>

ለውጡና ... ሕዝብ!!! (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም)

ለውጡና … ሕዝብ!!!
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም
አንዳንድ ሰዎች ለውጥ የለም ሲሉ አንዳንዶቹ ደግሞ ስር-ነቀል ለውጥ ተደርጓል ይላሉ፤ ለእኔ ግን ከደርግ የመጀመሪያ ዓመት የሚመሳሰል እንዲያውም ከፍ ያለ ለውጥ አይቼበታለሁ፤ ሆኖም እዚህ አጉል ክርክር ውስጥ አልገባም፤ነገር ግን የተከታተልሁትን ያህል እንደገባኝ እኔ ለውጥ የምለውን ልናገር፤ በዘር ፖሊቲካ የተለያዩ ወንጀሎች እየተለጠፉባቸው ከዕድሜ ልክ እሰከሞት በአሻንጉሊት ዳኞች እያስፈረዱ እስርቤቶቹን ሞልተው እንደነበረ እናውቃለን፤ ዛሬ እነዚህ ሰዎች ሁሉ በነጻ በየቤታቸው ናቸው፤ ይህ ለብዙ ቤተሰቦች ለውጥ ነው፤ ከሁሉም በላይ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ጋዜጦች፣ ራዲዮኖችና፣ ቴሌቪዥኖች እንደልባቸው እንዲጨፍሩ አድርገዋል፤ ይህም በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ለውጥ ነው፤ የፖሊቲካ ቡድኖች ሁሉ እንደልባቸው በነጻነት እየተሰበሰቡ ፐሮግራማቸውን መግለጽና መዘዋወር ችለዋል፤ እንዲውም አንዳንድ የፖሊቲካ ቡድኖች ለውጡ ያመጣውን ነጻነት ወደስድነት ለውጠውት ብዙ ጥፋትን ሠርተዋል፤ ስለዚህ የአገዛዙ ኃይል በለውጡ ምክንያት ሲላላ እኩይ ኃይሎች ይበረታሉ፤ እስከዛሬም ቢሆን እኩይ ኃይሎች እንደተጠናከሩ በመሆናቸው ብዙ ሰዎች መንግሥት መኖሩን ይጠራጠራሉ፡፡
የማስታወስ ችሎታችን ያነሰ በመሆኑና አዲስ ትውልድ በመፍላቱ አናስታውስ ይሆናል እንጂ ደርግ ሥልጣን ሲይዝ ከአንድ ዓመት ያህል በላይ መንግሥት አልነበረም ይባል ነበር፤ ጸሐፌ ትእዛዝ አከሊሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት በፈቃዳቸው ሲሰናበቱ ወንበሩ ለብዙ ወራት ብዙዎችን እያጓጓ ባዶውን ተቀምጦ ነበር፤ ለጥቂት ወራት በጭንቀት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቢሮ በተከታታይ የያዙት ልጅ እንዳልካቸው መኮንንና ልጅ ሚካኤል እምሩ ነበሩ፤ጃንሆይ ከዙፋናቸው የወረዱት ጸሐፌ ትእዛዝ አከሊሉ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰናበቱ ከዘጠኝ ወራት በኋላ ነው፤ በመሀከሉ የልጅ እንዳልካቸውና የልጅ ሚካኤል ጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደነበረ አልረሳሁም፤ ነገር ግን በልጅነት የተቀጩ በመሆናቸውና ፋይዳም ስላልነበራቸው ችላ ብያቸው ነው፡፡
ደርግ ሥልጣን ሲይዝ መንግሥት አልነበረም ቢባልም ሥርዓት አልባነትን የመቆጣጠሪያ ጉልበትና ቁርጠኛነት ነበረው፤ አሁን ግን የተፈለገው ከጉልበት ይልቅ ሕጋዊነት. ከዚያም አልፎ ፍቅር፣ ይቅር ባይነትና ሰላም በመሆኑ ለማኅበረ እኩያን ሁኔታዎችን ያመቻቸ ይመስላል፤ ስለዚህም በኢትዮጵያ ያለው ሥርዓት አልባነት ቢያንስ ለጥቂት ወራት የሚቀጥል ይመስለኛል፤ ይህንን የሥርዓት አልባነት ዘመን ለማሳጠር በሥልጣን ላይ ያሉት ከያዙት የክርስቲያን መንገድ የማይቃረን ዘዴ በቶሎ ቢፈልጉ ከብዙ ጥፋት እንድናለን፡፡
     1. ባለሥልጠኖችና ለውጡ
ዛሬ በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች የኢሕአዴግ አባላት ናቸው፤ ሁለቱም ዓቢይና ለማ የኦሕዴድ አባላት ናቸው፤ እንግዲህ ለውጥ አድራጊዎቹ ሁለቱም የኦሕዴድ አባሎች ናቸው፤ የብአዴን ሰዎች ጎልተው አልታዩም፤ እነዚህ ሁለት የኦሕዴድ ባለሥልጣኖች በአንድ በኩል ራሳቸውን ከአደጋ ለመከላከል በጣም ከባድ ጥረት ያደርጋሉ፤ በሌላ በኩል ለውጡን ወደፊት ለመምራት ይለፋሉ፤
የለውጡ ባለሥልጣኖች በሦስት ኃይሎች ተወጥረዋል።  በአንድ በኩል ሥልጣኑን የተቀማውና ያኮረፈው ቡድን ምቹ አጋጣሚ እየጠበቀ ሰላምን ያደፈርሳል፤ በየደረጃው በሥልጣን ላይ ያሉት ደግሞ እንዳይነጠቁ በየፊናቸው እንቅፋቶችን ይፈጥራሉ፤ በተጨማሪ ደግሞ ለውጡ ቀሰስተኛ ሆነብን እያሉ የሚጮሁ አሉ፤ ቆም ብሎ በማሰብ ፖሊሶችን፣ ዓቃብያነ ሕጎችን፣ ዳኞችን በሙሉ አስወጥቶ እንደሀገር መቀጠል እንደማይቻል መገንዘብ አያስቸግርም፤ በሌሎች የተለያዩ ሥራዎችም በወደቁት ባለሥልጠኖች የተሾሙት ሁሉ ስርስሩን መርዝ እየነሰነሱ የሚያደናቅፉ ናቸው፤  ትልቁ የለውጡ መሪዎች ፈተና በጎሠኞች መሀከል የተፈጠረው ፉክክርና ግጭት ነው፡፡
የለውጡ መሪዎች በአላቸው ችሎታ ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ሕዝቡን መምራት ይፈልጋሉ፡፡
 
2. ምሁራንና-ለዉጡ
ምሁራን ማለትን በትክክል ያሳወቀን የለም፤ ስለዚህ እኔ ሆዱ ሰፊ የሆነና ስምንተኛ ክፍል ጨርሶ በፌስቡክ ላይ የሚጽፍ ሁሉ ምሁር ነው ብዬ እነሣለሁ፤ ከዚያ በላይ በአሥራ ሁለተኛ ክፍል በኩልም ይሁን በሌላ በአቋራጭ መንገድ የሚገኙትን የትምህርት መጠሪያ ጌጦች ሁሉ ከነዝባዝንኬያቸው የታቀፉ ሁሉ ምሁራን ናቸው፤ ቄንጠኛ ባርሜጣ ያደረጉና ጥቁር መነጽር የሚያደርጉትንም እጨምራቸዋለሁ፤ የሚሽሎከሎኩም ይኖሩ ይሆናል፡፡
አብዛኛዎቹ ምሁራን ለለውጡ ገለልተኞች አይደሉም፤ እንዲያውም አብዛኛዎቹ ምሁራን ለውጡ የመጣባቸው ናቸው፤ እነዚህ የአንጀራ ምሁራን በእንጀራቸው ለሚመጣ ነገር ዕድሜያቸውም ሆነ ምኞታቸው ለገለልተኛነት አያበቃቸውም፤ በአጠቃላይ ነባር ምሁራን ነባር ሁኔታው የተኙበት ነውና ለውጥን አይደግፉም፤ የእነሱን እንጀራ ለማያወፍር ለውጥ  ተቃዋሚ እንጂ ደጋፊ ሊሆኑ አይችሉም፤ በመሠረቱም የእንጀራ ምሁራን ከለውጥ ጋር የሚሰለፉት የተሻለ ወፍራም እንጀራ የሚያቀርብላቸው ሲሆን ብቻ ነው፡፡
አንዳንዶቹ በአማካሪነት፣ በሎሌነት፣ ወይም በአጨብጫቢነት ከመሪዎቹ አጠገብ ለመጠጋት ይፈልጉ ይሆናል፤ አንዳንዶቹ ሥራቸውን፣ ችሎታቸውን በደህና ዋጋ ለመሸጥ ይጥራሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ መንጠላጠያ ጨብጠው ወደሌላ ዓለም ተምዠግዥጎ ለመብረር ይመኛሉ፤ በአገራቸው ተተክለው የሚቀሩ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡
ለምሁራን ራሳቸውን ከፍ ለማድረግ የለውጡን መሪዎች ዝቅ አድርጎ መገመት መነሻቸው ይመስለኛል፤ ጥንት በአጼ ዘመን ካሣ ወልደ ማርያም የኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት እንዲሆን ሲሾም እኔ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማኅበር ፕሬዚደንት ነበርሁ፤ በዚህም የተነሣ ለካሣ የምሥራች ደብዳቤ እንጻፍለት ብዬ ሀሳብ አቀረብሁ፤ በዚያን ጊዜ የሰማሁት ተቃውሞ ዛሬ በነዓቢይ ላይ ከሚሰነዘሩት የተለየ አልነበረም፤ ‹‹እኛ የምናውቀውን እነሱ አያውቁም፤ እኛ የምናየውን እነሱ አያዩም፤ እኛ የምንሰማውን እነሱ  አይሰሙም፤›› ለድንገተኛ አዲስ ነገር በደመ ነፍስ እንዲህ ዓይነቱን አስተያየት ስንሰጥ እጅግም አያስደንቅም ይሆናል፤ ነገር ግን ሲውል ሲያድር አስተያየታችን ካልተሻሻለ ለውጡን ወደፊት ከመግፋት ይልቅ ወደኋላና ወደጠብ አጫሪነት የሚወስድ ይሆናል፤ የለውጡ መሪዎች ምሁራን ከሚባሉት ያላነሰ እውቀት እንዳላቸው ለመቀበል ትንሽ መመራመርና እውነቱን ማወቅ አስተያየታችንን ያቃናልን ነበር፤ እንዲያውም እንደዓቢይ አህመድ ያለ በብዙ መስኮች በቃሉ የማውረድ ችሎታ ያለው አላውቅም፤ ሊቅ የሚባሉት እንትና እንዲህ አለ፤ እንትና እንዲህ አለ በማለት የሠለጠኑ ናቸው፡፡
3. ሕዝብ
በአጠቃላይ በሕዝቡ በኩል ስለለውጡ ያለው ስሜት እኔ እንደምገምተው በቀል ነው፤ በተለያዩ ሁኔታዎች በድለውናል የሚሏቸውን ባለሥልጣኖች ከሥልጣን ማውረድ ዋናው ፍላጎት ይመስለኛል፤ ይህ ስሜት ወደወጣቶቹ ዘንድ ሲደርስ ኃይልና እልህ ጨምሮ ለግጭት ሊያደርስ ይችላል፤ የማይፈለጉት ባለሥልጣኖች ሁሉ በአንድ ጊዜ ከሥልጣናቸው ቢነሡ የሚከተለውን ትርምስ መገመት አያስቸግርም፡፡
ሕዝቡ እየተረገጠና እየተጠቃ ለዘመናት ይኖራል፤ በደሉንና ቂሙን ድብቅ አርጎ ይዞ ኖሮ የአገዛዝ ለውጥ ሲመጣ የትእግስት ቋቱ ከጫፍ ጫፍ ይተረተራል፤ ፍቅር፣ ውለታና ጉርብትና መቃብር ተቆፍሮላቸው ይገባሉ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቂሙን አይረሳም፤ ቂሙን ደብቆ በምሥጢር ይይዝና ለዘመናት ቆይቶ አጥቂ የነበረው ኃይል ጥቃት ሲደርስበት የኢትዮጵያ ሕዝብ እየፎከረና እልል እያለ በቀሉን ለመወጣት ይጥራል፤ በሰዎች ላይም ሆነ በንብረት ላይ የሚያደርሰው ጥፋት ከፍተኛ ነው፤ በእንደዚህ ያለው ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለበቀልና ለዘረፋ እየፎከረ ይወጣል፤ የሕዝቡ አትኩሮት ባለፈው በደሉና በበቀል ናፍቆቱ ላይ ነው፤ ወደኋላው እንጂ ወደፊት አያይም፤ የወደቀውን አገዛዝ በተሻለ ለውጦ የወደፊት ኑሮውን ለማሻሻል እንዲያስብ መወያየት ያልተለመደ ነው፡፡
ሦስቱም ሃይማኖቶች በነገሡባት አገር፣ ኢትዮጵያ፣   በታሪክ ጸሐፊዎች ሁሉ የክርሰቲያን ደሴት ትባል ነበር፤ ታሪኩን የጠቀስኩት ዓቢይን ለማስገባት ነው፤ ዓቢይ አህመድ በዓቢይ ስሙ ላይ አህመድን ጨምሮ ብቅ ሲል ያልተደነቁት ወሎዬዎች ብቻ ይመስሉኛል፤ ኢትዮጵያ የተደነቀችው ዓቢይ አህመድ ፍቅር፣ ይቅር ባይነት፣ ሰላም … እያለ ብርቅ የሆነበትን ክርስትና መስበክ ሲጀምር ነው! የእናቱ ወሎዬነት አደናቅፎበት አልፎት ይሆናል እንጂ ክርስትና በኢትዮጵያ ከተሰበከ ከሁለት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በላይ ሆኖታል፤ አበሻ ክርስትናን ያሸነፈው በሆዱ ነው፤ አበሻ ለሆዱ ያለውን ፍቅር ዓቢይ መማር ያስፈልገዋል፡፡
ከተለያዩ የውጭ ኃይሎች ጋር የተቃቀፉ ኢትዮጵያውያን ስለኢትዮጵያ የወደፊት ሁኔታ እያጠቆሩና እያመረሩ ያወራሉ፤ ገና ካልደረሰችበት አፋፍ እያንከባለሉ ሊያወርዷትም ይዳክራሉ፤ ሲአይኤ ከሠላሳ ዓመታት በፊት የጠነሰሰውን የኢትዮጵያ ውድቀት ትንበያ ገና አሁን ያነበቡት ምሁሮች ያለማቋረጥ ዛሬ ያነበንቡታል፤ ኢትዮጵያን ትተው ሄደው አሁንም የዳቦ መብያቸው ኢትዮጵያ ነች፤ የፈረንጆችን ዓላማ ለማሳካት ኢትዮጵያን መደፍጠጥ ዳቦ የሚያበላ ሥራ አድርገውታል፤ ለውጡን ለመምራት፣ አቅጣጫውን ለማስለውጥ፣ ፍጥነቱን ለመቀነስ፣ አካሄዱን ለማደናቀፍ የሚጥሩ ክፍሎች በውጭ እርዳታ እንደልባቸው ይንቀሳቀሳሉ፤ ልናውቃቸው ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደእግዚአብሔር ትዘረጋለች፤ ይዞ ይደግፋታል!
Filed in: Amharic