>

የጸረ-ጥላቻ ንግግሩ አዋጅ የሚያጠላው ጥላ?!? (በፍቃዱ ኃይሉ)

የጸረ-ጥላቻ ንግግሩ አዋጅ የሚያጠላው ጥላ?!?
በፍቃዱ ኃይሉ
በዚህ የፖለቲካ ለውጥ ውስጥ አፋኝ ናቸው የተባሉት ሕግጋት ክለሳን ያክል «ለውጡን» ሕጋዊ ዋስትና የሚሰጠው ሌላ ነገር የለም። ይሁን እንጂ የፀረ ጥላቻ ንግግር አዋጅ ረቂቅ መውጣቱ በሕግ ክለሳ ሒደቱ ላይ የቅሬታ ጥላ አጥልቷል!!!

በዚህ የፖለቲካ ለውጥ ውስጥ አፋኝ ናቸው የተባሉት ሕግጋት ክለሳን ያክል «ለውጡን» ሕጋዊ ዋስትና የሚሰጠው ሌላ ነገር የለም። ይሁን እንጂ የፀረ ጥላቻ ንግግር አዋጅ ረቂቅ መውጣቱ በሕግ ክለሳ ሒደቱ  ላይ የቅሬታ ጥላ አጥልቷል። የፀረ ጥላቻ ንግግር አዋጅ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ከሚገደብባቸው የሕግ አግባቦች አንዱ ስለሆነ፥ በአንድ በኩል የንግግር ነጻነትን የሚገድቡ ሕግጋት እያወጡ፣ በሌላ በኩል አፋኝ ሕግጋትን የመከለስ ተቃርኖ እንዴት ይታያል? ክለሳው ሳይጠናቀቅ የአዲሱ አዋጅ ረቂቅ መውጣቱስ ምንን ያመለክታል? መንግሥት ምኅዳሩን በመክፈቱ እየተቆጨ ይሆን?

የሕግ ማሻሻያው ሒደት

የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ ባለፈው ዓመት ከተሰየመ ወዲህ በሥሩ በተቋቋሙ ግብረ ኀይሎች አማካይነት “አፋኝ” ናቸው የተባሉ ሕግጋትን ክለሳ ሲሠራ ቆይቷል። በክለሳው የተዳሰሱት የበጎ አድራጎት እና ሲቪል ማኅበራት አዋጅ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ፣ ሚዲያ ነክ ሕግጋት እና ምርጫ ነክ ሕግጋት ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ሥራቸው ተጠናቆ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሁንታ ለመፅደቅ የበቁት ሁለት አዋጆች ብቻ ናቸው፤ የሲቪል ማኅበራት አዋጅ እና የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የሁለት ዓመት ዕቅዱን በአንድ ገጽ ባወጀበት ጊዜ የፀረ ጥላቻ አዋጅ ለማውጣት መወሰኑን አሳውቆ ነበር። ሆኖም የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት እስከ ባለፈው ወር ድረስ አዋጁ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ አልነበረም። ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በድንገት ጉዳዩን የሚዲያ አጀንዳ አድርጎ አነሳው። በመንግሥት ይዞታ ውስጥ ያሉ ሚዲያዎች ሁሉ ስለ አስፈላጊነቱ መናገር ጀመሩ፤ ረቂቁም ለሕዝብ ይፋ ሆነ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከፈተውን የፖለቲካ ምኅዳር ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያዎችም ይሁን መደበኛ ሚዲያዎች ላይ በርካታ ውይይቶች እና በይዘታቸው አሳሳቢ የሆኑ ንግግሮች እየተስተናገዱ ነው። ምንም እንኳን ደረጃው የተጋነነውን ያህል ባይሆንም የጥላቻ ንግግር እያደገ መሆኑን መካድ አይቻልም። ይሁን እንጂ አዋጅ በማወጅ ለመከላከል መሞከር ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል።

አዋጁ ማንን ይጎዳል?

የፀረ ጥላቻ አዋጅ በማውጣት ችግሩን ከመሠረቱ መቅረፍ የማይቻልባቸውን ቢያንስ ሦስት ምክንያቶች ማስቀመጥ ይቻላል። አንደኛው የሕግ ቁርጠኝነት እና የማስፈፀም ብቃት አለመኖሩ ነው። ከዚህ ቀደም ያለው የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ‘አመፅ ቀስቃሽ’ ንግግሮችን በወንጀልነት ይፈርጃል።  የፀረ ጥላቻ ንግግር ረቂቅ አዋጁ ላይ የተቀመጠው ትርጉምም እንደሚያሳየው፣ የሚከለከለው አመፅ ቀስቃሽ የጥላቻ ንግግር ነው። ስለሆነም፣ የጥላቻም ይሁን አይሁን ‘አመፅ ቀስቃሽ’ የሆነ ንግግር ወንጀል እስከሆነ ድረስ ቁርጠኝነቱ እና አቅሙ ቢኖር ኖሮ አሁንም ያለው የሕግ ማዕቀፍ አመፅ ቀስቃሽ የጥላቻ ንግግሮችን ለመከላከል ይቻል ነበር።

ሁለተኛ፣ ከዚህ በፊት ያለው የሕግ አተገባበር ክፍተት አዲሱንም ተአማኒነት ያሳጣዋል። እንደሚታወቀው አስፈፃሚው አካል የፍትሕ አካላቱን በመጠምዘዝ ከአጥፊዎች ይልቅ የተቃዋሚዎቹን የንግግር ነጻነት ሲያፍን ከርሟል። ለዚህም ነው የሕግ የአስፈፃሚው አካል የአፈና መሣሪያ ሆኗል በሚል ወደ ክለሳ የተገባው። አሁንም ቢሆን፣ ተቋማቱ መልሰው በነጻነት እና ገለልተኝነት ባልተዋቀሩበት፣ ሕዝባዊ አመኔታ ባላተረፉበት እና አስተማማኝ ሚዛን እና ቁጥጥር በመንግሥት ቅርንጫፎች መካከል ባልተዘረጋበት ሁኔታ የንግግር ነጻነትን የሚገድብ አዋጅ ማውጣት ለአስፈፃሚው አካል መጠቀሚያ ከመሆኑም በላይ፥ የለውጡን ድባብ ይቀለብሰዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን የጥላቻ ንግግር አስተናግደዋል በሚል ዕውቆቹ የጋዜጣ እና ቴሌቪዥን ጣቢያ አዘጋጆች ቢከሰሱ፥ ንግግራቸው ከሚያመጣው ጉዳት በላይ የነርሱን መከሰስ በመቃወም ሊነሳ የሚችለው አመፅ ሊብስ ይችላል።

ሦስተኛው ችግር የጥላቻ ንግግር የሚናገሩት በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያሉት ብዙዎቹ ራሳቸውን ደብቀው የሚጽፉ እና አንዳንዶቹም ኢትዮጵያ ውስጥ የማይኖሩ መሆናቸው ንግግሩን ለመከላከል በጣም ውስብስብ ያደርገዋል። በዚህም ምክንያት የመንግሥት ቁጥጥርም ይሁን የአዋጁ መውጣት የሚፈጥረው የፍርሐት ስሜት ተፅዕኖ የሚያሳድረው በአገር ውስጥ ሆነው፣ በይፋ በሚጽፉት ሰዎች ላይ ነው።

እና ምን ይደረግ?

የፖለቲካ ምኅዳሩ መከፈት የልብ ልብ የሰጣቸው ግልብ የፖለቲካ አስተያየት ሰጪዎች፣ ታፍነው የከረሙ ሐሳባቸውን እንዴት ከጥላቻቸው ነጥለው መናገር የማያውቁ አማተሮች እና/ወይም አጋጣሚውን ተጠቅመው ሁከት በመፍጠር የፖለቲካ ትርፍ መሸመት የሚፈልጉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን የጥላቻ ንግግሮች እየተበራከቱ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ይህንንም መከላከል ያስፈልጋል። በሕግ ለመከላከል የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የማይፈቅድ ስለሆነ፥ የሚዲያ አረዳድ ግንዛቤን መጨመር እና የመረጃ ተደራሽነትን ከፍ ማድረግ የተሻሉ እና ያልተሞከሩ አማራጮ ናቸው።

የሚዲያ አረዳድ ግንዛቤን ማሳደግ አንደኛው መፍትሔ ነው። በኢትዮጵያ የሚዲያ ተደራሲዎች በመደበኛውም ይሁን በማኅበራዊ ሚዲያ የተነገረውን ነገር አምኖ መቀበል የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ ተደራሲዎች ሒሳዊ ግንዛቤ የሚወስዱበትን አቅም መገንባት/ማስተማር ያስፈልጋል። የሐሰት ወሬዎች የጥላቻ ንግግሮችን መጋቢ ናቸው። አንባቢዎች የሐሰት ወሬዎችን ከእውነተኛው፣ አስተያየቶችን ከዜናው የሚለዩበትን ክሕሎት ለመገንባት ከፍተኛ ተዳራሽነት ያላቸውን የመንግሥት ሚዲያዎች እና ከሲቪል ማኅበራት ጋር ጥምረት በመፍጠር ብዙኀኑ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሥራት ይቻላል።

የመረጃ ተዳራሽነትን ማሻሻል ሌላኛው መፍትሔ ነው። ብዙውን ጊዜ አመፅ የሚቀሰቅሱ እና የሐሰት ወሬዎች ከፍተኛ ተዳራሽነት የሚኖራቸው እውነታው፣ በተለይም ከመንግሥት ወገን ያለው ሳይታወቅ ስለሚቀር ነው። የመንግሥት ተቋማት አሠራራቸውን ሁሌም ግልጽ ቢያደርጉ እና ለማብራሪያ በተፈለጉ ጊዜ ሁሉ የሚገኙ ቢሆኑ ኖሮ እነዚህ የሐሰት የአመፅ ቅስቀሳ ወሬዎች በቀላሉ ይስተባበላሉ፣ ተደራሲዎችም አምነው አይቀበሏቸውም ነበር።

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሐፊውን እንጂ የ«DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።

 

Filed in: Amharic