>

“ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል!” (ኤርሚያስ ለገሰ)

“ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል!”
ኤርሚያስ ለገሰ
ተላከ: – ለአዲስ አበባ ባለአደራ ምክርቤት(ባልደራስ)
የከበረ ሰላምታዬ ካላችሁበት ይድረሳችሁ፣
የባለአደራ ምክር ቤት “መንግስታዊ የመሬት ወረራ” እየተፈፀመ መሆኑን በጋዜጣዊ መግለጫችሁ ተመልክቻለሁ። የምክርቤት አባላት የወሰዳችሁትን ጠንካራ አቋም ከልቤ እንደምደግፍ ከወዲሁ ለማሳወቅ እፈልጋለሁ። ይህ እምነቴ የሚመነጨው ተቀጥሬ ከማገለግልበት ኢሳት አቋም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌለው ሲሆን እንደ አንድ አዲስአበቤ እኔም ያገባኛል ከሚል ስሜት ነው። አዲስ አበባ የአዲስአበቤዎች፣ ከተማነቷ ደግሞ የሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሆኑ!
እንደ እውነቱ ከሆነ አዲስ አበባ እና አዲስአበቤ ህይወቱን ጭምር መስዋዕት አድርጐ የሚታገልላት ሃይል በማግኘቷም መጠነኛ የህሊና እረፍት አግኝቻለሁ። እርግጥም በተስፋይቱ ከተማ የተስፋ ጭላንጭል እንዲፈነጥቅ በማድረጋችሁ ክብር ይገባችኃል። እናንተ በሰላማዊ ትግል እስከመጨረሻው በፅናት ለመታገል የቆረጣችሁ ብርቅዬ የአዲስ አበባ ፍሬዎችን እንዴት መደገፍና ማገዝ እንዳለብን ከቅርብ ወዳጆቼ ጋር ዘወትር የምናሰላስለው ነው።
ወደ መግለጫው ስመለስ የባላደራ ምክር ቤቱ በአንድ በኩል “መንግስታዊ ወረራ” ሊካሄድ እንደሆነ የገለጠበት ምክንያት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን እንደሚያፈርስ መግለፁን ተከትሎ እንደሆነ ከመግለጫው ተከታትያለሁ። በሌላ በኩል የባልደራስ ምክር ቤቱ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ መስፋፋት እንደሌለበት የፀና እምነት እንዳላችሁ አመላክታችኃል።
በሌላ በኩል ፀሎታችን የባሰ አታምጣ የሚለው ቢሆንም ሰሞኑን ከሚኒስትሮች ምክርቤት የተሰማው የማሻሻያ አዋጅ ከድጡ ወደ ማጡ የሚወስድ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የሚመራው የሚኒስትሮች ምክርቤት አዲስ ማሻሻያ አዋጅ አውጥቶ ለፓርላማ እንዲፀድቅ ልኳል። ማሻሻያ አዋጁ “ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትና ለንብረት ካሳ የሚከፈልበት ሁኔታ ለመወሰን የወጣ አዋጅ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
ይህ ረቂቅ አዋጅ በዜና መልኩ ቀርቦ ስመለከት ወዳጄና የቀድሞ የፓርላማ አባል ግርማ ሰይፋ “የሊዝ አዋጅ!” በታወጀ ሰአት የተሰማውን ስሜት ተስተካካይ እኔም ዛሬ ተሰምቶኛል። ግርማ “የተከበሩ!” በሚለው መፅሐፋ ገፅ 103 ላይ የሊዝ አዋጅን አንብቦ ሲጨርስ በፍፁም ኢትዮጵያዊ መሆኑን የጠላበት ቀን እንደሆነ አስፍሯል። እርግጥም የተከበሩ እንደከተቡት የሊዝ አዋጅ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ባይተዋር እንደሚያደርጋቸው በገፅ 104 ላይ እንደሚከተለው ከትቧል፣
   “ ይህ አዋጅ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው በዘላቂነት ሀብት ለማፍራት የሚያስችላቸውን እምነት የሚጐዳ ብቻ ሳይሆን፣ ምናልባትም ከተሳካ አገሪቱ አላት የሚባለውን የከተማ ቦታ በሊዝ ስም ሀብት ላላቸው የውጪ ዜጐች አሳልፎ የሚሰጥ እና ኢትዮጵያዊነትን የሚንድ ነው። አዋጁ የግል ባለ ይዞታዎች ቀደም ሲል በሕጋዊ መንገድ የያዙትን ቦታ በማስተላለፍ ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅም ሆን ብሎ እንዳያገኙ በማድረግ፣ ቀጥሎም ለልማት ይፈለጋል በሚል በረጅም ጊዜ ልፋት ያለሙትን ቦታ የሚያሳጣ ነው። መንግስት ይህን ይህን ከዜጐች ያለአግባብ የሚቀማውን ሀብት በችሮታ ለፓለቲካ ወገንተኞቹ በተለያየ መልኩ በመስጠት ስልጣኑን ሊያራዝምበት መፈለጉን የሚያሳይ ነው።… አዋጁ ዜጐች ስደትን እንደ አማራጭ እንዲያስቡ የሚገፋፋ በምንም መመዘኛ የኢትዮጵያዊነት ስነ ልቦና ያላገናዘበ ነው። …ዜጐችን በኢኮኖሚ መደብ በመከፋፈል በአገራችን ግጭትንና አለመተማመንን የሚያበረታታ ነው” በማለት በፓርላማው ውስጥ ብቻውን መቃወሙን ይፋ አድርጓል።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የተከበሩ ግርማ ሰይፋ በፍፁም ኢትዮጵያዊነቴን ጠላሁበት ያሉት አዋጅ ሳይሰረዝ ለአዋጅ ዋነኛ ግባት የሆነው “ ለህዝብ ጥቅም ሲባል” በሚል ማጭበርበሪያ ዜጐችን ከመሬታቸው ለመንቀል አዲስ ማሻሻያ አዋጅ ብቅ ብሏል። የማሻሻያ ህጉ ተፈፃሚነት በመላው ኢትዮጵያ ቢሆንም ማዕከሉ አዲስ አበባ እንደሚሆን ለጥያቄ የሚገባ አይደለም።
በመሆኑም የባልደራስ ምክርቤት “ ለህዝብ ጥቅም ሲባል!” በሚል ርዕስ አዲስአበቤን ከመሬታቸው ለማፈናቀል የተዘጋጀ አዋጅ በጥልቀት በመመርመር ውሳኔ እንዲያሳርፍበት ጥቆማዬን አቀርባለሁ።
 አክባሪያችሁ ኤርሚያስ ለገሰ
( ለግንዛቤ እንዲረዳ የዛሬ ሁለት አመት በኦሮሞ ጥናት ማዕከል (OSA) የቀድሞውን አዋጅ በተመለከተ ያቀረብኩት ማብራሪያ አያይዤዋለሁ።)
Filed in: Amharic