>
5:13 pm - Sunday April 19, 3068

አውሮፕላኖቻችንን የበላ ጅብ ! (በውብሸት ታዬ )

አውሮፕላኖቻችንን የበላ ጅብ !
(በውብሸት ታዬ )
   የሜቴክ አመራሮች ከተከሰሱባቸው የአገርና ሕዝብ ሃብት ምዝበራ አንዱ የደረሱበት አልታወቀም የተባሉት አንድ መርከብና አውሮፕላኖቻችን ጉዳይ ነው። ለነገሩ ብዙዎቻችን የጠፋው አንድ አውሮፕላን ብቻ ይመስለን ነበር ።
   እውነታው ግን ከዚህ በጣም የከፋ ኖሯል። ከአንድ የወዳጄ ወዳጅ የሆነ ለጉዳዩ ቅርብ የነበረ ሰው ጋር ስለሁኔታው ገፋ አድርገን የምናወጋበት አጋጣሚ በመፈጠሩ እስኪ ለወዳጆቼ ጥቂት ላጋራችሁ ብዬ ነው።
   መቶ አለቃ ተመስገን እያሱ ይባላል። በሙያው ኢሌክትሪካል ኢንጂነር ሲሆን በሜቴክ የደጀን አቪዬሽን የውጭ ጉዳይ ሃላፊ ነበር። እንግዲህ የመረጃ ምንጬ ይኼ ነው ካልኳችሁ ዘንድ ፍሬ   ነገሩ ሲጠቃለል ቀጥሎ ያለውን ይመስላል።
   2001 ዓ.ም ላይ ስድስት መጠነኛ የሰው ሃይል ማመላለስ የሚችሉ ወታደራዊ ቢች ክራፍት አውሮፕላኖች እንዲገዙ ተፈለገ።
   በውሉ ላይ ስድስት ያገለገሉ አውሮፕላኖች እንዲገዙና አራቱ በእስራኤል፤ ሁለቱ ደግሞ በኢትዮጵያ ቴክኒሻኖች አገር ውስጥ ተጠግነው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ “Avoriga Company” ከተባለ የተለያዩ የንግድና የኮሚሽን ሥራ የሚሠራ የእስራኤል ካምፓኒ ጋር ሜቴክ ስምምነት ተፈጸመ።
   ይህ ወዳጄ በወቅቱ ከአንድ ሌላ ኤክስፐርት ጋር በመሆን እስራኤል ድረስ ሄደው ስለአውሮፕላኖቹ ሁኔታ ቴክኒካል ጉዳዮች በስፍራው ካለው ቡድን ጋር ተለዋውጠው ተመልሰዋል።
   የዚህ ጉዞ አስፈላጊነት አራቱ አውሮፕላኖች ተጠግነው የሚመጡት ከዚያው በመሆኑ የኢትዮጵያ ባለሙያዎች መገኘትና ሁኔታውን ማስተዋል አለባቸው በመባሉ ነበር። ይህ ከሆነ ታዲያ ቀናት ነጎዱ፤ ወራት ተቆጠሩ። ሰማይ ሰማይ ሰማይ ቢታይ ምንም የለም። በመጨረሻ በወርሃ ጥር የጥምቀት ዕለት አንዷ አውሮፕላን እንደምንም ኢትዮጵያ ገባች።
   ሌሎቹስ? ማለታችሁ አይቀርም። የበላቸው ጅብ አልጮህ አለ። ኢትዮጵያ እንደዋዛ አምስት አውሮፕላኖች ተበላች! በዚህ ለመስማት የሚከብድ ሌብነት የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋል በጀመሩት ሰሞን “በብሔራችን” የተነሳ የሚል ነጠላ ዜማ ተለቆ ነበር።
#የፎቶ መግለጫ ፦ *1 እና *2 መቶ አለቃ ተመስገን እያሱ በእስራኤል ተገኝቶ የአውሮፕላኖቹን ቴክኒካዊ አቋም ሲገመግም *3- መቶ አለቃ ተመስገን (በወቅቱ) *4ይህን ምስጢር ካጋራኝ በኋላ  “ሞጋች እውነቶች” የተሰኘውን መጽሐፌን ሳበረክትለት።
ቸር ቀን ይሁንላችሁ።
Filed in: Amharic