>
5:13 pm - Wednesday April 18, 1432

ከድጡ ወደማጡ (ከይኄይስ እውነቱ)

ከድጡ ወደማጡ

ከይኄይስ እውነቱ

በቅድሚያ በሰሜን ሸዋ እና በወሎ ክፍላተ ሀገራት በተፈጸመው ጦርነት-አከል የሽብር ተግባር የሞቱ ወገኖቻችን ነፍስ ልዑል እግዚአብሔር ዕረፍተ ነፍስን ይስጥልን፡፡ ዜጎች በሙሉ የተጎዱ ወገኖቻችንን ባስቸኳይ እንታደግ፡፡ መንግሥት ካለ÷ የአገር መከላከያ ሠራዊት የሚባል ኃይልም ካለ (በኦሕዴድ የሚመራው ማለቴ ነው) ፣ አሸባሪዎቹን በሚገባ ያውቃቸዋልና (መግለጫና ውግዘት አንፈልግም) ያለምንም ማድበስበስ የሚደመሰሱትን ደምስሶ፣ በቊጥጥር ሥር የሚያውላቸውን እና አመራር የሚሰጧቸውን የጐሣ ነጋዴዎች በሙሉ ባስቸኳይ ለፍርድ አቅርቦ ተገቢውን ፍትሕ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማሳየት ይኖርበታል፡፡

ግራ በተጋባ አገር ውስጥ ያሉን ግዙፍ አገራዊ ችግሮች እንደተጠበቁ ሆነው፤ የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን የሚያውኩን ነገሮች ደግሞ አያሌ ናቸው፡፡ ለዛሬው በሦስት መንግሥታዊ ተቋማት የታዘብኩትን በጥቂቱ እነሆ፡፡

1ኛ/ የኤሌክትረክ ኃይል

በወያኔ አገዛዝ በችግር ፈጣሪነቱና ከሕዝብ ጥቅም በተቃራኒ በመሥራት በግንባር ቀደምትነት የሚታወቀው ይህ (notorious) ድርጅት ጥቂት መሻሻሎችን አድርጓል ብለን ስናስብ ማሻሻያው የቅብ ነው መሰለኝ ይኸው የቀደመው ‹በሽታው› አገርሽቶበት ከሁለት ሳምንታት ወዲህ በአዲስ አበባ አንዳንድ ክ/ከተሞች በተለይም በቂርቆስ ክ/ከተማ ነዋሪው ችግር ውስጥ ይገኛል፡፡ ሕዝብ አቤቱታውን የሚያሰማበት ነፃ የስልክ መስመር ጭምር የተዘጋ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በአካባቢዬ ነዋሪ ከሆኑ በርካታ ግለሰቦች መስመሩን በጭራሽ ለማግኘት እንዳልቻሉ ለመረዳት ችዬአለሁ፡፡
በተለይም የበልግ ወቅት እንደመሆኑ ዝናብ ይጠበቃል፡፡ ገና ትንሽ ካፊያ ሲጀምር (አስቀድሞም በቋፍ ያለው ድርጅት) ወዲያውኑ ድርግም ያደርገዋል፡፡ የዝናቡ ወራት ሲገባ ምን ልንሆን ነው? በአካል ሂዶ ‹አቤት› ማለት ትርጕም እንደሌለው ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ርእስ በጻፍኩት አስተያየት ስለገለጽኹ አልመለስበትም፡፡ ብልሽት ሳይኖር ለይቶ የተወሰነ አካባቢ ማጥፋትና ለዚህም በቂ ምክንያት በብዙኃን መገናኛ አለመስጠት ዜጋን የመናቅ ምልክት ካልሆነ ምን ማብራሪያ እንደሚሰጠው ግራኸኸኸኹሀጀ ገብቶናል፡፡ ተራውም ሠራተኛ ሆነ ኃላፊዎች መሥራት/ማሠራት ካልቻሉ ድርጅቱን በበላይነት የሚመራው መንግሥታዊ አካል የሚጠብቀው ምንድን ነው?

2ኛ/ የኢምግሬሽንና ዜግነት መምሪያ

ሰሞኑን ፓስፖርት ለማሳደስ ወደዚህ መ/ቤት ጎራ ብዬ ነበር፡፡ የፓስፖርት ዕድሳቱን የፈለግኹት አንድም የአገልግሎት ጊዜው ሊያበቃ ጥቂት ወራት የቀረው በመሆኑ ሲሆን፣ ዋና ምክንያቴ ግን ቀደም ብዬ ሳደርግ እንደቆየሁት ወያኔ ያለፍላጎቴ የሰጠኝን የጐሣ መታወቂያ ካርድ ላለመጠቀምና በምትኩ ስምና ዜግነት የሚጻፍበትን ዓለም አቀፍ የመጓጓዣ ሰነድ እንደመታወቂያም ስለምጠቀምበትና የተለያዩ አገልግሎቶችም ስለማገኝበት ነው፡፡

የተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ወደኋላ ለመሄድ በማፈግፈግ ላይ ያለ ይመስላል፡፡ እንዴት? ቀደም ሲል ለፓስፖርት ዕድሳት የሚወስደው ጊዜ 3 ቀናት ነበር፡፡ አሁን ‹ተሻሽሎ› 2 ወራት ሆኗል፡፡ የተሰጠኝ ምክንያት ፓስፖርት ታትሞ የሚመጣው ከውጭ በመሆኑና ባሁኑ ሰዓት በበቂ ቊጥር ስለሌለን የሚል ነው፡፡ ይህንኑ የነገሩን የተቋሙ ሠራተኞች በዛው አንደበታቸው የዕድሳቱን አገልግሎት ለማግኘት በሂደት ላይ ላለው ተገልጋይ እንዲህ ሲሉ ተደምጠዋል፤ የታደሰ ፓስፖርታችሁን ባስቸኳይ (በ3 ቀናት) ለመውሰድ የምትፈልጉ ከሆነ ከ2 ሺህ ትንሽ ከፍ የሚል ገንዘብ ከፍላችሁ መውሰድ ትችላላችሁ ብለዋል፡፡ በመደበኛነት ለዕድሳት የሚከፈለው ብር 600 (ስድስት መቶ ብር) ነው፡፡ ይህንን ካዳመጥኹ በኋላ 2 ሺህ ብር መክፈል ለቻለ ሁሉ የታደሰውን ፓስፖርት በ3 ቀናት ማግኘት ይቻላል ወይ ብዬ ስጠይቅ ያገኘሁት መልስ አዎንታዊ ነው፡፡ ስለሆነም ችግሩ የፓስፖርት መኖር/አለመኖር ሳይሆን ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ነው ብዬ ላነሳሁት ጥያቄ ግን መልስ ለማግኘት አልቻልኩም፡፡

ሌላው ከፓስፖርት ዕድሳቱ  ጋር ያየሁት ችግር በተለያዩ ምክንያቶች የአገልግሎት ጊዜው ያለፈበት ፓስፖርት ይዘው የመጡ ዜጎች የሚስተናገዱበት ሥርዓት ያልያዘ፣ ወጥነት የሌለውና ግልጽነት የጎደለው አሠራር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በተገልጋዩና በመ/ቤቱ ሠራተኞች መካከል ፍጹም መጯጯህና መደናቆር አስተውዬአለሁ፡፡ ይህም የሆነበት ዋና ምክንያት ተገልጋዩ ሊያሟላ የሚገባቸውን ሰነዶችም ሆኑ ሌሎች ፎርማሊቲዎች የኢሚግሬሽን ሕጉን መሠረት አድርጎ የወጣ መመሪያ አለመኖር፤ ካለም በቅድሚያ ለሚመለከታቸው የመ/ቤቱ ሠራተኞች በቂ ገለጻ (orientation) አለመስጠት፤ ለተገልጋዩም በግልጽ ስፍራ በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ በጉልህ በመጻፍ ወይም በራሪ ወረቀቶች በማዘጋጀት የማሳወቅ አሠራር አለመኖር ይመስለኛል፡፡ ባንፃሩም በዚህ ረገድ ወጥ የሆነ መመሪያ ከሌለና በሚጠየቁት መረጃዎች ሕጋዊነት አለመተማመን ካለ ግልጽ አለማድረጉም ሆን ተብሎ ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት የሚሰጡም አሉ፡፡

ከዚሁ መ/ቤት ሳልወጣ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተመድበው የሚሠሩ አንዳንድ የኢምግሬሽን ሠራተኞች በውጭ ጉዞ ላይ እየፈጠሩ ያሉትን መሰናክል በተለይም ወደ አረብ አገራት የሚሄዱ ዜጎችን (በቤት ሠራተኝነት እና ለስደት ሳይሆን ለንግድና ለተለያዩ ጉዳዮች) በጭፍንና በደፈናው የመከልከል አዝማሚያ ይታያልና በቶሎ ሊታረም ይገባዋል፡፡ ወደተለያዩ አረብ አገራት በቤት ሠራተኝነት እና በስደት የሚሄዱ ልጆቻችንን መብት ለማስከበርና ጉዞአቸውንና ቆይታቸውን ሕጋዊ የማድረጉ ቁጥጥር ጥናትን መሠረት አድርጎ መፍትሄ የሚበጅለት እንጂ ሕጋዊ ጉዞን ለመከልከል በመመሞከርና የመዘዋወር ነፃነትን በመገደብ አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ስለሆነም መ/ቤቱ በአየር ማረፊያው ላሠማራቸው ሠራተኞች በቂ ሥልጠናና ገለጻ ሊሰጥ ይገባል፡፡

3ኛ/ በቂርቆስ ክ/ከተማ የመሬት አስተዳደር ጽ/ቤት

ከጥቂት ወራት በፊት ያንድ ጓደኛዬ አባት ዐርፈው በፍ/ቤት የተሰጠ የወራሽነት ማረጋገጫና ተጣርቶ የጸደቀ የውርስ ሀብት ሪፖርት በመያዝ በእናታቸው እና በወራሾች ስም የቤት ስም ዝውውር አገልግሎት ለማግኘት በተጠቀሰው ጽ/ቤት ተገኝቼ ነበር፡፡ ወደ ፍሬ ጉዳዩ ሳልገባ ትዝብቴ የጀመረው በየደረጃው በኃላፊነት የተቀመጡት የጽ/ቤቱ ሠራተኞች አለባበስ ነበር፡፡ ምንም እንኳን የሰው ማንነት በልብሱ ባይመዘንም እንደውሎአችን የአለባበስ ሥርዓት (clothing etiquette) አለን፡፡ ይህም በማኅበራዊ ሕይወት በሌሎች ዘንድ ኃላፊነት የሚሰማው ሆነን እንድታይ ይረዳናል፡፡ በተለይም በሥራ ቦታ (ከዛም ደግሞ ለሕዝብ አገልግሎት በሚሰጥበት ቦታ) በካናቴራ/ቲ-ሸርት እና በጂንስ ተጣብቆ (በተለይም ወንድም ሴትም መቀመጫቸውን አጋልጠው የሚያሳዩበት አለባበስ ከማኅበራዊ ደንብ የወጣ ነው) መታየት ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ጸጕርንም አንጨፍሮ መታየትም ለማኅበራዊው ደንብ ተቃራኒ ይመስለኛል፡፡ ነፃነት በቦታና በጊዜ እንደሁኔታው ለጋራ ጥቅም ሲባል በፈቃደኝነትና በሕግ አስገዳጅነት ገደብ ይደረግበታል፡፡ በኃላፊነት ያሉ ደግሞ ለተራው ሠራተኛም አርዓያ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተወሰነ መልኩ ለሥራ ዋጋ የመሰጠት ወይም ሥራን የማክበር ምልክትም ሆኖ ይታያል፡፡ ይህ አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ ወደ አገልግሎቱ መስተንግዶ ስመለስ፤ 1/ ከሁሉም በላይ ቅንነት መጓደል፤ 2/ ባለጉዳይን ትኩረት ሰጥቶ አለማናገር፤ 3/ በቂና የተሟላ መረጃ አለመስጠት፤ 4/ አንድ ሠራተኛ በሕማም ወይም በተለያዩ ምክንያቶች የሥራ ገበታው ላይ ሳይገኝ ሲቀር በምትኩ ሰው ከመመደብ ይልቅ (ወይም ሌሎች ሸፍነው እንዲሠሩ ከማድረግ ይልቅ) ሰው የለንም በሚል ተያያዥነት ያላቸው አገልግሎቶች ለቀናት አንዳንዴም ለወራት ይስተጓጎላሉ፡፡ 5/ ቀጠሮ ለመቀበል እየተመላለሳችሁ ጠይቁ ማለት ከታዘብኳቸው ጉድለቶች መካከል ይገኙበታል፡፡

አንድ የመንግሥት ተቋም ከሚያስተናግዳቸው ተገልጋዮች ጉዳይ ተመሳሳይነትና ድግግሞሽ ተነስቶ በጉዳዩ ውስጥ የተካተቱ የሥራ ሂደቶችን፣ እያንዳንዱ የሥራ ሂደት ለማከናወን የሚወስደውን አማካኝ ጊዜ፣ ለአገልግሎቱ የሚፈጸመውን ክፍያ መጠን፣ ጉዳዩ የመስክ ሥራ ካለውም ባለሙያዎች መቼና በምን ሰዓት አገልግሎቱን እንደሚሰጡ ከዚህም ጋር የተያያዙ ክፍያዎችን፣ ባጠቃላይ ጉዳዩ ከመነሻው እስከ ፍጻሜው በአማካይ ግምት ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ መረጃ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፤ ወይም ይህንኑ በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ በመጻፍ ወይም በበራሪ ወረቀት አማካኝነት ለተገልጋዩ ማሳወቅ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ሁሉ ራሳቸውን ቢፈትሹ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይህን መ/ቤት ጨምሮ በሌሎችም የአስተያየት መስጫ ሳጥኖች እንዲሁም የቅሬት ማሰሚያ ሥርዓቶች ከመዋቅር አኳያ ተዘርግተው ይታያሉ፡፡ ይሁን እንጂ ባግባቡ ግዴታቸውን ሲወጡ አይታይም፡፡ ተገልጋዩም ጉዳዬ ይደናቀፍብኛል በሚል ሥጋትና ፍራቻ ኃላፊነታቸውን ባግባቡ ከማይወጡ ሠራተኞችም ሆኑ ኃላፊዎች ጋር መላተሙን አይፈልግም፡፡ ላገር ለወገን መጨነቅና መሥራት እያንዳንዳችን ከተመደብንበት ሥራ እና በኃላፊነት ከተቀመጥንበት ቦታ ይጀምራልና ለሰው ክብር በመስጠትና በማስተዋል መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል፡፡

Filed in: Amharic