!
Filed in: Amharic