>

ኑ . . . አብረን እንፀልይ ! (አሰፋ ሃይሉ)

ኑ . . . አብረን እንፀልይ !
አሰፋ ሃይሉ
*  እኛ ኢትዮጵያውያን ወገን ወገኑን እንዳይጠላ፣ ወገን ከወገኑ እንዳይበላላ የእምዬ ምኒልክ ግዝት አለብንና። ምክንያቱም እኛ የቴዎድሮስ አደራ አለብንና። ምክንያቱም እኛ የዮሐንስ አብነት አለብንና። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ሁላችን ያባቶቻችን በደም የተሳሰረ ህያው የወገንነት ቃል ኪዳን አለብንና።
አሁን – በዚህ ጊዜ – ወገን ወገኑን ፈራ? ወገን ወገኑን ጠላ ? – አዎ ጠልቷል። ትረካዬን የምጀምረው በዚህ ነው። መፍትሔ የምለውን ሀሳብ አቅርቤ እሰናበታለሁ።
አዎ ጥርጥር የለውም። ዛሬ ወገን ወገኑን ጠልቷል። ወይም እንዲጠላ፣ እንዲፈራ ሆኗል። ግን። ግን። በሀገራችን ወገን ወገኑን የጠላው እኮ እንዲህ ባንድ ጀምበር አይደለም። አሁን ፈልቶ ሲንተከተክ የምናየው ለዓመታት የተጠመቀልንን የጥላቻ ብቅል ነው። አሁን እያወራረድን የምንገኘው ለዓመታት የተጠነሰሰልንን የመለያየት ጌሾ ው። አሁን አቅላችንን እያሳተን ያለው ለዓመታት የተጠመቀልን ሀገራዊ አስካሪ አብሾ ነው። አሁን ላይ እያፋጀን ያለው ለዓመታት ማር እየላሰ ሲብላላብን የቆየው የጥላቻና የቁርሾ ብሔራዊ ቂጣ ነው።
ይህን ጥቂት በጥቂት ከተወዘተበት የህገመንግሥት ጋን እየቆነጠርን ለህዝባችን በጥብጠን ስንግተው የኖርነውን የመለያየትና የጥላቻ ድፍድፍ – ዛሬ ላይ እስካሁን ከሆነው ነቅተን – በጥበብ የላሰውን ማር በጥበብ አስቀርተን – ደፍረን ከተጠመቀበት ሀገራዊ እንስራ አንጋለን ካልደፋነው በቀር – ታዳሚዎቹ ትውልዶች የገባንበት ብሔራዊ ሥካራችን በቀላሉ ይለቀን ይሆን ወይ?!! (እያልኩ እሳቀቃለሁ – አንድዬ ተራዳኢ ፈጣሪያችን ይወቅልን እንጂ – በዚሁ ከቀጠልን – መጨረሻችንን በምናባቴ አውቄው?።)
መጨረሻችንን ባላውቀውም፣ ባናውቀውም – አሁን ዛሬ ላይ ቆሜ ግን – አንድ የምለው አብይ ቁምነገር አለ። ዛሬ በህይወት ያለን ኢትዮጵያውያን ሁሉ – ሁላችንም – ወደተሻለ የአብሮነት ህይወታችን መመለስ ከሻትን  መፍትሔው በእጃችን ያለ መሆኑን። መፍትሔው ምንድነው??!!
መፍትሔው ቀላል ነው። ሁላችንም የጥላቻን ጠላ ስንጠጣ ኖረናልና አንዳችንም እንኳ ባንድ ወይም በሌላ መልኩ ከሀገራዊ ስካሩ እንዳላመለጥን አምነን እንቀበል። እና በውስጣችን የረሰረሰውን መሪር የጥላቻ እንቆቆ ከውስጣችን ፍቀን እናውጣው። ወገን ወገኑን ይውደድ። ዘር ከልጓም አይሳብ። ሀገር ከጎጥ በላይ ይስፋ። ዕውቀት ከስሜት ልቆ ይስፋፋ። ሁሉም ኢትዮጵያዊ – ከዛሬው ለተሻለ – እጅግ ለተሻለ – ነገው ሲል – በፍቅር ስም – ስለ ፍቅር ብሎ – ትውልድ ይዳን በእኛ ይብቃ ብሎ ቆርጦ ይነሳ።
– ቁርሾና ቂም በቀልን እያሰቡ – ከፍርሃታቸው ለመደበቅ ሲሉ ጥቂት ፈሪ ፖለቲከኞች ተሰባስበው – ለዓመታት በኢትዮጵያውያ ሕዝብ ላይ የጫኑብንን ሀገራዊ የጭቆናና የክፍፍል ትርክት – ከነሰንኮፉ ነቅሎ ለመጣል ሁሉም ቀና አሳቢ ኢትዮጵያዊ በሙሉ ልብ ይዘጋጅ።
እኛን ኢትዮጵያውያንን – ታሪክ ካለያየን በላይ የለያየንን፣ ኑሮ ካራራቀን በላይ ያራራቀንን፣ ቋንቋና ዘር ካላግባባን በላይ እርስ በእርስ ያናከሰንን (እና የሚያናክሰንን) – ሐይማኖትና ዕምነት ካሰባጠረን በላይ እርስበርስ ያጠራጠረንን – ይሄን የብሔር፣ የጎሳ፣ የቋንቋ፣ የዘር፣ የዘርማንዘር አሻሮ በደከመ ጫንቃችን ላይ ያሸከመንን፣ ባልበላ አንጀታችን ሀሞቱን ባፍ በገደፉ የጎሰጎሰብንን – በጎሣ ልዩነት ላይ የተመሠረተ ህገመንግሥታዊ አሻሮአችንን – ለነገው የተሻለ ወገናዊ ኅብረታችንና አኗኗራችን ስንል – በሁላችን ኢትዮጵያውያን ቀና ትብብር – እና በሁላችን ኢቴዮጵያውያን ፅኑ ሠላማዊ ወገናዊ ትግል – ከነጥላቻው፣ ከነሥካሩ፣ ከነሸሩ፣ ከነደባው – ከሥሩ መንግለን ከላያችን ለመጣል ቆርጠን እንዘጋጅ። የጥላቻንና የመለያየትን ብሔራዊ ፅልመት ያለበሰንን ሀገራዊ የዳጉሳ ጠላ ከማዕዳችን ላይ ገሸሽ እናድርግ።
ካደረግን በኋላስ?? ሁላችንን በልዩነትና በክፍፍል ከረጢቱ አብሮ የከተተንን ጎሣዊ ህገመንግሥት በኢትዮጵያውያን ይሁንታና ፈቃድ ቀድደን ከጣልን በኋላስ??!! በምትኩ እንደምን ያለ ሀገራዊ ታዛ ሊኖረን ይችላል???
– ይሄማ ሳይታለም የተፈታ ነው። ጥላቻን የሚዘራብንን የነገር ብቅል በሌላ የነገርና አተካሮ ብቅል አንተካውም። የጥላቻንና የልዩነትን ጣሪያ የምንቀደው በምትኩ ሁላችንም የፍቅርን ፀሐይ ለማየት እንችል ዘንድ ነው። እንጂ ጥላቻን በሌላ ጥላቻ ለመተካት አይደለምና – በመለያየታችን ፋንታ ኅብረትን፣ በቂማችን ፋንታ እርቅን በመካከላችን የሚያወርድ የእውነት፣ የሠላም፣ የፍቅር ኢትዮጵያዊ ቃልኪዳን በመካከላችን እናቆማለን።
– ይሄማ ሳይታለም የተፈታ ነው። መለያየትን፣ ጎሰኝነትን፣ የብሔር ልዩነትን፣ የዘር የቋንቋ የሁሉ ነገር ልዩነትን የህልውናው ምንጭ በማድረግ ዜጎችን እርስበርስ እያናከሰ ሊኖር በላያችን በተሠራው የመለያየት ህገመንግሥት ምትክ – ፍቅርን፣ ኅብረትን፣ ወገናዊነትን፣ አብሮነትን፣ መረዳዳትን፣ አንዱ ለሁሉም – ሁሉም ለእያንዳንዱነትን ይዞ –  በኢትዮጵያውያን ደጋግ አባቶችና እናቶች መሐል ሀገራዊ የፍቅር ሰንደቁን ከፍ አድርጎ እያውለበለበ የሚቆምን የመዋደድ ሕገመንግሥት ሁላችን፣ ስለሁላችን፣ በሁላችን፣ እንቀርፃለን።
– ይሄማ ሳይታለም የተፈታ ነው። መለያየትን ቋሚ መሠረቱ አድርጎ በተተከለው ዘውጌያዊ ህገመንግሥት ምትክ ፦ የአብሮነትን፣ የአንድነትን፣ የወገንነትን፣ ያንዲት ሀገር ልጅነትን፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ ፈሪሃ እግዜርን፣ ፈሪሃ ህሊናን፣ ፈሪሃ ግፍን፣ ወገን ወዳድነትን፣ ህዝብን አክባሪነትን፣ ለሀገር ለወገን ውለታ መላሽነትን፣ ለወገን ተቆርቋሪነትን፣ ‘ሀገሬ አለሁሽ እማማዬ’ ብሎ ቋሚነትን፣ የእናት ሀገር ፍቅርን፣ መረዳዳትን፣ ለሀገር መሠዋትን፣ እጅ ለእጅ ተያይዞ ባንድነት ለእድገት መዘመርን፣ ተረዳድቶ መቆምን፣ አብሮ በፍቅር መኖርን… ለመጪው ትውልዳችንና ለእኛም ለአሁኖቹ ህያዋን የሚሰብክ፣ የሚናገር፣ የሚያሰርፅ የአዲሲቷን ብሩኋን ኢትዮጵያ የፍቅር ቃልኪዳን የሚያፀና አዲስ ህገመንግሥት እና ህገልቦና በኢትዮጵያችን ላይ ከፍ አድርገን ለመትከል ነዋ መነሣሣት ያለብን!!!!
እና ወገኔ – ለዓመታት ወገን ከወገኑ ጋር እንዲለያይ፣ እንዲጠላላ፣ እንዳይተማመን፣ እንዲባላ፣ በክፋት እንዲጠባበቅ፣ በጎሪጥ እንዲተያይ … በላያችን በተዘራብን የጥላቻ አብሾ ጨርሰን በስካራችን ነጉደን – በተለይ ዛሬ ፊደል ቆጥረናል የምንል ኢትዮጵያውያን ወገኖች – ለዝንተ ዓለም በየዋህነት፣ በፍቅር እና በጀግንነት የኖሩትንና አነሰችም በዛችም ይህቺኑ ምስኪኒቱን እናት ሀገራችንን ያቆዩልንን የዋሃን እናትና አባቶቻችንን አናስጨንቅ። ደምን አናፍስ። አናስለቅስ። አናንገላታ። ወገናችንን አናፈናቅል። አንግደል። አንቆሳሰል። እና ዛሬውኑ ልቦናችንን እናዘጋጀው።
ሁላችንም በዚህች ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላዬ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ሁሉ – ዛሬውኑ ልባችንን ለፍቅር እና ለለውጥ ካላጀገንነው … ለሶስት አሰርት ዓመታት የቃምነው የጥላቻ እንኩሮ – ህዝባችንን ሳያጫርስ – በቀላሉ እንደማይለቀን በምድራችን ላይ ዕለት በዕለት እየተሰማ ያለው የወገን ግፍ፣ እንደ ውሃ እየፈሰሰ ያለው የወገናችን ደም እየጮኸ እያረዳን ነው።
እና – አንዴ ብቻ ሳይሆን ደግመን ደጋግመን – ከጥላቻና ከመለያየት – ከመጋደልና ከመደማማት – አብረን እንውጣ። በአንድ ቃል – ከጠብና መጋደል ፍቅርና አብሮ መኖር አይሻለንም ወይ?? ኅብረት አይሻልም ወይ? አንድነት አይበጅም ወይ? ዜግነት ወገንነት አይበልጥም ወይ?? የሰውነት ዋጋው እጅግ ውድ አይደለም ወይ?? ሌላውን ሁሉ ፖለቲካ ትተን – ይህን ታላቅ ወገናዊነት እንደሐፈክር አንስተን ሁላችን ዛሬውኑ ለለውጥ ሰንቀን ብንነሣ እንደ ኢያሪኮ ጩኸት በጥላቻ አጥር የተለያየች ውዲቱን ምድራችንን በፍቅር ኃይል እናንቀጠቅጣለን።
እና ኖረን ኖረን ወደማይቀረው የሠማዩ ቤታችን ልንጓዝ ስንል በፈጣሪ የሚቀርብልን ጥያቄ ይህ ይመስለኛል ፦ እውን በህይወት ዘመናችን – ለፍቅር፣ በፍቅር፣ ወደ ፍቅር፣ ፍቅርን ታጥቀን – ባንድ ላይ መነሣት ትችሉ ነበረ ወይ?? ለምንስ በዕድላችሁ አልተጠቀማችሁበትም?? የሚል። የእኔም ጥያቄ ይሄ ነው። ራሴንም እሞግተዋለሁ። ፈጣሪንም እጠይቀዋለሁ። በፍቅር ጥላቻን ድል ማድረጌ እንችላለን ወይ ????
በበኩሌ – እኛ ኢትዮጵያውያን ይህን ለማድረግ እንችላለን የሚል ፅኑ (የፅኑ ፅኑ) ዕምነት አለኝ። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ወገን ወገኑን እንዳይጠላ፣ ወገን ከወገኑ እንዳይበላላ የእምዬ ምኒልክ ግዝት አለብንና። ምክንያቱም እኛ የቴዎድሮስ አደራ አለብንና። ምክንያቱም እኛ የዮሐንስ አብነት አለብንና። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ሁላችን ያባቶቻችን በደም የተሳሰረ ህያው የወገንነት ቃል ኪዳን አለብንና።
እና ይህን ሁሉ በትዕግሥት ያስተዋለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ – ዛሬ ላይ – ኑ እያመሠን ካለው የጥላቻ ድፍድፍ አብረን እንቃመስ አይልም። ከህሊናው የታረቀ የወገን ልጅ ኑ አብረን እንስከር አይልም። ከቀልቡ የሆነ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የገዛ ወገኑን ኑ አብረን እንጋደል፣ ኑ አብረን እንለቅ አይለውም።
ዛሬ ማለት የሚገባን – ኑ በላያችን ስለሆነብን ሁሉ አብረን እንዘን ነው። ኑ ስለመጋደላችንና መደማማታችን አብረን እናልቅስ ነው። ኑ ስላስነባናቸው እመበለቶቻችን አብረን ተቃቅፈን ወገን ከወገን ጋር በእንባ እንረጫጭ ነው። ኑ እያመከንን ስላለነው የመጪ ህፃናት ተስፋ አብረን ተጋግዘን በሀዘን ጎርፍ እንራስ ነው ማለት ያለብን። ኑ አብረን ሟቾቻችንን እንቅበር ነው ማለት የሚገባን።
አዎ። ኑ አብረን እርማችንን እናውጣ። ኑ አብረን የፈጣሪን ምህረት እንለምን። ኑ አብረን እንፀልይ። እና – ኑ ጥላቻን በፍቅር አብረን ድል እንንሳ!
“We are sailing
We are sailing
Across the sea,
The Holy waters
To be near you
To be free!
To be near you,
To be free!”
  (- A song by Rod Stewart, GREATEST HITS, #SAILING )
ፈጣሪ ኢትዮጵያችንን ይባርክ። ከጥላቻም እኛን ልጆቿን ይፈውስ።
Filed in: Amharic