>
5:13 pm - Saturday April 18, 0189

"ቁልፉ ማን ዘንድ ነው???   " (በሚስጥረ አደራው)


“ቁልፉ ማን ዘንድ ነው???
በሚስጥረ አደራው
የተዘጋ በር የብዙ ነገሮች ምሳሌ ነው። ምኞቶቻችን፤ ፍላጎቶቻችን እንዲሁም ህልሞቻችን በተቆለፈ በር ይመሰላሉ። መጠየቃችን፤ መፈለጋችንና ልፋታችን ደግሞ በሩን እንደማንኳኳት ይቆጥራል። “አኳኩ ይከፈትላችኋል” የሚለው ቃል በብዙዎቻችን ህሊና ውስጥ የተቀረጸ ቅዱስ ቃል የሆነውም የእድሜ ጀንበር ግዜዋ ደርሶ እስክትጠልቅ ድረስ በሮች መዘጋታቸው እኛም ማንኳኳታችን ስለማይቀር ነው። ስለ በርና ማንኳኳት መጻፍ ስጀርም ሶስት ግጥሞች በህሊናዬ መጡ ፤ ሁለቱ የሃገሬ ገጣሚያን ኤፍሬም ስዩምና በውቀቱ ስዩም ግጥሞች ሲሆኑ ሶስተኛው  የጃላላዲን ሩሚ  ግጥም ነው። ሶስቱም ግጥሞች ስለበርና ማንኳኳት የተለያዩ ምልከታዎች ስለሰጡኝ ቆነጻጽዬ ላካፍላችሁ ወደድኩኝ-እነሆ
ከኤፍሬም ስዩም በር ልጀምር ፤ ገጣሚው የተዘጋበት ቁልፍ በተሰኘው ግጥሙ ውስጥ የሚከተሉት ስንኞች ተቋጥረዋል።
“ለካስ በዛች አገር እያንኳኳ ነበር ትውልድ የሚኖረው
እልሁ በርትቶ በሩን እስኪሰብረው
አዎ በዛች ሀገር አባት በልጁ ላይ ቆልፎበት ነበር
በእዳ በተሰራ በታላቅ ብረት በር
የዛች ምስኪን ሀገር ቁልፉ ግን የጠፋው
ከደጅ አልነበረም ውስጡ ጓዳዋ ነው”
በነዚህ ስንኞች ውስጥ በር የችግሮች መውጫ ( Exit) ሆኖ ተቀምጧል። ትውልድ በትውልድ ላይ እየቆለፈ፤ ከስቃይ ለማምለጥ የተሳናቸው ህዝቦች ከተዘጋው በር ፊት ተሰልፈው ያለመታከት ሲያንኳኩ ይታያሉ። የሚያንኳኳውን ትውልድ በህሊናዬ ስስለው፤ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ የተሰማራ ይመስለኛል። በር በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ትልቅ መልዕክት ያለው ምሳሌ ነው። ከበር ወዲያ ፤ ማምለጥ፤ ነጻ መሆን፤ መተንፈስ፤ ማወቅ፤ መክነፍ፤ መሻሻል የምንላቸው ጽንሰ ሃሳቦች ሲለሚገኙ። ይህ ድንቅ በር ታዲያ ክፍት አይደለም፤ ማንም እንደሳሎን በሩ ዥው አድርጎ በርግዶ የሚወጣበት አይደለም። ቁልፍ ነው!!! የጽሁፌ መነሻ የሆነው ሃሳብም ይህ ነው፤ ቁልፉ ማን ዘንድ ነው ያለው? በገጣሚ ኤፍሬም ግጥም ውስጥ “የዛች ምስኪን ሀገር ቁልፉ ግን የጠፋው ፤ከደጅ አልነበረም ውስጡ ጓዳዋ ነው” የሚል ድንቅ ስንኝ አለ። ምናልባት ቁልፉ ማን ዘንድ ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሆናል። በእራሳችን ላይ የምቆልፈው እራሳችን ብንሆንስ?
በርን ከነጻነት ጋር ካዋሃድን አይቀር በዚህ አባባል የኤፍሬምን ሃሳብ እንቋጨው ” Freedom is not given by the Oppressor; it must be demanded by the oppressed”- Martin Luther King. “ነጻነት በጨቋኙ እንካችሁ ተብላ አትሰጥም ፤ በተጨቋጩ ትጠየቃልች እንጂ”- ማርቲን ሉተር ኪንግ። እንግዲህ ገጣሚው እንዳለው፤ ቁልፉን እደጅ ስንፈልግ ብዙ ትውልዶች ከበር መልስ መታፈናቸው ነው። የብዙ በሮች ቁልፍ የጠፋው ከደጅ አይደለምና። ከውስጥ የሚመለከት ሰው አጥተን ነው እንጂ፤ ቁልፉስ በውስጣች ነበር።
የበውቀቱ ስዮም በር
አንኳኳ! ይከፈትልሃል
ስትገባ ሌላ በር ይጠብቅሃል
“ህይወት እልፍኟ በዝቶ
እልፍኟ በበር ተሞልቶ
የመኖር መፍትሔ ቃሉ
“ሲያንኳኩ መኖር” ነው ካሉ
አንኳኩተው ከሚያስከፍቱ፤ ከውጭ የቆሙ ተሻሉ።
ከላይ በሰፈሩት የገጣሚው ስንኞች ውስጥም በድጋሜ በር እንደ እንቅፋት ተመስሎ ይታያል። ነገር ግን በዚህ ግጥም ውስጥ ሰው ከሚያልመው ነጻነት የማይደርሰው የበሩ ቁልፍ ጠፍቶበት ሳይሆን፤ ሰው አንዱን በር ዘልቆ ሲገባ ሌላ በር እየጠበቀው ነው። “ሲያንኳኩ መኖር ነው” ያለው፤ የሰው እጣፋንታ “የማይድን ህመምን ማከም ነው” ሲለን ነው። ነገር ግን በመጨረሻው ሃሳብ በግሌ አልስማማም፤ “አንኳኩተው ከሚያስከፍቱ፤ ከውጭ የቆሙ ተሻሉ” የሚለው ስንኝ፤ ከላይ ያሰፈርኩትን የኤፍሬምን ትንቢት የሚያስፈጽም ሃሳብ ስለሚመስለኝ ነው፤ ልቀበለው ያልወደድኩት። የተሻለ ነገር አይመጣም ብለን ማንኳኳት ስናቆም አይደለም እንዴ፤ ከእኛ አልፎ ትውልዱ ላይ የምንቆልፍበት? እኛ ቀድመን ከበሩ የተገኘነው ካልወጣን፤ ከእኛ በኋላ ለሚመጡት እንዴት እንዲወጡ እድል እንፍጥርላቸው?
የሩሚ በር
ማሳረጊያዬ ደግሞ የባህር ማዶው ገጣሚው የጃላላዲን ሩሚ ሃሳብ ነው፤ ይህ የሁሉም መፍትሄ ስለመሰለኝ ነው ሃሳቤን ለመቋጨት የተጠቀምኩበት
“I have lived on the lip
of insanity, wanting to know reasons,
knocking on a door. It opens.
I’ve been knocking from the inside.”- The door that we are knocking opens from inside.
ይህ እጅግ ጥልቅ ሃሳብ ነው። ብዙውን ግዜ፤ እንደግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ የምንጨነቀው እና የምንጠበበው መፍትሄው ላይ አረፍ ብለን ተቀምጠን ነው። እንግዲህ ሶስቱን ግጥሞች ልብ በሏዋቸው፤ ሶስቱም ከበሩ ወዲያ የተሻለ ነገር እንዳለ ያመላክታሉ፤ ነገር ግን የበሩን ቁልፍ ፍለጋ እድሜያችንን እናባክናለን። የሚያሳዝነው አብዛኛውን ጊዜ የምናንኳኳው ከውስጥ ሆነን ነው፤ የምንከፍተውም የምንቆልፈውም እኛው እራሳችን ሆነን ሳለን፤ ሌላ ነጻ አውጪ ስንጠብቅ ይረፍድብናል።
በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ሁላችንም የሆነ በር እያንኳኳን ነው። አንዳንዶቻችን የሃብት፤ አንዳንዶቻችን የፍቅር፤ አንዳንዶቻችን የሰላም፤አንዳንዶቻችን የለውጥ፤ እንደሃገር እና እንደማህበረሰብ ደግሞ የአንድነት በር እያንኳኳን ነው። የምናንኳኳው ግን ከውስጥ ሆነን ቢሆንስ? ቁልፉ በእጃችን ሆኖ ቢሆንስ? እኔ ግን እላለው፤ ምናልባት ሳናውቀው ከሚገባን በላይ እያንኳኳን ከበሩ ላይ ቆመናል፤ እስካሁን ያልተከፈተልን ቁልፉ በውስጣችን ስለሆነ ነው። ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሄውን በቅድሚያ ከውስጣችን እንፈልግ።
ሌላው የሩሚን ጥቅስ በመጥቀስ ልሰናበታችሁ “ስለምን በየበሩ እየዞርክ ታንኳኳለህ? ሁሉንም በር ትተህ የልብህን በር አንኳኳ” ያላል።  ያኔ ሌሎች በሮች መከፈታቸው አይቀርምና። ማንም ሰው የሌላ ሰውን ነፍስ ቆልፎ ሊያኖር አይችልም። ደስታችን፤ ስኬታችን፤ ህልምና እራያችን ላይ የተቆለፈበት ከመሰለን፤ ቁልፉ ከየትም ሳይሆን ከእኛው ከራሳችን ጋር ነውና፤ ከፍተን እንውጣ!!!
Filed in: Amharic