>

"እርዳታውን በብሔር ልንመነዝረው ከሞከርን ወደ እንስሳነት መውረድ ነው!!!" (ግሎባል አሊያንስ ሊቀመንበር ታማኝ በየነ) 

“እርዳታውን በብሔር ልንመነዝረው ከሞከርን ወደ እንስሳነት መውረድ ነው!!!”
የዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት ሊቀመንበር ታማኝ በየነ 
 
  በመላው ዓለም ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ያሰባሰበውን ከ31.4 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ለማዋል ቃል ለገባው ወርልድ ቪዥን ዛሬ አስረከበ።
«ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት» (Global Alliance for the Rights of Ethiopians) በጌድዮ ጉጅ ዞን በተከሰተው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እና መልሶ ለማቋቋም የሚያስችለውን ስምምነት አዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ውስጥ ዛሬ ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ጋር ተፈራርሟል። በሌላ በኩል በአማራ ክልል ጎንደር አካባቢ ለተፈናቀሉት ተብሎ የተሰባሰበውን 3 ሚሊዮን ብርም አስረክቧል።
የትብብሩ ሊቀመንበር ታማኝ በየነ እንዳሉት ሥራውን ለማከናወን ወርልድ ቪዥንን የተመረጠው ስፍራው ድረስ ይህንን ሥራ ሙሉ ለሚሉ ለመሥራት ገንዘቡንም ጥቅም ላይ ለማዋል ፈቃደኛ በመሆኑ ነው። ከሚደረገው የምግብና መሰል ጊዜያዊ ርዳታዎች በላይ ገንዘቡ በተፈናቃዮች የቀደመ መኖሪያቸው ላይ ቤቶች ተገንብተውበት  እንዲቋቋሙ ለማድረግ የሚውል ነው ተብሏል።
«ርዳታውን በብሔር ልንመነዝረው ከሞከርን በጣም ወደ እንስሳነት እየሄድን ነው። ኢትዮጵያዊ የኾነ ሁሉ ርዳታ ማግኘት አለበት» ሲል የ«ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት» ሊቀመንበር ታማኝ በየነ በገንዘብ ርክክቡ ወቅት ተናግሯል።
Filed in: Amharic