>
5:13 pm - Sunday April 20, 4656

ሽሚያ ውስጥ ላለመግባት ዝምታን ከመረጥንባቸው  እውነቶች አንዱ. . .  !?! (አቻምየለህ ታምሩ)

ሽሚያ ውስጥ ላለመግባት ዝምታን ከመረጥንባቸው  እውነቶች አንዱ. . .  !?!
አቻምየለህ ታምሩ
ዛሬ መጣ የተባለው ለውጥ ወይንም ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነበት ትግል  በማን ትግል እንደመጣ ባልናገር እመርጥ ነበር። ሆኖም ግን የኦሮሞ ብሔርተኞች  ዛሬ ላይ  መጣ የሚሉትን  ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነበት «ለውጥ» የኦሮሞ ትግል ውጤት አድርገው  በተደጋጋሚ ሲያቀርቡት ማየቴ  ዝምታየን እንድሰብር አድርጎኛል።
ዛሬ መጣ የተባለው ለውጥ ወይንም ዐቢይ አሕመድ  የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነበት  ለውጥ የመጣው በአማራ ተጋድሎ እንጂ በኦሮሞ ተቃውሞ አይደለም። ዐቢይ አሕመድን ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትርነት የበቃው ጎንደር ላይ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ “ጎንደር ተወልጄ እጄን አልሰጥም” ብሎ በለኮሳት ተጋድሎና  እዚያው ጎንደር  በዐፄ ቴዎድሮስ አደባባይ “የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው” በሚል የተካዱት የአማራ ወጣቶች ባስተጋቡት የተጋድሎ ድምጽ ነው።
የዛሬው ለውጥ እየተባለ የሚነገርለት ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነበት ትግል በምንም መልኩ  የኦሮሞ ተቃውሞ ወይንም #OromoProtest ያመጣው ለውጥ  ወይንም  ውጤት አይደለም።
የመዘንጋት በሽታ ተጠቂዎች ካልሆንን በስተቀር  የኦሮሞ ተቃውሞ ወይንም #Oromoprotest አላማ ምን እንደነበር  ልንረሳት የምንችለው ጉዳይ አይደለም። የኦሮሞ ተቃውሞ ወይንም #OromoProtest አላማው ምን እንደነበር  «የኦሮሞ ትግል መሪዎች» ነን ያሉ  የትግሉ ፊታውራሪዎች   እ.ኤ.አ. በ2016 ዓ.ም.  ለንደንና አትላንታ ባካሄዱት ጉባኤ ነግረውናል። ለንደንና አትላንታ «የኦሮሞ ትግል መሪዎች ኮንቬንሽን»  በሚል ርዕስ የተሰባሰቡት እነዚህ የኦሮሞ ተቃውሞ ወይንም   #OromoProtest መሪዎች ነን ያሉን ፊታውራሪዎች  ኦሮሞ ነጻ የሚወጣው ኢትዮጵያ ስትፈርስ ነው ብለው በአትላንታ  ባደረጉት ጉባኤ  «የኦሮምያ ሽግግር መንግሥት ቻርተር» አዘጋጅተው ነበር። የቄሮ ወይንም የ #OromoProtest መሪዎች ነን ያሉን «የኦሮሞ ትግል መሪዎች» ያዘጋጁት  «የኦሮምያ ሽግግር መንግሥት ቻርተር» ረቂቅና ቃለ ጉባኤ በእጄ ይገኛል። ባዘጋጁት የኦሮምያ ሽግግር መንግሥት መሰረት አላማቸው ባለፈው ጃዋር  የአዲስ አበባ ጉዳይ  በሚመለከት በጣቢያው ቃለ መጠይቅ ሲሰጥ  «በየመንደሩ ቄሮን እየዞርሁ ከማረጋጋት  በል ቄሮ ሂድ  ጨርሰው ማለት ይቀለኛል» ያለው ነበር።
የቄሮ ወይንም የ #OromoProtest መሪዎች ነን ያሉን «የኦሮሞ ትግል መሪዎች»  በአትላንታ  «የኦሮምያ ሽግግር መንግሥት ቻርተር» ያሉትን   አዘጋጅተው ከጨረሱ በኋላ  በጉባዔያቸው ማገባደጃ  የሽግግር መንግሥቱ መሪ ጃዋር መሐመድን የመረጡ ሲሆን ምክትሉ ደግሞ በቀለ ገርባ ነበር።  የአትላንታው የኦሮሞ የሽግግር መንግሥት ምስረታ ከጃዋርና ከበቀለ ገርባ በተጨማሪ ሌሎች ሹመቶችም ሰጥቶ ነበር። በወቅቱ አስመራ የነበረው ዳውድ ኢብሳ በወያኔ ቋንቋ  የ«ኮማንድ ፖስት» አዛዥ ተደርጎ የተሰጠው ኃላፊነት ከአትላንታው ሹመቶች መካከል አንዱ  ነበር።
ለዳወድ ኢብሳ የተሰጠው «ኮማንድ ፖስት» «የምዕራብና የምስራቅ ኮማንድ ፖስት» ይባል ነበር። «የደቡብ ኮማንድ ፖስት»  የሚባል ነበር። ይህ ኮማንድ ፖስስ  ቦረናን፣ ባሌንና አርሲን የሚያጠቃልል ሲሆን  የዚህ ኮማንድ ፖስት አዛዥ ደግሞ የኦነግ መሪ እንዲሆን በጉባኤ ከተመረጠ በኋላ ዳዎድ ኢብሳ መፈንቅለ መሪ አካሂዶ በማባረር ስልጣኑን የቀማው በደርግ ዘመን ሻዕብያ ማርኮት ለወያኔ በምርኮ ከተሰጡና ኦሕዴድን እንዲመሰርቱ ከተደረጉት ምርኮኞች አንዱ የሆነው ከማል ገልቹ ነበር።
ከማል ገልቹ አስመራ ብቻ ሳይሆን ተመልሶ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ ሥልጣን የረጋለት አይመስልም። ከማል ኢትዮጵያ እንደገባ demobilize ሳይደረግ «የኦሮምያ ክልል የአስተዳደርና ጸጥና ቢሮ ኃላፊ» ሆኖ  በለማ መገርሳ ተሹሞ ነበር። ከጫካ እንደመጣ demobilize ሳይደረግ የተሾመው ከማል ገልጁ  የአስተዳደርና ጸጥታ ቢኖር ኃላፊ ሆኖ እንደተሾመ  ስራውን የጀመረው አስመራ በነበረው ልምዱ  መሳሪያ በየጉረኖው ማከማቸትና እሱን ለሚመስሉት ኦነጋውያን ማስታጠቅ ነበር። ባሌ በየመስጂዱ ያከማቸው የጦር መሳሪያ ስለተገኘበት  ከሰሞኑ  ስልጣኑ ተነስቷል።
ወደ አትላንታው የኦሮሞ የሽግግር መንግሥት ቻርተር  ጉባኤ ስመለስ ጉባኤው ከከማልና ዳወድ በተጨማሪ  ሌሎች ኮማንድ ፖስቶችንም ፈጥሮ አዛዦችን ሾሞ ነበሩ። የኮማንድ ፖስቶቹ ሁሉ  ጠቅላይ አዛዦች  በአትላንታ  «የኦሮሞ ትግል መሪዎች ኮንቬንሽን»  የኦሮሞ የሽግግር መንግሥት  መሪዎች ተደርገው የተሰየሙት  ጃዋር መሐመድና  በቀለ ገርባ ነበሩ።
ቄሮን እንመራለን የሚሉን #OromoProtest  መሪዎች  ያካሂዱት የነበረው ትግል እውን ቢሆኖ ኖሮ አትላንታ ላይ ያረቀቁት የኦሮሞ የሽግግር መንግሥት ቻርተር ተተርጉሙ ዛሬ ላይ ኦሮምያ የምትባለዋ ፍጡር ጃዋር የሚባል ይፋዊ የኦሮምያ የሽግግር መንግሥት መሪና በቀለ ገርባ የሚባል ምክትልነት ስልጣን … እንጂ ዐቢይ ዐሕመድ የሚባል የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አይኖርም ነበር።  ሊፈጸም ጠረጴዛ ላይ የነበረው የአትላንታው የኦሮሞ ሽግግር መንግሥት ቻርተር ወደ    መሳቢያ ገብቶ  ዐቢይ አሕመድ  የሚባል መሪ ወደፊት የመጣው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ “ጎንደር ተወልጄ እጄን አልሰጥም” ብሎ የለኮሰው የአማራ ተጋድሎ የወለደው “የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው” የሚል ድምጽ ከፍ ብሎ ሲሰማ እሳትና ጭድ የተባሉትን አማራና ኦሮሞ እጅና ጓንት መሆናቸው ለማሳየት በመነሳቱ ነው።
ባጭሩ የአማራ ተጋድሎ ባይፈነዳ ኖሮ ቄሮን እንመራለ ያሉን  በአትላንታ የኦሮሞ የሽግግር መንግሥት ቻርተር ያዘጋጁት የኦሮሞ ትግል መሪዎች ፍኖተ ካርታ መሰረት ዛሬ  ላይ ይኖር የነበረው ጃዋር መሐመድ የሚባል የኦሮምያ የሽግግር መንግሥት ይፋዊ መሪና  በቀለ ገርባ  የሚባል ምክትል እንጂ  የኢትዮጵያን ስም የሚከተል ዐቢይ አሕመድ የሚባል መሪ አይኖርም ነበር።
 እንዴውም  የቄሮ ትግል መሪዎችን ነን የሚሉን የኦሮሞ ትግል መሪዎች  የአትላንታ የኦሮሞ የሽግግር መንግሥት ቻርተር  ዳር ቢደርስ ኖሮ  የዐቢይ እድል ፈንታ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ሳይሆን ምናልባትም  ጃዋር በተገኘበት  ሻሸመኔ ተዘቅዝቆ እንደተሰቀለው ድሀ  ተዘቅዝቆ ይሰቀል ነበር አልያም ወለጋ ብሄድ ይገድሉኛል እንዳለው  ገድለው አስከሬኑን ያቃጥሉት ነበር። ይሄው ነው!
Filed in: Amharic