>
5:13 pm - Thursday April 19, 8356

ጋዜጠኛ ደረጀ ደስታ ከ5 ሚሊዮኑ ዶላር ሎተሪ እድለኛ ከጋዜጠኛ ሰሎሞን ክፍሌ ጋር ያደረገው ቆይታ


“ሎተሪው ባለቤቴ እንደቆረጠችው ነው የምቆጥረው!!!”
ሰሎሞን ክፍሌ
 
ጋዜጠኛ ደረጀ ደስታ ከ5 ሚሊዮኑ ዶላር ሎተሪ እድለኛ ከጋዜጠኛ ሰሎሞን ክፍሌ ጋር ያደረገው ቆይታ
ድሮ በህብረ ትርኢት የቴሊዝቪዥን ፕሮግራምና በስፖርት ዘገባው፣ አሁን በቪኦኤ ጋዜጠኝነቱ ይታወቃል። ሰሞኑን ደግሞ ሎተሪ ቆርጧል። በዚህ የተነሳ ወሬ አቀባዩ ራሱ ወሬ ሆኗል። ወዳጆቹም ከሱ ጋር ሆነን ወሬውን ተጫውተንበታል።
ሶስታችን አልፎ አልፎ እንደምናደርገው ጋሽ አያልነህና ከቪ.ኦ.ኤው ጋዜጠኛ ሰሎሞን ክፍሌ ጋር ምሳ ለመብላት ተቀጣጠርን። ሁሌ እማይለያቸው የቅርብ ወዳጃቸን ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ ቢኖር ምናልባት አራት እንሆን ነበር። ለማንኛውም ሎተሪው ከወጣለት በኋላ የመጀመሪያው ምሳችን መሆኑን ነው። በተለይ ከኔ ጋር። እነሱ ቀድመውኝ በቦታው ደርሰው ነበር። ሰሎሞንን ገና ስጨብጠው “እርግጠኛ ነኝ ሚሊዮነር ስትጨብጥ የመጀመሪያ ጊዜህ ነው” አለኝ። ወደ ጋሽ አያልነህም ዞሮ – “አንተስ ብትሆን ሚሊዮኔር ጨብጠህ ታውቃለህ- ምን ልትል ነው?” አለው ። ይቺ ገና ለገና እማትቀርለትን ተረብ ለመከላከል መሆኗ ገብታናለች። አልማርነውም።
ከሁቴሉ ገብተን ምሳ ልንበላ ምግባችንን አዘዝንና “እሚጠጣስ?” ሲባል “ለሁላችንም ዋይን!” አለና “በቦትል አድርጊው!” አላት ሰሎሞን። እድልም አልሰጠን። መቸም ሚሊየነሮችና ባለሥልጣናት የሰውን ምርጫ መወሰን ይወዳሉ። አጋጣሚ ሆኖ አስተናጋጃችን ሀበሻ ነበረች። የቀልዴን ጣልቃ ገብቼ “የእኔ እህት እባክሽን በጣም ትልቁንና እጅግ ውድ የሆነውን ዋይን አምጭልን…” ስላት፣ ሁላችንም ተሳሳቅን። መቸም የአምስት ሚሊዮን ሎተሪ ፋቅ ፋቅ ሲያደርጉት ሳቅ ሳቅ ያደርጋል። ሰሎሞን ክፍሌ ስቋል። እኛም አብረን እየሳቅን ትንሽ እንደቆየን ሌላ ሳቅ መጣ። ፈረንጁ የሆቴሉ ማኔጄር ዋይናችንን ይዞ መጣ። በጣም በኩራትና በአክብሮት በቤቱ ውስጥ ያለን ውድ ዋይን ይኼ ነው አለን። የገዛ ቀልዴ ዋጋ ልታስከፍለን መሆንዋ ገብቶኝ ከሰውየው ጋር መራር ጭቅጭቅ ልጀምር ስል ሌላ ሳቅ ሆነ።
ሰሎሞን በቃ ግድ የለም ተወው እንጠጣዋለን አለኝ። “ያለው ማማሩ..” ብለን አንዳችን ከአሳ ኮተሌት፣ አንዳችን ከጾም ፓስታ ሹታችን ጋር ወይን ጠጅቱን አጣጣምናት። የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ ገረፍ ገረፍ አድርገን ወደ ሎተሪው ተመለስን። በጋዜጠኛ ሆድ ሚሊዮን እንጂ ወሬ አያድርምና አፌንም ጆሮዬንም በላኝ። በል እስኪ አጫውተን። እንዴት ቆረጥከው? ሲደርስህ ምን አልክ? ምንስ አደረግክ? ስንት ተቀበልክ? ምን አደረግክበት? በእጅህ ምን ያህል ቀረህ? ሥራህን በቃ ደህና ሰንብች ትላታለህ? ብቻ ምን ያልተጠየቀው ነገር አለ? የወዳጅነትም የጋዜጠኝነትም ተጠይቋል። የወዳጅነቱን አስቀርቼ የጋዜጠኝነቱን ላካፍላችሁ።
ከሥራው ነው የጀመረው። “በሙያዬ እንኳ ቀልድ የለም! እኔ ሎተሪ የወጣልኝ ጋዜጠኛ ስሆን ነው። ጋዜጠኝነት ሙያዬ ብቻ አይደለም ህይወቴ ነው። ሰው እኮ ሎተሪ ሲደርሰው እሚወደውን ነው ማድረግ እሚፈልገው። ያን እያደረግኩ ነው። ሎተሪው ኑሮዬን እንጂ ሙያዬን አይለውጠውም። ይቺን ከያዝክልኝ ሌላውን ምንም ሳላስቀር ላጫውትህ” – አላቋረጥኩትም።
እንግዲህ የደረሰኝ ወጣ የተባለው ሎተሪ 5 ሚሊዮን ነው። ይህን ለመውሰድ ስትሄድ ምርጫ አለህ። በ20 ዓመት ወስደህ እምትጨርሰው ከሆነ በየወሩ እሚሰጡህን ታገኛለህ። ወይም ካሹን ባንዴ ልትውሰድ ትችላለህ። ካሹን ባንዴ ካልክ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ያነሱለታል። እኔ ይሁን ብዬ 3.5 ሚሊዮኑን ተቀበልኩ። ቆይ እንጂ ከሱም ደግሞ እኮ የፌደራልና የስቴት ታክስ ይነሳለታል አሉኝ። ወደ 1.1 ሚሊዮን አካባቢ ሲያነሱለት 2.4 ሚሊዮን አካባቢ ቀረኝ። ለነገሩማ የደረሰኝ እኮ 500ሺ ነበር። ሚሊዮን እሚባል አልነበረም፡፡
“ምን አልከኝ?” አልኩት።
ይኸውልህ ሎተሪውን ፍቄ ያየሁት ማታ ቤት ገብቼ ቴሌቪዥን እያየሁ ነው። 500ሺ ዶላር ነው ያኔ የታየኝ። በጣም በጣም ደስ አለኝ። አናቴ ላይ እሚዘፍን ብዙ እዳ ነበር። እንደምታወቀው ልጄን ልድር ነው። ለሠርጉ ተለቅቼም ይሁን ተበድሬ እስካሁን ከ30 ሺብር በላይ አውጥቼበታለሁ። ገና ሌላ 10 ሺህ ያስጨምረኛል።  በዚያ ላይ የቤት እዳ አለ። የኔም የልጄም የትምህርት ቤት (“ስቱደንት ሎን”) እዳ አለ።  ስቱደንት ሎኑ ብቻ ከሁለት መቶ ሺህ በላይ ነው። የሞርጌጁም 300ሺብር በላይ ይሆናል። እና ያቺ 500ሺ ብር ስትመጣ ቢያንስ በትልቁ ትገነድስልኛለች። እና ማታ እግዜሐብሔርን አመስግኜ ተኛሁ። ጧት ስራ ገባሁ። ሎተሪዪቱን ከኋላ ኪሴ ነው ያስቀመጥኳት።  ሥራ ጋብ ሲል –  ወጣ አድርጌ አየኋት። አይኔን ማመን አልቻልኩም። ለካ ማታ የዓይንም የደስታም ነገር ሆኖ በደንብ አላነበብኳትም። 500ሺ ሳይሆን 5 ሚሊዮን ተሸክማ ነበር። ከዚያ በኋላማ በቃ ምን እነግርሃለሁ። ጥቃቅንም ብትሆን ብዙ ጊዜ ስለማሸነፍ የት ሄዶ እንደሚወሰድ አውቃለሁ። ወደዚያ መቀበያው ቢሮ ሄድኩ። ኃላፊዎቹ ከኔ በላይ በጣም በጣም ጮኹ። ግን ከኔ ያዩት ምላሽ መልሶ ግራ አጋባቸው። አምስት ሚሊዮን እኮ ነው የደረሰህ አሉኝ። እሱን አውቄ እኮ ነው ልቀበል የመጣሁት አልኳቸው።
እኔ ያቀዘቀዘኝ ይሄ ፎቶ ተነስ እሚሉት ምናምን ነገር መኖሩ ነው። ፎቶ መነሳት አለብህ አሉኝ። ባልነሳ ምን ይመጣል አልኳቸው። ምንም አይመጣም ግን አንተ ገንዘብህን አታገኝም አሉኝ። በቨርጂኒያ ህግ ፎቶ መነሳት ግዴታ ነው። ፍቶውን ተነስቼ ወደ ባንኬ ሄድኩ። በቃ እንዳልኩህ የቤቱን ፣ የመኪናውን፣ የክሬዲት ካርዱን ያለውን እዳ ሁሉ ዘጋሁ። የስቱደንት ሎኑን እዳ ከፋፈልኩ። ልጄ ከሠርጉ በሁዋላ ወደኔ አካባቢ ልትመጣ ነው። አሁን ኒዮርክ ናት። ለሷ ተለቅ ያለ ቤትና መኪና እገዛለሁ። ያለ እዳ እንድትኖር ነው የምንጊዜም ሃሳቤ። እዚህ አገር ትልቁ እዳ የቤት ሞርጌጅ ነው። የኔ ራሱ ትልቁ ደስታዬ ከቤት ኪራይ መገላገሌ ነው።
ሌላው የማደርገው ነገር – ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ህጻናት መርጃ እሚውል ድጋፍም ለመስጠት እየሰራሁ ነው። በተፈረው እንግዲህ ለኢንቨስትመንት ጣል ካደረግኳት፣ የቀረችውን ለህይወቴ ጡረታ አደርጋታለሁ። ከሁሉ ከሁሉ ግን ትልቁ ነገር የባለቤቴ ነገር ነው። ሎተሪውን ባለቤቴ እንደገዛችልኝ እቆጥረዋለሁ ብዬሃለሁ። ልብ በል ይህ የሆነው የሙት ዓመቷን በቤተከርስቲያን ጸሎት ባከበርኩበት ሳምንት ውስጥ ነው። ሎተሪውን የገዛሁት ማርች 27 ነው ። ሰባት ሰዓት አካባቢ ከምሽቱ። ባለቤትም ያረፈችው የዛሬ አምስት ዓመት ማርች 29 በዚያ ሰዓት ላይ ነበር። እርሷ ካረፈችበት ሁለት ቀናት በፊት መሆኑ ነው ሎተሪው የደረሰኝና አጋጣሚው ያስገርማል።
ሰሎሞን እንዳለው – እኔም አምስት ዓመትና አምስት ሚሊዮን መገጣጠሙ ገረመኝ። ሳያቋርጥ እቤት ውስጥ ፎተግራፏ ካለበት ጠረጲዛ ጎን በየሳምንቱ አዲስ አበባ እየገዛ  እንደሚያስቀምጥ አውቃለሁ።
“ባለቤቴ ለልጇ ሠርግ የድርሻዋን ማዋጣቷ ነው። ገንዘቡን ግን ትንሽ አበዛችው።” አለ በማጉተምተም። ከዚያ በኋላ ወሬው ሁሉ እጅግ ስለሚወዳት ስለ ባለቤቱ ወይዘሮ ገነት ገረመው ቀማው ብቻ ሆነ።
ከዚህ በኋላ ዝም ማለት ነበረብኝ። የሎተሪውን ደስታ ወደ ሀዘን መለወጥ አልፈለግኩም። እግዚአብሔር የራሱ መንገድ አለው።
Filed in: Amharic