>
5:13 pm - Thursday April 19, 4323

"ምርጫው እንዲራዘም እንፈልጋለን!!!"  (የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ አንዷለም አራጌ) 

“ምርጫው እንዲራዘም እንፈልጋለን!!!” 
የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ አንዷለም አራጌ 
 
 የቀድሞው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የመላ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አርበኞች ግንቦት 7፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ የጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄና አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ራሳቸውን አክስመው የመሰረቱት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ትላንት መሪና ምክትል መሪ መርጧል። ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበርም ሾሟል።
 
አመራሮቹ ፓርቲው ሁለት ዓይነት የአመራር አወቃቀር አለው ብለዋል። በዚህም መሰረት የፓርቲው ሊቀ መንበር እና የፓርቲው መሪ የተለያዩ ናቸው። የፓርቲው ሊቀ መንበር የፓርቲውን የአደረጃጀትና የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ የሚመራ ሲሆን፤ የፓርቲው መሪ ፓርቲው ለፖለቲካ ስልጣን የሚያደርገውን ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴ፤ የፓርቲውን አቋም በመንግሥት ስልጣን ውስጥ የሚያስፈፅም አካል ነው በማለትም ያብራራሉ።
 
ባጠቃላይ ፓርቲው አሸንፎ ስልጣን ቢይዝ የመንግስትን ሥልጣን እና የፖለቲካ ስልጣንን ለመለያየት ታስቦ የተዋቀረ አደረጃጀት ነው። በዚህም መሰረት የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ሲሆኑ፤ የፓርቲው መሪ ደግሞ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ሆነው ተመርጠዋል። እኛም ከምክትል መሪው አቶ አንዷለም አራጌ ጋር ቆይታ አድርገናል
አቶ አንዷለም አራጌ፡ በፕሮግራምና በደንብ የያዝነው እምነት አለ። በዋነኛነት ለብሔር ጉዳይ ብለን ያነሳነው ሳይሆን ኢትዮጵያን ወደተሻለ አቅጣጫ ይወስዳታል ብለን የምናምነውን በዜግነት ላይ መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ነው የምናራምደው። ይህ ደግሞ እያንዳንዱን ዜጋ ይመለከታል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚወከልበት ነው። በእያንዳንዱ [ሰው] ቤት ውስጥ የሚገባ ነገር ነው። ሕዝቡ በተፈጥሮው ሕብረ ብሔራዊ ነው። በመልኩ፣ በአኗኗሩ፣ በባህሉ፣ በእምነቱ በሁሉ ነገር ተሰባጥሮ የሚኖር ሕዝብ ነው። ሕዝቡ ውስጥ ያለውን ነገር መልሰን ለሕዝቡ ነው የምንነግረው። ሕዝቡ ልብ ውስጥ ያለውን መልሶ መንገር አያከስርም። በቀላሉ ፍሬ ያፈራል ብዬ አስባለሁ። በብሔር ፓለቲካ የተሰማሩት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንም ቢሆኑ ከዚህ አስተሳሰብ ጨርሰው ይርቃሉ ብዬ አላስብም። በተለያዩ ወቅቶች የተነሱ ግጭቶች ሊያሻቅቡ ይችላሉ። ግን ውሎ አድሮ ሥራውን ሲያዩት እነሱም ወደቀናው መንገድ ይመለሳሉ ብዬ አምናለሁ።
፦ ለምሳሌ ቅንጅትን ብናይ ሕዝቡን አሳምኖ የሕዝቡን ድጋፍ አግኝቶ ኢህአዴግን መገዳደር ቀላል ነበር የሆነለት። አሁን ግን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ተቀባይነት አላቸው። ኢህአዴግ ይህን ያህል ተቀባይነት ያለው መሪ ባለው ሁኔታ ፓርቲውን መገዳደር ቀላል ይሆናል? ምን ያህል ውጤታማ ያደርጋችኋል?
አቶ አንዷለም አራጌ፡ በእርግጥ [ቀድሞና አሁን ከኢህአዴግ ጋር መፎካከር] ልዩነት አለው። ዞሮ ዞሮ ዶ/ር ዓብይ ጋር ያለው ቀናነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ የኢትዮጵያዊነት ስሜት በኢህአዴግ ውሰጥ ከተለመደው የተለየ ነው፤ በጎ ነገረ ነው። ለዛ ሁላችንም ድጋፋችንን ቸረናቸዋል። ነገር ግን ኢህአዴግ የሚከተላቸው አላማዎቹና መርሆቹ አሁንም እንደቆሙ ናቸው። ለውጡም ቢሆን ከዶክተር ዓብይ ብዙ አልወረደም። ስለዚህ በ547ቱም ወረዳዎች የሚወዳደሩት ዶ/ር ዓብይ ብቻ አይደሉም። ዶ/ር ዓብይ የሚወከሉት በአንድ ወረዳ ላይ ነው። ሕዝቡ በየወረዳው የሚመርጣቸው ሰዎች ውድድር የሚካሄደው ኢህአዴግ በሚያቀርባቸውና እኛ [በምናቀርባቸው ተፎካካሪዎች] አላማ፣ ማንነትና ሥነ ምግባር መካከል ነው። በብዙ ቦታዎች እናሸንፋቸዋለን ብዬ አምናለሁ። አልጠራጠርም።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ፣የኢዜማ፣ ደጋፊ ማነው? ተከታያችን ማነው ትላላችሁ?
አቶ አንዷለም አራጌ፡ የኛ ደጋፊ በሕብረ ብሔራዊ አስተሳሰብ፣ በኢትዮጵያ አንድነት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ የሚኮራው፣ አሁንም በኢትዮጵያ ተስፋ የሚያምነው አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያውያን ሁሉ የኛ እምነት ደጋፊዎች ናቸው። እኛ የምናወራው ስለአንድ ብሔር፣ ስለአንድ ክልል ወይም ስለአንድ ቀበሌ አይደለም። እኛ የምናወራው ስለጠቅላላ ሀገራችን፣ ስለጋራ ተስፋችን፣ ስላለፈው በጎም መጥፎም ታሪካችን [እና] የዚያ ሕብር፣ የዚያ ግማጅ መሆናችንን ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ የዚህ ሁሉ ነገር ወራሽና አስፈጻሚም ስለሆነ አብዛኛው የኛ ደጋፊ ነው ብለን እናምናለን። በአስተሳሰብ ልዕልና የሚያምን፣ በአመክንዮ ልዕልና የሚያምን እና ለኢትዮጵያ ያለንን ፖሊሲ መዝኖ ይበጃል፤ አይበጅም ብሎ ፍርድ መስጠት የሚችል፤ ቀና አስተሳሰብ፣ በጎ ህሊና ያለው ሁሉ የኛ ደጋፊ ነው ብለን እናምናለን።
፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲባለፉት አመታት በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ የሚታወቁ ሰዎችን ወደአመራር አምጥቷል። በሌሎች ፓርቲዎች መከፋፈልና መፈራረስ ውስጥ የነበሩ ሰዎች አሁን የኢዜማ ፊት ሆነው መምጣታቸው አሉታዊ ነገር ያስከትላል የሚል ስጋት አላችሁ?
አቶ አንዷለም አራጌ፡ እኛ ስጋት የለብንም። የድሮ ነገር ሲነሳ እንኳን በኛ መካከል አይደለም፤ ትላንት ልጆቻንን ሲያስለቅሱ የነበሩ፤ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በየመንገዱ፣ በየታዛው የገደሉ ኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ሰዎችንም ይቅር ብለናል። ስለዚህ በይቅርታ እናምናለን። በፍቅር እንጸናለን። ሰዎችን የምንመዝነው ለዛሬዋና ለነገዋ ኢትዮጵያ በሚኖራቸው ትልቅ አስተዋጽኦ እንጂ ትላንት የነበሩበትን በደል ሁሉ እየቆጠርን በዛ ልንመዝናቸው አንሞክርም። የሰው ልጅ ትልቁ የሰብዕናው አካሉ ካለፈው ማንነቱ የመማር አቅሙ ነው። ስለዚህ የኛ ደጋፊ እነዚህን መሪዎች ሲመርጥ ይህንን ሁሉ ግንዛቤ ውስጥ በመክተት ነው ብዬ አምናለሁ። ሁላችንም የተለያየ ፓርቲ ውስጥ ነበርን። መራጩ ግን ያለውን ሉአላዊ ስልጣን ተጠቅሞ መርጧል። ሕዝቡም የይቅርታ መንፈስና ልብ አለው። መቻቻልን፣ አንድነትን ይደግፋል። ትልንት ላይ ሳይሆን ዛሬ ላይ ቆሞ ነገን ማየት ይፈልጋል ብለን እናምናለን። ስለዚህ ችግር ያመጣል ብለን አናስብም። ብዙ አዳዲስ መሪዎችም አሉ። አሁን የመጀመሪያው ጉባዔ ስለሆነ እንጂ ነገ ከነገ ወዲያ ታላላቅ መሪዎች የሚያፈራ ፓርቲ ነው የፈጠርነው። አሁን አመራር ውስጥ የተወሰነ ልምድ ያላቸው ሰዎች መካተታቸው ለድርጅቱ ጥንካሬ እንጂ ድክመት አይሆንም ብዬ ነው የማምነው።
፦  በቀድሞ ፓርቲዎች መከፋፈል ውስጥ የነበሩና አንዳንዶች ‘የከሰሩ ፖለቲከኞች’ የሚሏቸውን ወደ ፓርቲው አመራር ማምጣታችሁ ጥሩ አይደለም የሚል አስተያየት አለ?
አቶ አንዷለም አራጌ፡ የምንታገለው ስለሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነት ነው። እሱ ደግሞ መራጩ ሕዝብ ነው ብለን እናምናለን። ነገ ከዚህም በላይ በጠነከሩ ቃላት የሚገለጹ ሰዎች ምርጫ ሊያሸንፊ ይችላሉ። የዴሚክራሲ ውበቱ ደግሞ ተሸናፊና አሸናፊ ይኖራል። ተሸናፊው ጊዜውን ጠብቆ ለማሸነፍ ይሠራል። ስለዚህ የከሰሩ ፓለቲከኞች ሌላም ስም ሊሰጥ ይችላል። ግን እነዚህ የሚባሉትም ሰዎች ኪሳራ ከማን አንጻር. እንደሚለካ አናውቅም። በዚ ሀገር እንደዚህ አይነት የሚያሳፍር ነገር መስማት የተለመደ ነው። ትላንት ብዙ ነገር ሲሠሩ የነበሩ ሰዎች ሌሎችን በባንዳነት፣ ሌሎችን በገዳይነት የሚከሱ ሰዎች እናውቃለን። እንደዚህ አይነት መፈራረጅና ጭቃ መቀባባት ውስጥ መግባት አንፈልግም። እንዲያውም የከሰረ ማለት ይሄ ነው። በጣም ከሥነ ምግባር የወጣና ጸያፍ በሆነ የፖለቲካ ስርአትና ብሂል ውስጥ መቆየት አንፈልግም። ፓለቲካው መታደስ አለበት። መዘመን አለበት። ሀሳብ ላይ ትኩረት አድርጎ መታገል ተገቢ ነው ብልን እናምናለን። የኛ አባላት ግን ሉአላዊ መብታቸውን ተጠቅመው ይበጁኛል ያሏቸውን ሰዎች መርጠዋል። ስለዚህ እሱን ሁልጊዜ እናከብራለን። ዜጋው ሰውን የመመዘን አቅም አለው። የከሰረ ፓለቲከኛ ብሎ የሚሳደበው ስው፤ የመሳደብ መብት ባይኖረውም፤ሀሳቡን የመግለጽ መብት እንዳለው ሁሉ፤ የመመርጥ መብት ያላቸው ዜጎች መሪዎቻቸውን መርጠዋል። ዋናው ያ ነው። በሚመረጥ ሰው ሁሉንም ማስደሰት አይቻልም።
ቀደም ሲል ተቃዋሚዎችን በፕሮፓጋንዳም ይሁን በተለያዩ መንገዶች የሚገዳደረው ገዢው ፓርቲ ነበር። አሁን ግን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተዋናዮች በዝተዋል። አክቲቪስቶችና ተጽዕኖ ፈጣሪ ቡድኖችም አሉ። በማኅበራዊ ሚዲያም በጣም ጠንካራ እንቅስቃሴ አለ። በዚህ የፖለቲካ ጨዋታው በተቀየረበት ጊዜ ራሳችሁን ለማስተዋወቅና የሚሰነዘርባችሁን ለመመለሰ ምን አይነት ለመከተል አስባችኋል?
አቶ አንዷለም አራጌ፡እኛ እየሞከርን ያለነው አዲስ የፖለቲካ ባህል ለማስተዋወቅም ነው። በኛ በኩል መንገዳችን ፍቅር ነው። ያንን ደግሞ በተግባር እናሳያለን። ኢትዮጵያውያን ስንል የሚደግፉን፣ የሚመስሉንን ብቻ አይደለም። እንዲያውም ሀሳባቸው ከኛ የሚለየውንም በጣም እናከብራለን። ለነሱ ጆሮ እንሰጣለን። ምክንያቱም ያለንን የሚደግሙልን ሳይሆን የሌለንን የሚነገሩን ሰዎች ናቸው። እኛ ያላየነው እነሱ ጋር ያለው ምንድንነው ብለን ትኩረት ሰጥተን እንከታተላለን። ሁልጊዜም የሀሳብ ልዩነት እንዲኖረን እንፈልጋለን። ምክንያቱም ሕዝብ የሚጠቀመው ከሀሳብ ልዩነት ነው። አንድ ላይ ተመሳሳይ ነገር ብናስተጋባ ትርጉም የለውም። ይህን የምናደርገው በፍቅርና በስርዐት ነው። ለኛ አክቲቪስትም፣ ሌላ ዘርፍ ተከትሎ እምነቱን የሚያራምድ አንድ ነው። በቀናነት እናስተናግዳለን። ጭቃ መቀባባት አልጠቀመንም።
፦ ገና ከምስረታው ቅሬታዎች እየተነሱባችሁ ነው። የሚሰነዘርባችሁን ነገር ግን ፍቅር ብቻ ይመልሰዋል?
አቶ አንዷለም አራጌ፡ ፍቅር ውስጥ ምክንያት አለ። ዝምብሎ እንወዳችኋለን አይደለም። ፍቅር ውስጥ የምናደርገውን ነገር በንጽህና በትህትናና በፍቅር እናደረገዋለን። እኛ እውነት የምንለውን ነገር በፍቅር፣ በትህትናና በክብር እናቀርባለን። ሕዝቡ ይፈርዳል። ያለንን ነገር የምናቀርበው ከሥነ ምግባር ባፈነገጠ ሁኔታ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ በማይመጥን ሁኔታ ጭቃ በመቀባባት፣ ነውረኛ የሆነ አቀራረብ በመከተል አይደለም። እኛ ኢትዮጵያውያን አስተዳደጋችን ባህላችንም እንደዚህ ነው ብለን አናምንም። ለሀሳባቸው ክብር እንሰጣለን። ለሀሳባቸው ትኩረት እንሰጣለን። ግን ያንን በፍቅር፣ በንጽህና፣ በትህትናና በአከብሮት ምላሽ እንሰጣለን።
ሀገራዊው ምርጫ እንደታሰበው በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄድ ከሆነ ኢዜማ ዝግጁ ነው? ለመሳተፍ ያህል ሳይሆን ለማሸነፍ ወደምርጫ የመግብት አቅም አለው?
አቶ አንዷለም አራጌ፡ እንኳን የዚህ ሀገር ፓርላማ የሌላውም ሀገር ፓርላማ ደሞዝ ብዙም የሚያስቀና አይመስለኝም። ገንዘብንም ታርጌት [ኢላማ] አድርጎ መኖር ከአንድ የመርህ ሰው የሚጠበቅ አይደለም። እኛ የምናስቀድመው ሀገራችንን ነው። እኛ የምናስቀድመው ለውጥን ነው። ሀገራችን በተስተካከለ የለውጥ ጎዳና ላይ እንድትሆን፤ አሁን የተጀመረው መንገድ በደንብ ተጠርጎ ይህችን ሀገር ለዘመናት ከቆየችበት የድክርት ጨለማ ታሪክ አውጥተን ብርሀን ወደነገሠበት የዴሞክራሲ ምድር ልናሻግራት እንፈልጋለን። ትልቁ ህልማችን እንዲወለድ ስጋና ደም እንደለብስ የምንፈልግው ይህንን ነው እንጂ ምርጫ ማሸነፍ ሁለተኛ ነገር ነው። እኛ [ምርጫው] መራዘም አለበት [እንላለን]። ምክንያቱም [ያለን] ትልቅ አላማ የታሪክን ወንዝ የመቀየር አላማ ነውና በደንብ ተዘጋጅተን፣ የተቋማቱ ምሰሶዎች ቆመው፣ በማያዳግም ሁኔታ ለሁልጊዜም አርአያ የሚሆነን ምርጫ እንድናደርግ [እንፈልጋለን]። ያለፊት አይነት ምርጫ እንዳይደገም እንፈልጋለን። ምርጫው የሚደረግ ከሆነ ግን፤ በግድ ይሁን ተብሎ ብንወዳደር እኛ በ312 ወረዳዎች በጣም ጠንካራ የሚባል አደረጃጀት ፈጥረናል። ምክር ቤቶች ፈጥረናል። በቀሩት ወረዳዎችም በአጥጋቢ መልኩ መንቀሳቀስ እንችላለን። በጣም ሕዝብ እንደሚደግፈን እናምናለን። ሕዝብ ያውቀናል። ይህንን በድፍረት የምናገረው በፍርደ ገምድልነት ሳይሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሀሳብ ይዘን እንደተነሳን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀሳብ፣ እምነቱን ተስፋው አብሮ ተከባብሮ መኖር እንጂ መገዳደልና መለያየት መበታትን ስላልሆነ ነው። እኛ ደግሞ የዚህ ሀሳብ ደጋፊዎችና አራማጆች ስለሆንን ሕዝቡ ለእምነቱ፣ ለተስፋው ዘብ ይቆማል፣ ይታገላል ብለን እናምናለን። ስለዚህ በቀረው ጊዜ ቢሆን ተደራጅተን መታገል እንችላለን። ማሸነፍ እንችላለን ብለን እናምናለን።
Filed in: Amharic