>

የወጣብንን የአፈና አዋጅ የመቃወም ዘመቻ ጥሪ!!! (አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

የወጣብንን የአፈና አዋጅ የመቃወም ዘመቻ ጥሪ!!!
አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

የጥላቻ እና የቂም (የውሸት) ሐውልት ሳይፈርስ  ጥላቻ ተናጋሪን የሚቀጣ ህግ አወጣለሁ ማለት ምፀት ነው:: ይህ የሃሰት ሐውልት ብቻውን ብዙ ያናግራል:: ይህ ሐውልት በጥላቻ የፀደቀው ህገ መንግስት ምልክት ነው::

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ምርዓየ ሁነት) ማምሻውን ባሰራጨው ዜና የሐሰተኛ መረጃ ዝውውርንና የጥላቻ ንግግርን ለመገደብ ወይም ለመከላከል አዋጅ መረቀቁን አስታውቋል፡፡ በቅርቡም “ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” ቀርቦ እንደሚጸድቅና ሥራ ላይ እንደሚውል ተነግሯል፡፡
በበኩሌ ይህ አዋጅ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽን ተፈጥሯዊ፣ ሰብአዊና ሕገመንግሥታዊ መብትንና ነጻነት በእጅጉ የሚጻረር የሚገድብና የሚጎዳ በመሆኑና ኢንቴንሽኑ (እሳቤው) ለውጥ የተባለውን የወያኔ/ኢሕአዴግን ድራማ (ትውንተ ሁነት) በተፈለገው ሕዝብን የማጭበርበር፣ የማታለል፣ የማጃጃል ደረጃ ማስቀጠል ስላልተቻለ በዚህ አዋጅ ሽፋን ነጻ የመረጃ ዝውውርንና ጠንካራ ትችትን በማፈን፣ በመገደብ በድራማው የተሳፈረውን አገዛዝ ሕልውና ለማስቀጠል በማሰብ የተሰናዳ አዋጅ በመሆኑ አጥብቄ እቃወመዋለሁ፣ አወግዘዋለሁ፣ አልቀበለውምም፡፡ ይሄንንም አፋኙን አዋጅ ባወጁ ማግስት ለአፈናቸው ባለመንበርከክ ለእስር በመዳረግ የማረጋግጠው ይሆናል፡፡ አዋጁ ጸድቆ ሥራ ላይ ከዋለ ሁላችንም ብንሆን አለመቀበላችንንና መቃወማችንን መግለጥ ይኖርብናል እንጅ ፈጽሞ እንደገና ወደ አፈና ዘመን ለመመለስ መፍቀድ አይኖርብንም!!!
እንደ ጃዋር ሞሐመድ ያሉ ፀረ ሕዝብ ፀረ ሀገር ዕኩይ ዓለማ ያላቸው አሸባሪዎችን ሊቀጣ ሊቀፈድድ የሚችል ሕግ እያለ እያጠፉ ባሉት ልክ ሕጉን በእነሱ ላይ ተፈጻሚ ለማድረግ ፈጽሞ ባልተፈለገበትና እንደፈለጉ ዕኩይ የጥፋት ዓላማቸውን እንዲፈጽሙ በተፈቀደበትና እያስፈጸሙም ባሉበት ሁኔታ “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን!” እንዲሉ “ሐሰተኛ መረጃ አዘዋውረሃል፣ የጥላቻ ንግግር ነዝተሃል!” እያሉ ተራ ዜጎችን ሁሉ እየለቀሙ ለማሰር ማሰብ ሲበዛ ቀልድ ነው!!! ዓላማውም ለበጎ እንዳልሆነ ማሳያ ነው!!!
ከዚህም ውጭ ግን አዋጁን ማውጣት ያስፈለገው ለዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) መብት፣ ነጻነት፣ ደኅንነት፣ ህልውና በማሰብ ነው ከተባለ ከዚህ አዋጅ ይልቅ የሚከተሉት ሦስት ዐበይት ጉዳዮች ተፈጻሚ ይደረጉ?፦
1ኛ. በሐሰት ተወንጅለው በመከሰስ ለእስር ተዳርገው ሲንገላቱ፣ ለአካላዊና ሥነልቦናዊ ጉዳትና ጥቃት ሲዳረጉ፣ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ (ጥሪታዊ) ቀውስ ሲዳረጉ ከቆዩ በኋላ ፍርድ ቤት “ነጻ!” ብሎ ለሚለቃቸው የግፍ ሰለባ ዜጎች አገዛዙ ስለሚከፍለው ካሳ የሚደነግግ አዋጅ ይውጣ!!!
2ኛ. ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ሽፋን ዜጎችን ለማሰርና ለማንገላታት ከመዘጋጀት ይልቅ የዜጎችንና የመገናኛ ብዙኃንን መረጃ የማግኘት መብትን ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ የሚያስከብርና (የሀገር ደኅንነትን ለአደጋ ከሚዳርጉ መረጃዎች በስተቀር) ይሄንን የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት በማያከብሩ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሥልጣናት ላይ ቅጣት የሚጥል ሕግ እንዲወጣ፡፡
3ኛ. የጥላቻ ንግግር በመፈጸምና ማሠራጨት ስም ለዜጎች ሌላ ዙር የአፈና ዘመን ለማወጅ ከመዘጋጀት ይልቅ እናንተ ባለሥልጣናትና የሥራ ኃላፊዎች እራሳቹህ ለሞራል ድንጋጌዎች ተገዥ ሆናቹህ፣ ሥነምግባርና ግብረገብ ያላቹህ ሆናቹህ፣ ሀገርንና ሕዝብን ለአደጋ ከሚዳርግ ኢሞራላዊ (ኢቅስማዊ) ሸፍጥ፣ ደባ፣ ሴራ፣ አሻጥር እርቃቹህ ለሕዝብ አርአያ በመሆን አሳዩ!!!
ይሄንን ስታደርጉ የሐሰተኛ መረጃ ዝውውርና የጥላቻ ንግግር በሕግ ለመከላከል፣ ገደብና ቅጣት መጣል ሳያስፈልግ እራሱ ይጠፋል!!! ያኔ ብትከፍሉትም እንኳ ሐሰተኛ መረጃ የሚያሠራጭና የጥላቻ ንግግር የሚነዛ አንድ ሰው እንኳ አታገኙም!!!
ከዚህ ውጭ ግን ከላይ የጠቀስኩትን ከእናንተ የሚጠበቀውን ግዴታ ሳትወጡና ለመወጣትም ጨርሶ ፍላጎቱ ሳይኖራቹህ ይሄንን አዋጅ በማውጣት የሐሰተኛ መረጃ ዝውውር የምትሉትንና የጥላቻ ንግግርን የምትሉትን ለመግታት ወይም ለመቆጣጠር መሞከር ችግሩን ተፈጥሯዊ ባልሆነ መንገድ ለመቆጣጠር እንደመጣር ያለ ከንቱ ድካም፣ ጅልነትና አደገኛ ሙከራ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የከፋ አደጋን ያስከትላል እንጅ የሚያመጣው አንዳችም መፍትሔ አይኖርም!!!
በሠለጠነው ዓለም ይሄ የጥላቻ ንግግርን የሚገድብ ወይም የሚቆጣጠርና መሰል ሕግ ወይም አዋጅ የሌለው ለምን ይመስላቹሃል??? ከላይ የጠቀስኳቸውን ግዴታዎች መንግሥቶቻቸውና ባለሥልጣኖቻቸው ስለሚያሟሉና ይሄ በሆነበት ሁኔታ ደግሞ ሐሰተኛ መረጃን በማዘዋወርና የጥላቻ ንግግርን በመንዛት ጊዜውን ገንዘቡን ጉልበቱን በከንቱ የሚያባክንና ተሰሚነት አገኛለሁ ብሎ የሚያስብ ዕብድ ስለሌለ ነው!!!
የሰው ልጅን የሚገራው፣ የሚያድበውና የሚገዛው የሕግ የበላይነት መረጋገጥና ተጠያቂነት የሰፈነበት ሥርዓት (system) መኖር እንጅ ዱላና ማስፈራሪያ አይደለም!!! ይሄንን ማሰባቹህ የሚያሳየው ከጉልበት አስተሳሰብ አለመውጣታቹህን አለመሠልጠናቹህንና ጭንቅላታቹህ ውስጥ ያለው ብዕር ሳይሆን ጠመንጃ መሆኑን ነው!!!
ለመሆኑ እናንተ እራሳቹህ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማፋጀት፣ ለማጠላላት፣ ለማራራቅ፣ ለማባላት ሌት ተቀን ተግታቹህ የምትሠሩ በሆናቹህበትና ይሄንንም ለማድረግ ያቆማቹህት የጥላቻ ሐውልት አሁንም በቦታው በክብርና በእንክብካቤ ቆሞ ባለበት ሁኔታ፣ ተጠያቂነት የሚባል ነገር ቢጠበስ የማይሸታቹህ በዘቀጠ የሞራል ደረጃ ባላቹህበት ሁኔታ ዜጎችን “የጥላቻ ንግግር አድርገሀል፣ ሐሰተኛ መረጃ አሠራጭተሀል!” እያላቹህ እየለቀማቹህ ለማሰር ምን የሞራል ብቃት አላቹህ???
የሞራል ብቃቱ ጨርሶ የሌላቹህ ከመሆኑም ባሻገር ለአፈና መዘጋጀታቹህን ነውና የሚያረጋግጠው ኢትዮጵያውያን ሆይ ይሄንን ሐሰተኛ መረጃን በማሠራጨትና የጥላቻ ንግግር በመከላከል ሽፋን ሊታወጅ የተዘጋጀውን አዲሱን የአፈና አዋጅ በሚቀጥሉት ቀናት ረቂቅ አዋጁ ውድቅ እስኪደረግ ድረስ አጥብቀን የመቃወምና የማውገዝ ዘመቻን እንድናደርግ አጥብቄ ማሳሰብ እወዳለሁ!!
?
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic