>
5:13 pm - Saturday April 19, 0842

ከእውነት፣ ከታሪክ እና ከእውቀት አትጣላ፤ አለምህን ታጠባለህ! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ከእውነት፣ ከታሪክ እና ከእውቀት አትጣላ፤ አለምህን ታጠባለህ!
ያሬድ ሀይለማርያም
እውነት ማንም እንደፈለገ የሚያበጃት አይደለችም። ለዛም ነው ትመነምናለች እንጂ አትበጠስም ወይም ከመቃብር በላይ ትኖራለች የሚባለው። ሰዎች በአንድ ጉዳይ ወይም ክስተት ዙሪያ ያለን እውነት እነሱ ላቀዱት አላማ በሚያመች መልኩ ባሻቸው መንገድ ሊያበጃጁት ወይም ሊቀይሩት ይችላሉ። ነገር ግን የሚቀይሩት እውነትን ሳይሆን ሰዎች ሰለዛ እውነት ያላቸውን ምልከታ እና ግንዛቤ ነው። ታሪክም እንዲሁ ነው። ታሪክን ማንም ሊቀይር አይችልም። ሁሉም በተረዳው መጠን እና ልክ ሊከትበው ወይም ሊገልጸው ይችል ይሆናል እንጂ። ትላንት የተፈጠረውን ነገር ዛሬ ልንቀይረው አንችልም።
እውነት እና ታሪክን በሁሉም ሰው ዘንድ ወይም በአብዛኛው ሰው ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ የሚያደርጋቸው ሳይንሳዊ እውቀት ነው። እውቀት የእውነት መሰረት ነው። እውነት ደግሞ የታሪክ መገለጫ ነው። እውነት ሲዛባ ታሪክ ይዛባል። እውነት ሲዛባ እውቀት ይዛባል። እውነትም፣ ታሪክም፣ እውቀትም የተዛቡበት ትውልድ ደግሞ እንደ ውሃ ላይ ኩበት ተንሳፋፊ ነው። አንድም የውሃውን ፍሰት ተከትሎ እሱ ወደማያውቀው መዳረሻ ይነጉዳል አልያም በንፋስ እና በማእበል ከግራ ቀኝ እየተማታ ከአንድ ጫፍ ሌላ ጫፍ እየደረሰ ሲዋልል ይኖራል።
በእውቀት ላይ በተመሰረተ እውነት፣ በእውነት ላይ በተመሰረተ የታሪክ ትርክት ዛሬውን ያጸና እና ነገውን ያማተረ ትውልድ መንገዱ ቀና፣ አለሙም ሰፊ ነው። መድረሻውን ያውቃል። የውሸት ማዕበል አይገፋውም ወይም ድንቁርናም ካላበት ደፍቆ አያስቀረውም። እርምጃው ሁሉ በእውቀት እና በጥንቃቄ የተሞላ ነው። በምንም ጉዳይ አቋም ከመያዙ ወይም አንደበቱን ከመክፈቱ በፊት ይማራል፣ ያነባል፣ ይመራመራል፣ በጥልቀት ያስባል፣ ያሰላስላል፣ ይጠይቃል።
ከታሪክ የተጣላ፣ ከእውነት የራቀ እና እውቀትን የተጠየፈ ትውልድ አለሙን ከማጥበብ አልፎ አገርን ይገላል። የነገ ተስፋውን ያጨልማል። አገራዊ ዕራይም ስለማይኖረው መንደርተኛ እንደሆነ ይቀራል። ቢባርምም እውቀቱን ለዛኑ ለቀበልኛ አስተሳሰቡ ማገዶ ነው የሚያደርገው። ሃሳቡም፣ ህልሙም፣ ተቆርቋሪነቱም፣ ወገንተኝነቱም ሆነ ስለ አገር ያለው እሳቤ ከመንደር አይዘልም። መንደርተኛ አለሙ እዛው መንደሩ ነች። በአካል ተሰደሞ ጭንቅላቱን እዛው መንደሩ ጥሎ ስለሚመጣ በድኑ አውሮፓና አሜሪካ ነፍሱ ደግሞ እትብቱ የተቀበረችበት መንደሩ ውስጥ ተሰንቅራ የሁለት አለም ግራ ፍጡር ይሇናል። ይህ መንደርተኛ አንዱንም ዘመን ሳይዋጅ ዘመን በላይ ላይ ይፈራረቁበታል። አካሉም፣ መንፈሱም ከመንደሩ ያልወጡም ከሆነ መንደሩ አለሙ እንደሆነ ያልፋል።
ሌሎች አገሮች የፓስፖርታቸውን ጥንካሬ የሚለኩት ዜጎቻቸው በመላው አለም በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸውን ለማስፋት በሚያደርጉት ጥረት ነው። ያለ ምንም ቪዛ ወደ ፈለጉት የአለም ክፍል ተጉዘው ያሻቸውን ሰርተው እንዲኖሩ ይጥራሉ። የዜጎቻቸውም ህልም በአገራቸው የታጠረ ሳይሆን አለምንት ያማከለ ነው። በየትም አገር ሄደው ተምረው፣ ሰርተው እና አትርፈው ለልጆቻቸው ሰፊ አለምን መተው ነው ትልማቸው።
እኛ ደግሞ ቁልቁል እየተንሸራተትን እንኳን አለማችንን ልናሰፋ የገዛ አገራችንም ውስጥ በነጻነት ዜጎች መንቀሳቀስ፣ መስራት፣ ያሻቸው ቦታ መኖር የማይችሉባት ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን ያለ የሌለ ጉልበታችንን ሁሉ እየተጠቀምን እንገኛለን። ብሄረተኝነት ከፖለቲካ ጋር ሲጋባ እና ሲከር ውጤቱ ይሄው ነው። እድለኛ ከሆን በዚሁ ያሽረን እና ወደቀልባችን እንመለስ ይሆናል። እኛ እና እድል ካልተገጣጠምን ግን የሚሆነውን ማሰብ ይዘገንናል።
ከመንደርተኝነት ወጥተን ሰፊዋን ኢትዮጵያ እና ሰፊውን አለም እናስብ!
Filed in: Amharic