>

የሀኪም ጥያቄ ቅንጦት ነው? (ዮሴፍ ወርቅ ነህ)

photo.php የሀኪም ጥያቄ ቅንጦት ነው?

ዮሴፍ ወርቅ ነህ

ትሰማኛለህ ሲኞር!

ሀኪም ለምን ከፍተኛ ክፍያ ሊከፈለው እንደሚገባ ታውቃለህ? ሰምተህ የማታውቀውን አስመራሪ የህክምና ህይወት ላስቃኝህ።

1) ማንም ሳይመርጥ ሀኪም የሆነ የለም!! እደግመዋለሁ! የትኛውም የአለማችን ክፍል ላይ የሚኖር ሀኪም ለሀኪምነት የታጨው በምርጫው ብቻ ነው። ውጤት አስገድዶት ሀኪም የሆነ የለም። ህክምናን ፈልገህ፣ ጥረህ ለፍተህ ግረህ ታገኘዋልህ እንጂ ፈልጎ አያገኝህም!! ህክምና ውስጥ የገባ ሰው የግድ ከፍተኛ ውጤት መያዝ ግድ ብሎታል። ይህ ሰው ሀኪም ባይሆን ኖሮ የትኛውንም ሞያ መርጦ… በየትኛውም ሞያ ሰቃይ ሆኖ የመጨረስ አቅም ነበረው። ህክምና ውስጥ የተሰገሰገው ጭንቅላት ለሰው ነፍስ ሲባል እየተኮረኮመ ወደግራም ወደቀኝም ሳያይ አመታቱን ያጠናቅቃል!! ስለዚህ ሀኪም ለሰዋው እድሉ ሲባል ከየትኛውም ሞያ የተሻለ ክፍያ ይገባዋል።

2) ከማንኛውም የትምህርት አይነት በተለየ ህክምና ለ7 አመታት የቀረበ ጊዜን በትምህርት ይጨርሳል። የሚገርምህ ነገር ሀኪም ክረምት፣ በጋ፣ ቀን፣ ለሊት ሳይል በአመት 365 ቀን፣ በሳምንት 7 ቀን፣ በቀን 24 ሰአት ይማራል። ይሰራል። የአመት ኮርሶቹ ሲያልቁ ሳምንት ወይ ሁለት ሳምንት ብቻ አርፎ ወደትምህርቱ ይመለሳል። ሌሊቱን ሙሉ ላይብረሪ ተቀምጦ ሳይነጋበት ሜዲስንን ያጠናቀቀ ተማሪ ካሳየኸኝ መሬት ላይ የሚኖር አሳ ፈልጌ ላሳይህ ፈቃደኛ ነኝ። በየጊዜው ለሚፈተናቸው ፈተናዎች በሳምንት እስከ ሁለት ሺ ገፅ ሀንዳውት ማንበብ ግድ ይለዋል። የመፅሀፉን ጉዳይ በገፅ ከምነግርህ በኪሎ ብንወያይበት ይሻላል። አመቱን ሙሉ የለፋ የህክምና ተማሪ የመጨረሻ እጣፈንታው የቃል ፈታኙ እጅ ላይ ይወድቃል። በ15 ደቂቃ ምዘና ቀጣዩን አመት ልትቀጥል አልያም እስከወዲያኛው ከህክምናው አለም ልትሰናበት የፍርድ ቀንህን ትጠባበቃለህ። ከእውቀትህም ባሻገር አይነውሃህ ለፈታኝህ አምሮ ሊታይ ግድ ይልሃል። ይሄ ክስተት በየሶስት ወሩ እየተደጋገመ ያጋጥምሃል። ነገውን ተስፋ እድርጎ በዚህ ሁኔታ የተማረን ሀኪም ደሞዝ አይገባህም ስትለው ምን ሊሰማው እንደሚችል ገምት።

3) የህክምና ትምህርቱን ጨርሶ ኢንተርን የሆነ ሀኪም እስከዛሬ ካየው ፍዳ የከፋ ነገር ይገጥመዋል። በሳምንት ሁለት ወይ ሶስቴ 36 ሰአታትን ያለእረፍት ይሰራል። ቅዳሜ፣ እሁድ፣ አመትበአል የሚባል ነገር የለም። ለደቂቃ ካንቀላፋ አንድ ክሪቲካል ፔሸንቱን ህይወት ሊያጣ ይችላል። ምሳና እራቱን እንኳ ሰአታት አሳልፎ በሩጫ በልቶ በሩጫ ይመለሳል። ከሀኪምነት ባሻገር የነርሱንም፣ የተሸካሚውንም፣ የአስታማሚውንም ስራ ደርቦ ይሰራል። በዚህ ሁሉ መሀል አንብቦ ለጠዋት ሞርኒንግና ራውንድ መፈጣፈጥ ይጠበቅበታል። ስለእያንዳንዱ ፔሸንት እየተነሳ ልቡ ከፍ ዝቅ እስኪል በጥያቄ ይፋጠጣል። አቋሙ ታይቶ 3 ወርም ስድስት ወርም አመትም ያለክፍያ እንዲያገለግል ቅጣት ሊጣልበት ይችላል። ይሄንን ኢንተርን ደሞዝህ በዝቶብሃል ለማለት ድፍረት ካለህ ተናገረው።

4) ሀኪም ከሆንክ… በስራው ምክኒያት ለኤች አይ ቪ የተጋለጠ ሀኪም በርግጠኝነት ታውቃለህ። ከፔሸንቱ መድሃኒት የለመደ ቲቢ ተላልፎበት አመት ከስድስት ወር ተኝቶ የታከመ ሀኪም ያጋጥምሃል። በንክኪ የሚተላለፉ እንደ ሄፓታይቲስ ያሉ የእድሜ ልክ በሽታዎች በጓንት እጥረት ምክኒያት ብቻ ቤተሰብህ ይሆናሉ። ታካሚውን ለማዳን ሲል ህይወቱን ያጣ ሀኪም ቤቱ ይቁጠረው። ይሄንን ሁሉ ሪስክ ለተቀበለ ሀኪም ደሞዙ ስንት ሊሆን ይገባዋል?

5) የህክምና ትምህርት በ7 አመት ዲግሪ አያበቃም። ካላነበብክ አደጋ ውስጥ ነህ። ያለምርጫህ የሆነ የገጠር ጫፍ ላይ ሄደህ ከ3 እስከ 5 አመት ህዝብህን በአነስተኛ ክፍያ አገልግለህ ድጋሚ ለሌላ የሬዚደንሲ ትምህርት ወደመጣህበት ተቋም ትመለሳታለህ። ትሰራለህ! ታክማለህ! ትማራለህ! እንደአዲስ እየተብጠለጠልክ፣ አመትህን እየጨመርክ ከ3— እስከ 5 አመት ትምህርትህን ታጠናቅቃለህ። እድሜውን በሙሉ እየተማረ ህዝቡን ሲያገለግል ለኖረ ሲኒየር ሀኪም 9,000 ብር በዝቶበታል ብለው ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ሲሳለቁ እንደማየት ምን የሚያም ነገር አለ?

6) ሀኪም ነህና ትምህርትህ አይቆምም። ሌላ ሰብ–ስፔሻሊቲ ፕሮግራም ለመማር አመታትትን ትጨምራለህ። እድሜህን ሙሉ ታነባለህ። እድሜህን ሙሉ ትማራለህ። ሴቶቻችን ልጅ የመውለጃ ጊዜያቸው እስኪያልፍ ድረስ ሲማሩ ማየት ምን ስሜት ይሰጣል? አንዲት እርጉዝ ሴት ሰርጅን ለ10 ተከታታይ ሰአታት ቆማ ያለእረፍት ኦፕሬሽን ስትሰራ ብታይ ምን ትላለህ? ለእነዚህ ልዩ ፍጡራን የሚገባቸውን ብትከፍላቸው ቅንጦት ነው?

7) ሀኪም ከሆንክ ቤትህ ከገባህ በኋላ ሚስትህን አቅፈህ ሙሉ ለሊት ለመጨረስ ምንም ዋስትና የለህም። ድንገተኛ ታካሚ ከመጣ በእኩለ ለሊት ተደውሎልህ ትጠራለህ። ቤተሰብህ እረፍት የለውም። ሁልጊዜ መናጋት አለ። ፍቺ አለ። ጭቅጭቅ ህይወትህ ነው። አሜሪካ ውስጥ በተደረገ ጥናት 28% ሀኪሞች የጭንቀት በሽታ (major depressive disorder) ተጠቂዎች ናቸው። ይሄ ቁጥር ገንዘብ በሌለው የሀገራችን ሀኪም ዘንድ ስንት ሊደርስ እንደሚችል መገመት አይከብድም። ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ሀኪም ራሱን ያጠፋል። የህክምና ትምህርት ቤት ገብተህ ከተማርክ ጤነኛ ልጅ ልከው ጨርቁን ጥሎ የሚሄድ የእዕምሮ ህመምተኛ ልጅ የተረከቡ ወላጆችን ትተዋወቃለህ። በርካታ ተማሪዎች ራሳቸውን ሲያጠፉ በአይንህ በብረቱ ትመለከታለህ። ከዚህ ሁሉ ተርፎ ለወጣ ሀኪም ደሞዙ ይበቃዋል እያልከኝ ነው?

8/ ሰላሳና አርባ አመት እድሜውን ትምህርት ላይ ጨርሶ ሰርጅን የሆነ ሀኪም እዛው ሆስፒታል ውስጥ በሸመተው በሽታ እጁ መንቀጥቀጥ ቢጀምር የሱና የቤተሰቡ ጉሮሮ እስከወዲያኛው እንደሚዘጋ ታውቃለህ? እድሜ ልኩን ሰው ሲያድን ኖሮ ወይ በእንቅልፍ ማጣት ምክኒያት የህክምና ስህተት ቢፈፅም ህይወቱን በሙሉ የገበረበት የህክምና ላይሰንሱ ተነጥቆ ወህኒ ሊወረወር እንደሚችል ታውቃለህ? ይህ ሀኪም ስራውን ቢያጣ ራሱንና ልጆቹን ለማኖር የሚያበቃ ገንዘብ ሊኖረው አይገባም?

ኢትዮጵያ ውስጥ ስለህክምና ያለው ግንዛቤ በጣም አናሳ ነው። ራሱ አብይ 10 ሺ የማትሞሉ ሀኪሞች ምንም የፖለቲካ ትኩሳት አትፈጥሩም ብሎ ትግሉን ሲያጣጥል ራሱን መጠየቅ የነበረበት ነገር ነበር። ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሀኪም ከዶ/ር ወርቅነህ ጀምራ ያስተማረቻቸው ሀኪሞች የት የት ሀገር ገብተው ነው 10 ሺ ሀኪም ብቻ ሀገሪቷ ውስጥ የቀረው?

በWHO ዳታ መሰረት አንድ ኢትዮጵያዊ ሀኪም በአመት የሚከፈለው ገንዘብ በአማካይ 4,660 ዶላር አካባቢ ነው። ይሄን ክፍያ ለ10,000 ሀኪም ብናባዛው ወደ 46 ሚሊዮን አካባቢ ይደርሳል። በወር 3.8 ሚሊዮን አካባቢ ማለት ነው። ይሄንን ገንዘብ ይዘህ ለአዲሱ ፕሮጀክት ቤተመንግስት ብትሄድ ከ20 ሰው በላይ ራት የመጋበዝ አቅም የለህም።

ስማኝማ ሲኞር… ዶ/ር አብይ ይህቺ ሀገር ደሃ ናት ገንዘብ የላትም እያለ ሲደልለን ለመስማት ዝግጁ ያልሆነው ደንቆሮዎች ስላልሆንን ነው። “ምንም አታውቅም እኔ ምልህን ዝም ብለህ ፃፍ” እያለ ቃል በቃል የዘለፈው ሀኪም ይህቺን ዳታ ሰርቶ የሚነገረውን እንቶፈንቶ ለመረዳት ጊዜ አይፈጅበትም። የኢትዮጵያ ሀኪሞች አንድላይ በወር የሚከፈላቸው ገንዘብ አንድ ባለስልጣን ውጪ አሳክሞ ለመመለስ ላይበቃ ሁላ ይችላል። ውጪ ቀለል ያለ ሰርጀሪ በስንት እንደሚሰራ ጉጉል አርግና ፍረደኝ።

አፍሪካ ውስጥ ዝቅተኛው የሀኪም ደሞዝ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። (ኧረ በዚህ የደሞዝ ደረጃ የሚቀራረባትም የለም) ትንሿ ሀገር ጅቡቲ እንኳ የኢትዮጵያን ሀኪም 11 እጥፍ ደሞዝ ለሀኪሞቿ ትከፍላለች። (ዳታውን ከታች አስቀምጬልሀለሁ) ይሄ ኢትዮጵያዊ ሀኪም ኑሮ ሲከብደው ሀገር ለቆ ተሰደደ ብለህ ትፈርድበታለህ? እስካሁን ባለን ዳታ የኢትዮጲያ ሀኪሞች የአሜሪካን የምዘና ፈተና (USMLE) ሲፈተኑ በከፍተኛ ውጤት አልፈው ወደስቴት እንደሚሄዱ መናገር ይቻላል።

አብይ እዛ አዳራሽ ውስጥ የሰራው ህዝቡን ይዞ ከሀኪሙ ጋር የማጠማመድ ስራ ነው። መች ንፅህናችሁን ትጠብቃላችሁ፣ ስራ ሰአት አታከብሩም አይነት ትችት ከመንደር አለሌ እንጂ ከአንድ ጠቅላይ ሚኒስቴር አይጠበቅም። የተባለው ነገር እውነት ቢሆን እንኳ የሚያስወቅሰው የቁጥጥር ስርአቱን የዘረጋው ራሱ መንግስትን ነው። የስራ ሰአትን አለማክበር ደግሞ የህክምና ብቻ ሳይሆን የየትኛውም የመንግስት መስሪያቤት ችግር ነው። 12 የልብ ቀዶ ህክምና ሰርጅኖች ብቻ ያላት ሀገር ላይ ለ10 አመት ህፃናትን በነፃ ስታገለግል የነበረችን የልብ ስፔሻሊስት እንደዛ አመናጭቆ መናገር ለሙሉ ህክምናው በነፍስ ወከፍ የታደለው ስድብ ነው። የራሱን ካድሬዎች ሰብስቦ በሀኪሙ ቁስል ላይ ራሱን ሀኪሙን እየሰደበ ሲያስጨበጭብ ውሎ መውጣት ከአንድ የሀገር መሪ የሚጠበቅ ነገር አይደለም። ሀኪሞች እድል ተነፍገው ጥያቄያቸውን ለመጠየቅ ከሰው እጅ ላይ በጉልበት ማይክ ሲነጥቁ ማየት ያሳፍራል።

አንድ የሀገር መሪ “ኢትዮጵያ ውስጥ ሀኪምም ህክምናም የለም” ብሎ ቃል በቃል ተናገረ ብል ማን ያምነኛል? የኢትዮጵያ ሀኪም እኮ CBC ና አልትራሳውንት በሌለው ሆስፒታል ውስጥ ጭንቅላቱን ጨምቆ ፔሸንቶቹን ሲያክም የሚውል ድንቅ ፍጥረት ነው። የላብራቶሪ እቃ በሌለበት፣ የባለሞያ እጥረት ባለበት፣ ታካሚውን ለኢንፌክሽን በሚያጋልጥ መሰረተ ልማት ላይ የሚሰራን ሀኪም ገምግሞ ችሎታው ላይ ጥያቄ ማቅረብ መሀይምነት ነው!

ገና ለገና ሙስና እንዳይቀበል ተብሎ ለገቢዎች ሰራተኛ ከፍተኛ ደሞዝ የምትከፍል ሀገር ላይ… የሰው ነፍስ እጁ ላይ የተቀመጠን ሀኪም በደሞዝም በንግግርም፣ በሞራልም መደቆስ ምን የሚሉት የህዝብ ጥላቻ ነው? የተማረረ ሀኪም አድማ መቶ ህዝብ ቢያልቅ እውነት መንግስት ከደሙ ንፁህ ነኝ ይለናል? ከገንዘብም በላይ ሀገራቸውን መርጠው፣ ከአብሮአደጎቻቸው ተነጥለው እዚሁ የተቀመጡ ጥቂት ሀኪሞችን ማዋረድ ለዚህች ሀገር ይጠቅማታል?

በአጠቃላይ አብይ የሰራው ስራ ተራ ፖለቲካ ነው። በየሚዲያው ስሙ ሲጠፋ የኖረን ሀኪም ከህዝቡ ጋር አለኳኩሶ ምንም አታመጡም አይነት ጨዋታ በጣም አደገኛ ነው። አንድ ሊታወቅ የሚገባው ጉዳይ… የሀኪሙ አመፅ ከሀኪሙ በላይ የሚጠቅመው ህዝቡን መሆኑን ነው። ሲሆን ሲሆን የሀኪሞቹ ጥያቄዎች ይመለሱላቸው ብሎ ሰልፍ መውጣት የነበረበት ራሱ ህዝቡ ነው። ህዝቡ ይሄን እውነት ቢረዳም ባይረዳም ግን ሀኪሙ የራሱን እርምጃ ከመውሰድ አይመለስም! የህዝብ ድጋፍ ማጣትና ማግኘት የሚያስጨንቀው ፖለቲከኛን እንጂ ባለሞያን አይደለም።

ሀኪም ደሞዙ እርካታው ነው አይነት ማባበያ የሚሰራው ላልተማረ ህዝብ እንጂ ቀንና ሌት ከሞትና ህይወት ጋር ተፋጦ ለኖረ ሀኪም አይደለም። “ስማይል ማድረግ አለባችሁ” እያልክ ስትመክር ብትውል… ህይወት ያስመረረው ሀኪም በአንተ ቀልድ እንጂ ታካሚው ፊት አይስቅም። በዚህ ንግግርህ ስንት ሀኪም በሀገሩ ተስፋ እንደቆረጠ ብታውቅ አንደበትህን ትሰበስብ ነበር። ከዛችው ደሞዙ ላይ ለታካሚው እያዋጣ መድሀኒት የሚገዛን ሀኪም ስለበጎ አድራጎት መምከር እንደዛ… በጅማቱ ክራር ሰርተው እንደቀለዱበት አይነት በሬ ተረት ተረት ነው። በሙስና ተግጦ አልቆ በአጥንቱ የቀረ ሆስፒታል ይዞ ስለሜዲካል ቱሪዝም፣ ስለነርስ ኤክስፖርት መለፍለፍ ያስቃል።

የስራው ፀባይ ራሱ በጋራ መቆምን ያስተማረውን ሀኪም ለመከፋፈልና ትግሉን ለማዳከም መሞከርም ሞኝነት ነው። የፖለቲካ ሀይል አለበት አይነት መደለያ ህዝብን ለማሞኘት ካልሆነ ሀኪሙ የገዛ ብሶት ከርሱ በላይ የሚያውቅለት የፖለቲካ ኃይል የለም።

ለማንኛውም እኛ የሞያ ጥያቄ ስንጠይቅ እናንተ በእኛ ጥያቄ ላይ የተጫወታችሁት ፖለቲካዊ ጨዋታ ፎርሿል። ገፍታችሁ ገፍታችሁ… ከምንጊዜውም በላይ ሀኪም አንድ አፍ ሆኖ በጋራ ድምፁን የሚያሰማበት ጊዜ ላይ አድርሳችሁናል። ሀኪም ከሆንክ አንድነትህን አጠንክር፣ ትከሻህን አስፋ። ለመብትህና ለታካሚዎችህ መብት እስከመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ታገል። የላብህን፣ የደምህን ውጤት… የሚገባህን ክፍያ ለመጠየቅ በፍፁም አትሸማቀቅ!! አንተ ለራስህ ካልቆምክ… እመነኝ! ማንም ከሀኪም ጎን የሚቆም የለም!! የመንግስት ጡጫም ሆነ የህዝብ ተቃውሞ ሳይበግርህ በተገፋህበት ተራራ ቁመት ልክ ከፍታህን አውጅ!!

ይሄን ፅሁፍ በውዴታ ሳይሆን በግዴታ ሼር በማድረግ እያንዳንዱን ሀኪም ከጎንህ እንዲቆም ጥራው!

ነጋቲ!

Filed in: Amharic