>

የአመራር ጉድለት የተከታዮች ሚና  (ዶ/ር ታደሰ ብሩ ከርሴሞ)

የአመራር ጉድለት የተከታዮች ሚና 
ዶ/ር ታደሰ ብሩ ከርሴሞ
መንደርደሪያ
ኢትዮጵያ በጥሩ መሪ እጦት ስትሰቃይ የኖረች አገር በመሆኗ ሊሆን ይችላል፤ የአመራር ድክመቶች ሁሉ ምንጭ የመሪ ጉድለቶች ብቻ የሆነ አድርገን መውሰድ ይቀለናል። ሀቁ ግን ይህ አይደለም። የምንጠብቀው ውጤት ባልተገኘ (ወይም ያልተገኘ በመሰለን) ጊዜ ሁሉ ጣቶቻችንን ወደ መሪ መጠንቆላችን ልናርመው የሚገባ ስህተት ነው የሚል እምነት አለኝ።
በድርጅትም ይሁን በአገር ደረጃ የምንጠብቀው ውጤት አለመገኘቱ ብቻውን የአመራር ጉድለት መኖር ገላጭ አይደለም። ምናልባት የምንጠብቀው ውጤት በወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ምኞት ሆኖ ሊሆን ይችላል። የጠበቅነው ውጤት ያላገኘነው በአመራር ጉድለት መሆኑን ካረጋገጥንም በኋላ የጉድለቱ ምክንያት መሪ ላይሆን ይችላል። የመሪው ጉድለት መኖሩ ብናረጋግጥ እንኳን መሪው ብቸኛ ተጠያቂ ላይሆን ይችላል። መሪ ለአመራር ስኬት ብቸኛ ተወዳሽ መሆን እንደሌለበት ሁሉ ለአመራር ጉድለት ብቸኛ ተጠያቂ መሆን የለበትም፤ ተከታዮች ወይም ተመሪዎች (followers) ከመሪ ያላነሰ ተጠያቂነት አለባቸው።
ለአመራር ስኬትም ሆነ ጉድለት ከፍተኛ ሚና ያላቸው አራት አካላት አሉ፤ እነሱም (1) መሪ፣ (2) ተከታዮች፣ (3) ሁኔታዎች፣ እና (4) ተግባቦቶች (communications) ናቸው። ከላይ እንደገለጽኩት የአመራር ችግር ያጋጠመን በመሰለን ጊዜ ሁሉ ጣቶቻችንን የምንቀስረው ወደ መሪዎቻችን በመሆኑ በዚህ ጉዳይ መፃፍ እጅግም ዋጋ የለውም። የኔ ትኩረት ሌሎቹ ሶስቱ (ተከታዮች፣ ሁኔታዎች እና ተግባቦቶች) እያንዳንዳቸው ከመጀመሪያው ያላነሰ አስተዋጽዖ ያላቸው መሆኑ ለማሳመን ጥረት ማድረግ ነው።
ይህ አጭር ጽሁፍ ለአመራር ጉድለት የተከታዮች ሚና ምን ያህል ጉልህ ሊሆን እንደሚችል ማመልከት ነው።
ደካማ ተከታዮች 
እኛ ኢትዮጵያዊያን ለብዙ ዓመታት “ወንዝ የሚሻግረን” መሪ አጥተናል እያልን ስናማርር ኖረናል፤ አሁን ደግሞ ወንዙን በሥርዓት ለመሻገር የሚደፍር ተከታይ የማጣት ችግር ውስጥ የገባን ይመስለኛል።  አንዳንዱ ተከታይ ወንዙን ለመሻገር የተዘጋጁትን ሳይቀር ማለቂያ በሌላቸው ክርክሮች ጠምዶ ጥረታቸውን ያስተጓጉላል፤ ያሰናክላል።
“በበግ የሚመራ የአንበሶች ሠራዊትን አልፈራም፤ በአንበሳ የሚመራ የበጎች ሠራዊትን ግን እፈራለሁ” የሚለው የታላቁ አሌክሳንደር ምሳሌዓዊ አነጋገር ትክክል አይደለም። መሪ የሚወጣው ከተከታዮች ነውና ከመጀመሪያውኑ አንበሶቹ፣ እውነተኛ አንበሶች ከሆኑ በበግ መመራት አይፈቅዱም። የታላቁ አሌክሳንደር ምሳሌያዊ አነጋገር የመሪን ሚና አጋኖ ከመግለጽ ያለፈ ተግባራዊ ፋይዳ ያለው አይደለም። በተግባር እንደታየው ራሱን አከል በሆኑ ጠንካራ ተከታዮችን ያልተደገፈ መሪ (በግሉ የቱን ያህል ጠንካራ ቢሆንም እንኳን) ውጤታማ መሆን አይችልም። የደካማ ተከታዮች መሪ ውሎ አድሮ ራሱ ደካማ መሆኑ አይቀርም።
ንቁ ተከታዮች መሪያቸውን ያነቃሉ፤ ትጉህ ተከታዮች መሪያቸውን ያተጋሉ። በአንፃሩ ደግሞ ትጉሁን መሪ የሚያሰናክሉ፤ ጠንካራውን መሪ የሚያዳክሙ ተከታዮች አሉ።
የመሪነት ያህል የበዙ ባይሆንም በተከታይነት ላይ የተደረጉ ጥናቶች አሉ። ለምሳሌ የሀርቫርድ ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር አብርሃም ዛሌዝንክ (Abraham Zaleznik)  አስገዳጆች (compulsive)  የሚሏቸው የተከታይ ዓይነቶች አሉ።  አስገዳጅ ተከታዮች መሪያቸው መቆጣጠርና መተቸት ያበዛሉ፤ ከዚያም አልፎ ደንቦችን እየጠቀሱ መሪያቸውን ያስፈራራሉ፤ እራሳቸው ኃላፊነት ወስደው ግን አይሠሩም። መሪያቸው ስህተት ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ይዞ ማጋለጥ ለእነሱ ትልቅ ስኬት ነው።  እነሱ ለማጋለጥ እንዲመቻቸው መሪዓቸው ቢሳሳት ደስተኞች ናቸው። አስገዳጅ ተከታዮች ስህተት ፈላጊዎችና ተቺዎች እንጂ የሥራ ሰዎች አይደሉም።  እንዲህ ዓይነት ተከታዮች በበዙበት አገርም ሆነ ድርጅት ውስጥ እጅግ ጠንካራ የተባለ መሪ እንኳን ስኬታማ አመራር ማስፈን አይችልም።
ሮበርት ኪሊይ (Robert Kelley)የተባሉ ሌላ ተመራማሪ ደግሞ ከላይ የተጠቀሱትን ተቃራኒ ሆኖም ግን ከላይኞቹ ባላነሰ አፍራሽ የሆኑ ሁለት የተከታዮች ዓይነቶች መኖራቸው ይገልፃሉ። እነዚህን –   “ተስማምቶ አዳሪዎች(conformist) እና  “ተነጂዎች” (passive) ይሏቸዋል።
ተስማምቶ አዳሪ ተከታዮች “እሺ ሰዎች” (the yes-people) ናቸው፤ ሁሌ ከመሪያቸው ጎን ይቆማሉ፤ የታዘዙትን ይፈጽማሉ፤ ሆኖም ግን ለትንሹም ለትልቁም ”መመሪያ“ እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፤ በራሳቸው አቅደው የሚሠሩት የለም። “ተስማምቶ አዳሪዎች” ራሳቸውን የሥራ ሰው አድርገው ሲገልጹ ይሰማሉ። “የኔ ኃላፊነት የታዘዝኩትን መፈፀም ነው፤ ማቀድ፣ ማሰብ፣ ማለም የመሪዬ ተግባር ነው” ይላሉ። የአመራር ድክመት ቢኖር እነሱ የሚጠየቁበት አንዳችም ጉዳይ ያለ አይመስላቸውም፤ እንዲታሰብላቸው እንጂ እንዲያስቡ፤ እንዲታቀድላቸው እንጂ እንዲያቅዱ የተፈጠሩ አይመስላቸውም።
“ተነጂ ተከታዮች”  መሪያቸውን ከመውደድና ከመከተል በስተቀር ስለሚሠሩት ነበር አይጨንቃቸውም፤ የመሪዓቸውን ድምጽ መስማት፤ እዋለበት መዋል፤ አደረበት ማደር ያነቃቃቸዋል። በዚህ ባህሪያቸው ምክንያት ተነጂ ተከታዮች “በጎች” (sheep) በሚል መጠሪያ ይታወቃሉ። “በጎች” ተከታዮችን ወደ ሥራ ማሠማራት፤ ጭንቀት ውስጥ በገቡት ጊዜ ሁሉ “አይዞዓችሁ” እያሉ ማባበል ለመሪው ራሱን የቻለ ትልቅ ሥራ ነው።
ተስማምቶ አዳሪና ተነጂ ተከታዮች (ተመሪዎች) የበዙበት ድርጅት ወይም አገር ውስጥ ጠንካራ መሪ ቢነሳም ውጤታማ መሆን ይቸግረዋል።  በእንዲህ ዓይነት ተከታዮች የተከበበ መሪ አምባገነን እንዲሆን ይወተወታል። እንዲህ ዓይነት ተከታዮች የበዙበት አገር ለአምባገነን መሪ መነሳት ምቹ ነው።
ባርባራ ኬለርማን (Barbara Kellerman) ደግሞ  “አክራሪዎች”  (Diehards)  የሚሏቸው የተከታይ ዓይነቶች አሉ። አክራሪ ተከታዮች ከመሪው ሀሳቦች ውስጥ እነሱ የሚደግፉትን ሰበዝ ከመጠን በላይ የሚያራግቡ፤ ነገሮችን በማጦስ መሪውን ከተቃዋሚዎቹ ጋር መደራደሪያ የሚያሳጡ ናቸው።  አክራሪዎች ቅራኔዎችን በማስፋት፤ ክርክሮችን ከሚያስፈልገው በላይ በማጦዝ መሪያቸውን አጣብቂኝ ውስጥ ይከታሉ።  አክራሪዎች ተቃራኒ አቋም የያዙ ወዳጆቻቸውን ሀሳብ የማዳመጥ ትዕግስት የላቸውም። አይሰሙም፤ አይደራደሩም። ትንሹን ጉዳይ አግዝፈው የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ያደርጉታል። ከነሱ ጋር ያልወገኑ ወዳጆቻቸውን በጠላትነት ለመፈረጅ አይቸገሩም። እንዲህ ዓይነት ተከታዮች የበዙበት ድርጅት ወይም አገር መሪ መሆን ትልቅ ፈተና ነው።
እንድምታ
የዚህ አጭር ትንተና እንደምታ የሚከተለው ነው።  መሪዎቻችን ከመተቸታችን በፊት እኛ እንደምን ያለን ተከታዮች ነን ብለን እንጠይቅ። አመራር መሪ ብቻውን የሚፈጥረው ነገር አይደለም። አመራር መሪ እና ተመሪ ተባብረው የሚፈጥሩት ነገር ነው። ስኬታማ አመራር በመሪ ብቃት ብቻ አይገኝም። በሀገራችን ስኬታማ አመራር እንዲኖር እኛም – ማለትም ተከታዮች (ተመሪዎች) – ኃላፊነት አለብን።
Filed in: Amharic