>
5:14 pm - Monday April 20, 6207

መንግስት ስርዓት አልበኝነት አደጋ ከመሆኑ በፊት ስርዓት ይሰፍን ዘንድ ግዴታውን ይወጣ! (አቶ ሙሼ ሰሙ)

መንግስት ስርዓት አልበኝነት አደጋ ከመሆኑ በፊት ስርዓት ይሰፍን ዘንድ ግዴታውን ይወጣ!
በአቶ ሙሼ ሰሙ።
ደቡብ ክልል ላይ ቀን በቀን እየተፈጸመ ያለው ነገር፣ እንዲህም አድርጎ ሪፖብሊክ፣ እንዲህም አድርጎ ፌደራሊዝም አልተፈጠረም የሚያስብል ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል። በሪፓብሊኳ ውስጥ ከ25 ሚሊዮን የሚበልጠውን ሕዝብ ያቀፈውና የክልሉ ስልጣን ባለቤት የሆነው የ”ደቡብ” ሕዝብ ተንቆና የስርዓተ አልበኞች መፈንጫ ሆኖ ኢትዮጵያ የሰላም አየር ትተነፍሳለች ብሎ መገመት የዋህነት ነው።
ከዚህ ቀደም ሐዋሳ ላይ የወላይታ ተወላጅ ወጣቶችን ከነሕይወታቸው የማቃጠል አረመኒያዊ ድርጊት ሲፈጸም ሁላችንም አይተን እንዳላየን አለፍን። ቀሪዎቹ የክልሉ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተደብድበውና ንብረታቸው ተነጠቆ፣ ተዋርደው እንዲሰደዱ ሲደረግ ይህንንም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ሕዝብ አይተን እንዳላየን ታዘብን በዝምታ አለፍን።
የክልሉ ሕዝብ እራሱን እንዳይከላከል በፌደራሊዝም አደረጃጀቱና ተሹመው በሚላኩለት መሪዎቹ ምክንያት እጁ የኃልዮሽ ታስሮ፤  መጤዎችን ከነነፍሳቸው እናቃጥላለን፣ በገጀራ እንቆራርጣለን በሚሉ ጋጠ ወጦች ሉዕላዊነቱ ሲደፈር በትዕግስት ማለፉና ለሕግ የበላይነት መገዛቱ እንደ ደካማነት ተቆጥሮ ስርዓተ አልበኝነቱ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለመሸጋገር በቅቷል።
ለዚህ ማረጋገጫ ለማግኘት፣ሌላ ርቀት መሄድ አያስፈልገም። የክልሉ ሉዕላዊነት መገለጫ የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ም/ ቤት ስብሰባ በጋጠ ወጦች ተደፍሮ፣ በመቶ ሺ የሚቆጠር የሕዝብ ውክልና ያላቸው የተከበሩ የም/ቤት አባላቱ ተደብድበውና ተዋርደው ለሆስፒታል መዳረጋቸውና የክልሉ ሰንደቅ ዓላማም ከማማው ላይ ወርዶ መቃጠሉ በቂ ምስክር ነው።
ባለፈው ሰሞን ደግሞ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኢንቨስተሮች፣ ነጋዴዎችና ባለሀብቶች ከሕግ ውጭ ለሦስት ቀን ስራ እንዲያቆሙ በር ለበር የተካሄደባቸው ዛቻና ማስፈራራት ሳያንስ “ከክልል ምስረታ በኋላ ንብረታችሁንና ሃብታችሁን ሐዋሳ ላይ ጥላችሁ ትወጣላችሁ!” የሚል ዘመቻ እየተካሄደባቸው እንደሆነ በመግለጽ  ስጋት ላይ ነን ቢሉም ደንታ የሰጠው ፍጡር አልነበረም።
ዛሬም ውርደቱና ግፉ እንደቀጠለ ነው። የወላይታ ዲቻ ስፖርተኞችና ደጋፊዎቻቸው ለእግር ኳስ ጨዋታ ሐዋሳ ላይ በመገኘታቸው ደጋፊዎቻቸውን ጨምሮ ሕይወታቸውን ለማሸነፍ ቆሉና ሸንኮራ ሸጠው የሚተዳደሩ የወላይታ፣ የከምባታና የሃዲያ ተወላጅ ሕጻናት ሳይቀሩ ተደብድበው፣ ተዋርደውና ተዘርፈው ወደ ዞናቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል።
ይህ ሁሉ ግፍ፣ ድፍረትና ጋጠ ወጥነት የሚካሄደው የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ተከብሮባታል፣ ልዮነታችን ጌጣችን ነው በሚባልላት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። እውነት እናውራ ከተባለ፣ እንደዚህ አይነት ወራዳ ድርጊትና ድፍረት ትልቅ ነን በሚሉት ክልሎች፣ በጨፌ ኦሮሚያ ፣ በአማራ ወይም በትግራይ ክልል ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ እንኳን ሊፈጸም፣ የሚቃጣ ጉዳይ አንዳልሆነ ልባችን ጠንቅቆ ያውቃል።
መሬት ላይ ያለው እውነታ ይህ እስከሆነ ደረስ ስለ እኩልነት፣ አንድነት፣ መቻቻልና መከባበር አታውሩ ፣ እፈሩ የምንለው ወደን አይደለም። የአሜሪካ የጥቁር መብት ታጋዮች “Black Life Matter ” እንደሚሉት የወላይታዎች፣ የጋሞዎች፣ የከምባታዎች በጥቅሉ የ25 ሚልዮን ብሔሮች  ” Life  Matters”
እዚህ ላይ ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ልንረሳው የማይገባ አንድ ነገር አለ። ለሕግ መገዛት በጋጠ ወጦችና ስርዓተ አልበኞች ለውርደት የሚዳርግ እስከሆነ ድረስ ሁሉም እራሱን፣ ቤተሰቡንና ልጆቹን መከላከል መብቱ ከመሆኑም በላይ የሞራል ግዴታው ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ይገባል። በዚህ መነሻነት ሊፈጠር በሚችለው ምስቅልቅልና አለመረጋጋት ውስጥ የኔ የምንለው ሁሉ ጠፍቶ ሁላችንም ያለጠያቂና ያለቀባሪ የምንቀርበት አሳዛኝ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል ማመዛዘን አለብን።
ስርዓተ አልበኝነት ቀይ መስመር የለውም። ከተሞክሮ  ተነስተን ስርዓተ አልበኝነት ዛሬ ወላይታ ላይ ፣ ነገ ከምባታ፣ ከነገ ወዲያ ሃድያ ላይ ብቻ የሚወሰን መስሎን ከሆነ ተሳስተናል። ውሉ አድሮ አማራነት፣ ኦሮሞነት እና ኢትዮጵያዊነትንም ሰለባዎቹ እንደሚያደርግ ጥርጥር የለውም። ዳሩ ሲነካ መሐሉ ዳር ሊሆን መቻሉ ግልጽ ነው።
“ደቡብ” የራሱ አጀንዳ ያረረበት አክቲቪስት ነኝ ባይ ሁላ ዘው እያለ እየገባ ሕዝብን የሚያጋጭበት፣ የሚያተራምስበት ክልል ነው። ክልሉ በሴራ ፖለቲካ አቅመ ቢስ ተደርጎ እራሱን መከላከል እንዳይችል የተኮላሸም ነው።
የፈረንሳዮ ንጉስ ሉዊ XV “Après moi le déluge” ከኔ በኃላ ጎርፍ ይምጣ እንዳለው ሁላ እንደዚህ ዓይነቱ ሌሎችን አሳንሶ በማየት እሳቱ እኔን ካልነካኝ፤ ቀሪው ቢቃጠል ችግር የለውም ማለት የከፋ መዘዝ አለው።  ውለው አድረው ስርዓተ  አልበኝነትና ስርዓተ አልበኞች ተንጠራርተው በየቤታችን መምጣታቸው አይቀርም።
የደቡብ ዋና ከተማ የሆነው ሐዋሳ ላይ የሚኖረውና ሐዋሳን የገነባው ወላይታ፣ ጋሞው፣ ሃዲያው፣ ስልጤው  ወይም ጉራጌው ብቻ አይደለም። አማራው፣ ኦሮሞው፣ ትግሬውም፣ ሱማሌም በተለይ ደግሞ  የፌደራሉ  መንግስት ፈሰስ ጭምር በስፋት ታክሎበት መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
መቼስ የመገንጠል ታናሽ ወንድም የሆነው ክልል የመሆን ጥያቄ ጡት ማስጣያ አጀንዳ ከሆነ ሩብ ምዕተ ዓመት አስቆጥሯል። መልካም። ክልል መሆን የሚፈልግ ሁላ መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት።  ነገር ግን የቀሪው ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ጥቅም በማይነካበትና በማይጎዳበት መልኩ ስርዓትና ሕግን ተከትሎ ክልል መሆን ይችላል። ክልል በመሆን ወይም በመገንጠል ስም ስርዓተ አልበኝነትንና ጋጠ ወጥነትን ማንገስ ግን በቃ ሊባል ይገባል።
ይህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚቀርብ ጥሪ ነው። ኢትዮጵያ ልጆቿና ዜጎቿን በእኩልነትና በስርዓት ትሰብስብ ዘንድ የሞራልም ሆነ የሕግ ግዴታ አለባት። የቤትና የደጅ ልጅ ሊኖራት አይገባም። ሁላችንም ስርዓት አልበኝነትን በጋራ ልንታገልና ልንጸየፍ ይገባል። ስርዓተ አልበኞችን “Enough is Enough” ሲበቃ ይብቃ! ማለት አለብን።
ስርዓተ አልበኝነት የሚጋባ ተላላፊ ወረርሽኝ ነው። መንግስት ስርዓተ አልበኝነት አደጋ ከመሆኑ በፊት ስርዓት ይሰፍን ዘንድ ግዴታውን ይወጣ፣ ዜጎችም በነቂስ ወጥተን ስርዓተ አልበኝነትን በተባበረ ድምጽ በቃ ማለት አለብን። ይህ አማራጭ መሆን ካልቻለ ግን፣ ቀሪው አማራጭ አንድ ነው። የፌደራል መንግስቱ የክልሉን ሕዝብና ልጆቹን ከምርኮኝነት ይልቀቃቸው። የክልሉ ሕዝብና ልጆቹ እራሳቸውን ከስርዓት አልበኞችና ጋጠወጦች ይከላከሉ።
Filed in: Amharic