>

ነጋዴውን በ33 ሺህ ፐርሰንት ጭማሪ እያፈናቀሉ ቄሮን የመትከሉ አጀንዳ እየተተገበረ ይሆን?!?  (ያሬድ ጥበቡ)

ነጋዴውን በ33 ሺህ ፐርሰንት ጭማሪ እያፈናቀሉ ቄሮን የመትከሉ አጀንዳ እየተተገበረ ይሆን?!? 
ያሬድ ጥበቡ
33 ሺህ ፐርሰንት የሱቆች ኪራይ የተጨመረባቸው ዝቅተኛ ነጋዴዎች ለጠቅላይ ሚኒስትራቸውና ምክትላቸው ቅሬታቸውን ለማሰማት ተሰልፈዋል። ከዚህ በፊት መንግስት ያስጠናው በካሬ ሜትር 71 ብር ከሃምሳ ብንከፍል ተገቢ ነው ሲሉም የመፍትሄ ሃሳብ ጨምረው አቅርበዋል ። የመንግስት አካል የሆነው የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ይህን የ33 ሺህ ፐርሰንት ጭማሪ ከየት አመጣው? ለምን? እነዚህን 6 ሺህ ነጋዴዎች በማፈናቀል ማንን በምትካቸው ለማስፈር ታስቦ የተወጠነ ነው? አዲስ መታወቂያ ለተሰጣቸውና ከሐረር፣ ባሌና አርሲ ለመጡ ቄሮዎች መቋቋሚያ ታስቦ ይሆን?
ዶክተር አምባቸው በአምቦው የኦሮማራ መድረክ ድጋፍ የሰጡት የኦሮሚያ ልዩ መብት በተግባር ሲተረጎም ይህ እንደሚሆን ደነዙ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራር የወንጀል ትብብር ውጤት ይህ ብቻ ሊሆን እንደሚችል ግልፅ አልነበረምን? ኢህአዴግ ሽግግሩን መምራት እንደማይችልና የጃዋርን አጀንዳ ከማስፈፀም ውጪ ተልእኮ እንደሌለው ከትናንት በስቲያ ኩዩ ፈጬ፣ ትናንት የለገዳዲ ውሃ ፕሮጀክት፣ ዛሬ ደግሞ የነዚህ 6ሺህ ነጋዴዎች መፈናቀል ግልፅ አያደርገውምን? አዲስ አበባ የነዚህን ነጋዴዎች መፈናቀል ዛሬ በዝምታህ ከደገፍክ ነገ ደግሞ የየቤትህን በር የሚያንኳኳ ችግር እየጋበዝክ መሆኑ ሊረዳህ ይገባል ።
 መንግስት ሃገሪቱ ለገጠማት የኢኮኖሚ ችግር መፍትሄ እንደመፈለግ፣ የኦሮሚያ ክልል ሥራአጥ ወጣት በዝርፊያ፣ በማስፈራራት፣ ቢዝነሶችን ቀረጥ በማድረግ ወዘተ እንዲሰማራ በመፍቀድ የመጨረሻው መፍትሄው ደግሞ “ነፍጠኛው ሥርአት ከፊንፊኔ ኦሮሞዎችን በማፈናቀል የወረሰውን ንብረት ማስመለስ” እንደ ዓላማ ሲይዝ በግዴለሽነት በመመልከት ላይ ይገኛል ። ከአዲስ አበባ የተፈናቀለ ኦሮሞም ሆነ፣ ዛሬ ተንሰራፍቶ ያለው ሃብት ዱሮ “በፊንፊኔ ዘመን” እንዳልነበርና፣ ፊንፊኔ የግጦሽ መሬት እንጂ ሥልጣኔ ያልነበረበት እንደነበር የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትም ሆነ የ”ለውጥ አመራር” ነኝ የሚለው ቡድን ወጣቶቹን ሲሞግት አይታይም ። አዲስ አበባን ውጠው ፊንፊኔ ለማድረግ ያሰፈሰፉ ሥራአጥ ወጣቶችን በጥቃቅንና አነስተኞችን ማደራጀት ስም ወደከተማዋ በማስረግ የህዝብ ስብጥርና የሃብት አያያዝ ለውጥን ለማድረግ እየሰሩ ነው። አዲስ አበባ ያንን አትፍቀድ ።
ዙሪያህን የኦሮሞ ክልል ሥራአጥ ወጣቶች ውሀ ቀጠነ ብለው በልብወለድ ላይ የተመሰረተ የአኖሌ ሃውልት ታሪክ ተተቸ ብለው ሃገርምድሩን በሰልፍ ሲያናውጡ የሚተባበር መንግስት፣ አንተ መንግስት 33ሺህ ፐርሰንት የቤት ኪራይ ጭማሪ ሲያደርግብህ የቤተሰብህንና ሠራተኞችህን መበተንና ለረሃብ መዳረግ በመቃወም ለአቤቱታ እንኳ እንዳትሰለፍ ያግድሃል ። ይህን አድልኦ የሚያደርግ መንግስት እንዴት የ”ለውጥ አመራር” መባል ይችላል? አማራውና ኢትዮጵያዊውን ብሄርተኛ በቃላት እየሸነገልን፣ መንግስታዊ መዋቅሮቹን እየተቆጣጠርን፣ የአዲስ አበባን ነዋሪ በዙሪያው ባለው የኦሮሞ ቄሮ እያስበረገግንና የሥነልቡና ጦርነት እያካሄድን ካሰብንበት እንደርሳለን ብለው ወስነዋል ።
እስከዚያው በቃላት እየሸነገሉህ፣ ጋዜጠኞችን ሳይቀር በገንዘብ እየገዙ፣ በህዝብ መዋጮ የተቋቋሙ የኢሳት ዓይነት ነፃ የህዝብ ተቋሞችን እያስጎበደዱና በበጀት እንደጉማችኋለን ብለው እያማለሉ ካሰቡበት ለመድረስ እየከነፉ ነው። አዲስ አበባም በዝምታህ እየተባበርካቸው ነው። ጥቃቱ መረን ከመልቀቁ የተነሳ፣ የኢሳቱ ሲሳይ አጌና ቤተመንግስት ተቀምጦ ርዕዮት ዓለሙ ከጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ፀጋዬ ጋር ያደረገችውን ቃለምልልስ እስከማገድ ደርሷል።  ብልግናው መረን ለቋል ።
አዲስ አበባም ብቻ ሳይሆን ኢሳትን በገንዘቡና ድካሙ የመሠረተው ዳያስፖራም እነዚህን የሰብአዊ መብት ግፊቶችና ዘረኛ እሳቤዎች ነገ ሳይሆን ዛሬ እምቢ ብለው መቆም አለባቸው። አዲስ አበባና ዳያስፖራው የሥራአጥ ቄሮዎችንና የመሪያቸውን የጃዋርን የሽብር አገዛዝ እምቢ ብለው መቆምና፣ የለውጥ አመራር ነኝ የሚለውም መንግስታዊ አካል ለነዚህ የፅልመት ሃይሎች የሚያሳየውን ትብብርና ተንበርካኪነት ለመታደግ ቆርጠው መነሳት አለባቸው ። ዝምታ ብዙ ያስከፍላል። ዝምታ በወንጀል ትብብር ወደመሆን የተሸጋገረበት ወቅት ላይ እየደረስን ነው ። ዝምታችን ይብቃ! እኔም ዝምታዬን ሰብሬአለሁ ። ለመብቶቻችን ዘብ እንቁም!
Filed in: Amharic