>
5:13 pm - Friday April 19, 7089

የዘውግ ፖለቲካና ዘር ማፅዳት!?! (ዶ/ር ሰማህኝ ጋሻው)

የዘውግ ፖለቲካና ዘር ማፅዳት!?!

ዶ/ር ሰማህኝ ጋሻው

የዘር ማፅዳት ወንጀል በአለማችን ታሪክ የነበረ ነገር ቢሆንም በተለይ ከቀድሞዋ ዩጎዝላቭያ መበተን ጋር ተያይዞ በተፈፀሙት ወንጀሎች ትኩረት ያገኘ በህዝብ ላይ የሚፈፀም የማሳደድድና የማፈናቀል ወንጀል ነዉ። እኤአ ከ1992-1995 በተካሄደዉ የቦስንያ ሄርዞጎቪና ጦርነት ሙስሊሞችና ክሩአቶችን ሰርቦች በግዳጅ ቀያቸዉን እንዲለቁ በማድረጋቸው ከአንድ መቶ ሽህ በላይ ሙስሊሞችና ክሮአቶች የዘር ማፅዳት ወንጀል ሰለባ ሆነዋል። በቅርቡም በባንግላዴሽ የሚኖሩት ሶስት መቶ ሽህ የሮሄንጊያ ማህበረሰብ አባላት በገፍ ከቀያቸዉ እንዲሰደዱ የተደረገበትን አለምን ያሳዘነ ድርጊት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘር ማፅዳት ወንጀል በሚል ኮንኖታል። የተባባሩት መንግስታትት ድርጅት የኤክስፐርቶች ኮምሽን የዘር ማፅዳት ወንጀልን “a purposeful policy designed by one ethnic or religious group to remove by violent and terror-inspiring means the civilian population of another ethnic or religious group from certain geographic areas” (ሆነ ተብሎ በተቀረፀ ፖሊሲ  አንድ  ዘዉግ ወይም የሃይማኖት ቡድን ሲቪል ህዝብን ወይም ሌላ ዘዉግን ወይም የሃይማኖት አባላትን በሃይል ወይም በማስፈራራት ከአንድ አካባቢ እንዲለቁ ማድረግ ነዉ።) የዘር ማፅዳት ወንጀል ዋና አላማ አንድ ቡድን የእኔ ብቻ ነዉ ከሚለዉ አካባቢ የሌላ ዘዉግ አባላትትን በማስወጣት አንድ ወጥ (homogenous) ማህበረሰብ ለመፍጠር ነዉ። የዘር ማፅዳት ወንጀል በብዛት የሚፈፀመዉ በአብዛኛዉ ዘዉጋዊ ስሜቶች በገነኑበትና የፖለቲካ መሳርያ ሆነዉ በሚያገለገሉበት የአለማችን አካባቢዎች ነዉ።

በአገራችን ሰሞኑን በለገጣፎ አካባቢ ብሄርን መሰረት አድርጎ የተፈፀመዉ መፈናቀል የህዝብን ትኩረት የሳበ አሳዛኝ ክስተት ሆኖ አልፎአል። ከዚህም በተጨማሪ በበርካታ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ ለኢትዮጵያዊነት ፍቅር አንገታቸዉን ይሰጣሉ የተባሉት አቶ ለማ መገርሳ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን ወደ ቀያቸዉ ከመመለስ ይልቅ በአዲስ አበባና በዙርያዋ አካባቢ እንዲሰፍሩ በማድረግ የእኔ የሚሉትን ህዝብ ከተሞችን እንዲቆጣጠር እየሰሩ እንደሆነ ገልፀዋል። ከዚህም በተጨማሪ ፊንፊኔ ኬኛ በሚባለዉ የስግብግብነት ፖለቲካ በህገወጥ መንገድ ለአንድ አካባቢ ሰዎች መታወቂያ እየተሰጠ እንደሆነ ማስረጃዎች ወጥተዋል። ይህን አይነት አይን ያወጣ አድልዎና የዴሞግራፊክ ምህንድስና አሰራር ህዝብን ያሳዘነዉ ቲም ለማ የሚባለዉ ቡድን ይምልና ይገዘትበት ከነበረዉና ህዝቡ ድጋፉን እንዲሰጠዉ ካደረገዉ ‘የኢትዮጵያዊነት’ ትርክት በተቃራኒ የቆመ መሆኑ ነዉ። ህወሃት ያደርገዉ የነበረዉ የዘረኝነት አካሄድ አሁንም መልኩን ቀይሮ በመካሄድ ላይ እንዳለ በቂ ምልክቶች እየታዩ ነዉ። ይህን አይነት አካሄድም በኬኛ ፖለቲካ ታጅቦ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል ለማወቅ ነብይ መሆን አይጠይቅም። ምናልባት ኢትዮጵያ የምትባለዉ አገር ታሪክ ከመሆንዋ በፊት ከዚህ አገር ከሚያፈርስ መርዘኛ የዘረኝነት አካሄድ ለመዉጣት የበሽታዉን ምልክቶች ሳይሆን የበሽታዉን ስርና መሰረት ማወቅና ማከም ያስፈልጋል።

ወደድንም ጠላን ለዘር ማፅዳት ወንጀል የዳረገን ሰሞኑን እነ ዶ/ር አብይ አንደራደርበትም ያሉት የዘዉግ ፌዴራሊዝም መሆኑን መገንዘቡ በጣም አስፈላጊ ነዉ። ስራ ላይ ያለዉ ህገ መንግስት የማእዘን እራስ የሆነዉ ‘የብሄሮችን የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል’ ርእዮተ አለም ታሪካዊ አመጣጡ፣ ትርጉሙና በእኛም ሆነ በሌሎች አገሮች ተግባራዊ የሆነበት መንገድ ከዴሞግራፊ ምህንድስናና ዘር ማፅዳት ጋር የቅርብ ትስስር ያለዉ ነዉ። በኢትዮጵያ የግራ ፖለቲካን ያራመዱት ሃይሎች የተከተሉት ‘የብሃር ጭቆና’ ትርክት በሩስያ ከተካሄደዉ  የሶሻሊስት አብዮት ጋር የቅርብ ትስስር ያለዉ ነዉ። ሌኒንና ስታሊን በሩስያ አብዮት ለማካሄድ ዝግጅት ሲያደርጉ ሩስያዊ ካልሆኑት ልሂቃን የሚነሳዉን የዘዉግ ጥያቅ ለመመለስ ሲሉ በብሄር ጉዳይ ላይ ያተኮረ ‘ ማርክሲዝምና የብሄር ጥያቄ’ የሚል  ፅሁፍ አወጡ። ስታሊን ለብሄር የሰጠዉ ትርጉም አሁን በእኛ ህገ መንግስት የተካተትዉን ትርጉም የያዘ ሲሆን ለብሄር ጥያቅ መፍትሄዉም ‘ የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል’ ነዉ ተብሎ ተቀመጠ። ከ1924 ጀምሮ በነበሩት ህገ መንግስቶች በሙሉ ይህ መርህ የህገ መንግስታቸዉ ዋና አካል ሆኖ ቀጠለ።

በአገራችን በየአካባቢዉ እየተካሄደ ያለዉን የዘር ማፅዳት ለመረዳት በሶቭየት ህብረት የነበረዉን ሁኔታ መረዳት በጣም ይጠቅማል። ሶቭየት ህብረት የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል የተባለዉን የስታሊን ሃሳብ ተግባራዊ ካደረጉ በሁዋላ ሌሎች ብሄሮች በሩስያ ጭቆና ዉስጥ ነበሩ በሚል ሁሉም ብሄሮች የኔ ነዉ የሚሉት ክልል እንዲኖራቸዉ ተደረገ። እያንዳንዱ ብሄር  የራሱ ባንዲራ ፥ መንግስትና መሬት እንዲኖረዉ ተደረገ። በየካባቢዉ ይኖሩ የነበሩ የሌላ ብሄር ተወላጆች በባቡር እየተጫኑ ወደ እናት ክልላቸዉ በገፍ እንዲመለሱ ተደረገ። እነ ስታሊን ህዝቡ አገራዊ አመለካከት እንዲኖረዉ የማይፈልጉ የነበረ ሲሆን እንደዉም ማንኛዉም ሰዉ በተቻለ መጠን አገራዊ ማንነት እንዳይኖረዉና አካባቢያዊ ማንነቱን እንዲያዳብር ያበረታቱ ነበር። በ1920ዎቹና 30ዎቹ ስታሊን በወሰደዉ የዘር ማጥራት ፕሮጀክት ራሳቸዉን እንደ አንድ ብሄር የማያዩ የነበሩትን ማህበረሰቦች መቀየር አስቸጋሪ እየሆነ ሲመጣ ሰዎች በግዳጅ አንድ ብሄር እንዲመርጡ ማስገደድ ተደረገ። ይህ የስታሊን ፕሮጀክት በተለያዩ ማህበረሰቦች መካከል የነበረዉን ሰላማዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ወደ ተቀናቃኝነትና ጠላትነት ቀየረዉ። ማህበረሰቦች የጎሪጥ መተያየት ጀመሩ። በአንድ መልኩ ልዩነትን እያበረታቱ በሌላ በኩል ደግሞ ኮሚኒስት ፓርቲዉ ሁሉንም ስልጣን መቆጣጠሩን መቀጠሉ የፈጠረዉ ቅራኔ አገሪቱን ሊበትናት ችሎአል።

ወደ ሃገራችን ስንመለስ ያላዋቂ ሳሚ የሆኑት ጥራዝ ነጠቆቹ የ 1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ መሪዎች አገራቸዉንም ሆነ ማርክሲዝምን በቅጡ ሳይረዱ የስታሊንን የብሄር ጭቆና ትርክት እንዳለ በመኮረጅ አማራን በጨቋኝነት ሌላዉን በተጨቋኝነት በመፈረጅ አገሪቱን ቀዉስ የከተተዉን መርዝ በአገሪቱ ፖለቲካዉ ዉስጥ ተከሉ። የዚህ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ዉላጅ የሆነዉና በአማራዉ ጥላቻ ያበደዉ ህወሃት ስልጣን ላይ ሲወጣ ከላይ የተገለፀዉን የስታሊንን መርህ በህገ መንግስት በማስፈር ተመሳሳይ ዘር የማፅዳት ስራ አካሄደ። ህዝቡን በጎሳ ክልል በማጠር ኢትዮጵያዊነትን ወንጀል በማድረግ ህዝቡ በሙሉ በግድ ጎሳ እንዲኖረዉ አደረገ። ይህ ሰይጣናዊ ተልእኮ ላለፉት 27 አመታት ያመጣዉን ቀዉስ ለመግለፅ አስቸጋሪ ነዉ።

ከአስር ወራት በፊት ወደ ስልጣን የመጡት ጠ/ሚኒስት አብይ ከተሾሙበት ቀን ጀምሮ ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚያደርጉት ዲስኩር ህዝብን አይደለም ወፍን ከሰማይ ማዉረድ የሚችል ነበር። ህዝቡ ከዚህ የዘረኝነት ስርአት የተላቀቀ መስሎት ከዳር እስከ ዳር ድጋፉን ሰጣቸዉ። ከአርባ አመታት በላይ ፖለቲካ ዉስጥ ነበርን የሚሉት የተቃዋሚ መሪዎችም የለዉጡ አቅጣጫና ፍኖተ ካርታ ምንድነዉ ብለዉ ሳይጠይቁ ለዉጡ እንዳይደናቀፍ በሚል አብረዉ መነዳት ጀመሩ። ዶሮ ብታልም ጥሬዋን እንደሚባለዉ በኢትዮጵያ ሱሴነት የሚታወቀዉ የቲም ለማ ቡድን በአፍ ከሚገለፀዉ ኢትዮጵያዊነት ዉጭ መሰረታዉ የፖሊስ ለዉጥ ካለማድረጋቸዉም በላይ በጎሳ ፌዴራሊዝም እንደማይደራደሩ፥ በአዲስ አበባ ላይ ያላቸዉን ልዩ መብትና አፋን ኦሮሞን ብሄራዊ ቋንቋ የማድረጉን ስራ አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ ግልፅ አደረጉ። ከዚህም ባላፈ እነዚህ ሰዎች ላለፉት 27 አመታት ከተሰነቀሩበት የጎሰኝነት ዋሻ ስለመዉጣታቸዉ ብዙ ማስረጃ ማቅረብ አልተቻለም። እንደዉም ባለፉት ወራቶች የተፈፀሙትን ድርጊቶች ስንመረምር ለዉጡ በዋናነት ከህወሃት ወደ ኦዴፓ ስልጣን የመሸጋሸግ ጉዳይ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። እነ ኢትዮጵያ ሱሴዎች ለቡራዩ የዘር ማፅዳት ያሳዩት ወገንተኘነት፥ የአዲስ አበባን ህዝብ አፍሰዉ ያሰሩበት፥ የካቢኔ ቦታዎችን የተቆጣጠሩበት መንገድ፥ ጓደኞቻቸዉን ለፍርድ ማቅረብ አለመፈለጋቸዉ፥ በአዲስ አበባ የሚደረገው መታወቂያ እደላና የለገጣፎዉ ዘርን ያማከለ ማፈናቀል ሲታይ አዲሶቹ መሪዎች በመሰረታዊ ደረጃ ያንኑ የኖርንበትን የዘር መዘዉር እያሽከረከሩት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

አሁን ትኩረት እየተደረገበት ያለዉ ህዝቡን የሚያማልሉ ነገሮችን በማዉራት ከእለት ወደ እለት ስልጣንን እያጠናከሩ መሄድ ነዉ። በቅርቡ የቀረበዉ አንዱ ማደናገርያ ኢህአዲግ ወደ አንድ ፓርቲ መቀየሩ ከጎሳ ፖለቲካን እንደሚያወጣን ተደርጎ የቀረበበት መንገድ ነዉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ስራ ላይ ያለው ፌዴራሊዝም ለዜጐች እውቅና ያልሰጠ፥ ዜጋ ለመሆን ቅድሚያ የጐሳ አባልነትን የሚጠይቅና ብሄር ብሄረሰቦች የሚል ስም የወጣላቸው ጐሳዎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር እስከ መገንጠል መብት የሚሰጥ ነው። ይህ አይነት የአስተዳደር መዋቅር በጐሳ የተደራጁ ፓርቲዎችን መኖር ግድ ይላል። አንድ የፖለቲካ ድርጅት ከጐሳ ወደ አገራዊ አወቃቀር እቀየራለሁ ሲል እንዴት አድርጐ አልደራደርበትም የሚለውን የጐሳ ፌዴራሊዝም እንደሚያስቀጥለው ግልፅ አይደለም። የጐሳ አደረጃጀት ለዚህ የፌዴራል ስርአት አንቀሳቃሽ ሞተር ነው። ይህ የጐሳ ፌዴራሊዝም ያለጐሳ አደረጃጀት አንድ ኢንች መጓዝ አይችልም።

ጠ/ሚ አብይና ቡድናቸዉ እውነት እንደሚያወራውና እንደሚወራለት የኢትዮጵያዊነት ስሜት ካለው ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ይህንን ፀረ ሰብ የሆነ መርዝ ህገ መንግስት ለመቀየር ጥረት ማድረግ ነው። ይህ ሳይሆንና የራሱን ፓርቲ በዘረኝነቱ እፀናለሁ እያለ ኢህአዴግ የሚባለውን ሙት ድርጅት በብቃት ላይ የተመሰረተ አገራዊ ፓርቲ አደርገዋለሁ የሚለው ፉከራ በመርህም ሆነ በተግባር ትርጉም የማይሰጥ ነው። አገራዊ ፕሮግራም ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች አገራዊ ፕሮግራም ይዘው የሚንቀሳቀሱት ስልጣን ቢይዙ ይህንን የጐሳ ፌዴራሊዝም እንቀይረዋለን ከሚል እምነት በመነሳት እንጅ ይህን የጐሳ ፌዴራሊዝም በአገራዊ የፖለቲካ ፕሮግራም ልንመራው እንችላለን ከሚል እምነት አይደለም። ይህ ሊሆን እንደማይችል ያውቁታል። አንድ ስልጣን ላይ ያለ ፓርቲ ግን ከፈረሱ በፊት ጋሪውን አስቀድማለሁ ቢል ባዶ ቅጥፈት ከመሆን አያልፍም። ኢህዴግን ለስሙ አንድ ፓርቲ ነው ብሎ ማወጅ የሚቻል ቢሆንም ይህ የጐሳ ስርአት እስካለ ድረስ ውስጣዊ አደረጃጀቱ ጐሳዊ ባህርይውን እንደያዘ ይቀጥላል። ትግራይን በትግሬዎች፥ አማራውን በአማራና ኦሮሙውን በኦሮሞ ብቻ አስተዳድር የሚለው የፌዴራል ስርአት አወቃቀር የግድ ከላይ የዳቦ ስም ቢያወጡለትም ውስጣዊ ጐሳዊ አደረጃጀታቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ ያስገድዳቸዋል። ለዚህ ነው የዶ/ር አብይ የጐሳ ፌዴራሊዝም ሳይነካ ኢህአዴግን አንድ አገራዊ ፓርቲ አደርጋለሁ የሚለው ቃል አገሪቱ ከገባችበት አዙሪት ለመዉጣት አቅም የሚያንሰዉ።

ይህ የለዉጥ ሁኔታ ውልና አቅጣጫ የሌለዉ በመሆኑ አገሪቱ ወደ አጠቃላይ ቀዉስ እያመራችና የዘር ማፅዳቱ ሂደት በየአካባቢው እየቀጠለ ይገኛል። አገዛዞች በተቀያየሩ ቁጥር ራሳቸዉን እንደፃድቅ እየቆጠሩ ያለፉትን ስርአቶች ስህተት መድገማቸዉን ቀጥለዋል። እነሱ ቤተ መንግስቱን ሲቆጣጠሩት እራሳቸዉን እንደ ብፁእና ጥፋት እንደማይመጣባቸዉ አድርገዉ ያስባሉ። በቅዱስ መፅሃፍ የተገለፀ አንድ ታሪክ ሁኔታዉን ይገልፀዋል። አስቴር በቤተ መንግስት እየኖረች አይሁዳውያን እንዲጠፉ የሚያዝዘው አዋጅ ሲወጣ መርዶክዮስ ይህ አዋጅ እንዲሻር ንጉሱን ገብታ እንድታናግር ሲጠይቃት በማመንታቷ ” በንጉሥ ቤት ስለ ሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ ይልቅ እድናለሁ ብለሽ በልብሽ አታስቢ። በዚህ ጊዜ ቸል ብትዪ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፥ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ ወደ መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?” የሚል መልእክት ላከባት። ዶ/ር አብይና ቡድናቸዉ ወደ ስልጣን ሲመጡ የኢትዮጵያ ህዝብ የደገፋቸው ወያኔ ካመጣብን ዘረኝነትና የመበተን አደጋ ያድኑናል ከሚል እምነት ነበር። እየሆነ ያለው ግን ተቃራኒው ነው። አሁንም በዘር ተቧድነው ቤተ መንግስቱን ተቆጣጥረው የወያኔን ስግብግብነት እያስናቁት
ይገኛሉ። በአንደበት ስለ አንድነት እየተሰበከ በተግባር ግን ፊንፊኔ ኬኛ እያሉ በዘር ፌዴራሊዝም አልደራደርም ይላሉ። አገሩ እየፈራረሰ መሆኑን አይኑን ከፍቶ ለሚያይ ሰው ግልፅ ነው። የሚያሳዝነው እነ ዩጐዝላቭያን የበተነው የጐሳ አስተዳደር የእኛ የሚሉትን ህዝብ ጥቅም ያስጠብቅልናል ብለው ሙጭጭ ማለታቸው ነው። ያልገባቸው ነገር በዚህ የጐሰኝነት አዋጅ ማንም አትራፊ አይኖርም። ዛሬ ቤተመንግስቱን ስለያዙ ከጥፋት እድናለሁ ብለው ማሰብ አይገባቸዉም። እነሱም ሆኑ  እወክለዋለሁ የሚሉት ህዝብ ከሚመጣው ጥፋት አይድንም።

በተለይ በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ ተማምኖ ነገሮች ከዛሬ ነገ ይለወጣሉ በሚል በጎሳ ባለመደራጀት የሚጠብቀዉ ማህበረሰብና በአክራሪ ብሄርተኞች ጨቋኝ ነዉ ተብሎ የተፈረጀዉ ለረጅም ዘመን በጎሳ ሳይደራጅ የቆየው የአማራዉ ማህበረሰብ ለዘር ማፅዳት የተጋለጡ ናቸዉ። ለአክራሪ ብሄረተኞች የሚያደላ ህገ መንግስትና መዋቅር እንዲሁም ይህ ነዉ የሚባል የረባ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ አለመኖሩ  እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች ለከፋ አደጋ እንዲጋለጡ አድርጓል። በዚህ ከፋፋይ ህገ መንግስት ላይ ቆመን ዴሞክራሲና የተረጋጋ አገር ይኖረናል ማለት የህልም እንጀራ ከመሆን አያልፍም። ለዚች አገር መረጋጋትና እድገት የሚበጀዉ ከዚህ የጎሳ ፌዴራሊዝም ተላቀን የዜጎችን መበት፥ አገራዊ አንድነትንና የዘዉጌዎችን ባህላዊና እራስን በራስ ማስተዳዳር የሚያስችል አዲስ ህገ መንግስታዊ ስርአት መመስረት ሲቻል ነዉ። ይህ የማይቻልና ሁኔታዎች በዚህ የሚቀጥሉ ከሆነ ግን ሁሉም ራሱን ለመከላከል በየጎሳው የመደራጀቱ ሂደት በፍጥነት እየቀጠለ ይሄዳል ማለት ነዉ። ይህ ዘረኛ የጎሳ አስተዳደር በስራ ላይ እስካለ ድረስና ምንም አይነት መሰረታዊ የፖሊሲ ለዉጥ ሳይደረግ  በአንደበት በሚነገሩ ነገሮችን ብቻ ተማምኖ መዘናጋት በቡራዩ፥ ለገጣፎ፣ ጌዶኦ፥ ወልቃይት፥ ድርዳዋ፥ አዋሳና ሌሎች ቦታዎች እንዳየነዉ ዘርን መሰረት ላደረገ መፈናቀልና ዘር ማፅዳት መጋለጥ ይሆናል። አሁን ያለዉን አሳሳቢ ሁኔታ ለመለወጥና ምናልባትም እያንዣበበ ያለዉን ጥፋት ለማስቀረት ሁሉም ያዋጣኛል ብሎ በሚያምንበት አደረጃጀት በቁርጠኘነት መታገል ይኖርበታል። ከዳር ቆሞ ዘር ለገበሬ ነዉ እያሉ መዘናጋት ለአክራሪ ብሄረተኞች የዘር ማፅዳት ወንጀል ሲሳይ መሆን ነዉ።

Filed in: Amharic