>
5:14 pm - Friday April 20, 8170

ወርሀ ግንቦትና አይረሴ ታሪካዊ ክስተቶቿ!!!  (አንተነህ ቸሬ)

ወርሀ ግንቦትና አይረሴ ታሪካዊ ክስተቶቿ!!! 

አንተነህ ቸሬ

በአጋጣሚም ይሁን ታስቦበት … ግንቦት በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ወር ነው። ኢትዮጵያ በግንቦት ወር ታዋቂ ልጆቿን ወልዳለች፤ ወደማይቀረው ዓለምም ሸኝታለች፤ መሪዎቿን ወደ ስልጣን አምጥታለች፤ ከስልጣናቸው ሽራለች፤ አስከፊ ጦርነቶችን አስተናግዳለች፤ ከእነዚህ ታሪካዊ ክስተቶች በተጨማሪ ግንቦት ያልተለመዱ ክስተቶች የተስተናገዱበት ወርም ነው።

ታዲያ የ2011ን ግንቦት ልንቀበለው ሰዓታት ብቻ ቀርተውናልና ለዛሬ ኢትዮጵያ በግንቦት ወር ካስተናገደቻቸው ታሪካዊ ክስተቶች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ በአጭሩ ለመቃኘት እንሞክር። የመረጃው ምንጮች ልዩ ልዩ የታሪክ ጽሑፎች ናቸው። ግንቦት የልደት ወር ነው። ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 2004 ዓ.ም መገባደጃ ድረስ በመጀመሪያ በፕሬዚዳንትነት፣ በመቀጠልም በጠቅላይ ሚኒስትርነት ኢትዮጵያን የመሩት አቶ መለስ ዜናዊ የተወለዱት በግንቦት ወር ነው።

የገናናው የሸዋ ንጉሥ የንጉሥ ሳህለሥላሴ የልጅ ልጅ፣ የታላቁ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ የአክስት ልጅ እንዲሁም የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አባት የሆኑት ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል የተወለዱትም በግንቦት የመጀመሪያው ቀን በ1844 ዓ.ም ነበር። ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል የሐረርጌን ግዛት በማቅናትና በሚገባ በማስተዳደር ለንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ) ሀገር የማቅናት ተግባር ብርቱ አጋዥ የሆኑ ሰው ነበሩ። የውጫሌ ውል ያስከተለው የትርጉም ለውጥ መፍትሔው ጦርነት ሲሆንም ልዑል ራስ መኮንን ሠራዊታቸውን ይዘው ከአምባላጌ እስከ እስከ አድዋ በተደረጉት ውጊያዎች ላይ በመሳተፍ ጀግንነታቸውን አስመስክረዋል።

በግንቦት ወር መፈንቅለ መንግሥት የተሞከረባቸውና በግንቦት ወር አገር ጥለው የሸሹት የደርግ ሊቀመንበር ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምም የተወለዱት በግንቦት ወር ነው። ግንቦት የዕረፍት/ሞት ወርም ነው። በቀዶ ጥገና ህክምና ዘርፍ የመጀመሪያው ኢትየጵያዊ ሐኪም የሆኑት ፕሮፌሰር ዓስራት ወልደዬስ ያረፉት በግንቦት ወር 1991 ዓ.ም ነው። በታዋቂ የውጭ አገራት የሕክምና ሳይንስ ትምህርት ቤቶች የተማሩት ፕሮፌሰር ዓስራት ‹‹የጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት ስልጣንን አልፈልግም፤ የተማርኩት ሐኪም ሆኜ አገሬን ላገለግል ነው›› በማለት ወገናቸውን አገልግለዋል።

ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የህክምና ማሰልጠኛ እንዲከፈት በተደጋጋሚ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ምክንያት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሕክምና ትምህርት ቤትን እውን አደረጉ። የሕክምና ትምህርት ቤቱ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዲን ሆኑ። የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲቋቋምም የቴክኒክ ኮሚቴውን የመሩት እርሳቸው ነበሩ። ፕሮፌሰር ዶክተር ዓስራት በህክምናው ዘርፍም ‹‹አስራት የተባለ ጸበል ፈልቋል›› እስከመባል የደረሰ አንቱታን ያተረፉ ብቁ ሐኪም ነበሩ።

ፕሮፌሰር ዓስራት በመንግሥታት የሥራ ኃላፊዎች ይደርስባቸው የነበረውን ከፍተኛ ጫና ተቋቁመው ሐገራቸውን ሳይለቁ ህዝባቸውን ሲያገለግሉ የቆዩ አንጋፋ ባለሙያ ናቸው። ገናናውና መናኙ የታላቋ አክሱም ንጉሥ አፄ ካሌብ ያረፉት በግንቦት ወር በ20ኛው ቀን ነበር። አፄ ካሌብ ከአክሱምና አካባቢው አልፈው ቀይ ባሕርን ተሻግረው ከአይሁዳዊው ንጉሥ ፊንሐስ ጋር ያደረጉትን ጦርነት በድል አጠናቅቀው የደቡብ አረቢያ ሕዝቦችን ያስገበሩ ታላቅ ንጉሥ ነበሩ። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ስማቸው በጉልህ ከሚጠቀሱት እንስቶች መካከል አንዷ የሆኑት እቴጌ ምንትዋብ ያረፉትም በግንቦት ወር ነው።

የአፄ በካፋ ባለቤት የነበሩት እቴጌ ምንትዋብ፣ ጎንደር የኢትዮጵያ ነገሥታት ማዕከል በነበረችበት ወቅት የነበራቸው ተፅዕኖ ከፍ ያለ እንደነበር ታሪክ ያሳያል። ባለቤታቸው አፄ በካፋ ከሞቱ በኋላ በተከታታይ በነገሡት በልጃቸው ዳግማዊ አፄ ኢያሱ እንዲሁም በአፄ ኢዮአስ ዘመነ መንግሥታት ትልቅ ሚና ነበራቸው። ከፖለቲካ ተሳትፏቸው በተጨማሪም ዛሬ ድረስ በበርካታ ጎብኚዎች የሚጎበኙ አብያተ ክርስቲያናትን አሳንፀዋል። ከዚሁ ከመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ሳንወጣ አፄ ሠይፈአርዕድ እና አፄ እስክንድር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በግንቦት ወር ነው።

የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ባለቤት እቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ ያረፉትም በግንቦት ወር 1860 ዓ.ም ነው። እቴጌዋ ያረፉትም ከባለቤታቸው ሞት በኋላ ከልጃቸው ከልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ጋር ወደ እንግሊዝ ሲሄዱ ነው። አንጋፋውና ዝነኛው ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ይቺን ዓለም በሞት የተለያት ግንቦት 29 ቀን 1984 ዓ.ም ነው። የጳውሎስ ኞኞ ስም ሲነሳ ወደአብዛኛው ሰው ዓዕምሮ የሚመጣው በቀለም ትምህርት ብዙም ሳይገፋ በድፍን ኢትዮጵያ ዝነኛና ተወዳጅ ለመሆን ያበቃው የጋዜጠኝነት ሥራው ነው። ጳውሎስ በተፈጥሮ የታደለው የማንበብ፣ የመጠየቅና የመመራመር ተሰጥኦ በጋዜጠኝነት ሙያው አንቱታን አትርፎለታል።

በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲሁም በኢትዮጵያ ራዲዮ ሲሠራ ‹‹ጋዜጠኝነትስ እንደጳውሎስ!›› የተባለለት ይህ ሰው፣ በርካታ መፅሐፍትንና ትያትሮችንም ለአንባቢያን አበርክቷል። ጳውሎስ የፕሬስ ነፃነት እንዲከበር በተባ ብዕሩ ሞግቷል። ጳውሎስ ጋዜጠኛ ብቻ አይደለም፤ ብዙ የሙያ ዓይነቶችን ከባለሙያዎቹ ባላነሰ መልኩ ይከውን ነበር ይባላል።

ባለውለታችንና ‹‹የፊደል ገበታ አባት›› ቀኛዝማች ተሥፋ ገብረሥላሴ ግንቦት 26 ቀን 1992 ዓ.ም የዚህ ዓለም የመጨረሻ ቀናቸው ነበረች። ግንቦት የንግሥናና የሹመት ወር ነው። ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ወራሻቸው የልጅ ልጃቸው ልጅ ኢያሱ ሚካኤል መሆኑን በአዋጅ ያሳወቁት ግንቦት በገባ በ10ኛው ቀን በ1901 ዓ.ም ነው። የልጅ ኢያሱ አባት ራስ ሚካኤል አሊ ደግሞ ‹‹ንጉሠ ወሎ ወትግራይ›› ተብለው የነገሡት በግንቦት ወር መገባደጃ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ) አዲስ አበባን የተቆጣጠረውና ስልጣን የያዘውም በግንቦት ወር በ20ኛው ቀን በ1983 ዓ.ም ነው። ግንቦት የሽረት ወርም ነው። ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም አገር ጥለው የሄዱትና ደርግ የወደቀውም በግንቦት ነው። ግንቦት ለብዙ የጎንደር ነገሥታት የስልጣናቸው ማብቂያ እንደነበርም በታሪክ ተመዝግቧል። ደም አፋሳሽ ጦርነቶች የታዩበት ግንቦት፣ የንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ) እና የንጉሥ ተክለሃይማኖት ጦር እምባቦ ላይ በግንቦት የመጨረሻው ቀን ከባድ ውጊያ አደርጓል።

የደጋማው ክርስቲያን ነገሥታት እና የግራኝ አሕመድ ጦርነቶች የከፉት በግንቦት ወር ነበር። የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ዘርፎ መነኮሳቱን በግፍ የጨፈጨፈውም በዚሁ በግንቦት ወር ነው። ግንቦት 25 ቀን 1788 ዓ.ም አመድ ከሰማይ መዝነቡም ግንቦት ያልተለመዱ ክስተቶች የተስተናገዱበት ወር ለመሆኑ ማሳያ ነው። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት) እና የአንጋፋው ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ምስረታ የተከናወነው በግንቦት ወር ነው። እሥራኤል ቤተ-እሥራኤላውያንን ከኢትዮጵያ ወደ እሥራኤል ለመውሰድ ‹‹ዘመቻ ሰለሞን (Operation Solomon)››ን ያካሄደችውም በዚሁ በግንቦት ወር ነው።

በዘመቻ ሰለሞን 14ሺ325 ቤተ-እሥራኤላውያን በ36 ሰዓታት ውስጥ፣ በ35 አውሮፕላኖች ከኢትዮጵያ ወደ እሥራኤል ተወስደዋል። ፎቶ ግራፍና ኢትዮጵያ/ኢትዮጵያውያንም የተዋወቁት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ግንቦት 13 ቀን 1875 ዓ.ም በተነሱት የመጀመሪያ ፎቷቸው ነው። በአጭሩ ግንቦት እና ኢትዮጵያ የቀን ምልኪያ አላቸው የሚያስብል ትስስር አላቸው።

Filed in: Amharic