>

የጥላቻ ንግግርን (hate speech) እና ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት (freedom of speech) - የሕግ ክልከላ እና የሕግ ጥበቃ  (ያሬድ ሀይለማርያም)

የጥላቻ ንግግርን (hate speech) እና ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት (freedom of speech) – የሕግ ክልከላ እና የሕግ ጥበቃ 
ያሬድ ሀይለማርያም
የአለም አቀፉ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ድንጋጌ (The International Covenant on Civil and Political Rights) የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ እንዲህ ይላል “any advocacy of national, racial or religious hatred that constitutes incitement to discrimination, hostility or violence shall be prohibited by law”
የዚህ ድንጋጌ ዋና አላማ በማንኛውም ብሔረሰብ፣ ዘር፣ ኃይማኖት፣ ጽኦታ ወይም የህብረተሰብ ክፍል ላይ ያነጣጠረ የማግለያ፣ ጥላቻ ወይም ጥቃት እንዲሰነዘር የሚደረግ ቅስቀሳ ወይም ንግግር በሕግ እንዲከለከል አገሮች የገቡት የቃል ኪዳን አንቀጽ ነው። በአለማችን በርካታ አገሮች በሕገ መንግስታቸው፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጋቸው እና በሌሎች ሕጎችም ደንግገው የጥላቻ ንግግርን ይቆጣጠራሉ። በግለሰብም ሆነ በቡድን ላይ የሚሰነዘሩ የጥላቻ ንግግሮችን በተለያዩ መልኩ እየተቆጣጠሩ አጥፊዎችን በገንዘብ እና በእስር የሚቀጡበትን ሥርዓት ፈጥረዋል።
የቡዙዎቹ አገሮች የጥላቻ ንግግርን የሚመለከቱት ሕጎቻቸው ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ሲሆን ማንም ሰው በጽሑፍ፣ በንግግር፣ በምልክት፣ ወይም በሌሎች አኳኋን ሆነ ብሎ ሌላን ሰው ወይም ቡድን ወይም ሕዝብ በዘሩ፣ በቆዳው ቀለም፣ በሚናገረው ቋንቋ፣ በጽዎታው መገለጫ (ተመሳሳይ የጽዎታ ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች እና ጽዎታቸውን በሕክምና የቀየሩ ሰዎችን ጨምሮ)፣ በሚከተሉት እምነት (ሴጣንንም ቢያመልኩ)፣ በአካለ ጎዶሎች ላይ፣ በባህል ወይም በሌሎች መለያዎች በተሰባሰቡ ሰዎች ላይ ጥላቻን ያዘለ ንግግር በአደባባይ የሰነዘረን ሰው በወንጀል ይቀጣሉ።
አብዛኛዎቹ አገሮች በሚያወጧቸው ሕጎች ውስጥ አንዱ እና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያደርጉበት ጉዳይ ይህ የሕግ ክልከላ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ማድረጉ ላይ ነው።
የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ ሁለት መሰረታዊ ነገሮች አብረው ይነሳሉ፤
+ አንደኛው የጥላቻ ንግግሮችን አሻሚ በሆነ መልኩ በሕግ ደንግጎ የወንጀል ተጠያቂ ማድረግ የሃሳብ ነጻነትን ያጠባል ወይም ለመጣስ መንገድ ይከፍታል ከሚል ስጋት የሚመነጭ ነው። ይህ ስጋት በቸልታ የሚታለፍ አይደለም። የዲሞክራሲያዊ ባህል ባልዳበረበት፣ የከረረ እና የተወሳሰበ ብሔረተኝነት እና የጽንፍ ፖለቲካ በነገሰበ እና አንባገነናዊ ሥርዓት ባላሸቀው እና ታፍኖ በቆየ ማህበረሰብ ውስጥ ይቅርና የዳበረ የዲሞክራሲ ባህል ባለበት እና ጠንካራ የፍትህ ተቋማት ባሉበት አገርም በጥላቻ ንግግር እና ሃሳብን በመግለጽ ነጻነት በኩል ያለው ድንበር እጅግ ቀጭን መስመር ስለሆነ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። የጥላቻ ንግግሮች በተናጋሪውም በኩል ሆነ በተሰዳቢው በኩል ስሜታዊነትን የሚጋብዙ ናቸው። ተናጋሪውም በስሜት ውስጥ ሆኖ ነው የሚናገረው፤ ተሰዳቢውም ስድቡን ሲሰማ የሚሰማ ነገር ስሜትን የሚቀሰቅስ ቁጣ ነው። ለዚህም ነው የጥላቻ ንግግሮች ግጭትን እና እልቂትን ይጋብዛሉ የሚባለው።
+ ሁለተኛው የጥላቻ ንግግሮችን በሕግ የመቆጣጠሩ ጉዳይ የገጠመው ፈተና 
የኢንተርኔት ቴክኖሎጂን ተከትሎ የተስፋፋው የማህበራዊ ድህረ ገጾች አጠቃቀም እና የተጠቃሚው መጨመር ነው። የሕግ ክልከላው በዘመኑ ቴክኖሎጂ በተደገፈው የማህበራዊ ድህረ ገጽ እየተፈተነ ይገኛል። በማህበራዊ ድህረ ገጾች ከሚፈጸሙት በርካታ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ውስጥ የጥላቻ ንግግር ግንባር ቀደሙን ስፍራ እንደሚይዝ ጥናቶች ያሳያሉ። በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር ግለሰቦች ሃሳባቸውን በነጻነት በራሳቸው ስም እና ምስል ተደግፈው ለመግለጽ የፖለቲካ፣ የባህል እና ማህበራዊ ጫናም ጭምር በሚፈሩበት ስፍራ የፈረስ ስም ወይም ሌላ የሃሰት ስም ከፍተው ያሻቸውን ሲጥሉና ሲያነሱ፣ ሲያብጠለጥሉ፣ ሲሳደቡ እና ጥላቻን መሰረት ያደረገ አመጽ ሲቀሰ ማየት የተለመደ ሆኗል። ከዚያም አልፎ የአገዛዝ ሥርዓቱ ሳይቀር በጀት በጅቶ፣ በርካታ ደሞዘተኛ ተሳዳቢዎችን መድቦ በመንግስት ላይ የሚሰነዘሩ የማህበረ ድህረገጽ ነቀፌታዎችን ለመከላከል በሚል አንዱ የጥፋቱ ኃይል አካል እንደነበር ጭምር በይፋ ሲገለጽ ሰምተናል።
ሕግ መኖሩ ጥሩ ነው። ይሁና የሚወጣው ሕግ የአፈና መሳሪያ ላለመሆኑ ግን ዋስትና የሚሆን በበቂ ጥናት እና ዝግጅት ላይ የተመሰረተ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት የግድ ይላል። የሚወጣው ሕግም አሻሚ እና ለትርጉም ክፍት ያልሆኑ ቃላቶችን የያዘ፣ የዜጎችን ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን ለማፈን ያላለመ፣ የፖለቲካ ክርክሮችን እና አንዳንድ የፖለቲካ ስላቆችን እንደ ስድብ ያልቆጠረ፣ አስተማሪነትን ያስቀደመ እንዲሆን ከወዲሁ ለማሳሰብ እወዳለሁ። ነገ ፖለቲከኛው፣ ሹመኛው እና አፋሽ አጎንባሹ ሁሉ ተነስቶ በሰራው እና በአደባባይ በተናገረው አገራዊ ጉዳይ ሁሉ ሲተች የጥላቻ ንግግር ነው እያለ የሕግ ያለህ እንዳይል ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል።
ሲያጠሩ በዋሉት እንቅብ ሙሉ ስንዴ ውስጥ እንክርዳድ እንደማይጠፋው ሁሉ በአንድ ማህበረሰብም ውስጥ መቼም ቢሆን ከሞራል እና ከስነ ምግባር አፈንጋጭ አይጠፋምና ቀጪ ሕግ መኖሩ ጥሩ ነው። ይሁንና ስልጡን ማህበረሰብ ከሕግ ያላፈነገጠ ትውልድ የሚቀርጸው በትምህርት እና በውይይት ስለሆነ በሕግ የተጠረነፈ ትውልድ ሳይሆን በእውቀት፣ በምርምር እና በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ የመፍጠሩ ስራ ላይ ቢተኮር ዘላቂ ውጤት ይኖረዋል።
ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic