>

"ፌደራሊዝሙን ለማፍረስ መሞከር ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው!!!" (አቶ ሌንጮ ለታ)

ፌደራሊዝሙን ለማፍረስ መሞከር ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው!!!”

 

የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ

የዴሞክራሲ ግንባታን ከመንግስት ብቻ መጠበቅ ብዙ እንደማያስኬድ የሚናገሩት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሰፊና የረጅም ጊዜ ተሳትፎ ያላቸው አቶ ሌንጮ ለታ ናቸው። አቶ ሌንጮ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባርን በአመራርነት ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ ለ21 ዓመታት መርተዋል።

በምዕራብ ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ዶምቢዶሎ የተወለዱት አቶ ሌንጮ ድርጅታቸውን ወክለው ብዙ ድርድሮችን አድርገዋል። የሽግግር መንግስት በነበረበት ወቅት የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር ቡድንን በመምራት ከኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ጋር ያደረጉት ውይይት ባለመሳካቱ ብዙ ዘመናቸውን በውጭ እየተቃወሙ አሳልፈዋል።

አሁንም ከፖለቲካው ዓለም አልራቁም፤ የኦሮሞዴሞክራቲክ ግንባርን በማቋቋም የፓርቲው ሊቀመንበርሆነው የድርሻቸውን በመወጣት ላይ ናቸው። አሁን ያለውመንግስት ዴሞክራሲን የማስፈን ፍላጎት እንዳለውናሰዎች ግን ከመንግስት ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ የራሳቸውንሚና መወጣት እንዳለባቸው በመጠቆም ያለ ሁሉምተሳትፎ ዴሞክራሲን ማምጣት አዳጋች ነው ይላሉ።ከኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታጋር የነበረንን ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን፦ ለእርሶ አሁን ኢትዮጵያ በምን ሁኔታ ላይናት?

አቶ ሌንጮ፡– ለእኔ አሁን ኢትዮጵያ በጣም አስቸጋሪ በሆነ ለውጥ ውስጥ ናት የሚል እምነት አለኝ። ከዚህ በፊት ይህን የመሰለ ለውጥ መጥቶ አያውቅም። ይህን የምልበት ምክንያት ለውጡን እየመራ ያለው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ነው። ኢህአዴግ ራሱ ተለውጧል ወይስ አልተለወጠም የሚለው ያጠያይቃል? ኢህአዴግ በትክክል ስለመለወጡ አለመታወቁ ደግሞ በራሱ ችግር ነው።

እኔ እንደሚታየኝ በኢህአዴግ ውስጥ ለለውጥ ትግል እየተካሄደ ነው። የለውጡ ፈላጊዎች እና የለውጡ ተቃዋሚዎች አሉ። እነዚህ ደግሞ በአንዳቸው ውስጥ ብቻ ሳይሆን በኢህአዴግ አራቱም ድርጅቶች ውስጥ እንዳሉ እገምታለሁ። ይህ ቀላል አይደለም በጣም አስቸጋሪ ጉዳይ ነው።

ሁለተኛው የህዝብ ችግር ነው። ህዝቡ ለውጥ ሲባል የለመደው እና የሚጠብቀው የተለመደ ነገር አለ። አንድ ሃይል መጥቶ የነበርን ገርስሶ አብዛኞችን ያስራል ወይም ይገላል፤ እስከ አሁን በዚህ ለውጥ ውስጥ ይህ እየተጠበቀ ነው። ነገር ግን የተለመደው አልተከሰተም። ይህ መንግስት ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደራዊ ሥርዓት መግባት ይፈልጋል።

ስለዚህ በሥርዓት እና በህግ ብቻ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የሚፈልግ ይመስለኛል። በመሆኑም የተወሰኑ የህግ ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ ለማቅረብ እየሞከረ ነው። እዚህ አገር ደግሞ በታሪክ እንደሚታወቀው መንግስት ማለት የሚያስር የሚገድል የሚያሰቃይ ነው። ህዝቡ የለመደው ይህን ስለሆነ መንግስት አለ ወይስ የለም ወደሚል ጥያቄ እያመራ ነው። ከዚህ አንፃር ‹‹ለውጥ አለ›› የሚለው ጉዳይ የኢትዮጵያን ህዝብ አደናግሮታል።

አዲስ ዘመን፡– አሁን በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው ግጭትመንስኤው ከዚህ ጋር ይገናኛል?

አቶ ሌንጮ፡- በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው ግጭት ሁለት ዓይነት ነው። አንደኛው ሆን ተብሎ የሚካሄድ ግጭት እና የእውነት ሰዎች ከሰዎች ጋር ግጭት ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ ነው። የመጀመሪያው የለውጡ ተቃዋሚዎች የሚሸርቡት ሴራ አለ። ለ27 ዓመት ይህን አገር በበላይነት ሲቆጣጠር የነበረ ሃይል ተቃውሞ ወደ እርሱ እንዳይመጣ በህዝብ ግጭት ይጠቀም ነበር። ይህ ቀጥሏል።

በተጨማሪ የፌዴራሊዝሙ አያያዝ ብዙ ችግር የነበረበት ነው። አከላለሉም ስህተት የነበረበት በመሆኑ ብዙ ግጭቶች ተከስተዋል። በዛ ምክንያት ተቀብሮ የነበረ ስሜት ይፋ መውጣት ሲጀምር ሰዎች ግጭት እያጋጠማቸው ነው። ነገር ግን ይህ በሁለቱም ምክንያቶች እየተከሰተ ያለው ግጭት ሊያስገርመን አይችልም።

አዲስ ዘመን፡– ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው?

አቶ ሌንጮ፡– ዋነኛው መፍትሔው መመካከር ነው። መመካከር በተለይ በኢህአዴግ ውስጥ እጅግ ወሳኝ ነው። ይህን አገር ለ27 ዓመታት የመራው ኢህአዴግ ነው። በመራባቸው ዓመታት ደግሞ ሌላ ፓርቲ እንዲቀጭጭ እና እንዳይኖር በማድረግ ብቻውን ተቆጣጥሮ ሲገዛ ነው የኖረው። ኢህአዴጎች መንግስትን ሲያዋቅሩ ከኢህአዴግ ውጪ ማንም እንዳይገዛ አድርገው ማዋቀራቸው ትልቅ ችግር ነው። ስለዚህ መፍትሄው ሊመጣ የሚችለው ከኢህአዴግ ውስጥ ነው።

በእርግጥ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚና የላቸውም ማለት አይደለም። እነርሱም በሃላፊነት ቢንቀሳቀሱ ይሻላል። በተጨማሪ መገናኛ ብዙሃንም በሃላፊነት ስሜት መስራት አለባቸው። በዋነኛነት ህዝብን ለማረጋጋት መስራት አለባቸው። በተለይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመጣው የሃሜት እና የጥላቻን መርዝ የሚነሰንሰው ማህበራዊ ድረገፁ አደብ መያዝ አለበት። ይህ ችግር እንዴት ይገታል? የሚለው ትኩረት ማግኘት ይኖርበታል።

አዲስ ዘመን፡– ማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚፃፈውንየጥላቻ ሃሳብ ማስወገድ ይቻላል?

አቶ ሌንጮ፡- ማህበራዊ ድረገፁን የሚጠቀሙ እና ትክክል አለመሆኑን የሚያምኑ ሰዎች የጥላቻ መርዝ የመርጨት ተግባሩን ልክ እንዳልሆነ በዛው በማህበራዊ ድረገፁ ማሳወቅ አለባቸው። ሌላው መገናኛ ብዙሃን ደግሞ የተፃፈ ነገር ሁሉ እውነት እንዳልሆነ ህብረተሰቡ እንዲረዳ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ነገር ግን ለማስቆም በሚል ማገድ ደግሞ ተገቢ አይደለም የሚል እምነት አለኝ።

አንድን ሚዲያ ማገድ ከተጀመረ ወደ ሌላው ይዛመታል ያ ደግሞ ትክክል አይመጣም። በዚህ በኩል ስልጣን ላይ ያለው መንግስት አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ይመስለኛል። ዝም ብሎ እንዳይለቀው እየተሰራጨ ያለው የውሸት ፕሮፖጋንዳ ህዝብ ለህዝብ እስከ ማጋጨት ሊያደርስ ይችላል። ማገዱም ደግሞ ጥሩ አይሆንም። ይህ ሊገታ የሚችለው ሁላችንም የዜግነት ሃላፊነታችንን መወጣት ስንችል እና ህብረተሰቡን ስናስተምር ነው።

አዲስ ዘመን፡– በመንግስት በኩል ሰላም እንዲሰፍን እናመረጋጋት እንዲኖር መወሰድ ያለበት እርምጃ ብለውበዋናነት የሚጠብቁት ምንድን ነው?

አቶ ሌንጮ፡– መጀመሪያ ሰላምን ማረጋገጥ የመንግስት ሃላፊነት ነው። ጥፋት ሲፈፀም መንግስት ዝም ብሎ ማየት የለበትም። በአንድ በኩል የእርቅ ኮሚሽን አለ። የእርቅ ኮሚሽኑ ቶሎ ተንቀሳቅሶ የተጋጩትን ቡድኖች በምን መልኩ እናስታርቃለን የሚለውን ለይቶ ሥራ ላይ ማዋል አለበት። ይህንን ይፋ ማድረግ ለአገር መረጋጋት ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ።

አዲስ ዘመን፡– አለመረጋጋቱን ከስራ አጥነት አንፃር ማየትአይቻልም?

አቶ ሌንጮ፡- ስራ አጥነት ለዘመናት ሲጠራቀም የቆየ ጉዳይ ነው። ባለፉት ዓመታት በተለይ ትኩረት ያላገኘው የህዝብ ቁጥር መጨመር እጅግ አስጊ ሁኔታን ፈጥሯል። ባለፉት መሪዎች ሲነሳ የነበረው ‹‹ሴቶች ሲማሩ የሚወልዱበት ዕድሜ ይቆያል። የልጅ መጠን ይቀንሳል›› የሚል ነበር።

ይህ ትክክል ነው። ነገር ግን በቂ አልነበረም። አንድ አይነት ዘመቻ ተደርጎ፤ ህብረተሰቡ በሙሉ ተስማምቶ ወንዱንም ሴቷንም በዘመቻ የሚወልዱት መጠን እንዲቀንስ ማድረግ እና መቆጣጠር ጊዜ ሊሰጠው ለነገ ሊባል የሚገባ አይደለም። አሁን ያለው ሁኔታ ግን ወደ ፊትም ኢትዮጵያን የሚያሰጋ ነው።

አሁን ያለውን ሥራ አጥነት በተለመደው መልኩ ሥራ በመስጠት መቆጣጠር የሚቻል አይመስለኝም። ሥራ ፈላጊው በጣም ከፍተኛ ነው። በእኛ ጊዜ የነበሩት ዩኒቨርሲቲዎች ጥቂት ናቸው። ዩኒቨርሲቲ የሚገባው ሰው መጠን ቢበዛ ሁለት ሺ ነው። አሁን ግን ከአንድ ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ ተመርቆ የሚወጣው ሰው ቁጥር ብዙ ነው። ለዛ ሁሉ ስራ መስጠት አይቻልም። ሌላው ደግሞ ጦርነት የለም።

ድሮ በተለይ በመንግስቱ ጊዜ ጦርነት ነበር። ወጣቶች በጦርነት መሞታቸው የሰውን ቁጥር ይቆጣጠር ነበር። አሁን ጦርነት የለም። ስለዚህ አሁን ያለውን ሥራ አጥ በዘመቻ መልክ ሥራ ማስያዝ የግድ ነው። ለምሳሌ ጥናት ተጠንቶ ወጣቶች ተደራጅተው በረሃማነትን ለመቋቋም ዛፍ ተከላ ላይ እየተሰማሩ ገንዘብ እንዲያገኙ ማስቻል ያስፈልጋል።

አሁን ያለው ወጣት ነቅቷል። ተንቀሳቅሶ መንግስት መቀየር እንደሚችል ተረድቷል። ማፍረስም እንደሚችል ገብቶታል። ስለዚህ ይህን ትኩስ ሃይል ወደ ገንቢ ድርጊት ካላሰማራነው ያው ጥያቄ እንደሚቀጥል እርግጠኛ ነኝ። ከመንግስት ብቻ አይደለም ሁላችንም መተባበር ይጠበቅብናል። ሁላችንም ተባብረን ከላይ እስከታች ተስማምተን መፍትሄ መፈለግ ይገባናል የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡– እርሶ እና ፓርቲያችሁ ስለቀጣዩ ምርጫምን ትላላችሁ?

አቶ ሌንጮ፡– እኔ ምርጫ አልሳተፍም፤ ዘመኔ አልቋል። የኔ ዕድል ያለፈው ውጪ እያለሁ ነው። አሁን የምለው ለመመረጥ የሚወዳደሩትን ፈጣሪ ይርዳችሁ ብቻ ነው።

አዲስ ዘመን፡– እርሶ ብቻ ሳይሆኑ ፓርቲዎስ ስለምርጫው ምን ይላል?

አቶ ሌንጮ፡– እኛ ኦዲፒ ካሸነፈ አሸናፊ ነን። ኦዲፒ ላይ የሚደርሰው እኛም ላይ ይደርሳል ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡– ምርጫው መካሄድ አለበት ይላሉ?

አቶ ሌንጮ፡– ጊዜው ምርጫውን ለማካሄድ አመቺ አይደለም የሚል ግምት አለኝ። ነገር ግን ምርጫውን ማራዘምም አደገኛ ነው። ይህ አጣብቂኝ ነው። ለዚህም መፍትሄ ለመፈለግ ከመንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም የፖለቲካ ድርጅት ነኝ የሚል ሃሳቡን አቅርቦ በዛ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ የሚፈጠር ይመስለኛል።

አዲስ ዘመን፡– መንግስት ከእነዚህ ሁሉ አጣብቂኞች ለመውጣት ምን ማድረግ አለበት።

አቶ ሌንጮ፡– እኛ አንድ ነገር ለምደናል። ለሁሉም ነገር መንግስትን መጠበቅ ይስተዋላል። ነገር ግን ይህ ለዴሞክራሲ ግንባታ አይበጅም። በዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ ማንኛውም ዜጋ ሃላፊነት አለበት። መብት እና ግዴታ አብረው እንደሚስተናገዱ ሁሉ፤ በዴሞክራሲ ተጠቃሚ ለመሆን ዴሞክራሲን ለማስፈን ሚናችንን የመወጣት ግዴታ አለብን።

ስለዚህ ከአጣብቂኞቹ ለመውጣት ከመንግስት ባሻገር ሁሉም ሃላፊነቱን መወጣት አለበት። ቢያንስ ግጭት ውስጥ አለመግባት። ግጭት ውስጥ የሚያስገቡትን ቀስቃሾች ማጋለጥ ይገባል። ይህን በዜግነት ደረጃ ካልሰራነው እና መንግስት ሃይል እስኪያሰማራ ከጠበቅን አሁን ያለው የዴሞክራሲ ሽግግር ተስፋ አይኖረውም።

አዲስ ዘመን፡– አሁን ያለው የኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሁኔታበብሔር ፖለቲካ ሳቢያ መሆኑ ይገለፃል፤ ይህንንስ ማስቆምይቻላል?

አቶ ሌንጮ፡- የብሔር ፌዴራሊዝምን ለማፍረስ መሞከር ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው። ይህን መገንዘብ ያስፈልጋል። የብሔር የማንነት ችግር አንዴ ከወጣ በኋላ መልሶ መወተፍ ብዙ ደም መፋሰስን ያስከትላል። ስለዚህ እንዴት አድርገን እናስተዳድረው የሚለው ላይ ማተኮሩ ይሻላል። በዚህ ላይ አንድ መሟላት ያለበት እና ድንገት ሊያቀዘቅዘው የሚችለው፤ ላለፉት 27 ዓመታት የእውነት ያልነበር ለይስሙላ የተሰጠው ራስን የማስተዳደር ጉዳይ በትክክል ቢተገበር ምናልባት ሁሉም ሃላፊነቱን ወስዶ የሚሰራ ይሆናል።

በእውነት በህዝቡ የተመረጡ የሚያስተዳድሩ ሰዎች ሲኖሩ ለህዝባቸው ጥቅም ሲሉ ከሌሎች ጋር አብሮ የመኖርን ሃላፊነት ይገነዘቡታል። ስለዚህ ወደ ኋላ ከመመለስ ይልቅ ወደ ፊት በመግፋት ራስን የማስተዳደር ሁኔታ እውን የሚሆንበት ሁኔታ ላይ መስራት ነው።

ኦሮሞን በኦሮሞ ህዝብ የተመረጠ ሰው የእውነት በትክክል እንዲያስተዳድረው ቢደረግ በኦሮሚያ የተመረጠው ሰው ብሔሩ ከሌሎች ብሔሮች ጋር እንዳይጋጩ ያደርግ ይሆናል። ከዚህ ጎን በተለያዩ ደረጃዎች የህዝብ ወኪሎች ቢገናኙ፣ ቢተዋወቁ እና ቢወያዩ ችግሩ ሊረግብ ይችላል የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡– ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

አቶ ሌንጮ፡– እሺ እኔም አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2011

Filed in: Amharic