>

ይልመድባችሁ! (ኤርሚያስ ለገሰ)

ይልመድባችሁ!
ኤርሚያስ ለገሰ
የትኛው የመንግስት ባለስልጣን የኢቲቪ አርካይቭ እየተበረበረ እንዲወጣ ትእዛዝ እንዳስተላለፈ ባላውቅም ( የምጠረጥረው አለ!) በኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ለጋዜጠኞች የሰጠኃቸው መግለጫዎች ተቆራርጠው እየወጡ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሰሞኑን ” የፀረ -ሽብርተኝነት አዋጅ ረቂቅ” ላይ ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ጋዜጠኞች የሰጠሁት ማብራሪያ እየታየ ነው። ይሄ ለበጐ አላማ ታስቦ ከሆነ ጥሩ ይመስለኛል። የቪዲዬዎቹ ባለቤት እኔ ስላልሆንኩ የገፅታ ግንባታ ወይም ሾልኮ የወጣ ማለት አልችልም። በኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ስንከተለው የነበረው አሰራር ምንአልባትም ለአዲሱ የኢህአዴግ መንግስት ሊጠቅሙ የሚችሉ እንጥፍጣፊ ቁምነገሮች ስላሉት በመጠኑ ላንሳው።
 የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት በተቋቋመ በማግስቱ በኮሙዩኒኬሽን ስራ ጥሩ ልምድ አላቸው የተባሉትን የአሜሪካ፣ እስራኤል እና ደቡብ አፍሪካ ልምዳቸውን ለመቅሰም በኤምባሲዎቻቸው ሄደን ነበር። አሜሪካ እና እስራኤሎቹ በቤተ መንግስታቸው ስር የፕሬስ ሴክሬተሪያት አደራጅተው በየቀኑ ” ፕሬስ ብሪፊንግ” ይሰጣሉ። ደቡብ አፍሪካ በተመሳሳይ ( የደቡብ አፍሪካ ኮሙዩኒኬሽን ሊምቦዚ ይባላል) በሳምንት አንዴ ፕሬስ ብሪፊንግ ይሰጣሉ።
የእነዚህን አገሮች ልምድ ወስደን እኛም በሳምንት አንድ ቀን (ሰኞ ጠዋት) ከጋዜጠኞች ጋር የምንገናኝበት አሰራር ዘረጋን። በአንድ ወር ውስጥ ያሉትን ሶስት ተከታታይ ሰኞዎች የኮሙዩኒኬሽን የበላይ ሃላፊዎች፣ የመጨረሻዋን ሰኞ ደግሞ በሳምንቱ አበይት ጉዳይ ያላቸው የተቋማት የበላይ ሀላፊዎችን በመጋበዝ ማብራሪያ የሚሰጡበት ሁኔታ አመቻችተን ነበር። ለአብነት ያህል የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ላይ የኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ሚኒስትሩን፣ የቴሌ ታሪፍ ቅናሽ ሲካሄድ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊውን፣ ኮሌራ መሰል ወረርሽኝ ሲከተል የጤና ጥበቃ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎችን በመጋበዝ የተፈፀመ ነበር።
የፕሬስ ብሪፊንጉ ዋነኛ ስራ ሚኒስትሮች ምክርቤት ተወያይቶ ለፓርላማ የላካቸውን ረቂቅ አዋጆች እና መመሪያዎችን ማብራራት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰኛ እስከ ቅዳሜ የሚውልባቸውን ቦታዎች ማስተዋወቅ እና በሳምንቱ ውስጥ በኢትዮጵያ የሚከሰቱ አበይት ኩነቶችን መግለፁ ነበር። በዚህም ምክንያት በሚኒስትሮች ምክርቤት በአብዛኛው ሚኒስትሩን ወክዬ የምሳተፈው እኔ ነበርኩ። ይሄንንም በተደጋጋሚ ጊዜ ገልጨዋለሁ። በሚኒስትሮች ምክርቤት ተሳትፌ በሰኞው የጋዜጠኞች መገለጫ ካቀረብኩባቸው ጐላ ያሉ ጉዳዮች መካከል፣
      * የመያዶች አዋጅ
       * የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ
       * የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ
       * የኤርትራውያን ንብረት አመላለስ መመሪያ
       *  የኮሙዩኒኬሽን እና የብሮድካስት አዋጅ
        * የኢትዩጵያ ሰራዊት ከሱማሊያ ለቆ እንዲወጣ የተደረገበት ውሳኔ
        * የአሜሪካ የሰብአዊ መብት ሪፓርት ምላሽ… ወዘተ ከብዙ በጥቂቱ ናቸው።
እናም ዛሬ ከኢቲቪ አርካይቭ ወጥቶ እንዲሰራጭ እንደተደረገው ” የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ” ሁሉ ሌሎቹንም ለማስተማሪያ እንዲረዳ ይፋ ቢደረጉ ጥሩ ይመስለኛል። አርጌው ኢህአዴግ አይኑን በጨው ያጠበውን ጌታቸው ረዳ ጐትቶ በማምጣት በቪኦኤ ጭምር በመቅረብ የነበረንን ኃላፊነት ለማሳነስ ተሯሩጦ ነበር። የኢቲቪ እና የፓርቲው አርካይቮች ተደብቀው እንዲቀሩም ቀጭን ትእዛዝ አሳልፈው ነበር። አዲሱ ኢህአዴግ ደግሞ አላማው ምንም ይሁን ምን ተደብቀው የቀሩትን ማውጣት ጀምሯል። ይሄ ጥሩ ውሳኔ ነው። በተከታታይም እንዲቀጥል ትእዛዙን የስተላለፉትን ባለስልጣናት እጠይቃለሁ።
እዚህ ላይ አንድ ልብ ሊባል የምፈልገው ቁመነገር አለ። ትምህርት የሚቀሰምበት አሰራሩ ( አሁን ባለው አዲሱ ኢህአዴግ ስላላየሁት) እንጂ ይዘቱ አይደለም። ይዘቱማ አምባገነናዊ፣ ዘረኛ እና ፀረ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለማስቀጠል የተቀረፀ በመሆኑ መደገም የለበትም። የዚህ መጥፎ ይዘት ባለቤቶቹም በዛ ስርአት የነበርን ሁላችንም ነን።
   ሰምተሃል!!
Filed in: Amharic