>
5:13 pm - Sunday April 20, 7377

ክቡር ጠቅላይ ምኒስትሩ ሁለት ሺህ ዘመን ሰላምን ስታውጅ ለኖረች ቤ/ክርስቲያን ስለሰላም ሰበኩ!!! (ዘመድኩን በቀለ)

ክቡር ጠቅላይ ምኒስትሩ ሁለት ሺህ ዘመን ሰላምን ስታውጅ ለኖረች ቤ/ክርስቲያን ስለሰላም ሰበኩ!!!
ዘመድኩን በቀለ
          *★★★*
★ ሳምንት መጅሊሱን ዛሬ ደግሞ ሲኖዶሱን ባርከው ከፍተዋል!!!
★ በዘር የተደራጀ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር አብይ “ከዘረኝነት ውጡ…” ብለው ሸጋ ምክር ለግሰዋል!
•••
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን ብለው ንግግራቸውን ጀምረው ይሁን አይሁን የተነገረ ነገር የለም። የሆነው ሆኖ ግን ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ በዛሬው የቅዱስ ሲኖዶሱ የርክበ ካህናት ስብሰባ ላይ በአካል በመገኘት ንግግርም በማድረግ ጉባኤውን ማስጀመራቸው ተረጋግጧል።
★“ …እንደሚባለው አይደለም እንደሚወራውም አይደለም እኔ የምመራው መንግሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ያከብራታል። ሁላችሁ እንደምታውቁት ባለ በሌለ አቅሙም ይደግፋታል ማለታቸውም ተነግሯል ”
• አብዲ ኤሌን ጭዳ ለማድረግ በሶማሌ ክልል 9 አብያተ ክርስቲያናት እንደ ደመራ ነደዋል። ካህናትና ምእመናን  ታርደው ከሚነደው እሳት ተጥለዋል። በሰሜን ሸዋ ቤተ ክርስቲያን በቦንብ ተመትታለች፣ በእሳትም ተቃጥላለች። በእርስዎ የትውልድ ሀገር በጅማ እስከ አሁን ድረስ ካህናት እየታረዱ ነው። የቁልቢ ገብርኤል ገቢ ለቄሮ ይከፋፈልን የሚሉ ነውጠኞች በሬድዮ ሳይቀር ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉትና ይሄ ሁሉ እየሆነ ያለው እኮ እርስዎ በሚመሩት የኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት ነውና አቡነ ማርቆሬዎስን ሀገር ቤት ማምጣትዎንና ሁለት ህንጻ መመልስዎን ብቻ እየነገሩን በብዙው ግን አያክስሩን ብለው የጠየቁ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ስለመኖራቸው ግን የተነገረ ነገር የለም።
★ የአንድነት ጉባኤ የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ በዘረኝነት ከወደቀ “ክርስቶስን ረሳ፤”
• በአስተዳደራዊ ችግር እና በሙስና በየፍ/ቤቱ የሚንገላቱ ካህናትን ታደጉ፤
★ ሕዝቡን እርስ በርሱ አስተዋውቁት። አዋሕዱትም። እናንተ የሰላም መሪዎች እንድትኾኑ እንሻለን።
• ይሄን ያሉት ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ ናቸው። ማንን አትሉኝም። ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በቅዱስ ሲኖዶሱ የርክበ ካህናት የመክፈቻ ጉባኤ ላይ የተገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን። ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ነው ያስተማሩት። የመከሩት።
• ለሁለት ሺ ዘመናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሠራችውን ዓለምአቀፍ መንፈሳዊ ሥራ፣ የፈጠረችውን አንድነት ማንና መቼ ከእጇ ላይ ነጥቆ ቤተ ክርስቲያኒቱ የአንድ ብሔር ብቻ እምነት እንደሆነች አድርጎ ህዝቡን ሰብኮ እንደለያየው፣ አሁንም እንደጠላት የሚቆጥሯት፣ ልጆቿን ከሞሶሎኒ እኩል ቆጥረው የሚያሸማቅቁ ባለሥልጣናትና ባለ ጊዜዎች ስለመኖራቸው ለጠሚዶኮ በድፍረት የተናገረ የጉባኤው አባል ስለ መኖሩ እስከአሁን የወጣ መረጃ ግን የለም።
• የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ቤተ ክርስቲያን የተቀባችውን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ አጥፍታ በኦነግ ባንዲራ ታሸብርቅልን፣ “የነፍጠኛ እምነት ናት ከክክልላችን ትውጣልን” እያለ ህዝቡን የሚከፋፈውለውን ኦነግን የኦነግን ሠራዊት አስታግስልን ያሉ አባቶች ይኑሩ አይኑሩም መረጃው አያመለከትም።
★ ቤተ ክርስቲያን ዛፎችን መትከል ብቻ ሳይኾን መጠበቅም ታውቅበታለችና እኛም እንደ መንግሥት በመጪው ክረምት 4 ቢልዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ይዘናልና እንተም እባካችሁ እንድታግዙን እንፈልጋለ – ብለውም ለጉባኤው ጥሪ አቅርበዋል።
• በዋልድባ የሚገኘውን ጥብቅ ደን ከሥር መሠረቱ በግሬደር እየነቀለ፣ በእሳትም እያቃጠለ፣ ወጣቶችን አደራጅቶ ጥብቅ ደኖችን ከሰል እያከሰለ፣ በራስደጀን የቅዱስ ያሬድን ገዳም ተራራ በእሳት እያወደመ፣ በዝቋላ፣ በአሰቦት ጥብቅ ደኖችን እሳት እየለቀቀ የሚያወድመውን ኃይል መንግሥትዎ ያስታግስልን፣ ከቢሮዎ ፊት ለፊት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሳይቀር የሚጨፈጨፉትን የቤተ ክርስቲያን አጸዶች መች ታደጉልንና ነው ብሎ የጠየቀ ጉባኤተኛ ስለ መኖሩም እስከ አሁን አልሰማሁም።
★ ክርስቲያኑ ምእመን የሙስሊሙን፣ ሙስሊሙም ምእመን የክርስቲያኑን ደጅ እንዲያጸዳ አስተምሩ። እንዲያውም አሁን ከረመዳን ፍቺ ይሄን ማድረግ ጀምሩ። በመጪው መስከረም የመስቀል በዓልን ደግሞ ሙስሊሞቹ እንዲያጸዱ ትምህርት ስጡ ።
• እሱንማ በጎንደር፣ ወሎ፣ በባህርዳር፣ እዚህ አዲስ አበባ የአንዋር መስጊድና የአማኑኤል የራጉኤልም ምእመናን ሲሠሩት የኖሩት እኮ ነው። አዲስ አይደለም። ቤተ ክርስቲያን የሚያሠሩ ሙስሊሞች። መስጊድ የሚያሠሩ ክርስቲያኖች ለዘመናት የኖሩባት እኮ ናት ኢትዮጵያ። በአንድ ሠርግ፣ ለቅሶና ደስታ አብረው የሚታደሙ ደግ የዋሕና አማኞች የሚገኙባት ሀገር እኮ ነች ኢትዮጵያ። ይልቅ የሚያጫርሰንን፣ የሚያባላንን የሚታይ የሚጨበጠውን ክፉ መናፍስት መንግሥትዎ ይሠርልን። የጽዳቱን ነገር ለእኛ ይተዉልን ብሎ ከጉባኤው መሃል የጠየቀ ስለመኖሩ ግን የተነገረ ነገር የለም።
ቤተክህነቱ ዘመኑን በዋጀ መልኩ ይጠናከር። መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶቻችሁን አጣናክሩ። ከዘረኝነት መንደር ውጡ ብለዋል አቢቹዬ።
• ከዘረኝነት መንደር ውጡ ያሉት የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የተባለ በዘር የተደራጀ ፓርቲ መሪው አቢቹ ነው። እናም እኛ እኮ እዚህ የተሰበሰብነው በዘር አይደለም። ኢትዮጵያውያን ነን። ቤተ ክርስቲያናችንም ስሟ ራሱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ብሎ ነው የሚጀምረው። እናም የኦሮሚያ ኦርቶዶክስ፣ የትግሬ ኦርቶዶክስ ብለው የሚሯሯጡትን ፖለቲከኞች፣ ዘረኞች ያስታግሱልን። ዘር መቁጠሩ የእኛ ባህል አይደለም። አልነበረምም። ኢህአዴግ የሚባለው ፓርቲዎ አምጥቶ የተከለብን በሽታ እንጂ እኛማ የት አውቀነው ብለው የሞገቱት፣ ያስተማሩት አባቶች ስለመኖራቸው ግን እስከ አሁን የተሰማ ወሬ የለም።
★ “ የሰላም አባት ሁኑ ”
• ይሄን ሲሰማ ኦነግ ምን ብሎ ይሆን?
•••
ሻሎም  !  ሰላም  !
ግንቦት 14/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic