>

ኢሳት ወዴት! ወደ ባርነት ወይስ ወደ ነጻነት? (ሀይለገብርኤል አያሌው)

ኢሳት ወዴት! ወደ ባርነት ወይስ ወደ ነጻነት?
ሀይለገብርኤል አያሌው
መጣ የተባለው ጉራማይሌ ለውጥ ብዙ ያልተጠበቁ ሁኔታዎችን ፈጥሯል:: ጽንፈኞች ነግሰው ኢትዮጵያዊነት ከመቼውም ግዜ በላይ ፈተና ላይ ወድቋል:: የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነት መንምኖ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው መሄድ የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: በሃገሪቱ በነጻነት ተዘዋውሮ መንቀሳቀስ እጅግ አደገኛ ሆኗል::
ጽንፈኛ ብሄረተኞች የመንግስትን አቋም የሚያስለውጡበት ባለስልጣናት በነጻነት እንዳይሰሩ ተጽዕኖ የሚያሳድሩበት ደረጃ ደርሰዋል::
የጽንፈኞች ሚድያ አቅምና ጉልበት የተደራሽነት ስፋትና የፕሮፖጋንዳ ጉልበቱ ከመቼውም ግዜ በላይ ጠንክሯል:: ያሾማል ያሽራል ሕዝብን ከህዝብ ያጋጫል በአንጻሩ በሚሊዮኖች ላይ የሚካሄድ ሰቆቃን ያፍናል:: ጥላቻ እንዲነግስ ሃገር እንዲፈርስ በትጋት ይሰራል::
ይህን መሰል ሃገራዊ አደጋ በግልጽ በሚታይበት ወቅት ከነብዙ ችግሮቹም ቢሆን የሕዝብ ልሳን ሆኖ ብዙ የሰራው ኢሳት ለሕልውና አደጋ መጋለጡ የሚያሳዝንም የሚያሳስብም ነው::ከመቼውም ግዜ በላይ ነጻ ሕዝባዊ ሚድያ ለሕዝባችን በሚያስፈልግብት ግዜ ኢሳትን ማጣት ለኢትዮጵያውያን ውድቀት ነው::
መጣ ከተባለው ለውጥ ማግስት ጽንፈኞች በስፋት  ሲደራጁ ሃገራዊ ሃይል ነኝ ሲል የነበረው ወገን መንበርከኩን አይተናል:: የዶር አብይ ቡድን በተጠናና በታለመ ሁኔታ በሃገራዊ ፖለቲካውና በሚድያው ዙሪያ ሕወሃትን ሲታገሉ የቆዩት ተቋማት ውስጥ ያሉ ግለሰቦችን  በቃላት በመደለልና በውዳሴ ከማሳበጥ አልፎ የቤተመንግስት ባለሟል በማድረግ አቋማቸውን ጥለው ምርኮኛ በማድረግ ተሳክቶለታል::
በኢሳት ውስጥ ያሉት ጋዜጠኞች ከብዙዎቹ  ጋር ጥሩ ወንድማማችነትና የቆየ ወዳጅነት አለኝ:: ከነልዩነታችንም ቢሆን ተስማምተን ቆይተናል:: ለብዙዎቹ አክብሮት አለኝ:: ዛሬ ኢሳት ለገባበት እጣብቂኝ ምክንያት በመሆናቸው አዝናለሁ:: ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ አቅጣጫ መነዳታቸው ለክብራቸውም ለዘለቄታዊ ተሳትፏቸውም አይበጅም:: የቆሙለት የሙያ ቃል ኪዳን ሕዝብ ላብና ደሙን የገበረለት ተቋም ላልተጨበጠ የለውጥ  ተስፋ ጭዳ እንዲሆን መፍቀድ አልነበረባቸውም::
ኢሳት ዛሬ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆሟል:: ሃሳብ የሚፈራ ትችትን የሚሸሽ መሪዎችን የሚያወድስ ባርነትን ምርጫው ያደረገ ወገን በአንድ በኩል ከሙሉ አቅም ጋር ከገዢዎች ጎን ተሰልፏል::
በሌላ በኩል ሕዝብ የማወቅ መብት አለው የሚል ወገን በደካማ አቅም ከሕዝብ ጎን ሆኖ ለነጻነት ይታገላል::
       ኢሳት ከሕዝብ እጅ ወጥቶ የገዥዎች ባሪያ ከመሆኑ በፊት ከሃቅና ሕዝባዊነታቸው ጋር የቆሙትን ወገኖች መደገፍና ሚድያውን ከውድቀት መታደግ የሃገር ወዳዶች ድርሻ ነው:: ስለዚህም ዛሬ በዲሲ በተጠራው የኢሳት የድጋፍ ዝግጅት ላይ ተገኝተን በሞራልም በገንዘብም ልንደግፍ ይገባል:: ነገ ዳር ሆኖ ከንፈር ከመምጠጥ ዛሬ ታግሎ ተቋምን ማቆየት የሕዝቡ ድርሻ ነው::
ሕዝብ የማወቅ መብት አለው!!
Filed in: Amharic