>

ምርጫ  97 እና  ምርጫ  2012 (በፍቃዱ ኃይሉ)

ምርጫ  97 እና  ምርጫ  2012
በፍቃዱ ኃይሉ
አሁን ያለንበት ጊዜ ከቅድመ ምርጫ 1997 ጊዜ ጋር የሚመሳሰልበት ብዙ ነገር አለ። በመሠረቱ የፖለቲካ ለውጡም ከምርጫ 97 ወዲህ የተለወጡትን ነገሮች ወደ ነበሩበት መመለስ የሚመስልበትም ጊዜ አለ።
ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን መግዛት ከጀመረ ወዲህ የ1997ቱ ምርጫ መሠረታዊ የአስተዳደር ለውጥ እንዲያመጣ የተገደደበት የመጀመሪያው ጊዜ ነው። 2010 ሁለተኛው ሊባል ይችላል።
የ1997ቱ አገር ዐቀፍ ምርጫ ከመካሔዱ በፊት የፖለቲካ ምኅዳሩ የሰፋበት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች በከፍተኛ ሁኔታ የተጠናከሩበት፣ ሐሳብን በነጻነት መግለጽ እምብዛም የማይገደብበት፣ የፖለቲካ እስረኞች እስር ቤቶቹን ያላጨናነቁበት ጊዜ ነበር። ይህ ሁሉ ግን በምርጫው ውጤት አጥቢያ ገዢው ፓርቲና ዋና ዋናዎቹ ተቃዋሚዎች፣ በተለይም ቅንጅት ሲወዛገቡ በአንድ ጊዜ ወደ ተቃራኒው ሁኔታ ተለወጧል።
ከ97ቱ ምርጫ በኋላ ቢያንስ ለስምንት ዓመታት የአደባባይ የተቃውሞ ሰልፍ አልተካሔደም። የዋነኛዎቹ ተቀናቃኞች የቅንጅት ለአንድነት እና ለፍትሕ አመራሮች፣ የሲቪል ማኅበራት አባላት እና ጋዜጠኞች በገፍ እና በግፍ ታስረው ተፈቱ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ተዳከሙ፣ በርካታ ብዙኀን መገናኛዎች ተዘጉ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን የሚያጠቡ ሕግጋት ወጡ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ገጽታም በዓለም ፊት ተበላሸ።
ከምርጫ 97 በኋላ የተከተለው ፖለቲካዊ አፈና ‘ኢሕአዴግ ዴሞክራሲን ለመገንባት የሚፈልገው ራሱ ምርጫ የሚያሸንፍ መሆኑን እስካረጋገጠ ድረስ ብቻ ነው’ በሚል እንዲተች አደረገው። የ2002 እና የ2007 ምርጫዎች ውጤት የእዚህ አባባል እና አፈናው ማረጋገጫ ማሳያዎች ነበሩ። ሁለቱም በኢሕአዴግ የ99.6 በመቶ እና 100 በመቶ አሸናፊነት የተጠናቀቁ ተወዳዳሪ አልባ ምርጫዎች ነበሩ።
 
ምርጫ 97ን ለመድገም
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ምርጫ 1997ን “እንከን አልባ” ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር። ይሁን እንጂ ያልታሰበው እና እርሳቸው “የስኒ ማዕበል” ነው የሚያስነሱት በሚል በትችት ይሸነቁጧቸው የነበሩት ተቃዋሚዎች፣ በአጭር ጊዜ በተፈጠሩ ቅንጅቶች እና ኅብረቶች ዋና ከተማዋን እና ሌሎች ብዙ መቀመጫዎችን ቀሟቸው። በምርጫው ውጤት ተወዛገቡ፤ መንግሥት ተቃዋሚዎቹን ለቃቅሞ በማሰር የ‘እንከን አልባ’ ምርጫ ቃል ኪዳኑን አፈረሰ። ያኔ መለስ ዜናዊ “የወሰድነው የተሰላ የአደጋ መጋፈጥ (calculated risk) እርምጃ ነበር እንጂ ይህ እንደሚመጣ [ተቃዋሚዎች ሲሸነፉ እንደሚበጠብጡ ማለታቸው ነው] እናውቅ ነበር” አሉ።
አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሔድ እንደሚፈልጉ ደጋግመው ተናግረዋል። ለዚህም ድኅረ ምርጫ 97 የተዋቸውን ርዝራዦች በማፅዳት ሥራ ተጠምደዋል። እነዚህም የተዳከሙ ብዙኀን መገናኛዎችን መልሰው እንዲጠናከሩ፣ ሲቪል ማኅበራት እንዲያብቡ እንዲሁም የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲጠናከሩ ጥረት እያደረጉ ነው። በድኅረ 1997 ወቅት የወጡ እና አፋኝ ናቸው የተባሉ ሕግጋትም ክለሳ ላይ ናቸው።
አሁን የቅድመ ምርጫ 1997ን ምኅዳር የመመለሱ ሙከራ ከሞላ ጎደል ተሳክቷል። ነገር ግን ያኔ እንደነበሩት ዓይነት ጠንካራ ሲቪል ማኅበራት አሁን ገና አልተገነቡም። መገናኛ ብዙኀንን በተመለከተ የጋዜጣና መጽሔቶቹ ቁጥር እና ተነባቢነት ቢቀንስም ማኅበራዊ ሚዲያ እና የቴሌቪዥን እንዲሁም ራዲዮ ጣቢያዎች በቁጥርም በአማራጭ ሐሳብ አስተናጋጅነትም በዝቷል። የፖለቲካ ድርጅቶችም እንዲሁ ብቅ ብቅ እያሉ ነው።
ምርጫ ቦርድ ከ100 በላይ የፖለቲካ ስብስቦች መኖራቸውን አምኗል። ሁሉም ግን መሥፈርቶች አሟልተው የተመዘገቡ አይደሉም። የሆነ ሆኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ድርጅቶች እየተመሠረቱ ነው። ከነዚህ ውስጥ ትላንት በይፋ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) አንዱ ነው። ይህ ፓርቲ ከዋነኛ የምርጫ 2012 ተዋናዮች አንዱ እንደሚሆን አያጠራጥርም። እስካሁን ድረስ ከታዩ ምሥረታዎች ሁሉ በተለየ ብዙ ድምፅ ሰጪዎች በመሥራች ጉባዔው የተገኙበት የፖለቲካ ድርጅት መሆኑ ለዙህ ምልክት ነው።
ኢዜማ በ1997ቱ ምርጫ ወቅት መሪ ተዋናይ የነበሩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ስብእናዎችን ያቀፈ በመሆኑ ምርጫ 97ን ለመድገም ከሚደረጉ ጥረቶች አንዱ አስመስሎታል።
ምርጫ 97ን ላለመድገም
የ1997ቱ ምርጫ ሒደቱ፣ ውጤቱ እና ድኅረ ውጥረቱ በርካታ እንከኖች ነበሩት። ሲጀመር የምርጫ ቦርድ እና ሌሎችም መንግሥታዊ ተቋማት ገለልተኛ አልነበሩም። ይልቁንም ለገዢው ፓርቲ ይወግኑ ነበር። ለዚህም ነው በተቃዋሚዎች እና ገዢው ፓርቲ መካከል የተነሳውን ውዝግብ ለገዢው ፓርቲ በወገነ ውሳኔ ቦርዱ ሊገላግል የሞከረው። ከዚያ በኋላ ሕዝባዊ አመፅ ሲቀሰቀስ የፀጥታ ኀይሉ ብዙ ያልታጠቁ ዜጎችን መንገድ ላይ ገድሏል። ተቃዋሚዎች ሲታሰሩ ፍርድ ቤት እስከ ሞት ፍርድ ድረስ በይኖባቸዋል።
አሁን ያ ጊዜ ማንም መልሶ እንዲደገም አይፈልግም። ለዚህም ይመስላል። እንደ ምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር እና የጠቅላይ ፍርድ  ቤት ፕሬዚደንት ሹመቶች ገለልተኛ እንዲሆኑ የተደረጉት። እምብዛም ባይሳካም የመንግሥት ብዙኀን መገናኛዎችን እና ሌሎችንም ተቋማት ነጻ እና ገለልተኛ የማድረግ ሙከራዎች ከመንግሥት በኩል እየተሠሩ ነው።
ተቃዋሚዎችም የምርጫ 97 ጊዜ እንከኖቻቸው እንዳይደገሙ እየሠሩ ይመስላል። አዲስ የተመሰረተው የኢዜማ አንዱ ቅዠት ይኸው ምርጫ 1997 እንዳይደገም መሥጋት ይመስላል። በወቅቱ ከተቃዋሚዎች ዘንድ መሪ ተዋናይ የነበረው ቅንጅት የአጭር ጊዜ ጥምረት ከመሆኑም ባሻገር ፈተና ሲገጥመው በቅፅበት መፈረካከሱ ይታወሳል። መሥራቾቹ ይህንን ሳይከሰት ለመከላከል ቅንጅት ወይም ጥምረት ወይም ግንባር በመፍጠር ፈንታ ነባሮቹ ድርጅቶች ከስመው እንደ አዲስ ከወረዳ ጀምሮ ወደ ላይ ተደራጅቶ መምጣትን መፍትሔ አድርገው እንደመረጡ ደጋግመው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በ2010 የጀመረችው የዴሞክራሲ ምጥ በሰላም እንደምትገላገል አሊያም እንደምትጨናገፍ የሚታወቀው በመጪው ምርጫ ነው። ይህ ምርጫ የ1997ቱን ምኅዳር እና ቅድመ ሒደት መድገም ይፈልጋል ወይም ያስፈልገዋል፤ ነገር ግን ድኅረ ምርጫ ቀውሱን ግን ማስወገድ አለበት። ይህንን እውነታ ገዢውም ይሁን ተቀናቃኞቹ ወገን ያሉት ዋና ዋና ፖለቲከኞች የተረዱት ይመስላል። ይሳካላቸው ይሆን?
Filed in: Amharic