>

የአንዷለም መመረጥ ለእኔ ሰቆቃ ነው!!  (ስዩም ተሾመ)

የአንዷለም መመረጥ ለእኔ ሰቆቃ ነው!! 
ስዩም ተሾመ
* ወዳጄ ሆይ… ከጭቃ ጅራፍ የሚታደግ ወፍራም ቆዳ ይስጥህ!!
በእርግጥ የፕ/ር ብርሃኑ መመረጥ አልገረመኝም። ሰውዬው ከአመሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከኤርትራ እስከ ኢትዮጵያ በገሃድ የሚታይ ታሪክ አለው። “ብርሃኑ ነጋ” የሚለው ስም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ራሱን የቻለ ታሪክ ነው። የዚህን ታሪክ ቀጣይ ክፍል ደግሞ በኢዜማ አማካኝነት የምናየው ይሆናል። እኔን ግን በጣም ያሳሰበኝ ነገር የአቶ አንዷለም አራጌ ምክትል መሪ ሆኖ መመረጥ ነው።
በፖለቲካ ባህላችን ውስጥ መከባበር ቀርቷል። የፖለቲካ ልሂቃኖች ከትችት ይልቅ መዘላለፍ፣ ከትብብር ይልቅ መጠላለፍ የበዛበት ነው። በእንዲህ ያለ ፖለቲካ ውስጥ የፓርቲ አመራር መሆን የጭቃ ማጥ ውስጥ እንደ መግባት ነው። የፓርቲ መሪ ሆኖ የማይሰደብ፣ የማይዘለፍ፣ የማይወረፍ፣ የማይንቋሸሽ የለም። የፖለቲካ ማጥ ውስጥ እስከከገባህ ድረስ ጭቃ መለጣጠፍ ያለና የነበረ ነው።
ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ለረጅም አመት የኖረበት ስለሆነ ይሄን የፖለቲካ ማጥ ለምዶታል። በእርግጥ አቶ አንዷለም አራጌም እንደ ፕ/ር ብርሃኑም ባይሆን የረጅም ግዜ ልምድ አለው። ሆኖም ግን በግሌ ለአንዷለም አራጌ በጣም እሳሳለታለሁ። አንዷለም በሀገራችን በተለምዶ ከምናውቃቸው የፖለቲካ መሪዎች ይልቅ የሃይማኖት መሪ ነው የሚመስለው። ከአንደበቱ ክፉ ቃል አይወጣም። አንዷለም በጣም ጨዋ ሰው ነው።
አንዷለም አራጌን በተደጋጋሚ አግኝቼዋለሁ። ከሁለት ሳምንት በፊት ስቱዲዮ መጥቶ በነፃ-ውይይት ፕሮግራም ላይ ቃለ-ምልልስ አድርገናል። ፖለቲካችንን በጥላቻና ዘረኝነት የጨቀየ ነው። ይህ ጭቃ እንደ እሾክ በሚዋጋ ስድብና ዘለፋ የተሞላ ነው። አንዷለም ደግሞ ለአክብሮትና አድናቆት እንጂ ለስድብና ዘለፋ የሚመች አይደለም። ትችትና ዘለፋ ቀርቶ ለጥያቄ እንኳን የሚያሳሳ ነው።
እንዲህ ያለ ስብዕና ያለው ሰው የኢዜማ ፓርቲ መሪ ሆኖ ተመርጧል። አንዷለም የፓርቲው ምክትል መሪ ሆኖ በመመረጡ ደስ ብሎኛል። ግን ደግሞ እንደ እሱ ያለ ጨዋ አንደበት እና ቅን ልቦና ያለው ሰው በጥላቻና ቂም ከጨቀየ ፖለቲካችን ውስጥ በመግባቱ አዝኛለሁ። እጅግ በጣም የማከብረው ሰው በስድብና ጥላቻ በተካኑ ግልብ ብሔርተኞች ከወዲሁ ሲሰደብና ሲዘለፍ እያሰብኩ መሳቀቅ ጀምሬያለሁ። ስለዚህ የአንዷለም መመረጥ ለእኔ ሰቆቃ ነው።
ወዳጄ ሆይ… አዲስ የተመሰረተው ኢዜማ ፓርቲ ምክትል መሪ መሆንህን ስሰማ በደስታዬ ልክ ተሳቅቄያለሁ። የፓርቲ መሪ ሆነሃልና እንደ ወትሮዬ በይፋ አንተን ከማድነቅ እቆጠባለሁ። ነገር ግን መነኩሴ የሚያስገርም ቅን ልቦና አለህ። የሚያስደምም ሰብዕና ሰጥቶሃል። ግን ደግሞ ፖለቲካችን ጨቅቷልና ከአሁን በኋላ ከስድብና ዘለፋ የተገመደ የጭቃ ጅራፍ ያርፍብሃል። ስለዚህ ይህን የምትቋቋምበት ወፍራም… በጣም ወፍራም ቆዳ ይሰጥህ ዘንድ እመኝልሃለሁ። ስቃይና መከራውን ችለህ ለሀገርና ህዝብ ቀና የሆነ ነገር ታደርግ ዘንድ የምመኝልህ ይሄን በዘረኝነትና ጥላቻ የጨቀየውን የመዘላለፍና የመጠላለፍ ፖለቲካ ለመቋቋም የሚያስችል ወፍራም ቆዳ እንዲሰጥህ ነው!! ይኼው ነው!!!!
Filed in: Amharic