>

የጥላቻ ንግግርን የሚከለክል ሕግ ሲወጣ….(ውብሸት ሙላት)

የጥላቻ ንግግርን የሚከለክል ሕግ ሲወጣ…..
 
ውብሸት ሙላት
 
መንደርደሪያ
የጥላቻ ንግግር፣ እጅግ ብዙ የሆኑ በጎ ዕሴቶችን ለመናድ መንደርደሪያ ነው፡፡ የጥላቻ ንግግር፣ ጥላቻ ላይ የተመሠረቱ ወንጀሎችን (Hate Crimes) መጥሪያ ነው፡፡ የጥላቻ ንግግር፣አድልኦ እና መገለልን ያመጣል፡፡ የጥላቻ ንግግር፣የአንድን ብሔር አባላት፣የሃይማኖት ተከታዮች፣ስደተኞችን እና ሌሎች ቡድኖችን እንበለ ምክንያት በጭፍኑ እንዲጠሉ መንገድ ያለሰልሳል፡፡ የከፋው ደግሞ የዘር ማጥፋትን ወይንም ቡድን ጠረጋን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በበርካታ አገራትም ተከሥቶ ነበር፡፡
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አይሁዶችን የጀርመን ናዚዎች ከማጥፋታቸው በፊት በርካታ አይሁዶች በጀርመን እና ሌሎች አገራት በተሻለ የኑሮ ደረጃ ይመሩ ስለነበር እንደ ባለጠጋ ጥገኛ ተሕዋስያን (wealthy parasite )ተደርገው ተሥለዋል፡፡ ጀርመኖች ደግሞ ከሌሎች የላቁ እንደሆኑ እራሳቸውን ቆጥረዋል፡፡ ሁቱዎች፣  በረሮ እንጂ ቱትሲዎች ብሎ መጥራት አቁመው ነበር፡፡
ይኽ እንግዲህ ጥላቻው በሕዝብ ደረጃ ከፍ ባለበት ወቅት ነው፡፡ አጠራሩንም አንዱ ቡድን  በጅምላ የሌላውን ተቀብሎ አጽድቆታል ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱን ፍረጃም ይሁን ስያሜ መነሻው እውነት እንዲሆን አይጠበቅም፡፡ ሕዝቡም የሚጋራው በምክንያታዊነት፣ ዐስቦ እና አሰላስሎ አይደለም፡፡ ምክንያታዊነት የግለሰብ ባሕርይ እንጂ የሕዝብ አይደለችም፡፡  ቡድንን ጅምላዊነት ያጠቃዋል፡፡ እንደ ግለሰብ ሲታሰብ ወለፈንድ እና ሐሰት መሆኑን የምንረዳውን ነገር፣ ከቡድናችን ጋር ስንቀላቀል ግን እንተወዋለን፡፡ የጥላቻ ንግግርም ቡድናዊ ቅርጽ ለመያዝ በእጅጉ የተጋለጠ ነው፡፡ ታሪክም ያሳየን ይሄንኑ ነው፡፡
በርካታ አገራት ከራሳቸውም ገጠመኝም ይኹን ከሌሎች የታሪክ ጠባሳ በመማር የጥላቻ ንግግሮችን የሚከለክሉ ሕግጋት አውጥተዋል፤ ተግባራዊ ለማድረግም ተቋማትን አደራጅተዋል፡፡
የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራትም የጥላቻ ንግግር ምንነቱን፣ ይዘቱን፣ መንስኤውን፣ መዘዙን እና ሌሎችም ጭብጦች ላይ በመመርኮዝ ጥናት ያጠናሉ፤የፍትሕ ተቋማትን ያሰለጥናሉ፤ ሕዝብን የማንቃት ሥራ ይፈጽማሉ፡፡ ብሎም፣ ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ለመገንባት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ በዚህ መንገድ ብዙ ማኅበረሰቦች በሠላም እና በመቻቻል እንዲኖሩ እያደረጉ ነው፡፡ 
 
የጥላቻ ንግግር ምንነት እና መለያዎቹ
የጥላቻ ንግግርን ምንነት በተመለከት ቁርጥ ያለ እና ወጥ ብያኔ የለም፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ ብያኔዎች የሚጋሯቸው ነጥቦች አሉ፡፡ በመሆኑም ማንኛውም የዘር ጥላቻን፣ የሌላ አገር ዜጋን ወይንም ስደተኛን በጭፍኑ መጥላትን፣ጸረ-ሴማዊነትን፣ ትዕግስት አልባ እና አግላይ የሆነ ብሔርተኝነትን፣ ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ብሔረሰቦችን ሰበብ እየፈለጉ መገለል እንዲደርስባቸው የሚሰብኩ፣ የሚያሰራጩ፣ የሚያነሳሱ፣ የሚያበረታቱ እና ትክክል እንደሆኑ ለማስረዳት የሚደረጉ ጥረቶች የያዙ ቃላዊ ገለጻዎች፣ ጽሑፎች፣ ምስሎች እና ሥዕሎች፣ቅርጻ ቅርጾች በሙሉ የጥላቻ ንግግር ይሰኛል፡፡
 ስለሆነም ንግግር (Speech) የሚለው ቃል ድምጽን ብቻ የሚያመለክት አይደለም፡፡ በዚህ ጽሑፍም ውስጥ የጥላቻ ንግግር ሲባል ድምጽን፣ጽሑፍን፣ምስልን፣ቅርጻ ቅርጽን፣የድምጽ እና ምስል ቅንብሮች፣ካርቱኖችን ያካትታል፡፡
የጥላቻ ንግግር አድራጊው የተለያዩ ቡድኖችን ባላቸው ማኅበራዊ መሠረት እና አቋም ወይንም ርእዮተ-ዓለምም ላይ በመመርኮዝ እነዚህ ቡድኖችን በጥቅል ወይንም በተናጠል አባሎቻቸውን መገለል እና መድልኦ እንዲደርስባቸው ማድረግ ነው፡፡  እንደ አይሁዶች፣ ቱትሲዎች፣ ጂፕሲዎች፣የአውስትራሊያ ነባር ሕዝቦች ብሔርን መሠረት ሊያደርግ ይችላል፡፡
በበርካታ አውሮፓ እና ሌሎች አገራትም እንደሚፈጸመው ሃይማኖታዊ መነሻ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ቀለም ላይ የተመሠረት ጥቁሮች ላይ እንደደረሰው ሊሆን ይችላል፡፡የጥላቻ ንግግር ውጤቱ ከማኅበራዊ ተቋማት ኢኮኖሚያዊ መስክ እንዲገለሉ ወይንም እንዳይሳተፉ ማድረግ፣ሲካፋው እንዲገደሉ ሊያደርግ ይችላል፡፡
በአጭሩ ዘርን፣ብሔርን እና ሃይማኖት እና እንደ ስደተኛነት ያሉ ማኅበራዊ መሠረቶችን ምርኩዝ አድርጎ የሚፈጸሙ ንግግሮች ከጥላቻ እስካልጸዱ ድረስ ወይንም ጥላቻ ካዘሉ የጥላቻ ንግግር ይባላሉ፡፡ሕግም ሲወጣ ይሄንኑ ለመከልከል ነው፡፡ ተናጋሪውንም፣ ጥላቻን ያዘለ ንግግር ካደረገ  የወንጀል ኃላፊነት እንዲኖርበት ያደርጋል፡፡
 ይሁን እንጂ የጥላቻ ንግግርን በቀላሉ መለየት አዳጋች ነው፡፡ አዳጋችነቱ የንግግሩ ሰለባ ለሆነው አይደለም፤ለሌላ ወገን እንጂ፡፡ በማር የተለወሰ ንግግር ሆነው የመቀርቡ አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ቅኔያዊ ንግግሮች ይሆኑና ስናነባቸው ወይንም ስንሰማቸው ወይንም ስናያቸው በአንዴ የማናስተውላቸው አሉ፡፡
እንዲህ ዓይነቶቹን፣ ከአውሮፓዊው የሕግ አተረጓጎም ልማድ የሚሳየን በዚህ መጠን የንግግር ነጻነት መገደብ ተገቢ አይደለም በሚል ምክንያት የሚያስቀጡ አለመሆናቸውን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጥላቻ የሌላቸው መሆናቸውን አያሳይም፡፡ 
 
ስለጥላቻ ንግግር የአሜሪካ መንገድ
አሜሪካ ትልቅ ቦታ የምትሠጠው ዕሴት ቢኖር ነጻነት (Liberty)  ነው፡፡ ነጻ ንግግር  ደግሞ አንድም የሰው ልጅ ህልውና አካል ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ነጻነት እና ዴሞክራሲ ያለ ነጻ ንግግር ምንጊዜም ጎደሎ እንደሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም፣ የአሜሪካ መርሕ ነጻነትን እራሱን የሚያጠፋ እስካልሆነ ድረስ ንግግር ላይ ገደብ አይኖርም፡፡ በተለይም ደግሞ የንግግሩ ይዘት ጥላቻን ያዘለ ነው በሚል ሰበብ ብቻ ክልከላ የለም፡፡
ገደብ የሚደረገው ንግግሩ የሚደረገበትን ዐውድ በማየት ይሆናል፡፡ የተደረገው ንግግር የኃይል ድርጊት ላይ የተመሠረተ ሕገ ወጥ ድርጊት ለማስነሳት ቅርብ ከሆነ ሊገደብ ይችላል፡፡ ካልሆነ ንግግርን መልሶ በንግግር በመጋፈጥ እንጂ በመገደብ እና በማፈን ዴሞክራሲ አይሰፍንም፣የሚል አካሔድ ነው የአሜሪካ፡
 
የብዙኃኑ መንገድ
በርካታ አገራት ከአሜሪካ የተለየ መንገድ ነው የሚከተሉት፡፡ አገራት ለተለያየ ዕሴት ቅድምና ይሰጣሉ፡፡ የዕሴቶቻቸው መነሻ ደግሞ የራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡ ለአንዳንዶች እኩልት፣ለሌሎች ሰብአዊ ክብር፣ ወይንም ተከባብሮ እና ተፈቃቅዶ መኖር ወይንም የእነዚህ ቅይጥ ሊሆን ይችላል፡፡
እኩልነትን የሚያስቀድሙት አንድን ግለሰብ ከሌላ ጋር ለሚኖረው ግንኙት ትኩረት ይሠጣሉ፡፡ ስለግለሰቡ ነጠላ ሕይወት ወይንም ምርጫ ሳይሆን ከሌሎች ጋር የሚኖረው መስተጋብር ነው ዋና ማጠንጠኛቸው፡፡ ሰብአዊ ክብርን የሚመርጡ ደግሞ ማንም ሰው የሌላውን ስም ሳያጎድፍ፣ ሳያንኳስስ፣ ሳያጣጥል፣ ሳያገልል ወዘተ እንዲኖር እና መከባበር እንዲሰፍን ይመርጣሉ፡፡ በቡድኖች መካከል የሚኖር ተከባብሮ እና ተፈቃቅዶ መኖርን የሚመርጡም አሉ፡፡
ለእነዚህ ዕሴቶች ከፍተኛ ቦታ ለሚሠጡ አገራት  ነጻ ንግግር ለእነዚህ ዕሴቶች ማጎልመሻ እንደምትሆን ይጠበቃ፡፡ ስለሆነም ሰብኣዊ ክብርን የሚነካ፣ ተቻችሎ እና ተፈቃቅዶ የሚኖርን ማኅበረሰብ እንዳይኖር እንከን የሚሆን፣ በማኅበረሰብ መከካል ያለው የባህል ሥሪት አንዱ ከአንዱ የሚበልጥ እንደሆነ የሚሰብክ ንግግር እንዲኖር አይፈቀድም ወይንም አይበረታታም፡፡
የኢትዮጵያንም ሕገ መንግሥት ስናጤነው ትልቁ ዕሴቱ የግለሰቦች ነጻነት ላይ የተመረከዘ እና ግለሰብ ዜጎችን ነጻነት ሳይሆን የብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እኩልነት እና ተከባብሮ እና ተፈቃቅዶ መኖርን የመረጠ ስለሆነ ነጻ ንግግር ወይንም ሐሳብን በነጻነት መግለጽ ለእነዚህ ዕሴቶች ተገዥ መሆኗ ግድ ነው፡፡ የአውሮፓውያኑም መንገድ ይኼው ነው፡፡
ከአሜሪካን ውጭ ያሉት አገራት በሙሉ የጥላቻ ንግግርን ወንጀል አድርገዋል ማለት አይደለም፤  ያደረጉትም ቢሆኑ ተመሳሳይ ይዘት የላቸውም፡፡ ወንጀል ያደረጉበት ነባራዊ ምክንያትም ይለያያል፡፡ ወንጀል እንዲሆን በተለያዩ ምሁራንም የሚቀርበው ክርክር እንዲሁ ወጥ አይደለም፡፡ ወንጀል የሆነባቸውም አገራትም ሕጎቻቸውን እንዲሰረዙ የሚቀርብ ክርክር እና ውትወታ አለ፡፡
የጥላቻ ሕግ የሚከለክል ሕግ የማዉጣትን ትርፍ እና ኪሳራዎቹን ለመለየት በሁለቱም ጎራ ከሚነሰት መከራከሪያዎች የተወሰኑትን ብቻ ላቅርብ፡
 
ንግግር፣ የጥላቻም ቢሆን ወንጀል መሆን የለበትም ባዮች
የመጀመሪያው መከራከሪያቸው ንግግርን ወንጀል በማድረግ ከሚገኘው ጥቅም ይልቅ፣ ጥላቻ ባለው ንግግር የሚፈጠረውን ጉዳት መታገስ የሚያስገኘው ይበልጣል፤የሚል ነው፡፡
ንግግርን ማፈን በርካታ መብቶችን እንዲጣበቡ ያደርጋል፤በርም ይከፍታል፤ ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውም መጥፎ ሐሳብ የሚጠፋው እና ማምከኛ ሊሆን የሚችል ተቃራኒ ሐሳብ በማቅረብ እንጂ ንግግሩን በመከልከል አይደልም፤ መንግሥትም የምንናገረውን ነገር ይዘቱን ሊመርጥልን አይገባም፤ ግለሰቦችም ክፉን ከበጎ ለይቶ የማወቅ አቅምም ችሎታም ስላላቸው ይሄንኑ ነጻነታቸውን ማክበር ተገቢ ነው፡፡ ሕግም ቢሆን ክፉ የማሰብንና እና የመናገርን ባሕርይን ሊቀይር አይችልም፤ስለሆነም ወንጀል ማድረጉ ፋይዳቢስ ነው ይላሉ፡
 
የጥላቻ ንግግር ይከልከል የሚሉት መከራከሪያዎች
ጥላቻን ያዘለ ንግግር በብዙ ምክንያት ጠቃሚ አይደለም፣አስጸያፊ ነው ይላሉ፡፡ ለዚህ ከሚያቀርቡት ምክንያቶች ውስጥ የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የንግግሩ ሰለባ የሚሆኑትን የአንድ ቡድን አባላት እንደ ጠላት እንዲቆጠሩ ያደርጋል፤ ለብዙ ነገሮች ተጠርጣሪዎች እንዲሆኑ ያመቻቻል፡፡
ሌላው መከራከሪያ ደግሞ ከሌሎች የማኅበረሰብ አባላት በእኩልነት አይታዩም፡፡ ለምሳሌ እንደ ተገንጣይ የሚሳሉ ከሆነ የመገንጠል ፍላጎት ከሌላቸው ጋር እኩል ተደርገው አይታዩም፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ፣በማሕበራዊ አቋማቸው ዝቅ ተደርገው እንዲታዩ ያደርጋል፡፡
 ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር  የተረጋጋ እና ቅንነት የተሞላባት ግንኙነት እንዳይኖር እንቅፋት ይፈጥራል፡፡ በግለሰቦች እና በቡድኖች መካከልም ጥርጣሬ እና ውጥረት እንዲሰፍን ያደርጋል፡፡  አንዱ የሃይማኖት ተከታይ ወይንም የብሔር አባላት የበለጠ ለአገር አሳቢ ሌላውን ጠላት አድርጎ የመሳል አዝማሚያን ይፈጥራል፡፡
ችሎታቸውን እና አቅማቸውን በተገቢው ሁኔታ እንዳይጠቀሙ ያደርጋል፤ የተወሰኑ ሰዎችን ባሕርይ ለጠቅላለው የማሳደግ አዝማሚያን ስለሚያበረታታ የቡድኑን አባላት በሙሉ ተጠቂና ሰለባ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም ጥላቻ አዘል ንግግር መከልከል አለበት ይላሉ፡፡
 
የንግግር ነጻነት የሚገደብባቸው ምክንያቶች
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(6) ላይ በማያሻማና በግልጽ ቋንቋ እንደተገለጸው ሐሳብን በፕሬስና በማናቸውም መገናኛ ብዙሃን ማንኛውም ሰው ሲገልጽ የሐሳቡ ይዘት ምንም ይሁን ምን፣ ሐሳቡ በመገለጹ የሚያስከትለው ውጤት ምንም ይሁን ምን፣ መከልከል አይቻልም፡፡ ይዘቱንም የሚያስከትለዉንም ዉጤት (Content and Consequence) መሠረት አድርጎ የንግግር ነጻነትን መገደብ አይቻልም፡፡
ከዚህ የምንረዳው አንዱ ነጥብ አንድን ቡድን ( ምሳሌ ብሔር) ባህል የሚተች ይዘት ያለው ጽሑፍ ማተም ወይንም ማሰራጨት አይቻልም የሚል ሕግ ሊኖር አይችልም፡፡ በመሆኑም ይዘቱን መሠረት በማድረግ ሐሳብን የመግለጽ ክልከላ አይኖርም ማለት ነው፡፡
 ሁለተኛው ደግሞ አንድ ጽሑፍ ታትሞ በመውጣቱ የመንግሥትን ተአማኒነት ያሳጣል በማለት መከልከል አይቻልም፡፡ ጠንከር ስናደርገው ደግሞ አንድ ጽሑፍ  መውጣቱ አንድን ብሔር ከሌላው ጋር ሊያግጭ ይችላል በሚል ምክንያት ክልከላ አይኖርም፡፡ የሚከለክል ሕግም ማውጣትም አይቻልም፡፡ ይህ ደግሞ የሚያስከትለውን ዉጤት በማሰብ ብቻ መገደብ አይቻልም ማለት ነው፡፡ ወንጀል ማድረግማ ፈጽሞ አይታሰብም!!!!
 
በሕግ የሚገደብባቸው ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸዉ፡፡ 
 
እነዚህም፡- 
 
የወጣቶችን ደህንነት የሚያናጉ፣
 
 የግለሰብን መብት የሚጥሱና ሰብኣዊ ክብርን  የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን ማድረግ፣
 
 የጦርነት ቅስቀሳ ማድረግ የሚሉት ብቻ ናቸው፡፡ 
ከእነዚህ ከሦስቱ ውጪ በሌሎች ምክንያት ፈጽሞ ሐሳብን በነጻነት በማናቸውም የፕሬስ ውጤቶችም ይሁን በኤሌክትሮኒክ መንገድ እንዳይገለጹ መከልከል ወይንም ወንጀል ማድረግ ፈጽሞ ሕገ መንግሥቱን መጣስ ነው፡፡
ከላይ ተገለጹትን ግቦች ለማሳካት ሲባል ብቻ ነው የንግግርን ነጻነት መገደብ የሚቻለው፡፡ ጥላቻ ያዘሉ ንግግሮችን ለመገደብ መነሻዎቹ እንዚህ ብቻ ናቸው፡፡
ከዚህ አንጻር ሕጉ ቢወጣ፣ሕገ መንግሥታዊ ይሆን ዘንድ ንግግሮቹ የጦር ፕሮፓጋንዳ፣የወጣቶችን አስተዳደግ ላይ ችግር የሚፈጥሩ ከሆነ፣ ወይንም የግለሰብን መብት ወይንም ክብር እና ሰብአዊ ክብር የሚቃረኑ ንግግሮችነ ብቻ ነው በጥላቻ ንግግርነት ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉት፡፡
ከእነዚህ ውስጥ የጥላቻ ንግግርን ለመከልከል የሚወጣዉ ሕግ፣ ሕገ መንግሥታዊ ለማድረግ የሚቻለው  በአንዱ ብቻ ነው ፡፡ የአንድን ግለሰብ  ብሔሩን፣ ሃይማኖቱን፣ዘሩን ወይንም ሌላ ማኅበራዊ መገለጫን መሠረት አድርጎ የሰውን ክብር (Individual Honour) ወይንም ሰብአዊ ክብርን (Human Dignity) የሚጻረሩ ንግግሮችን አስቀድሞ ሕግ በማውጣት መገደብ ይቻላል፡፡ ከሕገ መንግሥቱ በመነሳት በሥራ ላይ ያሉትን ሌሎች ሕጎችን እንቃኝ፡፡
ሃይማኖትን፣ ፖለቲካን፣ ዘርን (ብሔርን አይልም) መሠረት ያደረገ በሐሰት የሚያነሳሳ፣ የሚያጥላላ፣ የሚስፋፋ ማናቸውም ድርጊት ወንጀል እንደሆነ በወንጀል ሕጉ በግልጽ አለ፡፡
 ከዚህ በተጨማሪም አንድ ሃይማኖት  ጋር  የተያያዙ ማናቸውንም ጸያፍ እና የአማኙን ስሜት የሚነካ ድርጊት የፈጸመ ሰው በደንብ መተላለፍ ሊቀጣ የሚቻልበት ሕግ አለ፡፡
ሕዝብን በተለያዬ መንገድ ወደ ግጭት እና አመጽ የሚመሩ ንግግሮችን ማድረግ ወንጀል እንደሆነ በመደበኛው የወንጀል ሕግም ይሁን የኮምፒውተር ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ላይ አሉ፡፡ እንዲሁም በርካታ ሕጎች ብሔርን፣ ዘርን፣ ሃይማኖትን፣ ጾታን፣ የፖለቲካ አቋምን መሠረት አድርጎ አድልኦ መፈጸም እንደማይቻል ተደንግጓል፡፡
ይህ እንግዲህ በተወሰነ መልኩ የጥላቻ ንግግርን ወንጀል መሆናቸውን እና በሌሎች አስተዳደራዊም ይሁን ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔርን ወይንም ሃይማኖትን መሠረት አድርጎ በሚኖር ያልተገለጠ ውስጣዊ ጥላቻ ቢኖር እንኳን አድልኦ ማድረግ የተከለከለ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ዓለማቀፍ ሰነዶችን ኢትዮጵያ ስላጸደቀች እነዚህ ስምምነቶችም የዘር፣ የብሔር፣ የሃይማኖት እና ሌሎች ነገሮችን ታሳቢ ያደረገ ማዳለት ስለሚከለክሉ ያው የአገራችን ሕጎች ናቸውና እነሱም አሉን፡፡ ነገር ግን ክልከከላው የወንጀል ስላልሆነ በወንጀል አያስቀጡም፡፡ በመሆኑም እነዚህ አገራዊም ይሁኑ ዓለማቀፋዊ ሕጎች የንግግር ነጻነት ወይንም መብት ፍጹማዊ ስላልሆነ በምን ሁኔታ እንደሚገደቡ፣ ከገደቡ ሲታለፍም ሊያስቀጡ መቻላቸውንም ነው ለመግለጽ የተሞከረው፡፡
 
ሕገ መንግሥቱን የሚጥሱ ሕጎች
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀ ወዲህ ከላይ ከገለጽናቸው መሥፈርቶች ጋር የማይሔዱ በርካታ ድርጊቶች ወንጀል ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ የመንግሥትን ስም ማጥፋት፣ መንግሥትን መስደብ፣ አገራዊ አርማንና ባንድራን መስደብ፣ ሌሎች ሀገራትን፣ ዓለማቀፍ ተቋማትን፣ አርማዎቻቸውንና ባንድራዎቻቸውን መስደብና ስም ማጥፋት እና የሀገርን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መረጃዎች ለጠላት ሀገር አሳልፎ መስጠት ወዘተ፡፡
 በዓለም ላይ በሕገ መንግሥቷ የአገር ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥል መረጃም ቢሆን እንኳን ያልከለከለች ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ይሁን እንጂ፣ ሕገ መንግሥቱ ላይ ከሰፈረው በእጅጉ በራቀ እና በተቃረነ ሁኔታ ባንድራን መስደብ፣የመንግሥት ስም ማጥፋት የመሳሰሉትን ወንጀል ሆነዋል፡፡ በየትኛውም አገር ደግሞ የሀገራትን የደህንነት ሁኔታ አደጋ ላይ የሚጥል መረጃን ለጠላት መንገርን ወይንም መግለጽን መከልከል ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡
 በዚህ ረገድ ሕገ መንግሥታችን ከየትኛውም ዓለምአቀፋዊ የሰብአዊ መብት ሰነድ ይሻላል፡፡ የብዙዎቹ መለኪያዎች በሕግ መደንገግና ለዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ አስፈላጊ መሆን (Necessary for a democratic society) ሲሆኑ የሁለተኛውን መስፈርት አስፈላጊነቱን የመወሰን (margin of appreciation) በአብዝሃኛው የተተወው ለሚመለከታቸው ሀገራት ነው፡፡
እነዚህ መስፈርቶች፣ እንደፈለጉ ለመፈንጠዝ የተመቹ ሲሆኑ በተቃራኒው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የመረጣቸው ደግሞ ጥብቅ እንዲሁም ለመለካት የማያስቸግሩ መስፈርቶችን ነው፡፡
ይሁን እንጂ ከላይ እንዳየነው መንግሥት አሁን ባለው አሰራር ከቀጠለ የጥላቻ ንግግርን በተለይ ብሔርን ከብሔር፣ አንድ የሃይማኖት ተከታይን ከሌላው ለማጋጨት የሚያነሳሱ፣ወይንም ጥላቻን በቡድኑ ላይ የሚነዙ ንግግሮች መከልከል አይሳነውም፡፡ ብዙ ያልተሳኑትን ሕጎች እንዳወጣ እና እስካሁንም ለመሻር የሚደረግ ፍላጎት አለመኖሩንም ጭምር ዐይተናል፡፡ 
 
የተጨማሪ ሕግ ወይንም ሥርዓት ሲያስፈልግ፤
ኢትዮጵያ፣ ከአሁን በፊት ስለ ሰብኣዊ መብት አፈጻጸሟ  ሪፖርት ስታቀርብ በተሰጣት ግበረ-መልስ ውሥጥ የጥላቻ ንግግርን ወንጀል ማድረግ አንዱ ነበር፡፡ በበጎም ተቀብላው ነበር፤ ምንም እንኳን ሕግ ማውጣቱ ላይ እመርታ ባታሳይም፡፡
ስለምን ሕግ ያስፈልገናል ብንል በርካታ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ የጉዳዩ አሳሳቢነትም መንግሥትም የተረዳው ይመስላል፡፡ በቴሌቭዥን የተለያዩ ፕሮግራሞች ሲቀርቡ ተመልክተናል፡፡ በተለይ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ስለሚተላለፉ እና ስለሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችንም መጨመር ይቻላል፡፡
ይሁን እንጂ ይህንን ከሚያስፋፉት ውሥጥ አንደኛው መንግሥት ራሱ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ አንዱን የመንግሥት አድራጎት ብቻ እንመልከት፡፡ እሱም መንግሥታዊ ፍረጃን ይመለከታል፡፡ እርግጥ ነው የአገራችን መለያ ከሆነ ቆይቷል፡፡  ነፍጠኛ፣ትምክህተኛ እና ጠባብ፣ የቀን ጅብ፣ ወዘተ የሚሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የንግግር ነጻነት ላይ ገድብ የሚጣለው ለዲሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ግንባታ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ደግሞ መቻቻል እና ብዙሃነት ከመለያ ባሕርያቱ መካከል ናቸው፡፡ መቻቻልን የሚያጠፋ እና ብዙሃነትን የሚቃረንን ንግግር ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ግንባታ ጠንቅ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ንግግሮችን መረን እንዲለቁ ማድረግ  ውሎ አድሮ ራሱን ዴሞክራሲን ያጠፋል፡፡ ስለሆነም፣ ዴሞክራሲን ራሱን ከጥፋት ለመታደግ የዴሞክራሲ መገላጫ የሆነው የንግግር ነጻነት ላይ ገደብ መኖሩ በብዙ አገራት የተለመደ አካሄድ ነው፡፡
ለዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ግንባታ የሚያስፈልጉ ነገሮች ደግሞ ከአገር አገር ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ ፈረንሳይ እና ቱርክ ሃይማኖታዊ የሆኑ ጉዳዮች ወደ መንግሥታዊ ተቋማት ብቅ ማለትን ለዴሞክራሲ እንደ ጠንቅ ያይቱታል፡፡
ጀርመን የናዚ እና የፋሽት አዝማሚያ፣ በስፔን ደግሞ መገንጠልን የሚያነሳሳ ወይም የሚደግፍ፣ በእስራኤል የአገሪቱን መኖር የማይቀበል ወዘተ ለዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ጸር እንደሆነ ይቆጠራል፡፡ ይሁንና እነዚህን ጉዳዮች አስቀድሞ በሕግ ማሳወቅን ይጠይቃል፡፡
ለማጠቃለል ያህል ረቂቅ አዋጁ በመጀመሪያ ደረጃ ቢያንስ ሕገ መንግሥቱን የማይጥስ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በመቀጠል፣ የጥላቻ ንግግርን በፊታዉራሪነት ሲያጋፍር የነበረዉ ራሱ መንግሥት ነዉ፡፡ ዜጎችን በወንጀል ለመቅጣት አስቀድሞ ሕግ ከማዉጣት፣ መንግሥት ራሱ ግልጽ ፖሊሲ መከተል፣ እስከዛሬ በሚሊዮን ቅጅ ያሰራጫቸዉን ጥላቻ ያዘሉ መንግሥታዊ ሰነዶቹን በኦፊሴል ማስወገድ እና ከጥቅም ዉጭ ማድረግ፣ ሕጻናት ሁሉ በሚማሩባቸዉ መጻሕፍት ዉስጥ የተሰገሰጉ የጥላቻ መልእክትና ጹሑፎች አስቀድሞ ማረም ወዘተ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት የራሱን ኃላፊነት ሳይወጣ ወደ ሕዝቡ በመሮጥ የግዴታ ቀንበር ለመጫን መታተር፣ የሚወጣዉን ሕግ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል ማለት ዘበት ነዉ፡
Filed in: Amharic